በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋ ‘ሸክሜን በየዕለቱ ይሸከምልኛል’

ይሖዋ ‘ሸክሜን በየዕለቱ ይሸከምልኛል’

የጤንነቴ ሁኔታ አስተማማኝ አለመሆኑ ነገሮች ከአቅሜ በላይ እንደሆኑ እንዲሰማኝ ቢያደርገኝም ውዱ ሰማያዊ አባታችን በፍቅር ተነሳስቶ የሚያደርግልኝ ድጋፍ በሕይወቴ ሁሉ እንዳልተለየኝ ይሰማኛል። ከ20 ለሚበልጡ ዓመታት ይሖዋን በአቅኚነት በማገልገል ልዩ ደስታ አግኝቻለሁ።

በ1956 ስወለድ ስፓይና ቢፊዳ የሚባል ከአከርካሪ አጥንቴ ጋር የተያያዘ እክል እንዳለብኝ ታወቀ። ይህ እክል በነርቮቼ ላይ ባስከተለው ጉዳት የተነሳ በእግር መሄድ የሚያስቸግረኝ ከመሆኑም ሌላ ሌሎች ከባድ የጤና ችግሮችም አሉብኝ።

ከመወለዴ ጥቂት ቀደም ብሎ ወላጆቼ የይሖዋ ምሥክሮች ከሆኑ ሚስዮናውያን ባልና ሚስት ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀምረው ነበር። ያደግሁት ኡሳኮስ በምትባል በናሚቢያ የምትገኝ ከተማ ሲሆን ልጅ እያለሁ በዚያ የነበሩት አስፋፊዎች ጥቂት ነበሩ። በመሆኑም በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ የሚቀርበውን ትምህርት የምንወስደው በቤተሰብ ሆነን ነበር። በሰባት ዓመቴ ዩሮስቶሚ የተባለ ቀዶ ሕክምና ተደረገልኝ፤ ዩሮስቶሚ በታካሚው ሆድ ላይ ክፍተት በማበጀት ከሰውነቱ ሽንት ለማስወገድ የሚያስችል ቀዶ ሕክምና ነው። በ14 ዓመቴ ደግሞ የሚጥል በሽታ ያዘኝ። በአካባቢያችን ያለው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እኔ ካለሁበት ስለሚርቅና እኔም የወላጆቼ ልዩ እንክብካቤ ያስፈልገኝ ስለነበረ ትምህርቴን መጨረስ አልቻልኩም።

ያም ቢሆን በመንፈሳዊ ራሴን ለማጠናከር ወስኜ ነበር። በዚያን ጊዜ ብዙዎቹ ክርስቲያናዊ ጽሑፎቻችን የአፍ መፍቻ ቋንቋዬ በሆነው በአፍሪካንስ አልተተረጎሙም። ስለዚህ ከጽሑፎቻችን ብዙዎቹን ማንበብ እንድችል እንግሊዝኛ ማንበብ ተማርኩ። ከዚያም የመንግሥቱ አስፋፊ ሆንኩና በ19 ዓመቴ ተጠመቅሁ። በቀጣዮቹ አራት ዓመታት ውስጥ ከአካላዊ ጤንነትና ከስሜት ጋር የተያያዙ ብዙ ችግሮች አጋጥመውኛል። ከዚህም በላይ ባደግሁበት ከተማ ማኅበረሰቡ በጣም የተቀራረበ በመሆኑ የሰው ፍርሃት በስብከቱ ሥራ በቅንዓት እንዳልካፈል እንቅፋት ሆኖብኝ ነበር።

በ20ዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ ሳለሁ ከናሚቢያ ወደ ደቡብ አፍሪካ የተዛወርን ሲሆን በዚያም ለመጀመሪያ ጊዜ ከሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች ጋር የጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ቻልኩ። ይህ በጣም አስደሳች ነበር! ይሁን እንጂ ኮሎስቶሚ (በታካሚው ሆድ ላይ ክፍተት በማበጀት ሰገራ ከሰውነቱ እንዲወገድ ለማድረግ የሚያስችል ዘዴ) የተባለ ሌላ ቀዶ ሕክምና ተደረገልኝ።

ይህ ከሆነ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ አንድ የወረዳ የበላይ ተመልካች ስለ አቅኚነት ንግግር ሲሰጥ አዳመጥኩ። ንግግሩ ልቤን ነካው። በእርግጥ የጤንነቴ ሁኔታ አቅኚነትን ሊያከብድብኝ እንደሚችል አውቅ ነበር፤ ይሖዋ ግን ከዚያ ቀደም ያጋጠሙኝን ችግሮች ተሸክሞልኛል። ስለዚህ የዘወትር አቅኚ ለመሆን አመለከትኩ። ይሁን እንጂ ካሉብኝ የጤና ችግሮች አንጻር የጉባኤ ሽማግሌዎች ማመልከቻዬን ለመቀበል ከበዳቸው።

ያም ሆኖ በመንግሥቱ የስብከት ሥራ ላይ የቻልኩትን ያህል ለመካፈል ወሰንኩ። በእናቴና በሌሎችም እርዳታ ለስድስት ወራት ያህል በአገልግሎት ከአቅኚዎች የሚጠበቀውን ሰዓት ማሟላት ቻልኩ። ይህም አቅኚ ለመሆን እንደቆረጥኩ እንዲሁም የጤንነት ችግሬን ተቋቁሜ ማገልገል እንደምችል የሚያሳይ ነበር። አቅኚ ለመሆን በድጋሚ ያመለከትኩ ሲሆን በዚህ ጊዜ ማመልከቻዬ ተቀባይነት አገኘ። መስከረም 1, 1988 የዘወትር አቅኚ ሆንኩ።

አቅኚ ሆኜ ሳገለግል የይሖዋ ድጋፍ ምንጊዜም አልተለየኝም። በራሴ ሁኔታ ላይ ከማተኮር ይልቅ ለአዳዲሶች እውነትን ማስተማር ስሜቴ እንዲረጋጋ እንዲሁም በመንፈሳዊ እድገት እንዳደርግ ረድቶኛል። በርካታ ግለሰቦች ራሳቸውን ወስነው እንዲጠመቁ መርዳት በመቻሌ ከፍተኛ ደስታ አግኝቻለሁ።

የጤንነቴ ሁኔታ አሁንም ቢሆን የሚያስተማምን አይደለም። ይሁን እንጂ ይሖዋ ‘ሸክሜን በየዕለቱ ይሸከምልኛል።’ (መዝ. 68:19) ይሖዋ፣ ችግሬን ተቋቁሜ ከመኖር ባለፈ በሕይወቴ ደስተኛ እንድሆን ረድቶኛል!