በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘መታዘዝ ከመሥዋዕት ይበልጣል’

‘መታዘዝ ከመሥዋዕት ይበልጣል’

 ‘መታዘዝ ከመሥዋዕት ይበልጣል’

የጥንቷ እስራኤል የመጀመሪያ ንጉሥ ሳኦል ነበር። ሳኦልን የመረጠው እውነተኛው አምላክ ቢሆንም ይህ ንጉሥ ከጊዜ በኋላ ታዛዥ ሳይሆን ቀርቷል።

ሳኦል የፈጸማቸው ስህተቶች ምን ነበሩ? እንዲህ ዓይነት ስህተቶችን ከመሥራት መቆጠብ ይችል ነበር? የእሱን ታሪክ መመርመራችን የሚጠቅመን እንዴት ነው?

ይሖዋ የመረጠውን ንጉሥ አሳወቀ

ሳኦል ንጉሥ ከመሆኑ በፊት ነቢዩ ሳሙኤል በእስራኤል ውስጥ የአምላክ ወኪል ሆኖ ያገለግል ነበር። አሁን ሳሙኤል አርጅቷል፤ ልጆቹ ደግሞ ታማኞች አይደሉም። በዚያ ላይ ደግሞ የእስራኤል ጠላቶች በብሔሩ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር እየዛቱ ነው። የእስራኤል ሽማግሌዎች ወደ ሳሙኤል ቀርበው የሚዳኛቸውና በጦርነት ወቅት የሚመራቸው ንጉሥ እንዲያነግሥላቸው ጠየቁት፤ ይሖዋም ሳኦልን መሪያቸው አድርጎ እንዲቀባው ነቢዩን ያዘዘው ሲሆን ሳኦልን በተመለከተ “ሕዝቤን ከፍልስጥኤማውያን እጅ ይታደጋል” በማለት ተናግሮ ነበር።—1 ሳሙ. 8:4-7, 20፤ 9:16

ሳኦል “ወጣት” እንዲሁም ‘መልከ ቀና’ ነበር። ከዚህም ባሻገር እንደ ትሕትና ያሉ ጥሩ ባሕርያት ነበሩት። ለምሳሌ ያህል፣ ሳኦል ሳሙኤልን እንዲህ በማለት ጠይቆት ነበር፦ “እኔ ከእስራኤል ነገዶች ውስጥ በጣም አነስተኛ ከሆነው ከብንያም ወገን አይደለሁምን? ጐሣዬስ ከብንያም ነገድ ጐሣዎች ሁሉ የሚያንስ አይደለምን? ታዲያ እንዲህ ያለውን ነገር ስለ ምን ትነግረኛለህ?” አባቱ ቂስ “ታዋቂ” ቢሆንም ሳኦል ራሱንም ሆነ ቤተሰቡን ከፍ አድርጎ የሚመለከት ሰው አልነበረም።—1 ሳሙ. 9:1, 2, 21

ሳሙኤል፣ ይሖዋ የመረጠውን የእስራኤል ንጉሥ ለሕዝቡ ባስታወቀበት ወቅት ሳኦል ምን እንዳደረገም እንመልከት። ሳሙኤል መጀመሪያ ላይ ሳኦልን የቀባው ለብቻው እያለ ሲሆን “እጅህ ማድረግ የምትችለውን ሁሉ አድርግ፤ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነውና” ብሎት ነበር። ከዚያም ነቢዩ ይሖዋ የመረጠውን ሰው ለማሳወቅ ሕዝቡን ሰበሰበ። ይሁንና ሳሙኤል፣ የተመረጠውን ንጉሥ ማንነት ሲናገር ሳኦል ተፈልጎ ሊገኝ አልቻለም። ዓይናፋር በመሆኑ ተደብቆ ነበር። በመጨረሻም ሳኦል የት እንዳለ ይሖዋ ከገለጸ በኋላ ንጉሥ መሆኑ ታወጀ።—1 ሳሙ. 10:7, 20-24

በውጊያ አውድማ ላይ

ሳኦል ንጉሥ ሆኖ ሲቀባ ለዚህ ቦታ ብቃት ያለው መሆኑን የተጠራጠሩ ሰዎች ነበሩ፤ ብዙም ሳይቆይ ግን ሳኦል እነዚህን ሰዎች አሳፍሯቸዋል። አሞናውያን በአንዲት የእስራኤል ከተማ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር በተነሱ ጊዜ “የእግዚአብሔር መንፈስ [በሳኦል ላይ] በኀይል ወረደበት።” ሳኦል ብቃት እንዳለው በሚያሳይ መንገድ ሠራዊቱን ሰብስቦ ካደራጀ በኋላ በአሞናውያን ላይ በመዝመት ድል ነሳቸው። ይሁንና ሳኦል ይህን ድል ያገኘው  በራሱ ሳይሆን በአምላክ ኃይል መሆኑን ገልጿል፤ “ይህ ዕለት እግዚአብሔር እስራኤልን የታደገበት ቀን” እንደሆነ ተናግሯል።—1 ሳሙ. 11:1-13

ሳኦል ጥሩ ባሕርያት የነበሩት ከመሆኑም በላይ የአምላክ በረከት አልተለየውም። ይሖዋ ኃያል አምላክ መሆኑንም ተገንዝቦ ነበር። ያም ሆኖ እስራኤላውያንም ሆኑ ንጉሣቸው ስኬታማ መሆናቸው የተመካው በጣም አስፈላጊ የሆነ አንድ ባሕርይ በማዳበራቸው ላይ ነበር። ሳሙኤል ለእስራኤል ሕዝብ እንዲህ ብሏቸዋል፦ “እግዚአብሔርን የምትፈሩና የምታመልኩ፣ የምትታዘዙትና በትእዛዛቱ ላይ የማታምፁ ከሆነ፣ እንዲሁም እናንተና በእናንተ ላይ የነገሠው ንጉሥ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ከተከተላችሁ መልካም ይሆንላችኋል።” እስራኤላውያን ለአምላክ ታማኞች ከሆኑ ስለ ምን ነገር እርግጠኞች መሆን ይችሉ ነበር? ሳሙኤል እንዲህ ብሏቸዋል፦ “እግዚአብሔር የራሱ ሕዝብ ያደርጋችሁ ዘንድ ስለ ወደደ፣ ስለ ታላቅ ስሙ ሲል እግዚአብሔር ሕዝቡን አይተውም።”—1 ሳሙ. 12:14, 22

የአምላክን ሞገስ ለማግኘት ቁልፉ ታዛዥነት ነበር፤ ዛሬም ቢሆን ታዛዥነት አስፈላጊ ነው። የይሖዋ አገልጋዮች መመሪያዎቹን ሲታዘዙ ይሖዋ ይባርካቸዋል። ይሁን እንጂ ይሖዋን ለመታዘዝ አሻፈረን ቢሉስ?

“የማይገባህን አደረግህ”

ቀጥሎም ሳኦል በፍልስጥኤማውያን ላይ እርምጃ የወሰደ ሲሆን በዚህም የተነሳ ፍልስጥኤማውያን እስራኤላውያንን ለመውጋት በቁጣ ተነሱ። “እንደ ባሕር አሸዋ የበዛ ሰራዊት” ሳኦልን ለመውጋት ተሰበሰበ። “እስራኤላውያን፣ ያሉበት ሁኔታ እጅግ የሚያሠጋ መሆኑንና ሰራዊታቸውም በከባድ ጭንቀት ውስጥ መግባቱን ባዩ ጊዜ፣ በየዋሻውና በየቍጥቋጦው፣ በየዐለቱ መካከልና በየገደሉ እንዲሁም በየጕድጓዱ ሁሉ ተደበቁ።” (1 ሳሙ. 13:5, 6) ሳኦል በዚህ ጊዜ ምን ያደርግ ይሆን?

ሳሙኤልና ሳኦል በጌልገላ ለመገናኘት ቀጠሮ የነበራቸው ሲሆን በዚያም ሳሙኤል ለይሖዋ መሥዋዕት እንደሚያቀርብ ተነጋግረው ነበር። ሳኦል በቀጠሮው መሠረት ሳሙኤልን ቢጠብቀውም ነቢዩ ዘገየ፤ የሳኦል ሠራዊት ደግሞ መበታተን ጀመረ። በዚህም ምክንያት ሳኦል መሥዋዕቱን ራሱ አቀረበው። ልክ መሥዋዕቱን አቅርቦ እንዳበቃ ሳሙኤል መጣ። ሳሙኤል ሳኦል ያደረገውን ሲሰማ እንዲህ አለው፦ “የማይገባህን አደረግህ፤ አምላክህ እግዚአብሔር የሰጠህን ትእዛዝ አልጠበቅህም፤ ጠብቀኸው ቢሆን ኖሮ፣ መንግሥትህን በእስራኤል ላይ ለዘላለም ባጸናልህ ነበር፤ አሁን ግን መንግሥትህ አይጸናም፤ እነሆ፣ እግዚአብሔር እንደ ልቡ የሚሆንለትን ሰው አግኝቶአል፤ አንተ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ባለመጠበቅህም፣ እርሱን የሕዝቡ መሪ አድርጎ መርጦታል።”—1 ሳሙ. 10:8፤ 13:8, 13, 14

ሳኦል፣ ሳሙኤል መሥዋዕቱን ለማቅረብ እስኪመጣ ድረስ እንዲጠብቅ አምላክ የሰጠውን ትእዛዝ በመጣስ የማይገባውን ያደረገ ሲሆን ይህም እምነት እንዳልነበረው የሚያሳይ ነበር። ሳኦል የወሰደው እርምጃ የእስራኤል ሠራዊት አዛዥ የነበረው ጌዴዎን ካደረገው ነገር ምንኛ የተለየ ነው! ይሖዋ የሠራዊቱን ቁጥር ከ32,000 ወደ 300 እንዲቀንስ ጌዴዎንን አዞት ነበር፤ ጌዴዎንም እንደታዘዘው አድርጓል። ለምን? በይሖዋ ላይ እምነት ስለነበረው ነው። ጌዴዎን 135,000 የሚሆነውን ወራሪ ሠራዊት በአምላክ እርዳታ ድል አድርጓል። (መሳ. 7:1-7, 17-22፤ 8:10) ይሖዋ ሳኦልንም መርዳት ይችል ነበር። ሳኦል ባለመታዘዙ ምክንያት ፍልስጥኤማውያን እስራኤልን ወረሩ።—1 ሳሙ. 13:17, 18

እኛስ ችግሮች ሲያጋጥሙን ውሳኔ የምናደርገው እንዴት ነው? እምነት የሌለው ሰው መለኮታዊ መመሪያዎችን ችላ ማለት የተሻለ ሊመስለው ይችላል። ሳኦል፣ ሳሙኤል ከመምጣቱ በፊት የወሰደው እርምጃ ትክክል እንደሆነ ተሰምቶት ሊሆን ይችላል። ይሁንና የአምላክን ሞገስ ለማግኘት የሚፈልጉ ሰዎች ውሳኔ በሚያደርጉበት ጊዜ ሊከተሉት የሚገባው ትክክለኛ አካሄድ ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያዎች መከተል ነው።

ይሖዋ ሳኦልን ናቀው

ሳኦል አማሌቃውያንን ለማጥፋት ባደረገው ዘመቻም ሌላ ከባድ ስህተት ፈጽሟል። እስራኤላውያን ከግብፅ በወጡበት ወቅት አማሌቃውያን ያለ ምንም ምክንያት እስራኤልን በመውጋታቸው አምላክ እነዚህን ሕዝቦች እንዲጠፉ ፈርዶባቸው ነበር። (ዘፀ. 17:8፤ ዘዳ. 25:17, 18) ከዚህም በላይ በመሳፍንት ዘመን አማሌቃውያን ከሌሎች ሕዝቦች ጋር ተደርበው በአምላክ ምርጥ ሕዝብ ላይ ጥቃት ሰንዝረው ነበር። (መሳ. 3:12, 13፤ 6:1-3, 33) በዚህም የተነሳ ይሖዋ አማሌቃውያንን  ሊቀጣቸው ስለፈለገ ይህን ሕዝብ እንዲያጠፋ ሳኦልን አዝዞት ነበር።—1 ሳሙ. 15:1-3

ሳኦል ግን ክፉዎቹን አማሌቃውያን ሙሉ በሙሉ እንዲያጠፋቸውና ንብረቶቻቸውንም እንዲያወድም ይሖዋ የሰጠውን መመሪያ ከመታዘዝ ይልቅ ንጉሣቸውንና ምርጥ ምርጡን እንስሳት ማርኮ አመጣ። ሳኦል ይህን ያደረገው ለምን እንደሆነ ሳሙኤል ሲጠይቀው ምን ምላሽ ሰጠ? ሳኦል “ሰራዊቱ ከአማሌቃውያን ማርከው ያመጧቸው ናቸው፤ ምርጥ ምርጦቹ በጎችና በሬዎች ለእግዚአብሔር ለአምላክህ መሥዋዕት እንዲሆኑ ሳይገድሉ የተዉአቸው ናቸው” በማለት ጥፋቱን በሌሎች ለማላከክ ሞከረ። ሳኦል እንስሳቱን ማርኮ ያመጣቸው መሥዋዕት ሊያደርጋቸው አስቦ ሆነም አልሆነ አምላክን ሳይታዘዝ ቀርቷል። ሳኦል እንደ ቀድሞው ‘በዐይኑ ፊት ታናሽ’ አልነበረም። በመሆኑም የአምላክ ነቢይ፣ ሳኦል አምላክን እንዳልታዘዘ በግልጽ ነገረው። ከዚያም እንዲህ አለው፦ “ለእግዚአብሔር ቃል በመታዘዝ ደስ የሚለውን ያህል፣ እግዚአብሔር፣ በሚቃጠል ቍርባንና መሥዋዕት ደስ ይለዋልን? እነሆ! መታዘዝ ከመሥዋዕት . . . ይበልጣል። . . . አንተ የእግዚአብሔርን ቃል ስለ ናቅህ፣ እርሱም ንጉሥ እንዳትሆን ንቆሃል።”—1 ሳሙ. 15:15, 17, 22, 23

ይሖዋ ቅዱስ መንፈሱንና በረከቱን ከእስራኤል የመጀመሪያ ንጉሥ ሲወስድበት ሳኦልን “ክፉ መንፈስ” ያሠቃየው ጀመር። ሳኦል፣ ይሖዋ ከጊዜ በኋላ ንግሥናውን የሰጠውን ዳዊትን በጥርጣሬ ዓይን መመልከት የጀመረ ሲሆን በእሱ ላይ ቅናት አደረበት። ይህ ንጉሥ በተደጋጋሚ ጊዜያት ዳዊትን ለመግደል ሞክሯል። ሳኦል “እግዚአብሔር ከዳዊት ጋር እንደ ሆነ” ሲመለከት “እስከ ዕድሜውም ፍጻሜ ድረስ ጠላቱ” እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። ሳኦል ዳዊትን አድኖ ለመያዝ ከፍተኛ ጥረት ያደረገ ሲሆን 85 ካህናትንና ሌሎች ሰዎችን እንኳ አስገድሏል። ይሖዋ ሳኦልን መተዉ ምንም አያስገርምም!—1 ሳሙ. 16:14፤ 18:11, 25, 28, 29፤ 19:10, 11፤ 20:32, 33፤ 22:16-19

ፍልስጥኤማውያን እንደገና እስራኤልን ለማጥቃት ሲመጡ ሳኦል እርዳታ ለማግኘት ወደ መናፍስት ጠሪዎች ቢሄድም ያሰበው አልተሳካለትም። በቀጣዩ ቀን በውጊያ ላይ እንዳለ ከባድ ጉዳት የደረሰበት ሲሆን በዚያም የራሱን ሕይወት አጠፋ። (1 ሳሙ. 28:4-8፤ 31:3, 4) ታዛዥ ያልሆነውን የእስራኤል የመጀመሪያ ንጉሥ በተመለከተ ቅዱሳን መጻሕፍት እንዲህ ይላሉ፦ “ሳኦል እግዚአብሔርን ስላልታዘዘ ሞተ፤ የእግዚአብሔርን ቃል አልጠበቀም፤ ይልቁንም ከሙታን ጠሪ ምክርን ጠየቀ፤ ይህን ከእግዚአብሔር አልጠየቀም።”—1 ዜና 10:13, 14

ሳኦል የተወው መጥፎ ምሳሌ ለይሖዋ ማንኛውንም መሥዋዕት ከማቅረብ ይልቅ መታዘዝ የተሻለ መሆኑን በግልጽ ያሳያል። ሐዋርያው ዮሐንስ “አምላክን መውደድ ማለት ትእዛዛቱን መጠበቅ ማለት ነውና፤ ትእዛዛቱ ደግሞ ከባዶች አይደሉም” በማለት ጽፏል። (1 ዮሐ. 5:3) ከአምላክ ጋር ያለን ወዳጅነት ዘላቂ መሆኑ እሱን በመታዘዛችን ላይ የተመካ ነው፤ ይህ መቼም ቢሆን ልንዘነጋው የማይገባ መሠረታዊ ሐቅ ነው።

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሳኦል መጀመሪያ ላይ ትሑት መሪ ነበር

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሳሙኤል ለሳኦል ‘መታዘዝ ከመሥዋዕት ይበልጣል’ ያለው ለምን ነበር?