በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምን ዓይነት ሰዎች መሆን እንዳለባችሁ አስቡ

ምን ዓይነት ሰዎች መሆን እንዳለባችሁ አስቡ

“ቅዱስ ሥነ ምግባር በመከተልና ለአምላክ ያደራችሁ መሆናችሁን የሚያሳዩ ተግባሮች በመፈጸም ምን ዓይነት ሰዎች መሆን እንዳለባችሁ ልታስቡበት ይገባል!”—2 ጴጥ. 3:11

1, 2. በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ከፈለግን ‘ምን ዓይነት ሰዎች ልንሆን ይገባል’?

ማናችንም ብንሆን ሌሎች ለእኛ ያላቸው አመለካከት ያሳስበናል። ይሁንና ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ይሖዋ ስለ እኛ ያለው አመለካከት ይበልጥ ሊያሳስበን ይገባል። ምክንያቱም በጽንፈ ዓለም ውስጥ ከሁሉ የሚበልጠው ታላቅ አካል እንዲሁም “የሕይወት ምንጭ” እሱ ነው።—መዝ. 36:9

2 ሐዋርያው ጴጥሮስ፣ ከይሖዋ አመለካከት አንጻር ስንታይ “ምን ዓይነት ሰዎች” ልንሆን እንደሚገባ ሲገልጽ ‘ቅዱስ ሥነ ምግባር ልንከተልና ለአምላክ ያደርን መሆናችንን የሚያሳዩ ተግባሮችን ልንፈጽም’ እንደሚገባ አሳስቦናል። (2 ጴጥሮስ 3:11ን አንብብ።) በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት ከፈለግን ‘ሥነ ምግባራችን’ ቅዱስ ሊሆን ይኸውም በድርጊታችን፣ በአስተሳሰባችንና በመንፈሳዊነታችን ረገድ ንጹሕ ልንሆን ይገባል። በተጨማሪም ‘ለአምላክ ያደርን መሆናችንን የሚያሳዩ ተግባሮችን’ እንድናከናውን የሚያነሳሳን ለአምላክ ያለን ጥልቅ አክብሮትና ለእሱ ያለን ፍቅር መሆን አለበት። በመሆኑም በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ከፈለግን ምግባራችን ብቻ ሳይሆን ውስጣዊ ማንነታችንም ሊያሳስበን ይገባል። ይሖዋ ‘ልብን የሚመረምር’ አምላክ እንደመሆኑ መጠን ምግባራችን ቅዱስ መሆኑን እንዲሁም ለእሱ ብቻ ያደርን መሆን አለመሆናችንን ማወቅ ይችላል።—1 ዜና 29:17

3. ከአምላክ ጋር ያለንን ዝምድና በተመለከተ የትኞቹን ጥያቄዎች ልናስብባቸው ይገባል?

3 ሰይጣን ዲያብሎስ፣ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንድናገኝ አይፈልግም። እንዲያውም ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና የሚያበላሽ አካሄድ እንድንከተል ለማድረግ የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም። ሰይጣን በውሸትና በማታለያ ተጠቅሞ እኛን በማባበል ከምናመልከው አምላክ ሊያርቀን ይጥራል። (ዮሐ. 8:44፤ 2 ቆሮ. 11:13-15) በመሆኑም ራሳችንን እንዲህ እያልን መጠየቃችን ጥበብ ነው፦ ‘ሰይጣን ሰዎችን የሚያታልለው እንዴት ነው? ከይሖዋ ጋር ያለኝን ዝምድና ጠብቄ ለመኖር ምን ማድረግ ይኖርብኛል?’

ሰይጣን ሰዎችን የሚያታልለው እንዴት ነው?

4. ሰይጣን ከአምላክ ጋር ያለንን ዝምድና ለማበላሸት በዋነኝነት ዒላማው የሚያደርገው ምንን ነው? ለምንስ?

4 ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “እያንዳንዱ ሰው  በራሱ ምኞት ሲማረክና ሲታለል ይፈተናል። ከዚያም ምኞት ከፀነሰች በኋላ ኃጢአትን ትወልዳለች፤ ኃጢአት ደግሞ በተግባር ሲፈጸም ሞትን ያስከትላል።” (ያዕ. 1:14, 15) ምኞት የሚመነጨው ከልብ ነው፤ በመሆኑም ሰይጣን፣ ከአምላክ ጋር የመሠረትነውን ዝምድና ለማበላሸት በዋነኝነት ዒላማው የሚያደርገው ልባችንን ነው።

5, 6. (ሀ) ሰይጣን በልባችን ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር የሚሞክረው በምን መንገድ ነው? (ለ) ሰይጣን በልባችን ውስጥ የተሳሳተ ምኞት እንዲፈጠር ለማድረግ በየትኞቹ ማታለያዎች ይጠቀማል? በዚህ ረገድስ ምን ያህል ልምድ አለው?

5 ሰይጣን በልባችን ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር የሚሞክረው በምን መንገድ ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “መላው ዓለም . . . በክፉው ኃይል ሥር ነው” ይላል። (1 ዮሐ. 5:19) ሰይጣን ከሚጠቀምባቸው መሣሪያዎች መካከል ‘በዓለም ውስጥ ያሉት ነገሮች’ ይገኙበታል። (1 ዮሐንስ 2:15, 16 አንብብ።) ዲያብሎስ፣ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት ይህን ዓለም ሰዎችን ለማታለል በሚያስችለው መንገድ ሲቀርጸው ቆይቷል። እኛም የምንኖረው በዚህ ዓለም ውስጥ እስከሆነ ድረስ በተንኮል ዘዴዎቹ እንዳንታለል መጠንቀቅ አለብን።—ዮሐ. 17:15

6 ሰይጣን፣ በልባችን ውስጥ የተሳሳተ ምኞት እንዲፈጠር የሚያደርጉ ዘዴዎችን ይጠቀማል። ሐዋርያው ዮሐንስ፣ ዲያብሎስ የሚጠቀምባቸውን ሦስት ማታለያዎች ጠቅሷል፤ እነሱም (1) “የሥጋ ምኞት፣” (2) “የዓይን አምሮት” እና (3) “ኑሮዬ ይታይልኝ የሚል መንፈስ” ናቸው። ሰይጣን ኢየሱስን በምድረ በዳ በፈተነው ወቅት በእነዚህ ዘዴዎች ተጠቅሟል። ይህ አታላይ በእነዚህ ወጥመዶች በመጠቀም ረገድ ለዘመናት ያካበተው ተሞክሮ አለው፤ በመሆኑም በዛሬው ጊዜ እያንዳንዱን ሰው በሚማርከው ነገር በመጠቀም ሰዎችን በተለያየ መንገድ ለማጥመድ ይሞክራል። ከሰይጣን ወጥመድ ራሳችንን ለመጠበቅ ምን ማድረግ እንዳለብን ከመመልከታችን በፊት ዲያብሎስ ሔዋንን ለማሳሳት የተጠቀመባቸውን ማታለያዎች እስቲ እንመልከት፤ እነዚህ ዘዴዎች ሔዋንን ቢያታልሏትም የአምላክን ልጅ ግን ያላታለሉት ለምን እንደሆነም እንመረምራለን።

“የሥጋ ምኞት”

ሔዋን ‘በሥጋ ምኞት’ ተሸንፋለች (አንቀጽ 7ን ተመልከት)

7. ሰይጣን ‘የሥጋ ምኞትን’ በመጠቀም ሔዋንን የፈተናት እንዴት ነው?

7 የሰው ልጆች በሕይወት ለመኖር ከሚያስፈልጓቸው መሠረታዊ ነገሮች አንዱ ምግብ ነው። ፈጣሪም ምድርን የሠራት የተትረፈረፈ ምግብ እንድትሰጥ አድርጎ ነው። ሰይጣን የአምላክን ፈቃድ ከመፈጸም ወደኋላ እንድንል ለማድረግ ይህን ተፈጥሯዊ ፍላጎት ሊጠቀምበት ይሞክራል። ከሔዋን ጋር በተያያዘ ይህን ያደረገው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት። (ዘፍጥረት 3:1-6ን አንብብ።) ሰይጣን ለሔዋን “መልካምና ክፉን መለየት [የሚያስችለውን]” ዛፍ ፍሬ ብትበላ እንደማትሞት እንዲያውም ከፍሬው በበላች ቀን እንደ አምላክ እንደምትሆን ነገራት። (ዘፍ. 2:9) በሌላ አባባል ሰይጣን፣ ሔዋን በሕይወት ለመኖር እንድትችል አምላክን መታዘዝ እንደማያስፈልጋት መጠቆሙ ነበር። ይህ እንዴት ያለ ዓይን ያወጣ ውሸት ነው! ሔዋን፣ ሰይጣን የተናገረውን ከሰማች በኋላ ልትወስዳቸው የምትችላቸው ሁለት አማራጮች ነበሩ፤ ሐሳቡን ከአእምሮዋ ማውጣት አሊያም ስለ ጉዳዩ ማውጠንጠኗን መቀጠል ትችላለች፤ ስለ ጉዳዩ ማሰቧን ከቀጠለች ግን ፍሬውን የመብላት ምኞት በውስጧ እንዲቀሰቀስ ታደርጋለች። ሔዋን በአትክልት ቦታው ውስጥ ከሚገኙ ዛፎች በሙሉ መብላት  ትችል ነበር፤ እሷ ግን በኤደን ገነት መካከል ስለሚገኘው ዛፍ ሰይጣን የነገራትን ነገር ማሰቧን ቀጠለች፤ ከዚያም “ከፍሬው ወስዳ በላች።” ሔዋን ፈጣሪዋ የከለከላትን ነገር የመውሰድ ምኞት እንዲያድርባት በማድረግ ረገድ ሰይጣን ተሳክቶለታል።

ኢየሱስ ምንም ነገር እንዲያዘናጋው አልፈቀደም (አንቀጽ 8ን ተመልከት)

8. ሰይጣን ‘የሥጋ ምኞትን’ ተጠቅሞ ኢየሱስን ለማጥመድ የሞከረው እንዴት ነው? ያልተሳካለትስ ለምንድን ነው?

8 ሰይጣን፣ ኢየሱስን በምድረ በዳ በፈተነው ወቅትም ይህንኑ ዘዴ ተጠቅሟል። ኢየሱስ 40 ቀንና 40 ሌሊት ጾሞ በተራበበት ወቅት ሰይጣን ሊፈትነው ሞከረ፤ ዲያብሎስ በዚህ ወቅት የተጠቀመው ኢየሱስ ምግብ ለማግኘት ያለውን ተፈጥሯዊ ፍላጎት ነው። ኢየሱስን “እስቲ የአምላክ ልጅ ከሆንክ ይህ ድንጋይ ዳቦ እንዲሆን እዘዝ” አለው። (ሉቃስ 4:1-3) ኢየሱስ ሁለት አማራጮች ነበሩት፦ ተአምራዊ ኃይሉን ተጠቅሞ ረሃቡን ማስታገሥ አሊያም ኃይሉን በዚህ መንገድ ላለመጠቀም መምረጥ ይችላል። ኢየሱስ የራሱን ፍላጎት ለማርካት ኃይሉን ሊጠቀምበት እንደማይገባ ያውቃል። ተርቦ የነበረ ቢሆንም ረሃቡን ከማስታገሥ ይበልጥ ትልቅ ቦታ የሰጠው ከይሖዋ ጋር ላለው ዝምድና ነው። በመሆኑም ኢየሱስ “‘ሰው ከይሖዋ አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በምግብ ብቻ ሊኖር አይችልም’ ተብሎ ተጽፏል” በማለት መለሰ።—ማቴ. 4:4፤ ሉቃስ 4:4

“የዓይን አምሮት”

9. “የዓይን አምሮት” የሚለው አገላለጽ ምን ይጠቁመናል? ሰይጣን ሔዋንን ለማታለል በዚህ ዘዴ የተጠቀመው እንዴት ነው?

9 ዮሐንስ የጠቀሰው ሰይጣን የሚጠቀምበት ሌላው ማታለያ ደግሞ “የዓይን አምሮት” ነው። ይህ አገላለጽ እንደሚጠቁመው አንድ ሰው አንድን ነገር ስላየው ብቻ ያንን ነገር የማግኘት ምኞት ሊያድርበት ይችላል። ሰይጣን፣ ሔዋን እንዲህ ዓይነት ምኞት እንዲያድርባት ለማድረግ ሞክሯል፤ ሔዋን የዛፉን ፍሬ ከበላች ‘ዓይኗ እንደሚከፈት’ ነገራት። በመሆኑም ሔዋን ፍሬውን ባየችው ቁጥር ይበልጥ ማራኪ ሆኖ ይታያት ጀመር። የዛፉ ፍሬ “ለዐይን የሚያስደስት” እንደሆነ ተመለከተች።

10. ሰይጣን ‘የዓይን አምሮትን’ ተጠቅሞ ኢየሱስን ለመፈተን የሞከረው እንዴት ነው? ኢየሱስስ ምላሽ የሰጠው እንዴት ነው?

10 ሰይጣን፣ ኢየሱስን ለማታለልስ በዚህ ዘዴ የተጠቀመው እንዴት ነው? “የዓለምን መንግሥታት ሁሉ [ለኢየሱስ] በቅጽበት አሳየው፤ ከዚያም እንዲህ አለው፦ ‘ይህን ሁሉ ሥልጣንና የእነዚህን መንግሥታት ክብር ለአንተ እሰጥሃለሁ።’” (ሉቃስ 4:5, 6) ኢየሱስ የዓለምን መንግሥታት በሙሉ ቃል በቃል በቅጽበት ሊያያቸው አይችልም፤ ሆኖም ሰይጣን እነዚህን መንግሥታት ለኢየሱስ በራእይ መልክ በማሳየት ሊማርከው እንደሚችል አስቦ መሆን አለበት። ከዚያም “አንድ ጊዜ በፊቴ ተደፍተህ ብታመልከኝ ይህ ሁሉ የአንተ ይሆናል” በማለት ዓይን አውጥቶ ጠየቀው። (ሉቃስ 4:7) ኢየሱስ ግን ሰይጣን የሚፈልገውን ነገር ለማድረግ ፈጽሞ ፈቃደኛ አልነበረም። በመሆኑም ወዲያውኑ ምላሽ ሰጠ። “‘ይሖዋ አምላክህን ብቻ አምልክ፤ ለእሱም ብቻ ቅዱስ አገልግሎት አቅርብ’ ተብሎ ተጽፏል” አለው።—ሉቃስ 4:8

“ኑሮዬ ይታይልኝ የሚል መንፈስ”

11. ሔዋን በሰይጣን የተታለለችው እንዴት ነው?

11 ዮሐንስ፣ በዓለም ውስጥ ካሉት ነገሮች መካከል “ኑሮዬ ይታይልኝ የሚል መንፈስ” እንደሚገኝበት ጠቅሷል። አዳምና ሔዋን፣ በምድር ላይ ብቻቸውን ይኖሩ በነበረበት ወቅት “ኑሮዬ ይታይልኝ የሚል  መንፈስ” ሊያንጸባርቁ እንደማይችሉ የታወቀ ነው፤ ምክንያቱም ያላቸውን ነገር የሚያሳዩት ሰው በምድር ላይ አልነበረም። ሆኖም የትዕቢት ዝንባሌ እንዳላቸው አሳይተዋል። ሰይጣን፣ ሔዋንን በፈተናት ወቅት አምላክ አንድ ግሩም ነገር እንዳስቀረባት የሚጠቁም ሐሳብ ተናግሯል። ሔዋን “መልካምና ክፉን ከሚያሳውቀው ዛፍ” በበላች ቀን “መልካምና ክፉን በማወቅ፣ እንደ እግዚአብሔር” እንደምትሆን ዲያብሎስ ነገራት። (ዘፍ. 2:17፤ 3:5) ሰይጣን ይህን ሲል ሔዋን የይሖዋን መመሪያ መከተል ሳያስፈልጋት ራሷን መምራት እንደምትችል መጠቆሙ ነበር። ሔዋን ይህን ውሸት እንድታምን ያደረጋት ትዕቢት መሆን አለበት። ከተከለከለው ፍሬ ብትበላ እንደማትሞት ስለተሰማት ፍሬውን ወስዳ በላች። ምንኛ ተሞኝታ ነበር!

12. ሰይጣን ኢየሱስን ለመፈተን የሞከረበት ሌላው መንገድ ምንድን ነው? ኢየሱስስ ምን ምላሽ ሰጠ?

12 ከሔዋን በተቃራኒ ኢየሱስ በትሕትና ረገድ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ትቷል! ሰይጣን፣ ኢየሱስ ሌሎችን ለማስደመም ሲል አምላክን የሚፈታተን ነገር እንዲፈጽም በማድረግ ሊፈትነው ሞከረ፤ ኢየሱስ ግን እንዲህ ዓይነት ድርጊት ስለ መፈጸም ማሰብ እንኳ አልፈለገም። ሰይጣን ያለውን ነገር ቢያደርግ የትዕቢት ዝንባሌ እንዳለው የሚጠቁም ይሆን ነበር። ኢየሱስ ግን “‘አምላክህን ይሖዋን አትፈታተነው’ ተብሏል” በማለት ግልጽና የማያሻማ መልስ ሰጠ።ሉቃስ 4:9-12ን አንብብ።

ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና ጠብቀን ለመኖር ምን ማድረግ ይኖርብናል?

13, 14. ሰይጣን በዛሬው ጊዜ ሊያታልለን የሚሞክረው እንዴት እንደሆነ አብራራ።

13 ሰይጣን፣ ሔዋንን እና ኢየሱስን ለመፈተን የተጠቀመባቸውን ዓይነት ማታለያዎች በዛሬው ጊዜም ይጠቀማል። ዲያብሎስ ‘የሥጋ ምኞትን’ በመጠቀም ሰዎች በሥነ ምግባር ብልግና እንዲሁም ከልክ በላይ በመብላትና በመጠጣት ወጥመድ እንዲወድቁ ለማድረግ ይሞክራል። ‘የዓይን አምሮትን’ በመጠቀም ደግሞ ሰዎች የብልግና ምስሎችና ጽሑፎች ወጥመድ እንዲሆኑባቸው ለማድረግ ይጥራል፤ በተለይም በኢንተርኔት አማካኝነት፣ ንቁ ያልሆኑ ሰዎችን ያጠምዳል። በሌላ በኩል ደግሞ ትዕቢተኛ የሆኑና “ኑሮዬ ይታይልኝ የሚል መንፈስ” ያላቸው ሰዎች ቁሳዊ ነገሮች፣ ሥልጣንና ዝና ወጥመድ ስለሚሆኑባቸው በሰይጣን ፈተና ሊወድቁ ይችላሉ።

እነዚህ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙህ የትኞቹን የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ማስታወስ ይኖርብሃል? (አንቀጽ 13, 14ን ተመልከት)

14 ‘በዓለም ውስጥ ያሉት ነገሮች፣’ ዓሣ አጥማጆች ዓሦችን ለመሳብ መንጠቆው ላይ ከሚሰኩት ምግብ ጋር ይመሳሰላሉ። ምግቡ ለዓሦቹ ማራኪ ቢሆንም ከመንጠቆ ጋር ተያይዟል። ሰይጣን፣ ሰዎች የአምላክን ሕግ እንዲጥሱ ለማድረግ ሲል የተለመዱና ለዕለት ተዕለት ሕይወታችን አስፈላጊ እንደሆኑ የሚታሰቡ ነገሮችን ይጠቀማል። እንዲህ ያሉ የተንኮል ማታለያዎችን የሚጠቀምበት ዓላማ በልባችን ውስጥ የተሳሳተ ምኞት እንዲያድር ማድረግ ነው። ሰይጣን እነዚህን ማታለያዎች በመጠቀም፣ የአምላክን ፈቃድ  ከመፈጸም ይበልጥ ቅድሚያ ልንሰጥ የሚገባው ለግል ፍላጎታችንና ምቾታችን እንደሆነ ሊያሳምነን ይሞክራል። ታዲያ እንዲህ ባሉት ማታለያዎች እንታለል ይሆን?

15. የሰይጣንን ፈተናዎች በመቋቋም ረገድ ኢየሱስን መምሰል የምንችለው እንዴት ነው?

15 ሔዋን ለሰይጣን ማታለያዎች ተሸንፋለች፤ ኢየሱስ ግን ፈተናዎቹን መቋቋም ችሏል። እያንዳንዱ ፈተና ሲቀርብለት “ተብሎ ተጽፏል” ወይም “ተብሏል” በማለት ቅዱስ ጽሑፋዊ መልስ ይሰጥ ነበር። እኛም መጽሐፍ ቅዱስን በትጋት የምናጠና ከሆነ የአምላክን ቃል በደንብ ስለምናውቀው ፈተና በሚያጋጥመን ወቅት አስተሳሰባችን እንዳይዛባ የሚረዱንን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ማስታወስ እንችላለን። (መዝ. 1:1, 2) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ለአምላክ ታማኝ የሆኑ ግለሰቦችን ምሳሌ ማስታወሳችንም አርዓያቸውን ለመከተል ያነሳሳናል። (ሮም 15:4) ለይሖዋ ጥልቅ አክብሮት ማዳበር እንዲሁም እሱ የሚወደውን መውደድና የሚጠላውን መጥላት ጥበቃ ይሆንልናል።—መዝ. 97:10

16, 17. ‘የማሰብ ችሎታችንን’ የምንጠቀምበት መንገድ በማንነታችን ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል?

16 ሐዋርያው ጳውሎስ፣ የዓለም ሳይሆን የአምላክ ዓይነት አስተሳሰብ ያለን ሰዎች መሆን እንድንችል ‘የማሰብ ችሎታችንን’ እንድንጠቀም አበረታትቶናል። (ሮም 12:1, 2) አእምሯችን የሚያውጠነጥነውን ነገር መቆጣጠራችን ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ሲያጎላ እንዲህ ብሏል፦ “የአምላክን እውቀት የሚጻረሩ የመከራከሪያ ነጥቦችንና ይህን እውቀት ለማገድ የሚገነባውን ማንኛውንም ከፍ ያለ ነገር እናፈርሳለን፤ እንዲሁም ማንኛውንም አስተሳሰብ እየማረክን ለክርስቶስ እንዲታዘዝ እናደርጋለን።” (2 ቆሮ. 10:5) የምናስባቸው ነገሮች በማንነታችን ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ስለሚያሳድሩ የሚያንጹ ነገሮችን ‘ማሰባችንን ማቋረጥ’ የለብንም።—ፊልጵ. 4:8

17 ተገቢ ያልሆነ ሐሳብ ወደ አእምሯችን እንዲገባ የምንፈቅድ እንዲሁም መጥፎ ምኞቶችን የምናስተናግድ ከሆነ ቅዱስ ልንሆን አንችልም። ይሖዋን ‘በንጹሕ ልብ’ መውደድ ይኖርብናል። (1 ጢሞ. 1:5) ይሁን እንጂ ልብ “ተንኰለኛ” በመሆኑ ‘በዓለም ውስጥ ያሉት ነገሮች’ ምን ያህል ተጽዕኖ እያሳደሩብን እንዳሉ እንኳ አንገነዘብ ይሆናል። (ኤር. 17:9) እንግዲያው ጳውሎስ “በእምነት ውስጥ እየተመላለሳችሁ መሆናችሁን ለማወቅ ዘወትር ራሳችሁን መርምሩ፤ ማንነታችሁን ለማወቅ ራሳችሁን ዘወትር ፈትኑ” በማለት የሰጠውን ምክር መከተላችን አስፈላጊ ነው። ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያጠናናቸውን ሐሳቦች መሠረት በማድረግ ዘወትር ራሳችንን በሐቀኝነት እንመርምር።—2 ቆሮ. 13:5

18, 19. ይሖዋ እንድንሆን የሚፈልገው ዓይነት ሰው ለመሆን ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው?

18 ሰይጣን “በዓለም ውስጥ ያሉትን ነገሮች” በመጠቀም የሚያቀርባቸውን ፈተናዎች ለመቋቋም የሚረዳን ሌላው ነገር ዮሐንስ በመንፈስ መሪነት የጻፈውን የሚከተለውን ሐሳብ ማስታወስ ነው፦ “ዓለምም ሆነ ምኞቱ በማለፍ ላይ ናቸው፤ የአምላክን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል።” (1 ዮሐ. 2:17) የሰይጣን ሥርዓት እንዲሁ ለዘላለም የሚቀጥል ይመስል ይሆናል። ይሁን እንጂ አንድ ቀን መጥፋቱ አይቀርም። የሰይጣን ዓለም የሚያቀርበው ማንኛውም ነገር ዘላቂ አይደለም። ይህን እውነታ ማስታወሳችን በዲያብሎስ ማታለያዎች እንዳንታለል ይረዳናል።

19 ሐዋርያው ጴጥሮስ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ምን ዓይነት ሰዎች መሆን እንዳለብን ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ሰማያት በእሳት ተቃጥለው የሚጠፉበትንና ንጥረ ነገሮቹም ሁሉ በኃይለኛ ሙቀት የሚቀልጡበትን የይሖዋን ቀን መምጣት እየጠበቃችሁና በአእምሯችሁ አቅርባችሁ እየተመለከታችሁ ልትኖሩ ይገባል!” (2 ጴጥ. 3:12) በቅርቡ ይህ ቀን ይመጣል፤ በዚያ ቀን ይሖዋ የሰይጣንን ዓለም ጠራርጎ ያጠፋዋል። እስከዚያው ድረስ ግን ሰይጣን “በዓለም ውስጥ ያሉትን ነገሮች” በመጠቀም ሔዋንን እና ኢየሱስን እንደፈተናቸው ሁሉ እኛንም መፈተኑን አያቆምም። እንደ ሔዋን የራሳችንን ምኞት በማርካት ላይ ብቻ ማተኮር የለብንም። እንዲህ ማድረግ ሰይጣንን እንደ አምላክ አድርጎ ከመቀበል ተለይቶ አይታይም። ሰይጣን የሚያቀርባቸው ማታለያዎች የቱንም ያህል ማራኪና የሚያጓጉ ቢሆኑ ልክ እንደ ኢየሱስ በፈተናው ላለመሸነፍ መጣር አለብን። እንግዲያው ሁላችንም ይሖዋ እንድንሆን የሚፈልገው ዓይነት ሰው ለመሆን ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።