በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክና ክርስቶስ ለሴቶች ምን አመለካከት አላቸው?

አምላክና ክርስቶስ ለሴቶች ምን አመለካከት አላቸው?

አምላክና ክርስቶስ ለሴቶች ምን አመለካከት አላቸው?

ይሖዋ አምላክ ለሴቶች ያለውን አመለካከት ሙሉ በሙሉ መረዳት የምንችለው እንዴት ነው? አንዱ መንገድ ኢየሱስ ክርስቶስ የነበረውን አመለካከትና ተግባር በመመርመር ነው፤ ኢየሱስ “የማይታየው አምላክ አምሳል” ከመሆኑም በላይ የአባቱን አመለካከት ፍጹም በሆነ መንገድ ያንጸባርቃል። (ቈላስይስ 1:15) ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ወቅት ሴቶችን የያዘበት መንገድ፣ ይሖዋና ኢየሱስ ሴቶችን እንደሚያከብሩና በዛሬው ጊዜ በብዙ አገሮች በሴቶች ላይ እየተፈጸመ ያለውን ጭቆና እንደማይስማሙበት ያመለክታል።

ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ በውኃ ጉድጓድ አጠገብ ከአንዲት ሴት ጋር የተነጋገረበትን ወቅት እንመልከት። የዮሐንስ ወንጌል ስለ ሁኔታው ሲገልጽ እንዲህ ይላል:- “አንዲት ሳምራዊት ሴት ውሃ ለመቅዳት ስትመጣ ኢየሱስ፣ ‘እባክሽ የምጠጣውን ስጪኝ’ አላት።” ምንም እንኳ በወቅቱ የነበሩት አብዛኞቹ አይሁዳውያን ከሳምራውያን ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የሌላቸው ቢሆንም ኢየሱስ በአደባባይ ከአንዲት ሳምራዊት ሴት ጋር ለመነጋገር ፈቃደኛ ነበር። ኢንተርናሽናል ስታንዳርድ ባይብል ኢንሳይክሎፒዲያ እንደሚናገረው “በአደባባይ ከሴት ጋር ሲነጋገሩ መታየት [ለአይሁዳውያን] በጣም የሚያሳፍር ነገር ነበር።” ኢየሱስ ግን ለሴቶች አክብሮትና አሳቢነት ያሳይ የነበረ ከመሆኑም በላይ ሰዎችን በዘራቸው ወይም በጾታቸው ምክንያት የመጥላት ዝንባሌ አልነበረውም። እንዲያውም ከዚህ በተቃራኒ ኢየሱስ፣ መሲሕ መሆኑን ለመጀመሪያ ጊዜ በግልጽ የተናገረው ሳምራዊት ለሆነች ሴት ነበር።—ዮሐንስ 4:7-9, 25, 26

በሌላ ወቅትም በሚያሸማቅቅና አቅም በሚያሳጣ የደም መፍሰስ ሕመም ለ12 ዓመታት ስትሠቃይ የኖረች አንዲት ሴት ወደ ኢየሱስ መጥታ ነበር። ይህቺ ሴት ኢየሱስን ስትነካው ወዲያውኑ ተፈወሰች። “ኢየሱስም ወደ ኋላ ዘወር ብሎ ሴቲቱን አያትና፣ ‘አይዞሽ፤ ልጄ ሆይ፤ እምነትሽ አድኖሻል’ አላት።” (ማቴዎስ 9:22) በሙሴ ሕግ መሠረት ደም የሚፈሳት ሴት ሌሎችን መንካት ይቅርና ከሰዎች ጋር መቀላቀል እንኳ አይገባትም ነበር። ሆኖም ኢየሱስ ይህቺን ሴት አልተቆጣትም። ከዚህ ይልቅ በርኅራኄ ያጽናናት ከመሆኑም በላይ “ልጄ ሆይ” ብሎ ጠርቷታል። ይህ አነጋገር ምንኛ አበረታቷት ይሆን! ኢየሱስም እሷን በመፈወሱ ምንኛ ተደስቶ ይሆን!

ኢየሱስ ከሙታን ከተነሳ በኋላ በመጀመሪያ የተገለጠው ለመግደላዊት ማርያምና መጽሐፍ ቅዱስ “ሌላዋ ማርያም” በማለት ለሚጠራት አንዲት ሌላ ደቀ መዝሙር ነበር። ኢየሱስ ለጴጥሮስ፣ ለዮሐንስ ወይም ከሌሎቹ ወንዶች ደቀ መዛሙርቱ ለአንዱ መጀመሪያ ሊገለጥ ይችል ነበር። በዚህ ፈንታ የትንሣኤው የመጀመሪያ የዓይን ምሥክሮች ሴቶች እንዲሆኑ በማድረግ አክብሯቸዋል። አንድ መልአክ፣ ሴቶቹ ይህን ድንቅ ክንውን ለኢየሱስ ወንዶች ደቀ መዛሙርት እንዲነግሩ አዟቸዋል። ኢየሱስ ራሱም ለሴቶቹ “ሂዱና . . . ለወንድሞቼ ንገሯቸው” ብሏቸዋል። (ማቴዎስ 28:1, 5-10) ኢየሱስ፣ ሴቶች በሕግ ፊት ለምሥክርነት እንደማይበቁ የሚገልጸው በዘመኑ የነበረው የአይሁዳውያን ጭፍን አመለካከት ምንም ተጽዕኖ እንዳላሳደረበት ግልጽ ነበር።

ስለዚህ ኢየሱስ ሴቶችን ዝቅ አድርጎ ከመመልከት ወይም ደግሞ ወንዶች ይበልጣሉ የሚለውን አመለካከት ከመደገፍ ይልቅ እንደሚያከብራቸውና ከፍ አድርጎ እንደሚመለከታቸው አሳይቷል። በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃት ኢየሱስ ካስተማረው ነገር ጋር ይጋጫል፤ የእሱ አመለካከት ደግሞ የይሖዋን አመለካከት ፍጹም በሆነ መንገድ የሚያንጸባርቅ እንደሆነ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።

አምላክ ለሴቶች የሚያደርግላቸው እንክብካቤ

“በጥንታዊው የሜድትራኒያን ወይም የመካከለኛው ምሥራቅ አካባቢዎች ሴቶች በዘመናችን በምዕራቡ ዓለም ያላቸው ዓይነት ነፃነት የሚያገኙበት አንድም ቦታ አልነበረም። ባሪያዎች ለጌቶቻቸው እንዲሁም ትንንሾች ለታላላቆቻቸው እንደሚገዙ ሁሉ ሴቶችም ለወንዶች መገዛታቸው የተለመደ ነበር። . . . ወንዶች ልጆች ከሴቶች ልጆች ይበልጥ ከፍ ተደርገው የሚታዩ ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ሴት ሕፃናት ለሐሩርና ለቁር ተጋልጠው እንዲሞቱ ይጣሉ ነበር።” አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት፣ በጥንት ዘመን ሴቶችን በተመለከተ በብዙዎች ዘንድ ተስፋፍቶ ይገኝ የነበረውን አመለካከት የገለጸው በዚህ መንገድ ነበር። አብዛኛውን ጊዜ ሴቶች የሚታዩት ከባሪያዎች እኩል ነበር ለማለት ይቻላል።

መጽሐፍ ቅዱስ በተጻፈበት ዘመን የነበሩት ባሕሎች ይህን አመለካከት ያንጸባርቁ ነበር። እንደዚያም ሆኖ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸው መለኮታዊ ሕግ ለሴቶች ከፍ ያለ ቦታ ይሰጥ የነበረ ሲሆን ይህ ደግሞ በጥንት ዘመን ከነበሩት ብዙ ባሕሎች ፈጽሞ የተለየ ነው።

ይሖዋ ለሴት አምላኪዎቹ ሲል የወሰዳቸው በርካታ እርምጃዎች የሴቶች ደህንነት እንደሚያሳስበው በግልጽ ያሳያሉ። ውብ የነበረችው የአብርሃም ሚስት ሣራ እንዳትደፈር ይሖዋ ሁለት ጊዜ ጣልቃ ገብቶ ጥበቃ አድርጎላታል። (ዘፍጥረት 12:14-20፤ 20:1-7) አምላክ፣ ያዕቆብ እምብዛም የማይወዳት ሚስቱ ልያ ወንድ ልጅ እንድትወልድ ‘ማሕፀኗን በመክፈት’ ሞገስ አሳይቷታል። (ዘፍጥረት 29:31, 32) በግብጽ ፈሪሃ አምላክ የነበራቸው ሁለት እስራኤላውያን አዋላጆች፣ የራሳቸውን ሕይወት አደጋ ላይ ጥለው ዕብራውያን ወንድ ሕፃናትን እንዳይገደሉ በማትረፋቸው ይሖዋ የራሳቸው “ቤተ ሰብ” እንዲኖራቸው በማድረግ ክሷቸዋል። (ዘፀአት 1:17, 20, 21) ሐና ያቀረበችውን ልባዊ ጸሎትም ሰምቶላታል። (1 ሳሙኤል 1:10, 20) የአንድ ነቢይ ሚስት የነበረች መበለት ለተበደረችው ዕዳ ክፍያ እንዲሆን አበዳሪው ልጆቿን በባርነት ሊወስድባት በመጣ ጊዜ ይሖዋ አልተዋትም። ሴትየዋ ዕዳዋን መክፈል እንድትችል ብቻ ሳይሆን ለቤተሰቧም የሚበቃ ቀለብ እንዲተርፋት ነቢዩ ኤልሳዕ የነበራትን ዘይት እንዲያበዛላት በማድረግ ፍቅራዊ እርምጃ ወስዷል። በዚህ መንገድ ቤተሰቧንም ሆነ ክብሯን መጠበቅ ችላለች።—ዘፀአት 22:22, 23፤ 2 ነገሥት 4:1-7

ነቢያት፣ ሴቶችን መጠቀሚያ ማድረግን ወይም ደግሞ በእነሱ ላይ ጥቃት መፈጸምን በተደጋጋሚ ያወግዙ ነበር። ነቢዩ ኤርምያስ፣ ይሖዋን ወክሎ ለእስራኤላውያን እንዲህ ብሏቸዋል:- “ፍትሕንና ጽድቅን አድርጉ፤ የተበዘበዘውን ከጨቋኙ እጅ አድኑት፤ መጻተኛውን፣ ወላጅ የሌለውንና መበለቲቱን አትበድሉ፤ አትግፏቸውም፤ በዚህም ስፍራ ንጹሕ ደም አታፍስሱ።” (ኤርምያስ 22:2, 3) ቀደም ሲል በእስራኤል የነበሩ ባለጠጎችና ኃያላን ሰዎች ሴቶችን ከገዛ ቤታቸው ስላባረሩና ልጆቻቸውንም ስላንገላቱ ተወግዘዋል። (ሚክያስ 2:9) የፍትሕ አምላክ በሴቶችና በልጆቻቸው ላይ የሚደርሰውን እንዲህ ዓይነቱን መከራ ይመለከታል እንዲሁም ያወግዘዋል።

“ልባም ሴት”

ጥንታዊውን የምሳሌ መጽሐፍ የጻፈው ሰው ለልባም ሚስት ሊኖረን የሚገባውን ተገቢ አመለካከት አስፍሮልናል። የሚስትን የሥራ ድርሻና ሊሰጣት የሚገባውን ቦታ የሚዘረዝረው ይህ ውብ መግለጫ በይሖዋ ቃል ውስጥ ስለተካተተ እሱም እንደሚደግፈው እርግጠኞች መሆን እንችላለን። እዚህ ላይ የተገለጸችው ሴት ከመጨቆን ወይም ዝቅ ተደርጋ ከመታየት ይልቅ ከፍ ከፍ ትደረጋለች፣ ትከበራለች እንዲሁም እምነት ይጣልባታል።

በምሳሌ 31 ላይ የተጠቀሰችው “ጠባየ መልካም [“ልባም፣” የ1954 ትርጉም] ሚስት” ብርቱና ታታሪ ሠራተኛ ናት። “ሥራ በሚወዱ እጆቿ” ተግታ የምትሠራ ሲሆን በንግድ ሥራ ላይ ትሰማራለች፣ ሌላው ቀርቶ የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችን ሽያጭ እንኳ ታከናውናለች። እርሻን ተመልክታ ትገዛለች። የበፍታ መጎናጸፊያዎችን እየሠራች ትሸጣለች። ለነጋዴዎችም ድግ ታቀርባለች። በሥራዋም ብርቱና ጠንካራ ናት። ከዚህም በላይ የምትናገራቸው የጥበብ ቃላት እንዲሁም ፍቅራዊ ደግነቷ በእጅጉ ይደነቃሉ። በመሆኑም በባሏም ሆነ በልጆቿ ከሁሉም በላይ ደግሞ በይሖዋ ዘንድ በጣም ከፍ ተደርጋ ትታያለች።

ሴቶች የተፈጠሩት ወንዶች መጠቀሚያ እንዲያደርጓቸው፣ እንዲጨቁኗቸው፣ እንዲያንገላቷቸው ወይም ማንኛውንም ዓይነት በደል እንዲፈጽሙባቸው አይደለም። በዚህ ፈንታ አምላክ፣ ያገባች ሴት ደስተኛና ብቃት ያላት ሚስት ሆና ለባሏ “ረዳት” እንድትሆንለት ይፈልጋል።—ዘፍጥረት 2:18

አክብሯቸው

በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የጻፈው ጴጥሮስ ክርስቲያን ባሎች ሚስቶቻቸውን እንዴት መያዝ እንዳለባቸው ሲገልጽ ባሎች፣ የይሖዋንና የኢየሱስ ክርስቶስን አመለካከት እንዲኮርጁ አሳስቧቸዋል። “ባሎች ሆይ፤ እናንተም . . . አክብሯቸው” በማለት ጽፏል። (1 ጴጥሮስ 3:7) አንድን ሰው ማክበር ግለሰቡን በጣም ከፍ አድርጎ በመመልከት ላቅ ያለ ግምት መስጠትን ያመለክታል። በመሆኑም ሚስቱን የሚያከብር ወንድ አያዋርዳትም፣ አያንኳስሳትም ወይም ጥቃት አይፈጽምባትም። ከዚህ ይልቅ በሚናገራቸው ቃላትም ሆነ በተግባሩ እንዲሁም በሰው ፊትም ሆነ ለብቻቸው ሲሆኑ ከፍ አድርጎ እንደሚመለከታትና እንደሚያፈቅራት ያሳያታል።

ባል፣ ሚስቱን ማክበሩ በትዳራቸው ውስጥ ደስታ እንዲሰፍን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ምንም ጥያቄ የለውም። የካርሎስንና የሴሲሊያን ሁኔታ ተመልከት። በትዳር ውስጥ ለተወሰነ ጊዜ ከቆዩ በኋላ ሁልጊዜ ይጨቃጨቁ ጀመር። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ጭራሽ ይኮራረፉ ነበር። እነዚህ ባልና ሚስት ችግሮቻቸውን እንዴት እንደሚፈቱ አላወቁም። እሱ ግልፍተኛ የነበረ ሲሆን እሷ ደግሞ በቀላሉ የማትደሰትና ኩሩ ሴት ነበረች። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትና የተማሩትን በሥራ ላይ ማዋል ሲጀምሩ ግን ነገሮች መሻሻል ጀመሩ። ሴሲሊያ እንዲህ ትላለች:- “የኢየሱስ ትምህርትና ምሳሌነቱ የራሴንም ሆነ የባለቤቴን ባሕርይ ለውጦታል። ኢየሱስ ለተወልን ምሳሌ ምስጋና ይግባውና ከበፊቱ ይበልጥ ትሑትና የሰው ስሜት የሚገባኝ ሆኛለሁ። ኢየሱስ እንዳደረገው እኔም በጸሎት የይሖዋን እርዳታ መጠየቅን ተምሬያለሁ። ካርሎስም ይሖዋ በሚፈልገው መንገድ ሚስቱን ማክበር፣ ከበፊቱ ይበልጥ ታጋሽ መሆንንና ራሱን መግዛትን ተምሯል።”

የእነዚህ ባልና ሚስት ጋብቻ ፍጹም ባይሆንም ለብዙ ዓመታት ጸንቷል። በቅርብ ዓመታት ካርሎስ ሥራውን ከማጣቱም በላይ በካንሰር ምክንያት ቀዶ ጥገና ማካሄድ ስለነበረበት ከባድ ችግሮችን አሳልፈዋል። ሆኖም እነዚህ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ጋብቻቸው ይበልጥ እንዲጠናከር አደረጉት እንጂ የትዳራቸውን መሠረት አላናጉትም።

የሰው ልጅ ፍጽምናን ካጣበት ጊዜ አንስቶ በብዙ ባሕሎች ውስጥ ሴቶች የሚያዋርድ ነገር ሲፈጸምባቸው ቆይቷል። አካላዊ፣ አእምሯዊና ጾታዊ በደል ሲፈጸምባቸው ኖረዋል። ይሁን እንጂ ይሖዋ ሴቶች በዚህ መንገድ እንዲያዙ ዓላማው አልነበረም። የተለመደው የማኅበረሰቡ አመለካከት ምንም ይሁን ምን ሁሉም ሴቶች ሊከበሩና ከፍ ተደርገው ሊታዩ እንደሚገባ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያሳያል። መከበር አምላክ የሰጣቸው መብት ነው።

[በገጽ 4, 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሳምራዊት ሴት

[በገጽ 4, 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የታመመች ሴት

[በገጽ 4, 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መግደላዊት ማርያም

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ ለሣራ ሁለት ጊዜ ጥበቃ አድርጎላታል

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የካርሎስና የሴሲሊያ ጋብቻ አደጋ ላይ ወድቆ ነበር

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ካርሎስና ሴሲሊያ በአሁኑ ጊዜ