በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምድር ገነት ትሆናለች ብሎ ለማመን የሚያስችል ማስረጃ አለ?

ምድር ገነት ትሆናለች ብሎ ለማመን የሚያስችል ማስረጃ አለ?

ምድር ገነት ትሆናለች ብሎ ለማመን የሚያስችል ማስረጃ አለ?

ምድር ወደፊት ገነት ትሆናለች ብለው የሚያምኑት ሰዎች ቁጥራቸው ጥቂት ነው። እንዲያውም ብዙዎች ጨርሶ ትጠፋለች ብለው ያስባሉ። በብራያን ሊ ሞሊኖ የተዘጋጀው ዘ ሴክሪድ ኧርዝ የተባለው መጽሐፍ እንደሚለው ምድራችን ወደ ሕልውና የመጣችው በሚሊዮን ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት ‘በጠፈር ውስጥ በተከሰተ ከፍተኛ ፍንዳታ’ አማካኝነት ነው። ብዙዎች ሰው ራሱ ቀድሞ ካላጠፋት ምድርም ሆነች መላው ጽንፈ ዓለም ቀስ በቀስ “እያነሱ ሄደው ከፍተኛ ሙቀት ያለው ትንሽ ሉል” ይሆናሉ ብለው ያምናሉ።

በ17ኛው መቶ ዘመን የኖረው እንግሊዛዊ ባለቅኔ ጆን ሚልተን ምድር ትጠፋለች የሚል አመለካከት አልነበረውም። ፓራዳይዝ ሎስት በተባለው ግጥሙ ላይ አምላክ ምድርን የፈጠረው ለሰው ልጅ ገነት የሆነች መኖሪያ እንድትሆን ብሎ እንደሆነ ጽፏል። ይህች የመጀመሪያዋ ገነት ጠፍታለች። ይሁን እንጂ ሚልተን ይህች ገነት ተመልሳ እንደምትቋቋም እንዲሁም አዳኝ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ቀን “ታማኝ የሰው ልጆችን እንደሚባርክና በሰማይ ወይም በምድር ተድላና ደስታ ወደሞላበት ሕይወት እንደሚያስገባቸው” ያምን ነበር። ሚልተን “የዚያን ጊዜ መላዋ ምድር ገነት ትሆናለች” በማለት በሙሉ ልብ ተናግሯል።

ገነት​—⁠በሰማይ ወይስ በምድር?

በርካታ ሃይማኖተኞች የሰው ልጆች በዚህች ምድር ላይ ለሚደርስባቸው ሥቃይና መከራ ወደፊት አንድ ዓይነት ማካካሻ ያገኛሉ በሚለው የሚልተን አስተሳሰብ ይስማማሉ። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለውን ማካካሻ የሚያገኙት የት ነው? ‘በሰማይ ወይስ በምድር?’ አንዳንዶች በምድር ላይ የሚለው ሐሳብ ጨርሶ አይታያቸውም። ሰዎች “ተድላና ደስታ” ሊያገኙ የሚችሉት ምድርን ትተው በሰማይ ላይ በሚገኝ መንፈሳዊ ዓለም ውስጥ መኖር ሲጀምሩ ብቻ ነው ይላሉ።

ኮኔል ማክዳኔል እና በርንሃርድ ላንግ የተባሉት ደራሲዎች ሄቨን​—⁠ኤ ሂስትሪ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ በሁለተኛው መቶ ዘመን የኖረው የሃይማኖት ምሑር ኢራኒየስ ገነት ዳግመኛ የምትቋቋመው “ርቆ በሚገኝ ሰማያዊ ዓለም ሳይሆን በምድር ላይ ነው” ብሎ ያምን ነበር ብለዋል። መጽሐፉ እንደሚለው እንደ ጆን ካልቪንና ማርቲን ሉተር ያሉ ሃይማኖታዊ መሪዎች ወደ ሰማይ ለመሄድ ተስፋ ቢያደርጉም “አምላክ ምድርን ዳግመኛ ያድሳታል” የሚል እምነትም ነበራቸው። የሌሎች ሃይማኖት ተከታዮችም ተመሳሳይ አመለካከት ነበራቸው። ማክዳኔልና ላንግ አክለው እንደተናገሩት አንዳንድ አይሁዳውያን አምላክ በቀጠረው ጊዜ በሰዎች ልጆች ላይ የሚደርሱት ችግሮች በሙሉ “እንደሚወገዱና በምድር ላይ በእርካታ የተሞላ ሕይወት መኖር እንደሚቻል” ያምኑ ነበር። ዚ ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ሚድል ኢስተርን ሚቶሎጂ ኤንድ ሪሊጅን እንደሚለው የጥንት ፋርሳውያንም “ምድር ቀድሞ ወደ ነበረችበት ተፈጥሯዊ ሁኔታ ተመልሳ ሰዎች ዳግመኛ በሰላም ይኖራሉ” የሚል እምነት ነበራቸው።

ታዲያ ምድር ወደፊት ገነት ትሆናለች የሚለው እምነት አሁን ለምን ጠፋ? ምድራዊ ሕይወታችን በሌላ ዓለም ለምናገኘው ሕይወት መሸጋገሪያ ብቻ ነው? ፊሎ የተባለው በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖረው አይሁዳዊ ፈላስፋ እንዳለው ምድራዊ ሕይወት ወደ መንፈሳዊው ዓለም በምናደርገው ጉዞ ላይ ያለ “አጭርና በአብዛኛው በመከራ የተሞላ ገጠመኝ” ነው? ወይስ አምላክ ምድርን ከፈጠረ በኋላ የሰው ልጆችን በገነት ውስጥ ሲያስቀምጣቸው ሌላ ዓላማ ነበረው? የሰው ዘር በዚሁ ምድር ላይ መንፈሳዊ ፍላጎቱ ተሟልቶለት በተድላና በደስታ የሚኖርበት ጊዜ ይመጣ ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ ለእነዚህ ጥያቄዎች የሚሰጠውን መልስ ለምን አትመረምርም? በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እንደሚያምኑት አንተም ምድር ዳግመኛ ገነት ትሆናለች የሚል መደምደሚያ ላይ ልትደርስ ትችላለህ።

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ባለቅኔው ጆን ሚልተን ገነት ዳግመኛ እንደምትቋቋም ያምን ነበር

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ምድር:- U.S. Fish & Wildlife Service, Washington, D.C./NASA; ጆን ሚልተን:- Leslie’s