በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ

ጊዜህን በአግባቡ መጠቀም የምትችለው እንዴት ነው?

ጊዜህን በአግባቡ መጠቀም የምትችለው እንዴት ነው?

አብዛኞቻችን ተጨማሪ ጊዜ ማግኘት ብንችል ደስ እንደሚለን የታወቀ ነው። ጊዜ ሁሉንም ሰው እኩል የሚያደርግ ነገር ነው ማለት ይቻላል፤ ምክንያቱም ባለሥልጣናትም ሆኑ ተራ ሰዎች ወይም ባለጠጎችም ሆኑ ድሆች በእኩል መጠን ያላቸው ነገር ነው። ከዚህም በላይ ሀብታሞችም ሆኑ ድሆች ጊዜን ማጠራቀም አይችሉም። ጊዜ፣ አንዴ ካለፈ ተመልሶ አይመጣም። በመሆኑም የተሻለው አካሄድ ያለንን ጊዜ በአግባቡ መጠቀም ነው። እንዴት? ብዙ ሰዎች ጊዜያቸውን በጥበብ እንዲጠቀሙ ያስቻሏቸውን አራት ዘዴዎች እስቲ እንመልከት።

ዘዴ 1፦ መደራጀት

ቅድሚያ የሚያሻቸውን ነገሮች ለይ። መጽሐፍ ቅዱስ “ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለይታችሁ [እወቁ]” የሚል ምክር ይሰጣል። (ፊልጵስዩስ 1:10) በጣም አስፈላጊ የሆኑ አሊያም ደግሞ ወዲያውኑ መደረግ ያለባቸውን ነገሮች በአእምሮህ በመያዝ፣ ልታደርጋቸው የሚገቡ ነገሮችን በዝርዝር ጻፍ። እርግጥ ነው፣ አንድ ነገር በጣም አስፈላጊ ቢሆንም ወዲያውኑ መደረግ ላይኖርበት ይችላል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ወዲያውኑ መደረግ ያለበት ነገር በጣም አስፈላጊ ላይሆን ይችላል። ለምሳሌ ለራት የሚሆን ምግብ መግዛት አስፈላጊ ቢሆንም ወዲያውኑ መደረግ ላይኖርበት ይችላል። በአንጻሩ ደግሞ የምትወደውን የቴሌቪዥን ፕሮግራም መመልከት የግድ አስፈላጊ የሚባል ነገር ባይሆንም በሰዓቱ መድረስ ካልቻልክ ሊያመልጥህ ይችላል። *

አስቀድመህ እቅድ አውጣ። መክብብ 10:10 “መጥረቢያ ቢደንዝ፣ ጫፉም ባይሳል፣ ብዙ ጕልበት ይጨርሳል፤ ብልኀት ግን ለውጤት ያበቃል” ይላል። ከዚህ የምናገኘው ትምህርት ምንድን ነው? ጊዜህን በጣም ውጤታማ በሆነ መንገድ መጠቀም እንድትችል አስቀድመህ እቅድ ማውጣት በምሳሌያዊ አነጋገር መጥረቢያህን መሳል ያስፈልግሃል። ጊዜና ጉልበት ከመጨረስ ሌላ ፋይዳ የሌላቸውን ያን ያህል አስፈላጊ ያልሆኑ ሥራዎች ለሌላ ጊዜ አስተላልፍ ወይም ተዋቸው። ሥራህን ቶሎ ጨርሰህ ጊዜ ከተረፈህ ቀጥሎ ልትሠራው ወዳሰብከው ነገር ማለፍ ትችላለህ። አስቀድሞ መጥረቢያውን እንደሚስል ብልኅ ሠራተኛ አንተም አስቀድመህ እቅድ በማውጣት ይበልጥ ውጤታማ መሆን ትችላለህ።

ኑሮህን ቀላል አድርግ። አስፈላጊ ያልሆኑ ወይም ጊዜ ከማባከን ውጭ ብዙም ጥቅም የሌላቸውን ጉዳዮች መተውን ልመድ። ብዙ ጉዳዮችን ለማከናወን የምትሞክርና ቀጠሮ የምታበዛ ከሆነ በራስህ ላይ የማያስፈልግ ጫና ከመጨመርህም ሌላ ደስታ ልታጣ ትችላለህ።

 ዘዴ 2፦ ጊዜ የሚያባክኑ ነገሮችን ማስወገድ

ዛሬ ነገ አትበል እንዲሁም ወላዋይ አትሁን። “ነፋስን የሚጠባበቅ አይዘራም፤ ደመናትንም የሚያይ አያጭድም።” (መክብብ 11:4) ከዚህ የምናገኘው ትምህርት ምንድን ነው? ዛሬ ነገ ማለት ጊዜህን ያባክናል እንዲሁም ውጤታማ እንዳትሆን ያደርጋል። ሁሉ ነገር ሙሉ በሙሉ እስኪስተካከል የሚጠብቅ ገበሬ መቼም ቢሆን ዘር መዝራትም ሆነ ምርት መሰብሰብ አይችልም። እኛም በተመሳሳይ በሕይወት ውስጥ ሊያጋጥሙ ስለሚችሉ ነገሮች እርግጠኛ መሆን አለመቻላችን ወላዋይ እንድንሆን ሊያደርገን ይችላል። አሊያም ደግሞ ውሳኔ ከማድረጋችን በፊት እያንዳንዷን ጥቃቅን ጉዳይ ማጣራት እንደሚያስፈልገን ይሰማን ይሆናል። እርግጥ ነው፣ ከበድ ያሉ ውሳኔዎችን ከማድረጋችን በፊት ሁኔታዎችን ማጣራትና በጥሞና ማሰብ ያስፈልገናል። ምሳሌ 14:15 “አስተዋይ . . . ርምጃውን ያስተውላል” ይላል። ይሁን እንጂ ከአብዛኞቹ ውሳኔዎቻችን ጋር በተያያዘ እርግጠኛ መሆን የማንችልባቸው ነገሮች መኖራቸው አይቀርም።—መክብብ 11:6

ፍጽምና መጠበቅ። ያዕቆብ 3:17 “ከላይ [ወይም ከአምላክ] የሆነው ጥበብ . . . ምክንያታዊ” እንደሆነ ይናገራል። እርግጥ ነው፣ ነገሮችን ጥሩ አድርገን ለማከናወን የምንፈልግ መሆኑ ጥሩ ነገር ነው። አንዳንድ ጊዜ ግን ከራሳችን ብዙ እንጠብቅ ይሆናል፤ ይህ ደግሞ ለብስጭት ሊዳርገን አልፎ ተርፎም ውጤታማ እንዳንሆን ሊያደርገን ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ አዲስ ቋንቋ የሚማር ሰው ስህተት ሊሠራ እንደሚችል አምኖ መቀበል ይኖርበታል፤ ደግሞም ከስህተቱ ትምህርት ያገኛል። ከራሱ ፍጽምና የሚጠብቅ ሰው ግን አንድን ነገር በተሳሳተ መንገድ ሊናገር እንደሚችል ማሰቡ በጣም ያስፈራዋል፤ ይህ ደግሞ ችሎታውን እንዳያሻሽል እንቅፋት ይሆንበታል። በሌላ በኩል ግን ከራሳችን በምንጠብቀው ነገር ረገድ ምክንያታዊ መሆናችን በጣም የተሻለ ነው! ምሳሌ 11:2 “በትሑት ዘንድ . . . ጥበብ ትገኛለች” ይላል። ከዚህም በላይ አቅማቸውን የሚያውቁና ትሑት የሆኑ ሰዎች በራሳቸው ላይ በጣም ጥብቅ አይሆኑም፤ እንዲሁም ሲሳሳቱ በራሳቸው ላይ ስቀው ማለፍ ይችላሉ።

“አንድ ነገር ስትገዛ የምትከፍለው ጊዜህን እንጂ ገንዘብህን አይደለም።”—ዋት ቱ ዱ ቢትዊን በርዝ ኤንድ ዴዝ

 ዘዴ 3፦ ሚዛንን መጠበቅና ከእውነታው ያልራቀ አመለካከት ማዳበር

በሥራና በመዝናኛ ረገድ ሚዛናዊ መሆን። “በድካምና ነፋስን በመከተል ከሚገኝ ሁለት ዕፍኝ ይልቅ፣ በርጋታ የሚገኝ አንድ ዕፍኝ ይሻላል።” (መክብብ 4:6) ብዙውን ጊዜ፣ ከመጠን በላይ ሥራ የሚወዱ ሰዎች “ሁለት እፍኝ” ማለትም ሁለት እጥፍ ደክመው የሚያገኙትን ነገር ማጣጣም አይችሉም። ይህ የሚሆነው ኃይላቸው ስለሚሟጠጥና ጊዜ ስለማይኖራቸው ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ሰነፍ ሰው “ሁለት እፍኝ” ወይም ሁለት እጥፍ ማረፍ ስለሚፈልግ ውድ ጊዜውን ያባክናል። መጽሐፍ ቅዱስ ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖረን ይኸውም በርትተን እንድንሠራ እና በሥራችን ውጤት እንድንደሰት ይመክራል። እንዲህ ያለው ደስታ “የእግዚአብሔር ስጦታ ነው።”—መክብብ 5:19

በቂ እንቅልፍ አግኝ። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ “በሰላም እተኛለሁ፤ አንቀላፋለሁም” ብሏል። (መዝሙር 4:8) ለአቅመ አዳም የደረሱ አብዛኞቹ ሰዎች፣ በየቀኑ ስምንት ሰዓት ገደማ መተኛት ይኖርባቸዋል፤ ይህም አካላቸውና አእምሯቸው በተገቢው መንገድ እንዲሠራ እንዲሁም ጥሩ ስሜት እንዲኖራቸው ይረዳቸዋል። እንቅልፍ አእምሯችን በደንብ እንዲሠራ ስለሚያደርግ በእንቅልፍ የምናሳልፈው ጊዜ እንደባከነ ሊቆጠር አይገባም፤ በቂ እንቅልፍ ማግኘት ትኩረታችንን ለማሰባሰብ እንዲሁም የማስታወስ ችሎታችንን ለማሻሻል ይረዳናል፤ ይህ ደግሞ ትምህርት የመቅሰም ብቃታችንን ይጨምርልናል። በአንጻሩ ግን በቂ እንቅልፍ አለማግኘት የመማር ችሎታን ከመቀነሱም በላይ ለአደጋዎችና ለስህተቶች ያጋልጣል፤ በተጨማሪም ብስጩ እንድንሆን አስተዋጽኦ ያደርጋል።

ልትደርስባቸው የምትችላቸው ግቦች አውጣ። “ለምኞት ከመገዛት ይልቅ ባለ ነገር መርካት ይሻላል።” (መክብብ 6:9 የታረመው የ1980 ትርጉም) ነጥቡ ምንድን ነው? ጠቢብ የሆነ ሰው ፍላጎቱ ወይም ምኞቱ (በተለይ ደግሞ ሊሳካ የማይችል ከሆነ) መላ ሕይወቱን እንዲቆጣጠርበት አይፈቅድም። በመሆኑም በሚያማልሉ ማስታወቂያዎች አይታለልም፤ ወይም ዱቤ ማግኘት ቀላል ስለሆነለት ብቻ በዱቤ አይገዛም። ከዚህ ይልቅ ሊያገኝ በሚችላቸው ነገሮች ማለትም “ባለ ነገር” ረክቶ መኖርን ይማራል።

 ዘዴ 4፦ በመልካም መርሆች መመራት

የምትመራባቸውን መርሆች መርምር። የምትመራባቸው መርሆች ጥሩ፣ አስፈላጊና ጊዜህን ልትሰጣቸው የሚገቡ ነገሮች የትኞቹ እንደሆኑ ለማወቅ ይረዱሃል። ሕይወትህን በቀስት ብንመስለው ቀስቱ ዒላማውን እንዲመታ የሚረዱህ የምትመራባቸው መርሆች ናቸው። ጥሩ መርሆች ካሉህ በሕይወትህ ውስጥ ቅድሚያ ልትሰጣቸው የሚገቡ ነገሮችን ለመወሰን እንዲሁም እያንዳንዱን ቀንና ሰዓት በአግባቡ ለመጠቀም ይረዱሃል። ታዲያ እንዲህ ያሉ መርሆችን ማግኘት የምትችለው ከየት ነው? ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ የላቀ ጥበብ እንደያዘ ስለሚገነዘቡ የሚመሩባቸውን መርሆች ለማግኘት ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ዘወር ይላሉ።—ምሳሌ 2:6, 7

የምትመራበት ዋነኛው መርህ ፍቅር ይሁን። ቆላስይስ 3:14 “ፍቅር ፍጹም የሆነ የአንድነት ማሰሪያ ነው” ይላል። በተለይ በቤተሰባችን ውስጥ ፍቅር ከሌለ እውነተኛ ደስታ ሊኖረን ብሎም ስሜታዊ ፍላጎታችን ሊሟላልን አይችልም። ይህን ሐቅ ችላ በማለት ሀብት ለማካበት ወይም በሙያቸው ለማደግ ቅድሚያ የሚሰጡ ሰዎች ራሳቸውን ለሐዘን ይዳርጋሉ። በእርግጥም፣ ልንመራበት የሚገባው ዋነኛ መርህ ፍቅር እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ የሚገልጸው ያለ ምክንያት አይደለም፤ ፍቅር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ጊዜያት የተጠቀሰውም ለዚህ ነው።—1 ቆሮንቶስ 13:1-3፤ 1 ዮሐንስ 4:8

መንፈሳዊ ፍላጎትህን ለማሟላት ጊዜ መድብ። ጄፍ የሚባል አንድ ሰው አፍቃሪ ሚስት፣ ሁለት ደስተኛ ልጆች፣ ጥሩ ወዳጆችና ከሕክምና ጋር የተያያዘ የሚያረካ ሥራ ነበረው። ይሁን እንጂ ሥራው፣ በሰዎች ላይ የሚደርሰውን ሥቃይና ሞት ለማየት ያስገድደው ነበር። በመሆኑም “ወደ ሕልውና የመጣነው በዚህ ሁኔታ እንድንኖር ነው?” እያለ ራሱን ይጠይቅ ነበር። አንድ ቀን፣ በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጁ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን አግኝቶ ሲያነብብ የሚያረኩ መልሶች አገኘ።

ጄፍ የተማራቸውን ነገሮች ለሚስቱና ለልጆቹ ነገራቸው፤ እነሱም ይበልጥ የማወቅ ፍላጎት አደረባቸው። በመሆኑም ይህ ቤተሰብ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረ፤ እንዲህ ማድረጋቸውም የተሻለ ሕይወት እንዲመሩና ጊዜያቸውን ይበልጥ በአግባቡ እንዲጠቀሙበት አስችሏቸዋል። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናታቸው ከመከራ ነፃ የሆነና ትርጉም ያለው ሕይወት አግኝተው ለዘላለም የመኖር ተስፋ እንዲኖራቸው አድርጓል።—ራእይ 21:3, 4

የጄፍ ተሞክሮ “በመንፈሳዊ ድሆች መሆናቸውን የሚያውቁ ደስተኞች ናቸው” በማለት ኢየሱስ የተናገረውን ሐሳብ ያስታውሰናል። (ማቴዎስ 5:3) አንተስ መንፈሳዊ ፍላጎትህን ለማሟላት የተወሰነ ጊዜ ለመመደብ ፈቃደኛ ነህ? እያንዳንዱን ቀን ብቻ ሳይሆን መላ ሕይወትህን በተሻለ መንገድ ለመጠቀም የሚያስችል ከዚህ የተሻለ አካሄድ እንደሌለ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ።

^ አን.5 በሚያዝያ 2010 ንቁ! ላይ የወጣውን “ተጨማሪ ጊዜ ለማግኘት የሚረዱ 20 መንገዶች” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።