በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ባርቅ በእምነት አንድን ኃያል ሠራዊት ድል አደረገ

ባርቅ በእምነት አንድን ኃያል ሠራዊት ድል አደረገ

ባርቅ በእምነት አንድን ኃያል ሠራዊት ድል አደረገ

ከጠላት ሠራዊት ጋር ፊት ለፊት ተፋጠሃል እንበል። በዘመኑ ምርጥ የሚባለውን የጦር መሣሪያ የታጠቁ ሲሆን ይህን መሣሪያ ከመጠቀምም ወደኋላ አይሉም። አንተና አብረውህ ያሉት ወታደሮች ግን በእነሱ ዓይን ስትታዩ እዚህ ግቡ የምትባሉ አይደላችሁም።

እስራኤል በመሳፍንት ትተዳደር በነበረበት ዘመን ባርቅ፣ ዲቦራና 10, 000 የሚያህሉት እስራኤላውያን የገጠማቸው ሁኔታ ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ነበር። የጠላት ሠራዊቱ ሲሣራ በሚባለው የጦር አዛዥ የሚመሩት ከነዓናውያን ነበሩ። ከጦር መሣሪያዎቻቸው መካከል በጎማዎቻቸው ላይ ረጅም ስለታም ማጭድ የተገጠመላቸው ሰረገሎች ይገኙበት ነበር። የጦር አውድማው የታቦር ተራራና የቂሶን ወንዝ የሚገኝበት ሸለቆ ነው። በዚያ የተከናወነው ነገር ባርቅ በአርዓያነት የሚጠቀስ የእምነት ሰው እንደነበረ የሚያሳይ ነው። እስቲ ወደዚህ ፍጥጫ የመሩትን ሁኔታዎች እንመልከት።

እስራኤላውያን ለእርዳታ ወደ ይሖዋ ጮኹ

የመሳፍንት መጽሐፍ እስራኤላውያን በተደጋጋሚ ጊዜ ንጹሑን አምልኮ ስለመተዋቸውና በዚህም ሳቢያ ስለመጣባቸው መዘዝ ይናገራል። ችግር ላይ ሲወድቁ ይሖዋ ምሕረት እንዲያደርግላቸው ልባዊ ልመና የሚያቀርቡ ሲሆን አዳኝ በመሾም ነጻ ሲያወጣቸው ደግሞ እንደገና በእርሱ ላይ ያምጹ ነበር። ከሞዓባውያን ጭቆና ነጻ ያወጣቸው መስፍኑ ‘ናዖድ ከሞተ በኋላ የእስራኤል ልጆች’ እንደ ልማዳቸው “በእግዚአብሔር ፊት እንደ ገና ክፉ ሥራ ሠሩ።” እንዲያውም “አዲሶች አማልክትን መረጡ።” ይህስ ምን አስከተለባቸው? “እግዚአብሔርም በአሶር በነገሠው በከነዓን ንጉሥ በኢያቢስ እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፤ የሠራዊቱም አለቃ . . . ሲሣራ ነበረ። የእስራኤልም ልጆች ወደ እግዚአብሔር ጮኹ። [ሲሣራ] ዘጠኝ መቶ የብረት ሰረገሎች ነበሩትና፣ የእስራኤልንም ልጆች ሀያ ዓመት ያህል እጅግ ያስጨንቃቸው ነበር።”​—⁠መሳፍንት 4:​1-3፤ 5:​8

መጽሐፍ ቅዱስ በጊዜው በእስራኤል ስለነበረው ሁኔታ ሲናገር እንዲህ ይላል:- “[በዚያ ዘመን] መንገዶች ተቋረጡ፤ መንገደኞች በስርጥ መንገድ ይሄዱ ነበር። . . . ኃያላን በእስራኤል ዘንድ አነሱ።” (መሳፍንት 5:​6, 7) ሕዝቡ ከወራሪ ሰረገለኞቹ የተነሳ በጣም ፈርቶ ነበር። አንድ ምሑር እንዲህ ብለዋል:- “በእስራኤል ውስጥ ሕዝቡ የሚኖረው የፍርሃት ኑሮ ነበር። መላው ማኅበረሰብ በፍርሃት የተሽመደመደና ተስፋ የቆረጠ ይመስል ነበር።” በመሆኑም ቅስማቸው የተሰበረው እስራኤላውያን ከዚያ ቀደም ያደርጉት እንደነበረው እርዳታ ለማግኘት ወደ ይሖዋ ጮኹ።

ይሖዋ መሪ ሾመላቸው

የከነዓናውያን ጭቆና በእስራኤል ብሔራዊ ቀውስ አስከትሎ ነበር። አምላክ በወቅቱ ፍርዱንና መመሪያውን ለማስተላለፍ በነቢይቱ ዲቦራ ይጠቀም ነበር። በመሆኑም ይሖዋ በእስራኤል ምሳሌያዊት እናት ሆና የማገልገል መብት ለዲቦራ ሰጥቷታል።​—⁠መሳፍንት 4:​4፤ 5:​7

ዲቦራ ባርቅን አስጠርታ እንዲህ አለችው:- “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር:- ሄደህ ወደ ታቦር ተራራ ውጣ፣ ከአንተም ጋር ከንፍታሌምና ከዛብሎን ልጆች አሥር ሺህ ሰዎች ውሰድ፤ እኔም የኢያቢስን ሠራዊት አለቃ ሲሣራን ሰረገሎቹንም ሕዝቡንም ሁሉ ወደ አንተ ወደ ቂሶን ወንዝ እስባለሁ፣ በእጅህም አሳልፌ እሰጠዋለሁ ብሎ አላዘዘህምን?” (መሳፍንት 4:​6, 7) ዲቦራ ‘እግዚአብሔር አላዘዘህምን?’ በማለት ባርቅን የማዘዝ ሥልጣን እንደሌላት በግልጽ አሳይታለች። የእርሷ ኃላፊነት መለኮታዊውን ትእዛዝ ማስተላለፍ ብቻ ነበር። ታዲያ ባርቅ ምን ምላሽ ሰጠ?

“አንቺ ከእኔ ጋር ብትሄጂ እኔ እሄዳለሁ፤ አንቺ ግን ባትሄጂ እኔ አልሄድም” አላት። (መሳፍንት 4:​8) ባርቅ አምላክ የሰጠውን ኃላፊነት ለመቀበል ያንገራገረው ለምን ነበር? ፈርቶ ይሆን? ወይስ አምላክ የሰጠውን ተስፋ ተጠራጥሮ? በፍጹም። ባርቅ የተሰጠውን ሥራ አልቀበልም ወይም ይሖዋን አልታዘዝም አላለም። ከዚህ ይልቅ የሰጠው ምላሽ የአምላክን ትእዛዝ ብቻውን ለመፈጸም ብቁ እንዳልሆነ እንደተሰማው ያመለክታል። የአምላክ ወኪል የነበረችው ዲቦራ አብራው መሄዷ መለኮታዊ አመራር እንደማይለየው የሚያረጋግጥለት ከመሆኑም በላይ ለእሱም ሆነ ለሠራዊቱ ድፍረት ይጨምርላቸዋል። ስለዚህ ባርቅ ያስቀመጠው ቅድመ ሁኔታ የድክመት ምልክት ሳይሆን ጠንካራ እምነት እንዳለው የሚያሳይ ነበር።

ባርቅ የሰጠው ምላሽ ሙሴ፣ ጌዴዎንና ኤርምያስ ከሰጡት ምላሽ ጋር ተመሳሳይ ነበር። እነርሱም አምላክ የሰጣቸውን ተልእኮ ለመወጣት ብቃት እንደሌላቸው ተሰምቶአቸው ነበር። ቢሆንም እምነት እንደሌላቸው ተደርገው አልተቆጠሩም። (ዘጸአት 3:​11 እስከ 4:​17፤ 33:​12-17፤ መሳፍንት 6:​11-22, 36-40፤ ኤርምያስ 1:​4-10) ዲቦራ ስላሳየችው ዝንባሌስ ምን ሊባል ይቻላል? የበላይ ሆና ለመታየት አልሞከረችም። ከዚህ ይልቅ ቦታዋን የምታውቅ የይሖዋ አገልጋይ መሆኗን አሳይታለች። ባርቅን “በእውነት ከአንተ ጋር እሄዳለሁ” አለችው። (መሳፍንት 4:​9) ያለ ስጋት የምትኖርበትን ቤቷን ትታ ከባርቅ ጋር ለመዝመት ፈቃደኛ ሆነች። ዲቦራም በእምነቷና ባሳየችው ድፍረት በአርዓያነት የምትጠቀስ ናት።

ባርቅን በእምነት ተከተሉት

የእስራኤል ወታደሮች የሚሰበሰቡት ታቦር በሚባለው ግዙፍ ተራራ ላይ ነበር። ሥፍራው በአቅራቢያው የሚኖሩትን የንፍታሌምና የዛብሎን ነገዶች ለማሰባሰብ የሚያመች ነበር። ስለዚህ አምላክ እንዳዘዘው አሥር ሺህ ፈቃደኛ ተዋጊዎችና ዲቦራ ባርቅን ተከትለው ወደ ተራራው ወጡ።

ከባርቅ ጋር የሄዱት ሁሉ እምነት ማሳደር ይጠበቅባቸው ነበር። ይሖዋ በከነዓናውያን ላይ ድል እንደሚያቀዳጀው ለባርቅ ቃል ገብቶለት ነበር። ይሁንና እስራኤላውያን ምን ዓይነት የጦር መሣሪያ ነበ​ራቸው? መሳፍንት 5:​8 ‘በአርባ ሺህ እስራኤላውያን ዘንድ ጦርና ጋሻ አልታየም’ ይላል። ስለዚህ እስራኤላውያን የታጠቁት ቀላል መሣሪያ ብቻ ነበር። ጦርና ጋሻ ታጥቀው ቢሆን እንኳን ስለታም ማጭድ ከተገጠመባቸው ሰረገሎች ጋር ሲወዳደር ከቁጥር የሚገባ አልነበረም። ባርቅ ወደ ታቦር ተራራ መውጣቱን ሲሣራ ሲሰማ ሰረገሎቹና ወታደሮቹ በሙሉ ወደ ቂሶን ወንዝ እንዲሰበሰቡ አዘዘ። (መሳፍንት 4:​12, 13) ሲሣራ በዚህ ጦርነት የሚዋጋው ሁሉን ከሚችለው አምላክ ጋር መሆኑን አል​ተገነዘበም ነበር።

ባርቅ የሲሣራን ሠራዊት ድል አደረገ

ጦርነቱ የሚጀመርበት ሰዓት ሲደርስ ዲቦራ ባርቅን “እግዚአብሔር ሲሣራን በእጅህ አሳልፎ የሚሰጥበት ቀን ዛሬ ነውና ተነሣ፤ እነሆ፣ እግዚአብሔር በፊትህ ወጥቷል” አለችው። ባርቅና ሰዎቹ ከታቦር ተራራ በሸለቆው ውስጥ ወዳለው ሜዳማ ሥፍራ መውረድ ነበረባቸው። ነገር ግን የሲሣራ ሰረገሎች የሠፈሩበት ቦታ ወታደራዊ ጠቀሜታ ነበረው። በባርቅ ሠራዊት ውስጥ ብትሆን ኖሮ ምን ይሰማህ ነበር? መመሪያው የመጣው ከይሖዋ መሆኑን በማስታወስ ሳታንገራግር ትታዘዝ ነበር? ባርቅና አብረውት የነበሩት አሥር ሺህ ሰዎች ታዝዘዋል። “እግዚአብሔርም ሲሣራን ሰረገሎቹንም ሁሉ ሠራዊቱንም ሁሉ ከባርቅ ፊት በሰይፍ ስለት አስደነገጣቸው።”​—⁠መሳፍንት 4:​14, 15

ባርቅ በይሖዋ እርዳታ የሲሣራን ሠራዊት ድል አደረገ። የጦርነቱ ዘገባ ሁሉንም ነገር በዝርዝር አይገልጽም። ይሁን እንጂ የባርቅና የዲቦራ የድል መዝሙር ‘ሰማያትና ደመናት ውኃን አንጠባጠቡ’ ይላል። ኃይለኛ ዝናብ ዘንቦ የሲሣራ ሰረገሎች በጭቃ መያዛቸው ባርቅ በጦርነቱ ላይ የበላይነትን እንዲቀዳጅ ሳይረዳው አይቀርም። የከነዓናውያኑ ዋነኛ የማጥቂያ መሣሪያ የነበሩት ሰረገሎች ምንም ሳይፈይዱ ቀሩ። በጦርነቱ የተገደሉትን የሲሣራን ወታደሮች በሚመለከት መዝሙሩ “የቂሶን ወንዝ ጠርጎ ወሰዳቸው” ይላል።​—⁠መሳፍንት 5:​4, 21

ይህ ዘገባ ሊታመን የሚችል ነው? ቂሶን በክረምት ጊዜ የሚሞላና በበጋው ወራት አነስተኛ የውኃ ፍሰት ያለው ወንዝ ነው። እንዲህ ያሉ ወንዞች ኃይለኛ ዶፍ ከጣለ ወይም ያለማቋረጥ ለረጅም ሰዓት ከዘነበ በድንገት ይሞሉና አደገኛ ጎርፍ ይፈጥራሉ። በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በዚህ አካባቢ ለ15 ደቂቃ ብቻ የጣለ ዝናብ በፈጠረው ጭቃ ምክንያት የሠራዊቱ እንቅስቃሴ ተስተጓጉሎ እንደነበረ ይነገራል። በሚያዝያ 16, 1799 በናፖሊዮንና በቱርኮች መካከል በታቦር ተራራ ላይ ስለተደረገው ጦርነት የሚናገሩ ዘገባዎች “በርካታ የቱርክ ወታደሮች በቂሶን ጎርፍ በተጥለቀለቀው ሜዳ ላይ ሸሽተው ለማምለጥ ሲሞክሩ እንደሰጠሙ” ይናገራሉ።

አይሁዳዊው ታሪክ ጸሐፊ ፍላቪየስ ጆሴፈስ እንደተናገረው ከሆነ የሲሣራና የባርቅ ሠራዊቶች ሊጋጠሙ ሲሉ “ከሰማይ በረዶ የቀላቀለ ዶፍ ሲወርድ ውሽንፍሩ የከነዓናውያኑን እይታ ስለጋረደው ቀስታቸውና ወንጭፋቸው ምንም ሊፈይድላቸው አልቻለም።”

መሳፍንት 5:​20 “ከዋክብት ከሰማይ ተዋጉ፤ በአካሄዳቸውም ከሲሣራ ጋር ተዋጉ” ይላል። ከዋክብት ከሲሣራ ጋር የተዋጉት እንዴት ነው? አንዳንዶች ይህ አባባል መለኮታዊ እርዳታን እንደሚያመለክት ይናገራሉ። ሌሎች ደግሞ መላእክታዊ እርዳታን፣ የተወርዋሪ ኮከቦች መውደቅን ወይም ከንቱ ሆነው የቀሩትን ሲሣራ የታመነባቸውን የኮከብ ቆጠራ ትንበያዎች ያመለክታል ይላሉ። በዚህ ውጊያ ከዋክብት የተዋጉት እንዴት እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ስለማይገልጽ ጥቅሱ የእስራኤል ሠራዊት ያገኘውን አንድ ዓይነት መለኮታዊ እርዳታ ያመለክታል ብሎ መደምደሙ በቂ ይመስላል። ያም ሆነ ይህ እስራኤላውያን አጋጣሚውን ተጠቅመውበታል። “ባርቅም ሰረገሎችን. . . አባረረ፤ የሲሣራም ሠራዊት ሁሉ በሰይፍ ስለት ወደቀ፤ አንድ እንኳ አልቀረም።” (መሳፍንት 4:​16) የጦር አዛዡ ሲሣራስ ምን ሆነ?

ጨቋኙ “በሴት እጅ” ወደቀ

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሲሣራ ሲናገር “በአሶር ንጉሥም በኢያቢስና በቄናዊው በሔቤር ቤት መካከል ሰላም ነበረና ሲሣራ በእግሩ ሸሽቶ ወደ ቄናዊው ወደ ሔቤር ሚስት ወደ ኢያኤል ድንኳን ደረሰ” ይላል። ኢያኤል በድካም የዛለውን ሲሣራን ወደ ድንኳኗ አስገባችውና ወተት እንዲጠጣ ከሰጠችው በኋላ ሸፋፍና አስተኛችው። ከዚያም ኢያኤል በድንኳን የሚኖሩ ሰዎች ዘወትር የሚጠቀሙባቸውን መሣሪያዎች ማለትም ካስማና መዶሻ አመጣች። “ቀስ ብላም ወደ እርሱ ቀረበች፤ በጆሮግንዱ ካስማውን ቸነከረች፤ እርሱም ደክሞ አንቀላፍቶ ነበርና ካስማው ወደ መሬት ጠለቀ፣ እርሱም ሞተ።”​—⁠መሳፍንት 4:​17-21

ከዚያም ኢያኤል ባርቅን ልትቀበለው ወጥታ “ና የምትሻውንም ሰው አሳይሃለሁ” አለችው። ዘገባው በመቀጠል “ወደ እርስዋም ገባ፣ እነሆም፣ ሲሣራን ወድቆ ሞቶም አገኘው። ካስማውም ከጆሮግንዱ ውስጥ ነበረ” ይላል። ይህ ለባርቅ ምንኛ እምነት የሚያጠነክር ገጠመኝ ነበር! ቀድሞውንም ነቢይቱ ዲቦራ “እግዚአብሔር ሲሣራን በሴት እጅ አሳልፎ ይሰጣልና በዚህ በምትሄድበት መንገድ ለአንተ ክብር አይሆንም” ብላው ነበር።​—⁠መሳፍንት 4:​9, 22

ኢያኤል የፈጸመችው ነገር ክህደት አይደለም? ይሖዋ ከክህደት አልቆጠረውም። የባርቅና የዲቦራ የድል መዝሙር “በድንኳን ውስጥ ከሚኖሩ ሴቶች ይልቅ የተባረከች ትሁን” ይላል። ይህ መዝሙር ስለ ሲሣራ አሟሟት ተገቢ የሆነ አመለካከት እንዲኖረን ይረዳናል። የሲሣራ እናት የልጅዋን ከጦርነት መመለስ በጉጉት እንደምትጠባበቅ ተገልጿል። “ስለ ምን ለመምጣት ሰረገላው ዘገየ?” ብላ ጠየቀች። ሲሣራ በምርኮ ያገኙትን የሚያማምር ልብስና ሴቶች ለወታደሮቹ እያከፋፈለ ሊሆን እንደሚችል በመግለጽ “ብልሃተኞች ሴቶችዋ” ስጋቷን ሊያቃልሉላት ይጥራሉ። እንዲህ ይሏታል:- “ምርኮ አግኝተው የለምን? ተካፍለውስ የለምን? ለእያንዳንዱ ሰው ምርኮ አንዲት ወይም ሁለት ቆነጃጅት፤ ለሲሣራ ምርኮ ልዩ ልዩ ያለው ልብስ፣ በአንገትጌ ላይ በሁለት እጥፍ የተጠለፈ ዝንጉርጉር ልብስ።”​—⁠መሳፍንት 5:24, 28-30

እኛ የምናገኘው ጠቃሚ ትምህርት

ከባርቅ ታሪክ ጠቃሚ ትምህርት እናገኛለን። ይሖዋን የሚተዉ ሁሉ ችግርና መከራ እንደሚያገኛቸው አያጠራጥርም። ንስሐ ገብተው ወደ አምላክ የሚመለሱና በእርሱ የሚያምኑ ሰዎች ከተለያዩ ጭቆናዎች ነጻ ይወጣሉ። ታዲያ እኛም የታዛዥነት መንፈስ ማዳበር አይኖርብንም? አምላክ የሚፈልግብን ነገር ከሰብዓዊ አስተሳሰብ ጋር የማይጣጣም በሚመስልበት ጊዜም እንኳን እሱ የሚሰጠን መመሪያ ምን ጊዜም ዘላቂ ጥቅም የሚያስገኝልን እንደሆነ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። (ኢሳይያስ 48:​17, 18) ባርቅ ‘የባዕድ ጭፍሮችን ያባረረው’ በይሖዋ በመታመኑና መለኮታዊ መመሪያዎችን በመታዘዙ ነው።​—⁠ዕብራውያን 11:​32-34

የዲቦራና የባርቅ መዝሙር “አቤቱ፣ ጠላቶችህ ሁሉ እንዲሁ ይጥፉ፤ ወዳጆችህ ግን ፀሐይ በኃይሉ በወጣ ጊዜ እንደሚሆን፣ እንዲሁ ይሁኑ” በሚሉ ልብ የሚነኩ ቃላት ይደመደማል። (መሳፍንት 5:​31) ይሖዋ የሰይጣንን ክፉ ዓለም ወደ ፍጻሜ ሲያመጣው እነዚህ ቃላት ምንኛ እውነት ይሆኑ!

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ ባርቅን ለማዝመት በዲቦራ ተጠቅሟል

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የቂሶን ወንዝ ሞልቶ ሲፈስ

[ምንጭ]

Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የታቦር ተራራ