በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ትልቅ መብት እንዳገኘሁ ይሰማኛል”

“ትልቅ መብት እንዳገኘሁ ይሰማኛል”

ከሄይቲ የተላከ ደብዳቤi

“ትልቅ መብት እንዳገኘሁ ይሰማኛል”

በሄይቲ ጥር 12, 2010 ከደረሰው የመሬት መናወጥ በኋላ አደጋው ያስከተለውን ውድመት በዜና ላይ ማየት እንኳ ከባድ ሆኖብኝ ነበር። ይሁንና ጥር 20 ላይ ውድ ጓደኛዬ ካርመን ስልክ ደውላ ፈቃደኛ ሠራተኞች ሆነን ወደ ሄይቲ እንድንሄድ ሐሳብ አቀረበችልኝ። ከካርመን ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የተዋወቅነው ከጥቂት ዓመታት በፊት ፈቃደኛ ሠራተኞች ሆነን በመንግሥት አዳራሽ ግንባታ ላይ በነርስነት ባገለገልንበት ወቅት ነበር። ከዚያ ወዲህ በሌሎች ፕሮጀክቶች ላይም አብረን ስለሠራን የቅርብ ጓደኛሞች ሆነናል።

በሄይቲ ያለውን ሰቆቃ ለመቋቋም የሚያስችል አካላዊም ሆነ ስሜታዊ ጥንካሬ እንደሌለኝ ለካርመን ነገርኳት። እሷም ከዚህ በፊት ተግባብተን ስለሠራን አሁንም ቢሆን እርስ በርስ ተደጋግፈን ልንሠራ እንደምንችል ነገረችኝ። እሷ የተናገረችው ሐሳብ ስላበረታታኝ በብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ ወደሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ስልክ በመደወል በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ለሄይቲ የሚደረገውን እርዳታ የሚያስተባብረውን ግለሰብ አነጋገርኩት። ፈቃደኛ ሠራተኛ አድርጎ እንዲመዘግበኝ ስሜን ከሰጠሁት በኋላ ስለ ካርመን አንስቼ አብረን ብንመደብ ደስ እንደሚለን ነገርኩት። እኔም ሆንኩ እሷ እንደምንጠራም ሆነ አብረን እንደምንሠራ ማረጋገጫ ሊሰጠን እንደማይችል ነገረኝ።

ጥያቄዬ ተቀባይነት ያገኛል ብዬ ስላላሰብኩ የዕለት ተዕለት ተግባሬን ማከናወን ቀጠልኩ። ከአራት ቀን በኋላ ማለትም ሰኞ ጥር 25 ከብሩክሊን ስልክ ተደውሎ ከተቻለ በማግስቱ ወደ ሄይቲ መሄድ እችል እንደሆነ ተጠየቅሁ። ይህን ስሰማ ጆሮዬን ማመን አቃተኝ! እኔም በማግስቱ ለመሄድ የቻልኩትን ሁሉ እንደማደርግ ቃል ገባሁ። በመጀመሪያ፣ ከምሠራበት ቦታ ፈቃድ ጠየቅሁ። ከዚያም፣ ለካርመን ስደውል ፈረንሳይኛ መናገር ባለመቻሏ ምክንያት እንዳልተጋበዘች ነገረችኝ። በዚህ ጊዜ ድብልቅልቅ ያለ ስሜት ተሰማኝ፤ በአንድ በኩል ደስ ቢለኝም በሌላ በኩል ደግሞ ፍርሃት ተሰምቶኝ ነበር። ጥር 28 የአውሮፕላን ቲኬት ከቆረጥኩ በኋላ ከኒው ዮርክ ተነስቼ ሄይቲን ወደምታዋስነው ወደ ዶሚኒካን ሪፑብሊክ ዋና ከተማ ወደ ሳንቶ ዶሚንጎ በረርኩ።

አውሮፕላን ማረፊያ ስደርስ አንድ ወጣት የይሖዋ ምሥክር ተቀብሎኝ በዚያ ወደሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ በመኪና ወሰደኝ። በዚያ ቀን ሌሎች ሁለት ነርሶችም ከዩናይትድ ስቴትስ መጥተው ስለነበር ሌሊቱን ሦስታችንም በአንድ ክፍል ውስጥ አደርን። በማግስቱ ጠዋት በመኪና ሰባት ሰዓት ተኩል ተጉዘን በፖርት ኦ ፕራንስ ወደሚገኘው የሄይቲ ቅርንጫፍ ቢሮ ደረስን።

የሄይቲን ድንበር አቋርጠን ከገባን በኋላ የመሬት መናወጡ ያስከተለውን ውድመት ተመለከትን። በዚህች ውብ አገር ላይ ለ35 ሴኮንዶች ብቻ የቆየ የመሬት መናወጥ ይህን ያህል ጥፋት ማድረሱ የማይታመን ነገር ነው። የደረሰውን ጥፋት በቴሌቪዥን መመልከት እንኳ በጣም ከባድ ነበር፤ በአካል ተገኝቶ ሁኔታውን ማየት ደግሞ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ መግለጽ ይከብደኛል። የፕሬዚዳንቱን ቤተ መንግሥት ጨምሮ ብዙ ቤቶች ላይ ጉዳት የደረሰ ሲሆን ሌሎች ቤቶች ግን የፍርስራሽ ክምር ሆነው ነበር። ብዙ ሰዎች እነዚህን ቤቶች ለመሥራት ሕይወታቸውን ሙሉ ሲደክሙ ኖረዋል፤ ያም ሆኖ ቤቶቹ በጥቂት ሴኮንዶች ውስጥ የፍርስራሽ ክምር ሆነዋል። ይህን ስመለከት በሕይወት ውስጥ ትልቅ ቦታ ሊሰጠው የሚገባው ለቁሳዊ ነገሮች እንዳልሆነ ይበልጥ ተገነዘብኩ።

ቅርንጫፍ ቢሮው ከደረስን በኋላ በእንግዳ መቀበያ ክፍል ውስጥ የምትሠራው እህት ወደ ውስጥ ስንገባ ከሩቅ አይታን ከተቀመጠችበት ተነስታ ሮጣ በመምጣት እቅፍ አድርጋ ሰላም አለችን፤ በፊቷ ላይ የሚታየው ፈገግታ ልዩ ነበር። የራሳችንን ጥቅም መሥዋዕት አድርገን እዚያ በመገኘታችን አመሰገነችን። ምሳ ከበላን በኋላ በአቅራቢያው ወደሚገኝ ትልልቅ ስብሰባዎች ወደሚደረጉበት አዳራሽ ሄድን፤ ይህ አዳራሽ እንደ ሆስፒታል ሆኖ እያገለገለ ነበር። እዚያም ስንደርስ ፈቃደኛ ሠራተኛ ሆነው ለማገልገል የመጡ ሌሎች የይሖዋ ምሥክሮችን አገኘን፤ ከእነዚህ መካከል ከጀርመን የመጡ ባልና ሚስት ዶክተሮች፣ አብሯቸው የሚሠራ ረዳት ዶክተር እንዲሁም ከስዊዘርላንድ የመጣች አዋላጅ ይገኙበታል።

በዚያኑ ዕለት ምሽት ላይ ሥራ ጀመርኩ። በአዳራሹ ወለል ላይ ፍራሽ ተዘርግቶላቸው የተኙ 18 ሕሙማን ነበሩ፤ ከእነዚህ መካከል የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ ሰዎች ይገኙበታል። እያንዳንዱ ሕመምተኛ በይሖዋ ምሥክሮች የሕክምና ቡድን እኩል ትኩረት ይሰጠው የነበረ ከመሆኑም ሌላ ነፃ የሕክምና አገልግሎት ያገኝ ነበር።

በዚያኑ ሌሊት አንድ የ80 ዓመት አረጋዊ አረፉ። እኔ፣ አብራኝ የምታድረው እህትና ባለቤታቸው አጠገባቸው ነበርን። ከዚያ በኋላ ደግሞ ኬትሊ የምትባል አንዲት ወጣት ከሥቃይዋ የተነሳ መጮኽ ጀመረች። የመሬት መናወጡ ባደረሰባት ጉዳት የተነሳ ቀኝ እጇ ተቆርጧል። ኬትሊን መጽሐፍ ቅዱስ ታስተምራት የነበረች አንዲት የይሖዋ ምሥክር ከአጠገቧ አልተለየችም። ይህች እህት እያንዳንዱን ሌሊት ማለት ይቻላል ከጎኗ እየተኛች ታስታምማት ነበር።

እኔም የሕክምና እርዳታ ልሰጣት ወደ ኬትሊ ጠጋ አልኩ፤ ሆኖም ኬትሊን ያስለቀሳት ቁስሏ ያስከተለባት ሥቃይ ብቻ ሳይሆን ስሜቷ ስለተጎዳ ጭምር እንደሆነ ተረዳሁ። የመሬት ነውጡ በተከሰተበት ወቅት በአንዲት ጓደኛዋ ቤት እንደነበረች ነገረችኝ። ሁለቱም ምን እየተከሰተ እንዳለ ግራ ገብቷቸው ነበር። እጅ ለእጅ ተያይዘው ወደ ውጪ እየሮጡ ሳለ ግድግዳው ተደርምሶባቸው ፍርስራሹ ውስጥ ተቀበሩ። ከዚያም ኬትሊ ጓደኛዋን ስትጠራት መልስ ሳታገኝ ቀረች። በዚህ ጊዜ ጓደኛዋ መሞቷን ተረዳች። ከአራት ሰዓታት በኋላ የሕይወት አድን ሠራተኞች ደርሰው እስኪያወጧቸው ድረስ የጓደኛዋ ሰውነት በከፊል በኬትሊ ላይ ተጋድሞ ነበር። በአደጋው ምክንያት የኬትሊ ቀኝ እጅ ከትከሻዋ መጋጠሚያ ጀምሮ ሙሉ ለሙሉ ተቆርጠ።

እዚያ በሠራሁበት በመጀመሪያው ሌሊት ኬትሊ ሸለብ ባደረጋት ቁጥር የደረሰው አደጋ ወደ አእምሮዋ እየመጣ ይረብሻት እንደነበር አስተዋልኩ። እየተንሰቀሰቀች እንዲህ አለችኝ፦ “መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መጨረሻው ዘመንም ሆነ ስለ መሬት መናወጥ የሚናገረውን አውቃለሁ። ስለ ወደፊቱ ጊዜ አስደሳች ተስፋ እንዳለን አውቃለሁ። በሕይወት በመትረፌም አመስጋኝ መሆን እንዳለብኝ አውቃለሁ። ይሁን እንጂ እስቲ ራስሽን ለደቂቃ በእኔ ቦታ አስቀምጠሽ ለማሰብ ሞክሪ። ጥሩ ሕይወት እየመራሽ እያለ አንድ ቀን በድንገት ራስሽን በዚህ ሁኔታ ውስጥ ብታገኚው ምን ይሰማሽ ነበር?” ምንም ልረዳት ስላልቻልኩ እጇን ይዤ አብሬያት ማልቀስ ጀመርኩ። እንቅልፍ እስኪወስዳት ድረስ ሁለታችንም ስናለቅስ ቆየን።

የሕክምና ክትትል የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች ለመርዳት በየቀኑ አንድ ዶክተርና ሁለት ነርሶች ወደተለያዩ ቦታዎች ይላኩ ነበር። እኔም ከፖርት ኦ ፕራንስ በመኪና የሁለት ሰዓት ጉዞ ወደሚፈጀው ፔቲት ጎአቭ ተላኩኝ። የሄድኩት ከሁለት ሌሎች ፈቃደኛ ሠራተኞች ማለትም ከፍሎሪዳ ከመጣች አንዲት ነርስና ከፈረንሳይ ከመጣ አንድ ዶክተር ጋር ነበር። ከጠዋቱ 3:30 ላይ በቦታው የደረስን ሲሆን ዕቃችንን አውርደን በአካባቢው ባለ የመንግሥት አዳራሽ ውስጥ አስቀመጥን፤ ብዙ ሰዎች እየመጣን እንደሆነ ተነግሯቸው ስለነበር እዚያ ቁጭ ብለው እየጠበቁን ነበር።

ወዲያውኑ ሥራ ጀመርን። ቀኑ ሞቃታማ የነበረ ሲሆን ሕክምና ለማግኘት የተሰለፉት ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ይሄድ ነበር። ትንሽ አረፍ ያልነው ወደ ዘጠኝ ሰዓት ገደማ ነበር። በዚያ ቀን ሦስት ሆነን ለ114 ሰዎች ክትባት የሰጠን ሲሆን 105 ለሚሆኑ ሰዎች ደግሞ የሕክምና ምክር አገልግሎት ሰጥተናል። ደክሞኝ የነበረ ቢሆንም በችግር ላይ የወደቁ ሰዎችን ለመርዳት የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማበርከት በመቻላችን ደስ ብሎኝ ነበር።

በሄይቲ በእርዳታ ሥራ ላይ በጠቅላላው ከሁለት ሳምንት በላይ አሳልፌያለሁ። በእያንዳንዱ ሌሊት ማለት ይቻላል በትልልቅ ስብሰባዎች አዳራሽ ውስጥ በፈረቃ ለ12 ሰዓት ያህል እሠራ ነበር። ከዚያ በፊት እንዲህ ያለ ከባድ ሥራ አጋጥሞኝ አያውቅም። ያም ሆኖ እዚያ መሥራት መቻሌ ትልቅ መብትና በረከት እንደሆነ ይሰማኛል። ክፉኛ ለተጎዱት የሄይቲ ሰዎች በተወሰነ መጠንም ቢሆን መጽናኛና እርዳታ ማበርከት በመቻሌ በጣም ደስተኛ ነኝ።

ከሄይቲ ሕዝብ ብዙ የምንማረው ነገር አለ። ለምሳሌ ያህል፣ እንከባከባቸው ከነበሩ ሕመምተኞች መካከል አንዱ የሆነው የ15 ዓመቱ ኤሊዛ አንድ እግሩን መቆረጥ ነበረበት። ኤሊዛ ከሚሰጠው ምግብ ላይ የተወሰነውን እሱ ጋር ያድር ለነበረው ለጂሚ ሲያስቀር ተመለከትኩ። ጂሚ ለማደር ወደ እሱ ሲመጣ አብዛኛውን ጊዜ ራት ሳይበላ እንደሚመጣ ኤሊዛ ነገረኝ። ኤሊዛ ያደረገው ነገር ያለንን ለሌሎች ለማካፈል ሀብታም ወይም ጤነኛ መሆን እንደማያስፈልገን እንድገነዘብ አድርጎኛል።

እንዲህ ያለው መንፈስ እኔ በነበርኩበት ቡድን ውስጥ በሚሠሩ ፈቃደኛ ሠራተኞች መካከልም በግልጽ ይታይ ነበር። ከፈቃደኛ ሠራተኞቹ መካከል አንዷ ብዙም ጤና ያልነበራት ሲሆን ሌላዋ ደግሞ በጀርባ ሕመም ትሠቃይ ነበር። ሆኖም ሁሉም ከራሳቸው ምቾት ይልቅ ሕመምተኞቹን ለመርዳት ቅድሚያ ይሰጡ ነበር። ይህም በሥራዬ ለመቀጠል የሚያስፈልገኝን ብርታት ሰጥቶኛል። ሁላችንም ከጊዜ ወደ ጊዜ ስሜታዊ፣ አእምሯዊና አካላዊ ድካም ቢሰማንም እርስ በርስ በመደጋገፍ ሥራችንን መቀጠል ችለናል። እንዴት ያለ የማይረሳ ተሞክሮ ነው! ደግ፣ አፍቃሪና የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት የሚያደርጉ ግሩም ክርስቲያኖች ያሉበት ድርጅት አባል በመሆኔ አመስጋኝ ነኝ።

ቀኝ እጃቸውን የተቆረጡ ሁለት ሕመምተኞች ሄይቲን ለቅቄ ከመውጣቴ በፊት እንደምንም ብለው የምስጋና ደብዳቤ ጽፈው ነበር፤ ከዚያም ደብዳቤውን አውሮፕላን ውስጥ ከገባሁ በኋላ እንዳነበው ነገሩኝ። እኔም እነሱ እንዳሉኝ አደረግሁ። በደብዳቤዎቹ ልቤ ስለተነካ ለረጅም ሰዓት አለቀስኩ።

ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ከተመለስኩም በኋላ በሄይቲ ካገኘኋቸው አዳዲስ ጓደኞቼ ጋር ያለኝ ግንኙነት እስካሁን ቀጥሏል። ጠንካራ ወዳጅነቶች የሚመሠረቱትም ሆነ የሚፈተኑት በመከራና በችግር ጊዜ ነው። በመካከላችን ያለው ወዳጅነት ወደፊት የሚያጋጥመንን ማንኛውንም መከራና ችግር በጽናት እንደሚቋቋም አምናለሁ። በእርግጥም ትልቅ መብት እንዳገኘሁ ይሰማኛል።