በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ልጄን ትምህርት ቤት ማስገባት ይኖርብኛል?

ልጄን ትምህርት ቤት ማስገባት ይኖርብኛል?

ልጄን ትምህርት ቤት ማስገባት ይኖርብኛል?

ይህንን ጽሑፍ ማንበብ የማትችል ቢሆን ምን እንደሚሰማህ ለመገመት ትችላለህ? የአገርህን ብሔራዊ ቋንቋ መናገር ባትችልስ ኖሮ? ከዓለም ካርታ ላይ የትውልድ አገርህ የት ቦታ እንደምትገኝ ለይተህ መጠቆም ባትችል ኖሮ ምን ይሰማህ ነበር? በጣም ብዙ ልጆች በእንዲህ ያለ ሁኔታ ያድጋሉ። የእናንተስ ልጅ?

ልጃችሁን ትምህርት ቤት ማስገባት ይኖርባችኋልን? በብዙ አገሮች ውስጥ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት መማር ግዴታ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ ትምህርቱ የሚሰጠው ያለ ክፍያ ነው። ስለ ልጆች መብት የሚናገረው ድንጋጌ መደበኛ ትምህርት ከልጆች መሠረታዊ መብቶች መካከል አንዱ መሆኑን ይገልጻል። ዓለም አቀፋዊ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌም ተመሳሳይ አቋም አለው። ይሁን እንጂ በአንዳንድ አገሮች ትምህርት በነጻ የሚሰጥ ላይሆን ስለሚችል በወላጆች ላይ የኢኮኖሚ ጫና መፍጠሩ አይቀርም። እስቲ ልጆቻቸውን በመደበኛ ትምህርት ወይም በሌላ መንገድ ማስተማር በሚፈልጉ ወላጆች ቦታ ሆነን ይህን ጉዳይ በጥልቀት እንመርምረው።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ የተማሩ ሰዎች

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጠቀሱት የአምላክ አገልጋዮች ውስጥ አብዛኞቹ ማንበብና መጻፍ ይችሉ ነበር። የኢየሱስ ሐዋርያት የነበሩት ጴጥሮስና ዮሐንስ አይሁዳዊ ዓሣ አጥማጆች ቢሆኑም የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍትን የጻፉት በገሊላ አካባቢ በሚነገረው ቀበሌኛ ሳይሆን በግሪክኛ ነበር። a ወላጆቻቸው መሠረታዊ ትምህርት እንዲያገኙ አድርገው እንደነበር ከሁኔታዎቹ መረዳት ይቻላል። ተመሳሳይ ሁኔታ ከነበራቸው ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች መካከል እረኛው ዳዊት፣ ገበሬው አሞጽና፣ አናጢ እንደነበር የሚገመተው የኢየሱስ ግማሽ ወንድም ይሁዳ ይገኙበታል።

ኢዮብ ማንበብና መጻፍ የሚችል ሲሆን በስሙ የሚጠራው የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ መጠነኛ የሳይንስ እውቀት እንደነበረው ይጠቁማል። እንዲሁም በመጽሐፉ ውስጥ የሰፈሩት ኢዮብ የተናገራቸው ነገሮች ቅኔ ለበስ መሆናቸው ኢዮብ የሥነ ጽሑፍ ተሰጥኦ ሳይኖረው እንደማይቀር ያሳያሉ። በተጨማሪም በመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች የተጻፉ ሊሆኑ የሚችሉ ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስታወሻዎች የሰፈሩባቸው የሸክላ ስብርባሪዎች መገኘታቸው እነርሱም ማንበብና መጻፍ ይችሉ እንደነበር ይጠቁማሉ።

ትምህርት ለክርስቲያኖች አስፈላጊ ነው

ሁሉም ክርስቲያኖች አምላክን ለማስደሰት ከፈለጉ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀታቸው እያደገ መሄድ ይኖርበታል። (ፊልጵስዩስ 1:9-11፤ 1 ተሰሎንቄ 4:1) መጽሐፍ ቅዱስንና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን ማጥናታችን መንፈሳዊ እድገት እንድናደርግ ሊረዳን ይችላል። አምላክ ቃሉን በጽሑፍ ማስፈሩ አምላኪዎቹ በተቻለ መጠን የተማሩ እንዲሆኑ እንደሚጠብቅባቸው ያሳያል። መጽሐፍ ቅዱስን አንብበን መረዳታችን ምክሮቹን በሥራ ላይ ማዋል ቀላል እንዲሆንልን ያደርጋል። እርግጥ ነው፣ ሐሳቦቹን በሚገባ ተረድተን ልናሰላስልባቸው እንድንችል አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን ደጋግመን ማንበብ ሊያስፈልገን ይችላል።​—⁠መዝሙር 119:104፤ 143:5፤ ምሳሌ 4:7

የይሖዋ ሕዝቦች በየዓመቱ ‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ የሚዘጋጁ በርካታ ጠቃሚ ጽሑፎችን ያገኛሉ። (ማቴዎስ 24:45-47) እነዚህ ጽሑፎች የቤተሰብ ሕይወትን፣ የተለያዩ ባሕሎችን፣ ሃይማኖትን፣ ሳይንስንና ሌሎች ብዙ ርዕሰ ጉዳዮችን የሚዳስሱ ናቸው። ከሁሉም በላይ ደግሞ መንፈሳዊ ርዕሰ ጉዳዮችን በማንሳት ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክርም ይሰጣሉ። ልጆቻችሁ ማንበብ የማይችሉ ከሆነ በጣም ብዙ ጠቃሚ ትምህርቶች እንደሚያመልጣቸው የታወቀ ነው።

የሰውን ዘር ታሪክ ማጥናታችን ጠቃሚ ነው፤ ምክንያቱም የአምላክ መንግሥት ያስፈለገበትን ምክንያት ለመረዳት ያስችለናል። መሠረታዊ የጂኦግራፊ እውቀት መቅሰምም አስፈላጊ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንደ እስራኤል፣ ግብፅና ግሪክ ያሉ ብዙ አገሮችን ይጠቅሳል። ልጃችሁ ከዓለም ካርታ ላይ እነዚህ አገሮች የሚገኙበትን ቦታ ለይቶ መጠቆም ይችላል? የራሱን አገርስ ማመልከት ይችላል? አንድ ክርስቲያን ካርታ አንብቦ ቦታን መለየት አለመቻሉ በተመደበበት ክልል ውስጥ አገልግሎቱን የማከናወን አቅሙን ሊገድብበት ይችላል።​—⁠2 ጢሞቴዎስ 4:5

የጉባኤ መብቶች

ክርስቲያን ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች ከማንበብ ጋር የተያያዙ በርካታ ኃላፊነቶች አሏቸው። ለምሳሌ ያህል በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ የሚቀርቡ ክፍሎችን ይዘጋጃሉ። የጽሑፎችን አቅርቦትና መዋጮዎችን መዝግቦ መያዝ ያስፈልጋል። አንድ ወንድም ማንበብና መጻፍ የማይችል ከሆነ እነዚህን ኃላፊነቶች በአግባቡ መወጣት አስቸጋሪ ሊሆንበት ይችላል።

ፈቃደኛ ሠራተኞች በዓለም ዙሪያ በሚገኙ የቤቴል ቤቶች ውስጥ ያገለግላሉ። እነዚህ ሠራተኞች ከሌሎች ጋር ሐሳብ ለሐሳብ ተግባብተው ጽሑፎችን መተርጎምንና መሣሪያዎችን መጠገንን የመሳሰሉ ሥራዎችን በሚገባ ለመወጣት እንዲችሉ የሚኖሩበትን አገር ብሔራዊ ቋንቋ ማንበብና መጻፍ መቻል አለባቸው። ልጆችህ ወደፊት እንደዚህ ዓይነት መብቶችን ለማግኘት እንዲችሉ ብዙውን ጊዜ መደበኛ ትምህርት መቅሰም ያስፈልጋቸዋል። ልጆችህ ትምህርት ቤት መግባታቸው አስፈላጊ የሚሆንባቸው ሌሎች ምክንያቶችስ ምንድን ናቸው?

ድህነት እና አጉል እምነት

በድህነት የሚማቅቁ አንዳንድ ሰዎች ከድህነታቸው የሚላቀቁበት ምንም አማራጭ ላይኖራቸው ይችላል። ይሁን እንጂ በቂ ትምህርት ካለን እኛም ሆን ልጆቻችን ያለ ምክንያት በችግር ከመደቆስ ልንድን እንችላለን። ምንም ሳይማሩ የተሳካላቸው ሰዎች በጣት የሚቆጠሩ ናቸው። ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ገቢ ባላቸው ቤተሰቦች ውስጥ ልጆች አልፎ ተርፎም ወላጆች የሕክምና እርዳታ ለማግኘት ባለመቻላቸው ምክንያት ይሞታሉ። ምንም ያልተማሩ ወይም በቂ ትምህርት ያላገኙ ሰዎች በተመጣጠነ ምግብ ወይም በመኖሪያ ቤት እጦት ሲቸገሩ ማየት የተለመደ ነው። ትምህርት ወይም ቢያንስ ማንበብና መጻፍ መቻል ለእነዚህ ችግሮች መፍትሔ ሊያስገኝ ይችል ነበር።

በተጨማሪም ትምህርት በአጉል እምነት የመታለልን አጋጣሚ ይቀንሳል። እርግጥ ነው፣ አጉል እምነት በተማሩም ሆነ ባልተማሩ ሰዎች ዘንድ ተስፋፍቶ ይገኛል። ቢሆንም ያልተማሩ ሰዎች የአጉል እምነቶችን ስውር ደባ የሚያጋልጡ ጽሑፎችን ማንበብ ስለማይችሉ ከተማሩት ይበልጥ በቀላሉ ሊታለሉና ሊበዘበዙ ይችላሉ። በዚህ የተነሳ በቀላሉ በአጉል እምነት ተታልለው አንድ መናፍስታዊ ፈዋሽ ተአምራዊ ፈውሶችን ያከናውናል ብለው ሊያምኑ ይችላሉ።​—⁠ዘዳግም 18:10-12፤ ራእይ 21:8

የትምህርት ዓላማ ሥራ ለማግኘት ብቻ አይደለም

ብዙዎች የትምህርት ዋነኛ ዓላማ ገንዘብ ለማግኘት እንደሆነ ይሰማቸዋል። ሆኖም አንዳንድ የተማሩ ሰዎች ጭምር ሥራ አጥ አሊያም መሠረታዊ ፍላጎቶቻቸውን ለማሟላት የሚያስችል በቂ ገቢ የሌላቸው ናቸው። በዚህም የተነሳ አንዳንድ ወላጆች ልጆችን ትምህርት ቤት ማስገባት ምንም ፋይዳ እንደሌለው ይሰማቸው ይሆናል። ይሁን እንጂ አንድ ልጅ ትምህርት የሚማረው ገንዘብ ለማግኘት ብቻ ሳይሆን ለሕይወቱ የሚጠቅመውን እውቀት ለመቅሰም ነው። (መክብብ 7:12) አንድ ሰው የአገሩን ብሔራዊ ቋንቋ ማንበብና መጻፍ የሚችል ከሆነ ሐኪሞች፣ የመንግሥት ባለ ሥልጣናትና የባንክ ባለሙያዎች ፊት ቀርቦ ፍርሃት ሳይሰማው ጉዳዩን በቀላሉ ማስፈጸም ይችላል።

በአንዳንድ አገሮች ወላጆች ፊደል ያልቆጠሩ ልጆቻቸውን በግንበኝነት፣ በዓሣ አጥማጅነት፣ በስፌት ወይም በሌላ ዓይነት ሙያ እንዲሰለጥኑ በማሰብ ለሌሎች ሰዎች አሳልፈው ይሰጧቸዋል። አንድ ዓይነት የእጅ ሙያ መማር ጠቃሚ እንደሆነ አይካድም፤ ቢሆንም እነዚህ ልጆች ትምህርት ቤት ሳይገቡ ቢያድጉ በኋላ ማንበብና መጻፍ የሚማሩበት አጋጣሚ ላያገኙ ይችላል። በመጀመሪያ መሠረታዊ ትምህርት ቀስመው ከዚያ በኋላ የእጅ ሙያ ቢማሩ በሥራቸው ላይ ሊደርስባቸው የሚችለውን ብዝበዛ ለማስቀረትና እርካታ የሚያገኙበት ሕይወት ለመምራት እንደሚችሉ አያጠራጥርም።

የናዝሬቱ ኢየሱስ አናጢ የነበረ ሲሆን ይህን የእጅ ሙያ የተማረው ከእንጀራ አባቱ ከዮሴፍ እንደሆነ ከሁኔታው መረዳት ይቻላል። (ማቴዎስ 13:55፤ ማርቆስ 6:3) ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ ገና በ12 ዓመት ዕድሜው በቤተ መቅደስ ከምሁራን ጋር ለመወያየት መቻሉ የተማረ እንደነበረ ያሳያል። (ሉቃስ 2:46, 47) ኢየሱስ የእጅ ሙያ መማሩ ሌሎች ትምህርቶችን ከመቅሰም አላገደውም።

ሴቶች ልጆችም መማር ይኖርባቸዋል?

አንዳንድ ወላጆች ወንዶች ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት አስገብተው ሴቶቹን ግን እቤት ያውሏቸዋል። አንዳንዶች ይህን የሚያደርጉት ሴቶች ልጆቻቸውን ማስተማር ወጪ እንደሚያበዛባቸውና እቤት ውለው እናታቸውን ቢረዱ የተሻለ እንደሚሆን አስበው ይሆናል። ይሁን እንጂ ትምህርት አለመማር አንዲትን ልጅ በእጅጉ ይጎዳታል። የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ያዘጋጀው አንድ ጽሑፍ እንደሚከተለው ይላል:- “ከድህነት ቀንበር መላቀቅ ከሚቻልባቸው ውጤታማ መንገዶች አንዱ ሴቶች ልጆች ትምህርት እንዲያገኙ ማድረግ መሆኑን በርካታ ጥናቶች አሳይተዋል።” (ፖቨርቲ ኤንድ ቺልድረን:- ሌሰንስ ኦቭ ዘ 90ቲስ ፎር ሊስት ዴቨሎፕድ ካንትሪስ) የተማሩ ሴቶች ችግሮችን መፍታትና ማስተዋል የታከለባቸው ውሳኔዎችን ማድረግ ይችላሉ፤ ይህም የሚጠቅመው መላውን ቤተሰብ ነው።

የሕፃናትን ሞት በሚመለከት በምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር በቤኒን የተደረገ አንድ ጥናት እንደሚያሳየው ያልተማሩ እናቶች ከወለዷቸው 1, 000 ልጆች ውስጥ 167ቱ ዕድሜያቸው አምስት ዓመት ሳይሞላ የሚሞቱ ሲሆን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ካላቸው እናቶች መካከል ግን ከ1, 000 ልጆች ውስጥ የሚሞቱት 38ቱ ናቸው። ዩኒሴፍ ከዚህ በመነሳት:- “በመላው ዓለም እንደሚታየው በቤኒንም የእናቶች መማር አለመማር በሚሞቱት ሕፃናት ቁጥር ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል” በማለት ደምድሟል። ስለዚህ ሴቶች ልጆቻችሁን ማስተማር በርካታ ጥቅሞች ሊኖሩት ይችላሉ።

መሠረተ ትምህርት ብቻውን በቂ ነውን?

አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች ማንበብ የማይችሉ የጉባኤውን አባላት ለማስተማር መሠረተ ትምህርት ይሰጣሉ። b እንዲህ ያለው ጠቃሚ ዝግጅት ሰዎች ብዙውን ጊዜ የአካባቢያቸውን ቋንቋ ማንበብ እንዲማሩ ይረዳቸዋል። ይሁን እንጂ ይህ ዝግጅት መደበኛ ትምህርትን ሙሉ በሙሉ ሊተካ ይችላል? መደበኛ ትምህርት የሚሰጥባቸው ትምህርት ቤቶች እያሉም ጉባኤው ልጆቻችሁን ማስተማር ይጠበቅበታል?

ማንበብና መጻፍ ለማስተማር የሚቋቋሙት ክፍሎች የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች በደግነት ተነሳስተው የሚያደርጓቸው ዝግጅቶች ቢሆኑም ዓላማቸው በልጅነታቸው ትምህርት ቤት ገብተው ለመማር አጋጣሚ ያላገኙ አዋቂዎችን መርዳት ነው። ወላጆቻቸው የትምህርትን አስፈላጊነት አልተገነዘቡም ይሆናል፤ አሊያም ባደጉበት አካባቢ ትምህርት ቤቶች አልነበሩም ይሆናል። እንዲህ ዓይነት ሰዎች በየጉባኤው በሚሰጠው የመሠረተ ትምህርት ፕሮግራም እርዳታ ማግኘት ይችላሉ። ቢሆንም እነዚህ ዝግጅቶች መደበኛ ትምህርትን የሚተኩ አይደሉም፤ እንዲሁም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ለመስጠት ተብለው የተቋቋሙ አይደሉም። እንደ ሳይንስ፣ ሒሳብና ታሪክ ያሉ የትምህርት ዓይነቶች በእነዚህ ክፍሎች ውስጥ አይሰጡም። በመደበኛው ሥርዓተ ትምህርት ውስጥ ግን የሚካተቱ ናቸው።

በአፍሪካ መሠረተ ትምህርት በአብዛኛው የሚሰጠው በአገሪቱ ብሔራዊ ቋንቋ ሳይሆን በአፍ መፍቻ ቋንቋዎች ነው። መደበኛ ትምህርት ግን ብዙውን ጊዜ የሚካሄደው በአገሪቱ ብሔራዊ ቋንቋ ነው። ይህም ተጨማሪ ጥቅሞች አሉት፤ ምክንያቱም በአገሪቱ ብሔራዊ ቋንቋ ብዙ መጻሕፍትንና የተለያዩ ዓይነት ጽሑፎችን ማግኘት ይቻላል። በጉባኤው የሚሰጠው መሠረተ ትምህርት ለመደበኛው ትምህርት እገዛ ቢያበረክትም ምትክ ተደርጎ መወሰድ አይኖርበትም። እንግዲያው እነዚህ ጥቅሞች ልጆች መደበኛ ትምህርት በሚሰጥባቸው ትምህርት ቤቶች ገብተው መማር እንደሚኖርባቸው አያሳዩም?

የወላጆች ኃላፊነት

የጉባኤውን መንፈሳዊ ፍላጎቶች በማሟላቱ ሥራ ግንባር ቀደም የሚሆኑ ወንዶች አርዓያ የሚሆኑ ክርስቲያኖች መሆን አለባቸው። ቤታቸውንና ልጆቻቸውን “በመልካም” ማስተዳደር አለባቸው። (1 ጢሞቴዎስ 3:4, 12) “በመልካም” ማስተዳደር ልጆቻችን ወደፊት እንቅፋት ሊሆኑባቸው የሚችሉ ነገሮችን ለማስወገድ እንዲችሉ አቅማችን የሚፈቅደውን ሁሉ ማድረግን ይጨምራል።

አምላክ ለክርስቲያን ወላጆች ትልቅ ኃላፊነት ሰጥቷቸዋል። ልጆቻቸውን በቃሉ ኮትኩተው ማሳደግ ያለባቸው ሲሆን ‘እውቀትን እንዲወዱ’ ሊረዷቸው ይገባል። (ምሳሌ 12:1፤ 22:6፤ ኤፌሶን 6:4) ሐዋርያው ጳውሎስ “ነገር ግን ለእርሱ ስለ ሆኑት ይልቁንም ስለ ቤተ ሰዎቹ የማያስብ ማንም ቢሆን፣ ሃይማኖትን የካደ ከማያምንም ሰው ይልቅ የሚከፋ ነው” በማለት ጽፏል። (1 ጢሞቴዎስ 5:8) ስለዚህ አሳቢነታችንን ከምንገልጽባቸው መንገዶች አንዱ ልጆቻችን ተገቢውን ትምህርት እንዲያገኙ ማድረግ ነው።

አንዳንድ ጊዜ ትምህርት ቤቶች በተማሪዎች በመጣበባቸው፣ በቂ በጀት ባለመኖሩ አሊያም መምህራኑ በሥራቸው ደስተኛ ባለመሆናቸው ወይም በቂ ደሞዝ ስለማይከፈላቸው የትምህርቱ ጥራት ሊቀንስ ይችላል። ስለዚህ ወላጆች ልጆቻቸው የሚማሩበትን ትምህርት ቤት ሁኔታ ትኩረት ሰጥተው መከታተላቸው ጠቃሚ ነው። በተለይ በእያንዳንዱ መንፈቀ ዓመት መጀመሪያ ላይ ከመምህራኑ ጋር ቢተዋወቁ አልፎ ተርፎም ልጆቻቸው ጎበዝ ተማሪ እንዲሆኑ እንዴት መርዳት እንደሚችሉ ምክር ቢጠይቁ ጥሩ ይሆናል። እንዲህ ማድረጉ መምህራኑ ሥራቸው አድናቆት እንደተቸረው እንዲሰማቸውና የልጆቹን የትምህርት ፍላጎት ለማሟላት ከበፊቱ የበለጠ እንዲጥሩ ሊያነሳሳቸው ይችላል።

ትምህርት በአንድ ልጅ እድገት ላይ ወሳኝ ሚና ይጫወታል። ምሳሌ 10:14 “ጠቢባን እውቀት ይሸሽጋሉ” በማለት ይናገራል። ይህ በተለይ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውቀትን የሚመለከት ነው። የይሖዋ ሕዝቦች ወጣቶችም ሆኑ አረጋውያን ሌሎችን በመንፈሳዊ ለመርዳትና ‘የእውነትን ቃል በቅንነት በመናገር የማያሳፍር ሠራተኛ ሆነው፣ የተፈተነውን ራሳቸውን ለእግዚአብሔር ለማቅረብ’ በሚቻለው መጠን በቂ እውቀት የቀሰሙ መሆን አለባቸው። (2 ጢሞቴዎስ 2:15፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:15) እንግዲያው ልጆችህ ትምህርት ቤት ገብተው መማር ይኖርባቸዋል? ጉዳዩ በአብዛኛው የሚመካው በምትኖርበት አገር ሁኔታ ላይ ቢሆንም ‘ትምህርት ቤት መግባት አለባቸው’ ብለህ እንደምትመልስ አያጠራጥርም። ይሁን እንጂ ክርስቲያን ወላጆች ‘ልጆቼ መማር ያስፈልጋቸዋልን?’ የሚለውን ወሳኝ ጥያቄም መመለስ ይኖርባቸዋል። የምትኖረው የትም ይሁን የት የዚህ ጥያቄ መልስ “አዎን!” የሚል መሆን አለበት ቢባል አትስማማም?

[የግርጌ ማስታወሻ]

a አፋቸውን የፈቱት በገሊላ አካባቢ በሚነገር የአረማይክ ወይም የዕብራይስጥ ቀበሌኛ ነበር። በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል የተባለውን መጽሐፍ (እንግሊዝኛ) ጥራዝ 1 ገጽ 144-6 ተመልከት።

b የታኅሣሥ 22, 2000 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ገጽ 8ና 9ን ተመልከት።

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ልጆችህ ትምህርት ቤት ገብተው መማር በማይችሉበት አካባቢ የምትኖር ከሆነ ምን ልታደርግ ትችላለህ?