በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መንፈስ ቅዱስ በፍጥረት ሥራ ላይ የነበረው ድርሻ!

መንፈስ ቅዱስ በፍጥረት ሥራ ላይ የነበረው ድርሻ!

 መንፈስ ቅዱስ በፍጥረት ሥራ ላይ የነበረው ድርሻ!

“በእግዚአብሔር [“በይሖዋ፣” NW] ቃል ሰማያት ተሠሩ፤ በአፉም እስትንፋስ የከዋክብት ሰራዊት።”—መዝ. 33:6

1, 2. (ሀ) ሰዎች በሰማይ ስላሉት አካላትና ስለ ምድር ያላቸው እውቀት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው እንዴት ነው? (ለ) መልስ የሚያሻው የትኛው ጥያቄ ነው?

አልበርት አንስታይን አንጻራዊነት የተባለውን ልዩ ንድፈ ሐሳብ በ1905 ባቀረበበት ወቅት እሱም ሆነ ሌሎች በርካታ የሳይንስ ሊቃውንት በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ያለው አንድ ጋላክሲ ብቻ እንደሆነና ይህም ፍኖተ ሐሊብ የሚባለው እኛ የምንገኝበት ጋላክሲ እንደሆነ ያምኑ ነበር። የአጽናፈ ዓለምን ስፋት በተመለከተ የነበራቸው እውቀት ምንኛ አነስተኛ ነበር! በአሁኑ ጊዜ ግን በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ከ100 ቢሊዮን የሚበልጡ ጋላክሲዎች እንደሚገኙ የሚገመት ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ አንዳንዶቹ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ከዋክብትን ይዘዋል። የሳይንስ ሊቃውንት ይበልጥ የተራቀቁ ቴሌስኮፖችን በተጠቀሙ መጠን አዳዲስ ጋላክሲዎችን እያገኙ ነው።

2 በ1905 የሳይንስ ሊቃውንት ስለ ሰማይ አካላት የነበራቸው ግንዛቤ ውስን እንደነበረ ሁሉ ስለ ምድርም የነበራቸው እውቀት አናሳ ነበር። እርግጥ ነው፣ ከአንድ መቶ ዓመት በፊት ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ከእነሱ ቀደም ብለው ከነበሩት የበለጠ እውቀት ነበራቸው። በዛሬው ጊዜ ግን የሰው ልጆች፣ በምድር ላይ ስላሉት እጅግ አስደናቂና ውስብስብ የሆኑ ሕያዋን ፍጥረታት እንዲሁም እነዚህ ፍጥረታት በሕይወት እንዲኖሩ ስላስቻለው ሥርዓት ከመቶ ዓመት በፊት ከነበሩት ሰዎች በእጅጉ የተሻለ ግንዛቤ አላቸው። ወደፊትም ቢሆን ስለ ምድርና በሰማይ ስላሉት አካላት በጣም ብዙ ነገሮችን እንደምናውቅ ጥርጥር የለውም። ይሁንና ይበልጥ ትኩረት ልንሰጠው የሚገባው ጥያቄ ‘እነዚህ ሁሉ ነገሮች ወደ ሕልውና የመጡት እንዴት ነው?’ የሚለው ነው። የዚህን ጥያቄ መልስ ማወቅ የሚቻልበት ብቸኛው መንገድ ፈጣሪ በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ያሰፈረውን ዘገባ በማንበብ ነው።

በፍጥረት ሥራዎች ላይ የሚታየው ተአምር

3, 4. አምላክ አጽናፈ ዓለምን የፈጠረው እንዴት ነው? ሥራዎቹ ለእሱ ክብር የሚያመጡለትስ እንዴት ነው?

3 አጽናፈ ዓለም ወደ ሕልውና የመጣው እንዴት እንደሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ የመክፈቻ ሐሳብ ሲገልጽ “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማያትንና ምድርን ፈጠረ” ይላል። (ዘፍ. 1:1) ይሖዋ፣ ምንም ቁስ አካል ባልነበረበት ጊዜ መንፈስ ቅዱሱን ይኸውም በሥራ ላይ የዋለ ኃይሉን በመጠቀም ሰማይን፣ ምድርንና በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ያሉትን ነገሮች ሁሉ ፈጥሯል። አንድ የእጅ ባለሙያ ቅርጻ ቅርጾችን ለመሥራት በእጁና በተለያዩ መሣሪያዎች ይጠቀማል፤ አምላክ ግን ታላላቅ የሆኑ ሥራዎችን ለማከናወን ቅዱስ መንፈሱን ይልካል።

4 ቅዱሳን መጻሕፍት መንፈስ ቅዱስን ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ ‘የአምላክ ጣት’ በማለት ይገልጹታል። (ሉቃስ 11:20፤ ማቴ. 12:28) የይሖዋ ‘የእጅ ሥራዎች’ ይኸውም በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት የፈጠራቸው ነገሮች ለእሱ ታላቅ ክብር ያመጡለታል። መዝሙራዊው ዳዊት “ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፤ የሰማይም ጠፈር የእጁን ሥራ ያውጃሉ” በማለት ዘምሯል። (መዝ. 19:1) በእርግጥም ግዑዝ የሆኑት ፍጥረታት የአምላክ ቅዱስ መንፈስ እጅግ ታላቅ የሆነ ኃይል እንዳለው ይመሠክራሉ። (ሮም 1:20) እንዴት?

ገደብ የለሽ የሆነው የአምላክ ኃይል

5. ይሖዋ በፍጥረት ሥራው የተጠቀመበት ቅዱስ መንፈሱ ምን ያህል ኃይል እንዳለው በምሳሌ አስረዳ።

5 ማሰብ ከምንችለው በላይ እጅግ ግዙፍ የሆነው አጽናፈ ዓለም የይሖዋ ኃይልና ጉልበት ገደብ የለሽ መሆኑን ያሳያል። (ኢሳይያስ 40:26ን በNW አንብብ። *) ቁስ አካል  ወደ ጉልበት፣ ጉልበት ደግሞ ወደ ቁስ አካል ሊለወጥ እንደሚችል በዘመናዊ ሳይንስ ተደርሶበታል። ከከዋክብት አንዷ የሆነችው ፀሐይ፣ ቁስ አካል ወደ ጉልበት ሊለወጥ እንደሚችል ማስረጃ ትሆነናለች። ፀሐይ በእያንዳንዱ ሴኮንድ አራት ሚሊዮን ቶን ገደማ የሚሆን ቁስ አካል ወደ ብርሃን፣ ሙቀትና ሌላ ዓይነት ጉልበት ትለውጣለች። ፀሐይ ከምታመነጨው ጉልበት ውስጥ ወደ ምድር የሚደርሰው በጣም ጥቂት ቢሆንም በምድር ላይ ሕይወት እንዲኖር ለማድረግ ይህ በቂ ነው። ፀሐይንም ሆነ በቢሊዮን የሚቆጠሩትን ሌሎች ከዋክብት በሙሉ ለመፍጠር ይህ ነው የማይባል ኃይልና ጉልበት እንዳስፈለገ ምንም ጥርጥር የለውም። ይሖዋ እነዚህን ነገሮች ለመፍጠር የሚያስፈልገው ብቻ ሳይሆን ከዚያም የላቀ ኃይልና ጉልበት አለው።

6, 7. (ሀ) አምላክ በቅዱስ መንፈሱ ተጠቅሞ ነገሮችን የፈጠረው ሥርዓት ባለው መንገድ ነው የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) አጽናፈ ዓለም እንዲሁ በአጋጣሚ እንዳልመጣ የሚያሳየው ምንድን ነው?

6 አምላክ በቅዱስ መንፈሱ ተጠቅሞ ነገሮችን የፈጠረው ሥርዓት ባለው መንገድ መሆኑን የሚያሳዩ ማስረጃዎች በዙሪያችን ሞልተዋል። ይህን በምሳሌ ለማስረዳት፣ የተለያዩ ቀለማት ያሏቸው ኳሶች በአንድ ካርቶን ውስጥ ተቀምጠዋል እንበል። ካርቶኑን በመነቅነቅ ኳሶቹ በደንብ እንዲቀላቀሉ አደረግህ። ከዚያም ሁሉንም ኳሶች መሬት ላይ ዘረገፍካቸው። ኳሶቹ በየቀለማቸው ተለያይተው ለምሳሌ ሰማያዊ ቀለም ያላቸው ለብቻ፣ ቢጫ ቀለም ያላቸው ለብቻ ሆነው ይቀመጣሉ ብለህ ትጠብቃለህ? እንደማትጠብቅ የታወቀ ነው! በዘፈቀደ የሚሠራ ማንኛውም ነገር ሥርዓት ያለው የመሆኑ አጋጣሚ ጠባብ ነው። ይህ በተፈጥሮ ሕግ ውስጥ ተቀባይነት ያለው ሐቅ ነው። *

7 ቀና ብለን ሰማዩን ብንቃኝ አሊያም በቴሌስኮፕ ተጠቅመን ምርምር ብናደርግ ምን እንመለከታለን? እጅግ ግዙፍ በሆነው አጽናፈ ዓለም ውስጥ የሚገኙት ጋላክሲዎች፣ ከዋክብትና ፕላኔቶች በሚያስደንቅ ሁኔታ ሥርዓት ባለው መንገድ የተደራጁ መሆናቸውን ማስተዋል እንችላለን፤ ሁሉም ምንም ዝንፍ ሳይሉ የተመደበላቸውን መስመር ጠብቀው ይጓዛሉ። ይህ ደግሞ እንዲሁ በአጋጣሚ የተገኘ ወይም ታስቦበት ሳይሆን በድንገት የተከሰተ ነገር ሊሆን አይችልም። ስለሆነም ‘ሥርዓት ባለው መንገድ የተደራጀውን አጽናፈ ዓለም ለመፍጠር ያገለገለው ምን ዓይነት ኃይል ነው?’ ብለን መጠየቃችን የተገባ ነው። በሳይንሳዊ ምርምርና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመጠቀም የዚህን ኃይል ምንነት ማወቅ ከሰው ልጆች አቅም በላይ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ይህ ኃይል የአምላክ ቅዱስ መንፈስ እንደሆነ ይናገራል፤ የአምላክ መንፈስ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ከሁሉ የላቀ ኃይል ነው። መዝሙራዊው “በእግዚአብሔር ቃል ሰማያት ተሠሩ፤ በአፉም እስትንፋስ የከዋክብት ሰራዊት” በማለት ዘምሯል። (መዝ. 33:6) በምሽት ሰማያትን ብንመለከት ከእነዚህ የከዋክብት “ሰራዊት” ውስጥ በዓይናችን ልናይ የምንችለው ጥቂቶቹን ብቻ ነው!

መንፈስ ቅዱስና ምድር

8. ስለ ይሖዋ ሥራዎች የምናውቀው ምን ያህሉን ነው?

8 በአሁኑ ጊዜ ስለ ተፈጥሮ ያለን እውቀት በጣም ኢምንት ነው። ስለ አምላክ የፍጥረት ሥራዎች ያለን ግንዛቤ ከቁጥር የማይገባ በመሆኑ ኢዮብ የተባለው ታማኝ ሰው “እነዚህ የሥራው ዳር ዳር ናቸው፤ ስለ እርሱ የሰማነው ምንኛ አነስተኛ ነው!” በማለት ተናግሯል። (ኢዮብ 26:14) ኢዮብ ይህን ከተናገረ ከበርካታ ዘመናት በኋላ የይሖዋን የፍጥረት ሥራዎች በጥንቃቄ የመረመረው ንጉሥ ሰለሞን እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ “[አምላክ] ሁሉንም ነገር በጊዜው ውብ አድርጎ ሠራው፤ በሰዎችም ልብ ዘላለማዊነትን አኖረ፤ ይሁን እንጂ እግዚአብሔር ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ያደረገውን ማወቅ አይችሉም።”—መክ. 3:11፤ 8:17

9, 10. አምላክ ምድርን ሲፈጥር የተጠቀመበት ኃይል ምንድን ነው? በመጀመሪያዎቹ ሦስት የፍጥረት ቀናት ከተከናወኑት ነገሮች አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?

9 ይሁንና ይሖዋ ስለ ፍጥረት ሥራዎቹ መሠረታዊ የሆኑ  ነገሮችን ገልጾልናል። ለምሳሌ ያህል፣ ሕልቆ መሳፍርት ከሌላቸው ዘመናት በፊት የአምላክ መንፈስ በምድር ላይ የተለያዩ ነገሮችን ሲያከናውን እንደነበር ቅዱሳን መጻሕፍት ይነግሩናል። (ዘፍጥረት 1:2ን አንብብ።) በዚያን ወቅት የብስ የሚባል ነገርም ሆነ ብርሃን አልነበረም፤ ምናልባትም ሕያዋን ፍጥረታት ለመኖር የሚያስፈልጋቸው ዓይነት አየር በምድር ላይ አልነበረም።

10 መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ ተከታታይ በሆኑ የፍጥረት ቀናት ውስጥ ምን እንዳከናወነ ይነግረናል። እነዚህ ቀናት ቃል በቃል የ24 ሰዓት ርዝማኔ ያለውን ጊዜ ሳይሆን ዘመናትን ያመለክታሉ። በመጀመሪያው የፍጥረት ቀን ይሖዋ በምድር ላይ ብርሃን መታየት እንዲጀምር አድርጓል። ይህ ሂደት ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቀው ፀሐይንና ጨረቃን ከምድር ሆኖ በግልጽ ማየት በተቻለበት ጊዜ ነው። (ዘፍ. 1:3, 14) በሁለተኛው ቀን ከባቢ አየር መሠራት ጀመረ። (ዘፍ. 1:6) በዚህ ጊዜ በምድር ላይ ውኃ፣ ብርሃንና አየር የነበረ ሲሆን የብስ ግን አልነበረም። በሦስተኛው የፍጥረት ቀን መጀመሪያ አካባቢ ይሖዋ በመንፈስ ቅዱስ ተጠቅሞ የብስ እንዲኖር ያደረገ ሲሆን ይህንንም ያከናወነው ደረቁ ምድር ከፍተኛ በሆኑ የሥነ ምድር ኃይሎች ተገፍቶ ከውኃው በላይ እንዲወጣ በማድረግ ሊሆን ይችላል። (ዘፍ. 1:9) በሦስተኛው ቀንና ከዚያ በኋላ ባሉት የፍጥረት ዘመናት ሌሎች አስገራሚ ክንውኖችም ተፈጽመዋል።

መንፈስ ቅዱስና ሕያዋን ፍጥረታት

11. ሕይወት ያላቸው ነገሮች ውስብስብ፣ የተመጣጠነ ቅርጽና ውበት ያላቸው መሆናቸው ምን ያሳያል?

11 አምላክ፣ ሕያዋን ፍጥረታትን ሥርዓት ባለውና በተደራጀ መልኩ ለመፍጠርም በመንፈሱ ተጠቅሟል። አምላክ፣ ከሦስተኛው እስከ ስድስተኛው ባሉት የፍጥረት ቀናት ውስጥ ብዛታቸው የሚያስደንቅ ዕፅዋትንና እንስሳትን በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ፈጥሯል። (ዘፍ. 1:11, 20-25) ሕይወት ባላቸው ነገሮች መካከል የሚገኙት ውስብስብ፣ የተመጣጠነ ቅርጽ ያላቸውና ውብ የሆኑ በርካታ ፍጥረታት ከፍተኛ ችሎታ ያለው ንድፍ አውጪ መኖሩን ይጠቁማሉ።

12. (ሀ) የዲ ኤን ኤ ተግባር ምንድን ነው? (ለ) ዲ ኤን ኤ ውጤታማ በሆነ መልኩ ሥራውን ማከናወን መቻሉ ምን ያስተምረናል?

12 እስቲ ዲ ኤን ኤ (ዲኦክሲራይቦኑክሊክ አሲድ) የተባለውን ሞለኪውል እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ ዲ ኤን ኤ የሕያዋን ፍጥረታትን ባሕርይ ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማስተላለፍ ከሚረዱት ሞለኪውሎች አንዱ ነው። በምድር  ላይ ያሉ ሕያዋን ነገሮች በሙሉ ይኸውም ረቂቅ ተሕዋሲያን፣ ሣር፣ ዝሆን፣ ብሉ ዌል የተባለው ዓሣ ነባሪ እንዲሁም ሰዎች በውርስ የሚተላለፉ ባሕርያትን ለዘሮቻቸው የሚያስተላልፉት በዲ ኤን ኤ አማካኝነት ነው። በምድር ላይ ያሉት ፍጥረታት ዓይነታቸው እጅግ ብዙ ቢሆንም በዘር የሚወርሷቸውን አብዛኞቹን ባሕርያት የያዘው ዲ ኤን ኤ ሥራውን የሚያከናውንበት መንገድ ግን እምብዛም ለውጥ የለውም፤ ከዚህም ሌላ ዲ ኤን ኤ ባለፉት ዘመናት ሁሉ በዋና ዋናዎቹ ዝርያዎች ወይም ወገኖች መካከል ያለው ልዩነት ተጠብቆ እንዲቆይ አድርጓል። በመሆኑም በምድር ላይ ያሉት ልዩ ልዩ ፍጥረታት እጅግ ውስብስብ በሆነው ብዝሃ ሕይወት ውስጥ ይሖዋ አምላክ መጀመሪያ ባሰበው መንገድ የየራሳቸውን ሚና መጫወታቸውን ይቀጥላሉ። (መዝ. 139:16) እጅግ ውጤታማና ሥርዓታማ የሆነው ይህ አደረጃጀት ፍጥረት የተገኘው በአምላክ “ጣት” ወይም በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ለመሆኑ ተጨማሪ ማስረጃ ነው።

በምድር ላይ ካሉት ሁሉ የላቀው ፍጥረት

13. አምላክ ሰውን የፈጠረው እንዴት ነው?

13 በውል በማይታወቁ ረጅም ዘመናት ውስጥ አምላክ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሕያዋንና ግዑዛን ነገሮችን ፈጠረ፤ በመሆኑም ምድር “ቅርጽ የለሽና ባዶ” መሆኗ ቀርቶ በፍጥረታት ተሞላች። ይሁንና ይሖዋ በመንፈሱ ተጠቅሞ መፍጠሩን ገና አላበቃም ነበር። ምድር ላይ ካሉት ሁሉ የላቀውን ፍጥረቱን ሊሠራ ነው። በስድስተኛው የፍጥረት ቀን መገባደጃ አካባቢ ይሖዋ ሰውን ፈጠረ። ይሖዋ ሰውን የፈጠረው እንዴት ነው? መንፈስ ቅዱሱንና የምድርን ንጥረ ነገሮች በመጠቀም ነው።—ዘፍ. 2:7

14. ሰዎች ከእንስሳት የሚለዩበት ዋነኛው ነገር ምንድን ነው?

14 ዘፍጥረት 1:27 እንዲህ ይላል፦ “እግዚአብሔር ሰውን በራሱ መልክ ፈጠረው፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው።” ይሖዋ ሰውን የፈጠረው በራሱ መልክ ወይም አምሳል ነው ሲባል ፍቅርን የማንጸባረቅ እንዲሁም የመምረጥ ነፃነቱን የመጠቀም ችሎታ ሰጥቶታል ማለት ነው፤ ከዚህም በላይ ከፈጣሪው ጋር በግለሰብ ደረጃ ወዳጅነት መመሥረት ይችላል። የሰው አንጎል ከእንስሳት አንጎል በጣም የላቀ ነው። ይሖዋ የሰው ልጆችን አንጎል ሲሠራ ዓላማው ስለ እሱና ስለ ፍጥረት ሥራዎቹ ለዘላለም እውቀት እየቀሰምን በደስታ እንድንኖር ነው።

15. አዳምና ሔዋን ምን አጋጣሚ ተዘርግቶላቸው ነበር?

15 አምላክ አዳምንና ሔዋንን ሲፈጥር ምድርንና በላይዋ ያሉትን አስደናቂ ነገሮች ሁሉ የሰጣቸው ሲሆን ዓላማውም እነዚህን ነገሮች በመመርመር ደስታ እንዲያገኙ ነበር። (ዘፍ. 1:28) ይሖዋ የተትረፈረፈ ምግብና ገነት የሆነ መኖሪያ ሰጥቷቸው ነበር። ለዘላለም የመኖርና በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ፍጹም የሆኑ ዝርያዎችን የማፍራት አጋጣሚ ነበራቸው፤ እንዲሁም የሰው ልጆች በሙሉ የሚወዷቸው ወላጆች መሆን ይችሉ ነበር። ያም ሆኖ ነገሮች እንደታሰበው ሳይሆኑ ቀሩ።

የመንፈስ ቅዱስን ሚና መገንዘብ

16. የመጀመሪያዎቹ ሰዎች ቢያምፁም ምን ተስፋ አለን?

16 አዳምና ሔዋን ከአመስጋኝነት በመነጨ ስሜት ፈጣሪያቸውን ከመታዘዝ ይልቅ በራስ ወዳድነት ተነሳስተው ዓመፁ። በዚህም የተነሳ ዘሮቻቸው በሙሉ ፍጽምና የጎደላቸው በመሆናቸው የአዳምና የሔዋን ጦስ ለእኛም ተርፏል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን የተከተሉት የተሳሳተ ጎዳና ያስከተለውን ጉዳት ሁሉ አምላክ እንዴት እንደሚያስተካክለው ይገልጻል። ቅዱሳን መጻሕፍት ይሖዋ የመጀመሪያ ዓላማውን እንደሚፈጽምም ይናገራሉ። ምድር ለዘላለም በሚኖሩ ደስተኛና ጤነኛ በሆኑ የሰው ልጆች ትሞላለች። (ዘፍ. 3:15) በዚህ አስደሳች ተስፋ ላይ ያለንን እምነት ይዘን ለመቀጠል የአምላክ ቅዱስ መንፈስ እርዳታ ያስፈልገናል።

17. ምን ዓይነት አስተሳሰብን ማስወገድ አለብን?

17 ይሖዋ መንፈስ ቅዱስን እንዲሰጠን መጸለይ ይኖርብናል። (ሉቃስ 11:13) እንዲህ ማድረጋችን ፍጥረት የአምላክ እጅ ሥራ ስለመሆኑ ያለን እምነት እንዲጠናከር ይረዳናል። በዛሬው ጊዜ በተሳሳተና መሠረተ ቢስ በሆነ ጽንሰ ሐሳብ ላይ የተመረኮዙ የአምላክ የለሽነትና የዝግመተ ለውጥ ፕሮፖጋንዳዎች እንደ አሸን እየፈሉ ነው። እንዲህ ያለው የተሳሳተ አስተሳሰብ ግራ እንዲያጋባን ወይም ተጽዕኖ እንዲያሳድርብን መፍቀድ አይኖርብንም። ክርስቲያኖች በሙሉ እንዲህ ያለውን የፕሮፖጋንዳዎች ውርጅብኝና ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚመጣውን የእኩዮች ተጽዕኖ ለመቋቋም ራሳቸውን ማዘጋጀት ይኖርባቸዋል።—ቆላስይስ 2:8ን አንብብ።

18. አጽናፈ ዓለምና የሰው ዘር ወደ ሕልውና የመጡት እንዴት እንደሆነ በምንመረምርበት ጊዜ የማሰብ ችሎታ ያለው ፈጣሪ መኖሩን ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆን ማስተዋል የጎደለው አካሄድ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

18 አጽናፈ ዓለምና የሰው ዘር ወደ ሕልውና የመጡት በፍጥረት መሆኑን የሚያሳዩ ማስረጃዎችን በቅን ልቦና መመርመራችን በመጽሐፍ ቅዱስና በአምላክ ላይ ያለንን እምነት እንደሚያጠናክርልን ምንም ጥርጥር የለውም። ብዙዎች፣ በሳይንስ ሊረጋገጥ ከሚችለው ውጪ ለአጽናፈ ዓለምና ለሰው ዘር መገኘት ምክንያት የሆነ ሌላ ኃይል አለ ብሎ ማሰብ ይከብዳቸዋል። ይሁንና ነገሮችን ከዚህ አንጻር  የምንመለከት ከሆነ አመለካከታችን ሳይዛባ ማስረጃዎቹን በሙሉ መርምረናል ማለት አይቻልም። ከዚህም በላይ ሥርዓት ባለውና በተደራጀ መልኩ እንዲሁም በዓላማ የተሠሩ “ስፍር ቍጥር የሌላቸው” ፍጥረታት መኖራቸውን የሚያሳየውን ግልጽ ማስረጃ ገሸሽ ማድረጋችን ነው። (ኢዮብ 9:10፤ መዝ. 104:25) ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን በፍጥረት ሥራ ላይ የዋለው ኃይል የአምላክ ቅዱስ መንፈስ እንደሆነና ይሖዋ ይህን መንፈስ ከፍተኛ የማሰብ ችሎታ የተንጸባረቀባቸውን ነገሮች ለመፍጠር እንደተጠቀመበት እርግጠኞች ነን።

መንፈስ ቅዱስና በአምላክ ላይ ያለን እምነት

19. አምላክ እንዳለና ነገሮችን ለማከናወን በቅዱስ መንፈሱ እንደሚጠቀም አንተ በግልህ እንድታምን የሚያደርግህ ምንድን ነው?

19 በአምላክ ለማመን እንዲሁም እሱን ለመውደድና ለእሱ ጥልቅ አክብሮት ለማዳበር ስለ ፍጥረት እያንዳንዱን ነገር ማወቅ አያስፈልገንም። ሁኔታው ከሰዎች ጋር ከምንመሠርተው ወዳጅነት ጋር ይመሳሰላል፤ ስለ አንድ ሰው እያንዳንዱን ነገር ማወቃችን ብቻ የግለሰቡ ወዳጆች እንድንሆን አያደርገንም። በሌላ በኩል ግን በሁለት ጓደኛሞች መካከል ያለው ግንኙነት እየተጠናከረ እንዲሄድ እርስ በርስ በደንብ መተዋወቅ እንዳለባቸው የታወቀ ነው። በአምላክ ላይ ያለንን እምነት በተመለከተም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ስለ ይሖዋ ይበልጥ እያወቅን ስንሄድ በእሱ ላይ ያለን እምነት እየተጠናከረ ይሄዳል። በእርግጥም ለጸሎቶቻችን መልስ ሲሰጠንና መመሪያዎቹን በሕይወታችን ውስጥ ተግባራዊ ማድረጋችን ያለውን ጥቅም ስንመለከት ስለ ይሖዋ መኖር ይበልጥ እርግጠኞች እንሆናለን። ይሖዋ በአካሄዳችን እንደሚመራን፣ ጥበቃ እንደሚያደርግልን፣ በአገልግሎታችን የምናደርገውን ጥረት እንደሚባርክልን እንዲሁም የሚያስፈልጉንን ነገሮች እንደሚሰጠን የሚያሳዩ በርካታ ማስረጃዎችን ስንመለከት ወደ እሱ ይበልጥ እየቀረብን እንሄዳለን። እነዚህ ነገሮች ሁሉ አምላክ እንዳለና ነገሮችን ለማከናወን በቅዱስ መንፈሱ እንደሚጠቀም የሚያረጋግጡ አሳማኝ ማስረጃዎች ናቸው።

20. (ሀ) አምላክ አጽናፈ ዓለምንና ሰውን የፈጠረው ለምንድን ነው? (ለ) በአምላክ ቅዱስ መንፈስ መመራታችንን ከቀጠልን ምን መብት እናገኛለን?

20 ይሖዋ በመንፈሱ እንደሚጠቀም የሚያሳየው ከሁሉ የላቀ ማስረጃ መጽሐፍ ቅዱስ ነው፤ ምክንያቱም ጸሐፊዎቹ “ከአምላክ የተቀበሉትን ትንቢት በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው [ተናግረዋል]”። (2 ጴጥ. 1:21) ቅዱሳን መጻሕፍትን በቁም ነገር ማጥናት ሁሉንም ነገሮች የፈጠረው አምላክ እንደሆነ ያለንን እምነት ያጠናክረዋል። (ራእይ 4:11) ይሖዋ ሁሉንም ነገር የፈጠረው ማራኪ በሆነው የፍቅር ባሕርይው ተነሳስቶ ነው። (1 ዮሐ. 4:8) እንግዲያው ሰዎች በሰማይ ስላለው አፍቃሪ አባታችንና ወዳጃችን እንዲያውቁ ለመርዳት የተቻለንን ሁሉ እናድርግ። እኛም በአምላክ መንፈስ መመራታችንን ከቀጠልን ስለ ይሖዋ ለዘላለም የመማር መብት እናገኛለን። (ገላ. 5:16, 25) ሁላችንም ስለ ይሖዋና ስለ ታላላቅ ሥራዎቹ መማራችንን እንዲሁም በመንፈስ ቅዱሱ ተጠቅሞ ሰማያትን፣ ምድርንና የሰው ልጆችን ሲፈጥር ያሳየውን ወደር የለሽ ፍቅር በሕይወታችን ውስጥ ማንጸባረቃችንን እንቀጥል!

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.5 ኢሳይያስ 40:26 (NW)፦ “ዓይናችሁን ወደ ላይ አንስታችሁ ተመልከቱ። እነዚህን ነገሮች የፈጠረ ማን ነው? ልክ እንደ ሠራዊት በየቁጥራቸው የሚመራቸው እሱ ነው፤ በየስማቸውም ይጠራቸዋል። ገደብ ከሌለው ብርቱ ጉልበቱና ከታላቅ ኃይሉ የተነሳ አንዳቸውም አይጎድሉም።”

^ አን.6 ስለ አንተ የሚያስብ ፈጣሪ ይኖር ይሆን? (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 24 እና 25⁠ን ተመልከት።

ልታብራራ ትችላለህ?

• ሰማይና ምድር አምላክ መንፈስ ቅዱሱን ስለሚጠቀምበት መንገድ ምን ያስተምሩናል?

• በአምላክ መልክ መፈጠራችን ምን አስገኝቶልናል?

• አጽናፈ ዓለምና የሰው ዘር ወደ ሕልውና የመጡት በፍጥረት መሆኑን የሚያሳዩ ማስረጃዎችን መመርመር ያለብን ለምንድን ነው?

• ከይሖዋ ጋር ያለንን ወዳጅነት በየትኞቹ መንገዶች ማጠናከር እንችላለን?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አጽናፈ ዓለም ሥርዓት ባለው መንገድ የተደራጀ መሆኑ ስለ ፍጥረት ምን ያስተምረናል?

[የሥዕሉ ምንጭ]

Stars: Anglo-Australian Observatory/David Malin Images

[በገጽ 8 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

በእነዚህ ሁሉ ፍጥረታት ላይ ዲ ኤን ኤ የሚሠራበት መንገድ የሚመሳሰለው እንዴት ነው?

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ስለ እምነትህ ለማስረዳት ተዘጋጅተሃል?