በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለቤተሰብ | የወላጅ ሚና

ወጣት ልጃችሁ ውጥረትን እንድትቋቋም መርዳት

ወጣት ልጃችሁ ውጥረትን እንድትቋቋም መርዳት

ተፈታታኙ ነገር

ልጃችሁ በውጥረት ልትፈነዳ እንደሆነ ትናገራለች። ‘ገና በ13 ዓመቷ?’ ብላችሁ ትገረሙ ይሆናል። ‘አንድ ፍሬ ልጅ አይደለች እንዴ? በዚህ ዕድሜዋ ደግሞ ምን የሚያስጨንቃት ነገር አለ?’ ይህን ሐሳባችሁን ለልጃችሁ ከመናገራችሁ በፊት ግን በአሥራዎቹ ዕድሜ ለምትገኝ ልጅ፣ ሕይወት በጣም ከባድ መስሎ እንዲታያት ሊያደርጉ የሚችሉ አንዳንድ ምክንያቶችን እንመልከት።

ምክንያቱ ምንድን ነው?

አካላዊ ለውጦች። በጉርምስና ዕድሜ የሚመጣው ፈጣን እድገት አንዲትን ልጅ በጣም ሊያስጨንቃት ይችላል፤ በተለይ ደግሞ እድገቷ ከእኩዮቿ የፈጠነ ወይም የዘገየ በሚሆንበት ጊዜ ልትጨነቅ ትችላለች። አሁን ሃያ ዓመት የሆናት አና * እንዲህ ብላለች፦ “ቀድመው የጡት መያዣ ማድረግ ከጀመሩት ልጆች መካከል አንዷ እኔ ነበርኩ፤ ይህም በጣም አስጨንቆኝ ነበር። ከእኩዮቼ አንጻር ስታይ የተለየሁ ሰው እንደሆንኩ ይሰማኝ ነበር!”

ስሜታዊ ለውጦች። አሁን 17 ዓመት የሆናት ካረን እንዲህ ትላለች፦ “ቀኑን ሙሉ ደስ ብሎኝ ውዬ ማታ ላይ ዓይኔ እስኪጠፋ የማለቅስበት ምክንያት አይገባኝም ነበር። ችግሩ ምን እንደሆነ ግራ ይገባኝ ነበር። ስሜቴን መቆጣጠር አቅቶኝ ነበር።”

የወር አበባ መጀመር። ካትሊን የተባለች ወጣት “እናቴ አዘጋጅታኝ የነበረ ቢሆንም የመጀመሪያ የወር አበባዬን ባየሁበት ጊዜ በጣም ደንግጬ ነበር” ብላለች። “ሁልጊዜ እንደቆሸሽኩ ይሰማኝ ስለነበረ በቀን ውስጥ ደጋግሜ ሰውነቴን እታጠብ ነበር። በዚያ ላይ ደግሞ ሦስቱ ታላላቅ ወንድሞቼ ያሾፉብኝ ነበር። የወር አበባ ማየቴ አስቂኝ ነገር እንደሆነ ተሰምቷቸው ነበር።”

ማኅበራዊ ጫና። አሁን 18 ዓመት የሆናት መሪ የተባለች ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “ከ12 እስከ 14 ዓመት ባለው ዕድሜ ላይ በነበርኩበት ወቅት የእኩዮች ተጽዕኖ በጣም ከባድ ነበር። በትምህርት ቤቴ የነበሩ ልጆች፣ ከሌሎች ለየት ብሎ የሚታይን ማንኛውንም ልጅ በጣም ያስቸግሩት ነበር።” የአሥራ አራት ዓመቷ አኒታ ደግሞ “በእኔ ዕድሜ በጓደኞች ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት ትልቅ ነገር ነው፤ መገለል ደግሞ በጣም ያስከፋል” ብላለች።

ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

ልጃችሁ ውጥረት ስለፈጠረባት ነገር እንድትናገር አበረታቷት። መጀመሪያ ላይ ልጃችሁ ለመናገር ታመነታ ይሆናል። ቢሆንም ታገሷት፤ እንዲሁም “ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ፣ ለመናገር የዘገየ” እንዲሆን የሚያበረታታውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ተከተሉ።—ያዕቆብ 1:19

ጭንቀቷን አቅልላችሁ አትመልከቱት። ልጃችሁ የእናንተን ያህል የሕይወት ተሞክሮ እንደሌላት አስታውሱ፤ በመሆኑም ያጋጠማት ነገር ለእሷ በጣም ከባድ ሆኖ ሊታያት ይችላል። በዚያ ላይ ደግሞ ውጥረቷን እንዴት መቋቋም እንደምትችል አታውቅም።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ሮም 15:1

ልጃችሁ ከትምህርት ውጪ ባሉ ብዙ እንቅስቃሴዎች እንድትካፈል ጫና አታድርጉባት። ቲች ዩር ችልድረን ዌል የተባለው መጽሐፍ እንደሚለው ከሆነ በጣም የተጣበበ ፕሮግራም ያላቸው ልጆች “የውጥረት ምልክቶች በተለይም እንደ ራስ ምታትና የሆድ ሕመም የመሳሰሉ አካላዊ ችግሮች ብዙ ጊዜ ይታዩባቸዋል።”—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ፊልጵስዩስ 1:9, 10

ልጃችሁ በቂ እረፍት እንድታገኝ አድርጉ። አብዛኛውን ጊዜ ወጣቶች ችላ የሚሉት የመጀመሪያው ነገር እንቅልፍ ነው። ይሁን እንጂ ልጃችሁ በቂ እንቅልፍ ካላገኘች የማሰብ ችሎታዋም ሆነ ውጥረትን የመቋቋም አቅሟ ይዳከማል።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ መክብብ 4:6

ልጃችሁ ውጥረቷ ቀለል እንዲላት የሚረዱ ጤናማ መንገዶችን እንድታገኝ እርዷት። አንዳንድ ወጣቶች የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ውጥረታቸውን ይቀንስላቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስም “የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በጥቂቱ ይጠቅማል” ይላል። (1 ጢሞቴዎስ 4:8) ሌሎች ደግሞ የሚያጋጥሟቸውን ነገሮች ማስታወሻ ላይ ማስፈራቸው ስለ ጉዳዩ ተገቢውን አመለካከት ለመያዝ እንደሚረዳቸው ተናግረዋል። የ22 ዓመቷ ብሪታኒ እንዲህ ብላለች፦ “መፍትሔ ላገኝላቸው ያልቻልኳቸውን ችግሮች በማስታወሻዬ ላይ የምጽፍበት ወቅት ነበር። ይህም ስለ ችግሩ ያለኝን ስሜት በትክክል ለመረዳት ያስችለኛል፤ ከዚያ በኋላ ችግሩን መፍታት ወይም ጉዳዩን መተው ቀላል ይሆንልኛል።”

ምሳሌ ሁኗት። እናንተ ራሳችሁ ውጥረትን የምትቋቋሙት እንዴት ነው? ከአቅማችሁ በላይ ብዙ ነገሮችን ለማከናወን አስባችሁ ያንን ለመጨረስ ውጥረት ውስጥ ትገባላችሁ? በሕይወት ውስጥ ይበልጥ አስፈላጊ ለሆኑ ነገሮች ጊዜ ሳትሰጡ ራሳችሁን ከመጠን በላይ በሥራ በማስጠመድ እስክትዝሉ ድረስ ትሠራላችሁ? ፊልጵስዩስ 4:5 “ምክንያታዊነታችሁ በሰው ሁሉ ዘንድ የታወቀ ይሁን” ይላል። በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የምትገኘው ልጃችሁ የምታደርጉትን እንደምትመለከትና ጥሩም ይሁን መጥፎ የእናንተን ምሳሌ እንደምትከተል አትርሱ።

^ አን.6 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት ስሞች ተቀይረዋል።