በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰችው ገነት የምትገኘው የት ነው?

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰችው ገነት የምትገኘው የት ነው?

 አንባቢያን የሚያነሱት ጥያቄ . . .

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰችው ገነት የምትገኘው የት ነው?

ሞት አፋፍ ላይ የነበረ አንድ ሰው በኢየሱስ ላይ እምነት እንዳለው በልበ ሙሉነት በተናገረ ጊዜ ኢየሱስ “ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” በማለት ቃል ገብቶለት ነበር። (ሉቃስ 23:43) ለዚህ ሰው ቃል የተገባለት ስፍራ የሚገኘው የት ነው? ገነት የምትገኘው በሰማይ ነው ወይስ በምድር? ወይስ ሰዎች ፍርድ እስኪሰጣቸው ድረስ ይቆዩበታል ተብሎ በሚታሰብ በሰማይና በምድር መካከል በሚገኝ ቦታ?

የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን በአንድ ወቅት በገነት ውስጥ ይኖሩ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “እግዚአብሔር አምላክም በምሥራቅ በዔድን ገነትን ተከለ የፈጠረውንም ሰው ከዚያው አኖረው። . . . እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ወስዶ ያበጃትም ይጠብቃትም ዘንድ በዔድን ገነት አኖረው።”—ዘፍጥረት 2:8, 15 የ1954 ትርጉም

አንድ ባልና ሚስት የልጆቻቸው ቁጥር እየጨመረ ሲሄድ መኖሪያቸውን እያስፋፉ እንደሚሄዱ ሁሉ የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችንም ሰብዓዊው ቤተሰብ በቁጥር እየበዛ ሲሄድ የሚኖሩባትን ገነት ከኤደን ክልል አልፈው እንዲያስፋፉ ይጠበቅባቸው ነበር። አምላክ “ምድርን ሙሏት፤ ግዟትም” ብሏቸው ነበር።—ዘፍጥረት 1:28

በመሆኑም ፈጣሪያችን ለሰው ዘሮች ያወጣው ዓላማ በዚህች ምድር ላይ በገነት ውስጥ እንዲኖሩና ልጆችን እንዲወልዱ ነበር። መካነ መቃብር በሌለበት ምድራዊ ገነት ወይም የአትክልት ስፍራ ውስጥ ለዘላለም መኖር ይችሉ ነበር። ምድር ለሁሉም የሰው ዘሮች ዘላለማዊ መኖሪያ ትሆን ነበር። በእርግጥም በፕላኔታችን ላይ ባሉት የተፈጥሮ መስህቦች መደመማችን ምንም አያስገርምም! የተፈጠርነው ውብ በሆነችው ምድር ላይ ለመኖር ነው።

ታዲያ የአምላክ ዓላማ ተለውጧል? በጭራሽ! ምክንያቱም ይሖዋ እንዲህ የሚል ማረጋገጫ ሰጥቶናል፦ “ከአፌ የሚወጣውም ቃሌ፣ በከንቱ ወደ እኔ አይመለስም፤ ነገር ግን የምሻውን ያከናውናል።” (ኢሳይያስ 55:11) የሰው ልጅ ከተፈጠረ ከ3,000 ከሚበልጡ ዓመታት በኋላ መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ ‘ምድርን ያበጃትና የሠራት ባዶ እንድትሆን ሳይሆን የሰው መኖሪያ እንድትሆን’ መሆኑን ተናግሯል። (ኢሳይያስ 45:18) የአምላክ ፈቃድ አሁንም አልተለወጠም። ምድር እንደገና ገነት ትሆናለች።

የሚያስገርመው ስለ ገነት የሚናገሩት ብዙዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች በምድር ላይ ስለሚኖረው ሕይወት የሚገልጹ ናቸው። ለምሳሌ የኢሳይያስ ትንቢት እንዲህ ይላል፦ “ሰዎች ቤት ይሠራሉ፤ በውስጡም ይኖራሉ፤ ወይንን ይተክላሉ፤ ፍሬውንም ይበላሉ።” (ኢሳይያስ 65:21) ቤቶች የሚሠሩት፣ ወይን የሚተከለውና ፍራፍሬ የሚበላው የት ነው? ምድር ላይ ነው። ምሳሌ 2:21 “ቅኖች በምድሪቱ ይቀመጣሉ” በማለት በግልጽ ይናገራል።

ኢየሱስም ቢሆን ስለ ምድራዊ ገነት ተናግሯል። እርግጥ ነው፣ ኢየሱስ ስለ ሰማያዊ ገነትም ተናግሯል፤ ይሁንና በዚህ ስፍራ የሚኖሩት የተመረጡ ጥቂት ሰዎች ናቸው። (ሉቃስ 12:32) እነዚህ ሰዎች ከሞት ተነስተው ወደ ሰማያዊው ገነት በመሄድ ከክርስቶስ ጋር ገነት በሆነችው ምድር ላይ ይገዛሉ። (ራእይ 5:10፤ 14:1-3) በሰማይ የሚኖሩት እነዚህ ተባባሪ ገዥዎች ገነት የሆነችው ምድር ከአምላክ መሥፈርቶች ጋር በሚስማማ መልኩ በሚገባ እየተዳደረች መሆኑን ይከታተላሉ።

ኢየሱስ አምላክ ለምድር ያለው ዓላማ ይህ እንደነበር ያውቃል። ደግሞም ኤደን ገነት ስትፈጠር በሰማይ ከአባቱ ጋር ነበር። በአሁኑ ጊዜ እምነት እንዳላቸው በተግባር የሚያሳዩ ሁሉ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የመኖር አጋጣሚ ተዘርግቶላቸዋል። (ዮሐንስ 3:16) ኢየሱስ እንዲህ ያሉት ሰዎች ‘ከእሱ ጋር በገነት እንደሚሆኑ’ ቃል ገብቷል።—ሉቃስ 23:43

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

© FORGET Patrick/SAGAPHOTO.COM/Alamy