ሚክያስ 2:1-13

  • ጨቋኞች ወዮላቸው! (1-11)

  • እስራኤልን መልሼ በአንድነት አኖራለሁ (12, 13)

    • ምድሪቱ በሕዝብ ሁካታ ትሞላለች (12)

2  “መጥፎ ነገር ለሚሸርቡናበአልጋቸው ላይ ሆነው ክፉ ነገር ለሚያውጠነጥኑ ወዮላቸው! ጠዋት ሲነጋ ያሰቡትን ይፈጽማሉ፤ምክንያቱም ይህን የሚያደርጉበት ኃይል በእጃቸው ነው።+  2  እርሻን ይመኛሉ፤ ነጥቀውም ይይዙታል፤+ቤቶችንም ይመኛሉ፤ ደግሞም ይወስዳሉ፤የሰውን ቤት፣የሰውንም ርስት አታለው ይወስዳሉ።+  3  ስለዚህ ይሖዋ እንዲህ ይላል ‘እነሆ፣ በዚህ ወገን ላይ ጥፋት ላመጣ አስቤአለሁ፤+ እናንተም ከዚህ ጥፋት አታመልጡም።*+ ከእንግዲህ ወዲህ በትዕቢት አትመላለሱም፤+ ይህ የጥፋት ጊዜ ነውና።+  4  በዚያም ቀን ሰዎች እናንተን አስመልክተው ምሳሌ ይናገራሉ፤በእናንተም የተነሳ አምርረው ያለቅሳሉ።+ እንዲህ ይላሉ፦ “እኛ ፈጽሞ ጠፍተናል!+ የሕዝቤን ድርሻ ለሌሎች ሰጥቷል፤ ከእኔም ወስዶታል!+ እርሻዎቻችንን ለከዳተኛው ይሰጣል።”  5  ስለዚህ በይሖዋ ጉባኤ ውስጥ፣ምድሪቷን ለማከፋፈል በገመድ የሚለካ ሰው አይኖርህም።  6  “አትስበኩ!” ብለው ይሰብካሉ፤“እነዚህን ነገሮች መስበክ አይገባቸውም፤ውርደት አይደርስብንም!”  7  የያዕቆብ ቤት ሆይ፣ “የይሖዋ መንፈስ አይታገሥም? እነዚህንስ ነገሮች ያደረገው እሱ ነው?” ሲባል ሰምተሃል? ቀና በሆነ መንገድ ለሚሄዱ የገዛ ቃሌ መልካም ነገር አያስገኝም?  8  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የገዛ ሕዝቤ ጠላት ሆኖ ተነስቷል። ከጦርነት እንደሚመለሱ ሰዎች በልበ ሙሉነት ከሚያልፉት ላይየሚያምረውን ጌጥ ከልብሱ ጋር* በይፋ ገፈፋችሁ።  9  የሕዝቤን ሴቶች ከሚያምረው ቤታቸው አፈናቀላችኋቸው፤ክብሬን ከልጆቻቸው ለዘላለም ወሰዳችሁ። 10  ተነሱና ከዚህ ሂዱ፤ ይህ የማረፊያ ቦታ አይደለምና። ከርኩሰት የተነሳ+ ጥፋት ይመጣል፤ ጥፋቱም ከባድ ነው።+ 11  አንድ ሰው ነፋስንና ማታለያን ተከትሎ ቢሄድና “ስለ ወይን ጠጅና ስለ መጠጥ እሰብክላችኋለሁ” ብሎ ውሸት ቢናገር ይህ ሰው ለዚህ ሕዝብ ተቀባይነት ያለው ሰባኪ ይሆናል!+ 12  ያዕቆብ ሆይ፣ ሁላችሁንም በእርግጥ እሰበስባለሁ፤ከእስራኤል የቀሩትን ያላንዳች ጥርጥር አንድ ላይ እሰበስባለሁ።+ በጉረኖ ውስጥ እንዳለ በግ፣በግጦሽ መስክ ላይ እንዳለም መንጋ በአንድነት አኖራቸዋለሁ፤+ቦታውም በሕዝብ ሁካታ ይሞላል።’+ 13  የሚሰብረውም ከፊታቸው ይሄዳል፤እነሱም ሰብረው በበሩ በኩል ያልፋሉ፤ በዚያም ወጥተው ይሄዳሉ።+ ንጉሣቸው በፊታቸው ያልፋል፤ይሖዋም ከፊታቸው ይሄዳል።”*+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “አንገታችሁን አታወጡም።”
“ከልብሱ ላይ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ቃል በቃል “በራሳቸው ላይ ይሆናል።”