በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትልቅ ከተማ የሆነችው የዓሣ አጥማጆች መንደር

ትልቅ ከተማ የሆነችው የዓሣ አጥማጆች መንደር

 ትልቅ ከተማ የሆነችው የዓሣ አጥማጆች መንደር

ጃፓን የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

በነሐሴ ወር 1590 በአንድ ደስ የሚል የበጋ ቀን ኢያሱ ቶኩጋዋ (በስተቀኝ) በምሥራቅ ጃፓን ወደምትገኘው ኢዶ የተባለች የዓሣ አጥማጆች መንደር ደረሰ፤ ከጊዜ በኋላ ይህ ሰው የመጀመሪያው የቶኩጋዋ ሾገን * ለመሆን በቅቷል። ዘ ሾገንስ ሲቲ—ኤ ሂስትሪ ኦቭ ቶኪዮ የተሰኘው መጽሐፍ በዚያን ጊዜ “በኢዶ የነበሩት ገበሬዎችና ዓሣ አጥማጆች የቀለሷቸው በጥቂት መቶዎች የሚቆጠሩ ደሳሳ ቤቶች ብቻ” እንደሆኑ ይገልጻል። በአቅራቢያው ደግሞ ከመቶ ዓመት በፊት የተሠራና አገልግሎት የማይሰጥ ምሽግ ይገኝ ነበር።

ለብዙ መቶ ዘመናት ሳትታወቅ የኖረችው ይህች መንደር የጃፓን ዋና ከተማ ቶኪዮ ለመሆን ከመብቃቷም በላይ ከ12 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ የሚኖርባት በሕዝብ የተጨናነቀች በጣም ትልቅ ከተማ ሆናለች። ቶኪዮ በቴክኖሎጂ፣ በመረጃ ልውውጥ፣ በመጓጓዣና በንግድ ረገድ ዓለም አቀፋዊ ተጽዕኖ የምታሳድር እንዲሁም እውቅ የገንዘብ ነክ ተቋማት ዋና መሥሪያ ቤቶች የሚገኙባት ከተማ መሆን ችላለች። እንዲህ ዓይነቱ አስገራሚ ለውጥ ሊከሰት የቻለው እንዴት ነው?

የዓሣ አጥማጆች መንደር የሾገን ከተማ ሆነች

ከ1467 በኋላ ለአንድ መቶ ዓመት እርስ በርስ የሚዋጉ የፊውዳል ባላባቶች ጃፓንን በበርካታ ርስተ ጉልቶች ከፋፈሏት። በመጨረሻም የተራ ገበሬ ልጅ የሆነ ሂዴዮሺ ቶዮቶሚ የሚባል የፊውዳል ባላባት ብሔሩን በከፊልም ቢሆን እንደገና አዋሃደው፤ ከዚያም በ1585 የንጉሠ ነገሥቱ እንደራሴ ሆነ። መጀመሪያ ላይ ኢያሱ ከኃያሉ ሂዴዮሺ ጋር ጦርነት ገጥሞ ነበር፤ በኋላ ግን ከእሱ ጋር ግንባር ፈጠረ። ሁለቱ በአንድነት በመሆን ኃያል የሆነው የሆጆ ጎሣ ምሽግ የነበረውን በኦዳዋራ የሚገኝ ግንብ ከበው ድል በማድረግ በምሥራቅ ጃፓን የሚገኘውን የካንቶ ክልል ተቆጣጠሩ።

ሂዴዮሺ በአብዛኛው ቀደም ሲል የሆጆ ጎሣ ግዛት የነበሩትን ስምንት የካንቶ ክፍለ አገሮች የሚያጠቃልል ሰፊ ክልል ለኢያሱ በመስጠት የመጀመሪያ የግዛት ክልሉን ለቅቆ ወደ ምሥራቅ እንዲዛወር አደረገው። ሂዴዮሺ ይህን ያደረገው ለስም ብቻ የተቀመጠው የጃፓን ንጉሠ ነገሥት ከሚኖርባት ከኪዮቶ ሆን ብሎ ኢያሱን ለማራቅ ሳይሆን አይቀርም። ያም ሆኖ ኢያሱ በዚህ ዝግጅት በመስማማት በመግቢያው ላይ እንደተጠቀሰው ወደ ኢዶ ሄደ። ከዚያም ይህችን አነስተኛ የዓሣ አጥማጆች መንደር የግዛቱ ማዕከል ለማድረግ ቆርጦ ተነሳ።

ሂዴዮሺ ከሞተ በኋላ በ1600 ኢያሱ፣ ከምሥራቃዊ ጃፓን የመጡ ጥምር ኃይሎችን አስተባብሮ ምዕራብ ባለው ሠራዊት ላይ በመዝመት በአንድ ቀን ውስጥ ድል አደረጋቸው። በ1603 ኢያሱ ሾገን ሆኖ የተሾመ ሲሆን በይፋ የአገሪቱ መሪ ሆነ። በዚህ ጊዜ ኢዶ የጃፓን አስተዳደራዊ ማዕከል ሆነች።

ኢያሱ ግዙፍ ግንብ መሥራት የጀመረ ሲሆን ይህንንም ለማጠናቀቅ ባላባቶቹ የሰው ኃይልና ቁሳቁስ እንዲያቀርቡ አዘዘ። በአንድ ወቅት በስተ ደቡብ 100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው በኢዙ ባሕረ ገብ መሬት ላይ ካሉ ቋጥኞች  የተጠረቡ ትላልቅ ጥቁር ድንጋዮችን ለማጋዝ ወደ 3,000 የሚጠጉ መርከቦችን ተጠቅሟል። ጥቁር ድንጋዮቹ ወደብ ላይ ሲራገፉ መቶ ወይም ከዚያ በላይ የሚሆኑ ሰዎች በቡድን ሆነው ወደ ግንባታው ቦታ ይወስዷቸው ነበር።

በጃፓን ከተሠሩት ግንቦች ሁሉ እጅግ ግዙፍ የሆነው ይህ ግንብ ከ50 ዓመታት በኋላ በሦስተኛው የቶኩጋዋ ሾገን የግዛት ዘመን የተጠናቀቀ ሲሆን የኃያሉ የቶኩጋዋ አገዛዝ መታወቂያ ሆኖ ነበር። ሳሙራይ ተብለው የሚጠሩት የሾገኑ ተዋጊዎች በዚህ ግንብ ዙሪያ ሠፈሩ። የፊውዳል ባላባቶች በግዛት ክልላቸው ውስጥ ካላቸው ግንብ በተጨማሪ በኢዶ ከተማ የሚገኙ ትልልቅ ቤቶችን እንዲንከባከቡ ሾገኑ ይጠብቅባቸው ነበር።

በኢዶ መኖር የጀመረውን የሳሙራይ ኅብረተሰብ ፍላጎት ለማሟላት ከመላው አገሪቱ ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሚሄድ ነጋዴዎችና የእጅ ጥበብ ባለሙያዎች ወደ ከተማዋ መምጣት ጀመሩ። በ1695 ማለትም ኢያሱ ወደዚያ አካባቢ ከሄደ ከመቶ ዓመት ገደማ በኋላ የኢዶ ሕዝብ ብዛት አንድ ሚሊዮን ደረሰ! ኢዶ በወቅቱ በሕዝብ ብዛት ከዓለም አንደኛ ሆና ነበር።

ከሰይፍ ወደ አባከስ

የሾገኑ መንግሥት ሰላምን በማስጠበቅ በኩል በጣም ውጤታማ ከመሆኑ የተነሳ ተዋጊው የሳሙራይ ኅብረተሰብ ብዙም የሚሠራው ነገር አልነበረም። እርግጥ ነው፣ ሳሙራይ በዚያን ጊዜም ቢሆን በወታደራዊ ሙያቸው ይኮሩ የነበረ ቢሆንም ቀስ በቀስ ኃይላቸውን ለአባከስ ተጠቃሚው የነጋዴ ማኅበረሰብ ለቀቁ። አባከስ በሩቅ ምሥራቅ አገሮች በስፋት ይሠራበት የነበረ የሒሳብ ስሌት መሣሪያ ነው። ከ250 ለሚበልጡ ዓመታት በአገሪቱ ሰላም ሰፍኖ ነበር። በጥቅሉ ሲታይ ሲቪሉ ኅብረተሰብ በተለይም ነጋዴው ከመበልጸጉም በላይ የበለጠ ነፃነት ነበረው። በወቅቱ በዓይነቱ ልዩ የሆነ ባሕል ዳብሮ ነበር።

ሕዝቡ እንደ ካቡኪ (ታሪካዊ ድራማዎች)፣ ቡንራኩ (በአሻንጉሊቶች የሚሠራ ቲያትር) እንዲሁም ራኩጎ (አስቂኝ ተረቶች) ባሉት ተወዳጅ ጨዋታዎች ይዝናና ነበር። ሞቃት በሆኑት የበጋ ምሽቶች ሰዎች ኢዶ በተቆረቆረችበት በቀዝቃዛው የሱሚዳ ወንዝ ዳርቻ ላይ ይሰበሰቡ ነበር። በተጨማሪም እስከ ዘመናችን ድረስ የዘለቀውንና ተወዳጅ የሆነውን ርችት ይመለከቱ ነበር።

ይሁን እንጂ ኢዶ በሌላው የዓለም ክፍል አትታወቅም ነበር። ጃፓናውያን ከ200 ለሚበልጡ ዓመታት ያህል በጣም ውስን ለሆነ ጉዳይ ከደች ሕዝቦች፣ ከቻይናውያንና ከኮርያውያን ጋር ከሚያደርጉት ግንኙነት ውጪ ከሌላ አገር ሕዝቦች ጋር እንዳይገናኙ መንግሥት ከልክሎ ነበር። ከዚያም አንድ ቀን አንድ ያልተጠበቀ ክስተት የከተማዋንና የብሔሩን ሁኔታ ለወጠው።

ኢዶ ቶኪዮ ተባለች

በኢዶ የባሕር ጠረፍ አቅራቢያ ለየት ያሉ መርከቦች ጥቁር ጭሳቸውን እያትጎለጎሉ በድንገት ብቅ አሉ። በአካባቢው የነበሩት በግርምት የተዋጡ ዓሣ አጥማጆች መርከቦቹ የሚንሳፈፍ  እሳተ ገሞራ መስለዋቸው ነበር! የሚያሸብር ወሬ በኢዶ ከተማ ስለተነዛ ብዙ ሰዎች ከተማዋን ለቀው ሸሹ።

የዩናይትድ ስቴትስ ባሕር ኃይል አዛዥ በነበረው ካፒቴን ማቲው ካልፕሬዝ ፔሪ የሚመሩት እነዚያ አራት መርከቦች (በስተግራ) ሐምሌ 8, 1853 በኢዶ ባሕረ ሰላጤ መልሕቃቸውን ጣሉ። ፔሪ፣ በሾገን የሚመራው የጃፓን መንግሥት ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር የንግድ ልውውጥ ለማድረግ በሩን እንዲከፍት ጥያቄ አቀረበ። የፔሪ ጉብኝት፣ ጃፓናውያን አገራቸው በወታደራዊና በቴክኖሎጂ እድገት ረገድ ከቀረው ዓለም ምን ያህል ወደኋላ እንደቀረች እንዲገነዘቡ አደረጋቸው።

ይህም የቶኩጋዋ አገዛዝ አክትሞ የንጉሠ ነገሥቱ አገዛዝ እንዲመለስ ላደረጉት ተከታታይ ክንውኖች መነሻ ሆነ። በ1868 ኢዶ ስሟ ተቀይሮ ቶኪዮ የተባለች ሲሆን ትርጉሙም “ምሥራቃዊ ዋና ከተማ” ማለት ነው፤ ይህ ስም የተሰጣት ከተማዋ ከኪዮቶ በስተ ምሥራቅ ስለምትገኝ ነው። ንጉሠ ነገሥቱም በኪዮቶ የሚገኘውን ቤተ መንግሥት ለቆ በኢዶ ግንብ መኖር ጀመረ፤ የኋላ ኋላ ይህ ግንብ የንጉሠ ነገሥቱ አዲሱ ቤተ መንግሥት ለመሆን በቅቷል።

አዲሱ መንግሥት የምዕራባውያንን ባሕል በመከተል ጃፓንን ዘመናዊ ማድረጉን ተያያዘው። ምዕራባውያኑ የደረሱበት የሥልጣኔ ደረጃ ላይ ለመድረስ ብዙ መሠራት ያለበት ነገር ነበር። አንዳንዶች ይህንን ወቅት እንደ ተአምራዊ ዘመን ይቆጥሩታል። በ1869 በቶኪዮና በዮከሃማ ከተሞች መካከል የቴሌግራፍ አገልግሎት ተጀመረ። ብዙም ሳይቆይ ሁለቱን ከተሞች የሚያገናኘው የመጀመሪያውን የባቡር ሐዲድ መሥመር የመዘርጋቱ ሥራ ተከተለ። በእንጨት በተሠሩት ቤቶች መካከል ከጡብ የተሠሩ ሕንፃዎች ብቅ ማለት ጀመሩ። ባንኮች፣ ሆቴሎች፣ ትልልቅ የገበያ አዳራሾችና ምግብ ቤቶችም ተገነቡ። እንዲሁም የመጀመሪያዎቹ ዩኒቨርሲቲዎች ተቋቋሙ። አቧራማ መንገዶች በአስፋልት ጎዳናዎች ተተኩ። በእንፋሎት የሚሠራ ሞተር ያላቸው ጀልባዎች በሱሚዳ ወንዝ ላይ ይመላለሱ ጀመር።

ሕዝቡም ጭምር አለባበሱ ተቀየረ። አብዛኞቹ ሰዎች ባሕላዊውን ኪሞኖ ይለብሱ የነበረ ቢሆንም ቁጥራቸው እየጨመረ የሚሄድ ጃፓናውያን የምዕራባውያንን ልብሶች  መልበስ ጀመሩ። ወንዶች ሪዛቸውን አሳድገው፣ ረዣዥም ባርኔጣዎችን ጣል አድርገውና ምርኩዝ ይዘው መሄድ የጀመሩ ሲሆን አንዳንድ ሴቶች ደግሞ የሚያምሩ ቀሚሶችን ይለብሱና ዎልትስ የሚባለውን የምዕራባውያን ውዝዋዜ ይማሩ ጀመር።

ቢራ፣ ሴኪ ከሚባለው ከሩዝ ከሚዘጋጅ የጃፓናውያን የአልኮል መጠጥ እኩል ተወዳጅ ለመሆን የበቃ ሲሆን ቤዝቦል የሚባለው በአሜሪካ የሚዘወተር ስፖርትም ሱሞ እንደሚባለው የጃፓናውያን ስፖርት ተወዳጅነት አገኘ። ቶኪዮ የዘመኑን ባሕላዊም ሆነ ፖለቲካዊ አስተሳሰቦች በሙሉ እንደ ትልቅ ስፖንጅ በመምጠጥ ከራሷ ጋር አዋሃደቻቸው። ከተማዋ አንድ ቀን በድንገተኛ አደጋ እስከጠፋችበት ጊዜ ድረስ ማደግ መመንደጓን ተያያዘችው።

እንደገና ማንሰራራት

መስከረም 1, 1923 ብዙዎች ምሳቸውን እያዘጋጁ ሳሉ የካንቶን አካባቢ ኃይለኛ የምድር መንቀጥቀጥ አናወጠው፤ ከዚያም በመቶዎች የሚቆጠሩ አነስተኛ ነውጦች የተከሰቱ ሲሆን ከ24 ሰዓት በኋላ ደግሞ ሌላ ከባድ ነውጥ ተከተለ። የምድር መናወጡ በራሱ ያስከተለው ጉዳት በጣም ከፍተኛ ቢሆንም በምድር መናወጡ ሳቢያ የተነሳውና አብዛኛውን የቶኪዮ ክፍል አመድ ያደረገው እሳት ደግሞ የበለጠ ውድመት አስከትሏል። በጠቅላላው ከ100,000 በላይ ሕዝብ ሲሞት ከእነዚህ ውስጥ 60,000 የሚያህሉት የሞቱት በቶኪዮ ነበር።

የቶኪዮ ሕዝብ ከተማቸውን እንደገና የመገንባቱን ከባድ ሥራ ተያያዙት። ከተማዋ በተወሰነ መጠን ካንሰራራች በኋላ እንደገና ሌላ ጥፋት ደረሰባት፤ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በአውሮፕላን በቦምብ ተደበደበች። በተለይ አውዳሚ የነበሩት መጋቢት 9/10, 1945 ከእኩለ ሌሊት ጀምሮ እስከ ሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በከተማዋ ላይ የተጣሉት 700,000 እንደሚደርሱ የሚገመቱት ቦምቦች ናቸው። ቤቶቹ በአብዛኛው ከእንጨት የተሠሩ ሲሆኑ የተጣሉት ቦምቦች ደግሞ ናፓልም እንዲሁም ማግኒዚየምና ቤንዚን ያለባቸው ከፍተኛ እሳት የሚያስነሱ አዲስ የጦር መሣሪያዎች በመሆናቸው በሕዝብ የተጨናነቀው አካባቢ በእሳት ተያያዘና ከ77,000 በላይ ሰዎች አለቁ። ይህ ክንውን በታሪክ ውስጥ ኑክሌር ባልሆኑ መሣሪያዎች ተወዳዳሪ የሌለው ውድመት ያስከተለ ነው።

ቶኪዮ ታይቶ በማይታወቅ መንገድ ይህን መሳይ ጥፋት ቢደርስባትም ከጦርነቱ በኋላ ከአመድ ተነስታ እንደገና ለማንሰራራት በቅታለች። በ1964፣ ጦርነቱ ከተካሄደ 20 ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከተማዋ የበጋ ኦሎምፒክ ጨዋታዎችን ለማስተናገድ እስክትችል ድረስ እንደገና አንሰራርታ ነበር። ባለፉት አራት አሥርተ ዓመታት በከተማዋ ውስጥ መንገዶችንና ሰማይ ጠቀስ ፎቆችን በመሥራት መጠነ ሰፊ የግንባታ እንቅስቃሴ የተከናወነ ሲሆን ይህም ከተማዋ እንድትሰፋ አድርጓታል።

የቶኪዮ ሕዝብ መንፈስ ችግሮችን ለመቋቋም ረድቷል

በአሁኑ ጊዜ ቶኪዮ ተብላ የምትጠራው ከተማ የ400 ዓመታት ዕድሜ ብታስቆጥርም ከሌሎቹ የዓለም ታላላቅ ከተሞች ጋር ስትወዳደር ፈጽሞ አላረጀችም። የቀድሞውን ዘመን የሚያስታውሱ አንዳንድ የከተማዋ ክፍሎች ቢኖሩም በአጠቃላይ ሲታይ የጥንቱን አሠራር የሚያንጸባርቁት ሕንፃዎችና የግንባታ ሥራዎች በጣም ጥቂት ናቸው። ይሁን እንጂ ከተማዋን ቀረብ ብሎ ለተመለከታት ከጥንቷ ኢዶ ዘመን የመጣ ንድፍ እንዳላት ይታያል።

በከተማዋ መካከል ለምለም የሆነ ሰፊ መስክ አለ። የንጉሠ ነገሥቱ ቤተ መንግሥትና በዙሪያው ያለው መሬት እስከ ዛሬም የሚገኘው የቀድሞዋ ኢዶ ግንብ በነበረበት ሥፍራ ነው። ከከተማዋ የሚያስወጡት ዋና ዋና መንገዶች ከቤተ መንግሥቱ ተነስተው እንደ ሸረሪት ድር በየአቅጣጫው የሚወስዱ ሲሆን እነዚህ መንገዶች የተሠሩት የኢዶን ንድፍ ተከትለው ነው። በከተማዋ በሙሉ የሚገኙት ያለ ንድፍ የተሠሩትና ግራ የሚያጋቡት ጎዳናዎችም እንኳ ሳይቀር የጥንቷን ኢዶ ትዝታ ይቀሰቅሳሉ። እንዲያውም አብዛኞቹ ጎዳናዎች ስም እንኳ አልተሰጣቸውም! በሌሎቹ የዓለም ትላልቅ ከተሞች በሚታዩት በአራት ማዕዘን መልክ የተሠሩ ሠፈሮች ምትክ በቶኪዮ የሚታዩት የተለያየ ቅርጽና ስፋት ያላቸውና ቁጥር የተሰጣቸው ቦታዎች ናቸው።

ይሁን እንጂ ከጥንቱ ዘመን ቅሬታዎች መካከል ይበልጥ ጎልቶ የሚታየው የቶኪዮ መንፈስ ነው፤ አዲስ የሆነን ነገር በተለይም የውጭ አገር አስተሳሰብን የመቀበል ችሎታ እንዲሁም የመሬት መናወጥ፣ ለረጅም ጊዜ የዘለቀ የኢኮኖሚ ድቀት እንዲሁም የሕዝብ ቁጥር መብዛት የፈጠራቸው ችግሮች ቢኖሩም እንደገና አንሰራርቶ በቆራጥነት ወደፊት የመጓዝ መንፈስ በሕዝቡ ላይ ይታያል። ተሰውራ ትኖር ከነበረች ትንሽ የዓሣ አጥማጆች መንደር ተነስታ ዓለም አቀፋዊ እውቅና ያገኘች ትልቅ ከተማ ለመሆን የበቃችውን የቶኪዮን ሕዝብ ሐሞተ ኮስታራ መንፈስ ራስህ መጥተህ ተመልከት።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.3 ሾገን የሚለው ማዕረግ የሚያመለክተው ከትውልድ ወደ ትውልድ ይተላለፍ የነበረውን የጃፓናውያን ሠራዊት አዛዥነት ሲሆን አዛዡ በንጉሠ ነገሥቱ አገዛዝ ሥር ገደብ የለሽ ሥልጣን ነበረው።

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ጃፓን

ቶኪዮ (ኢዶ)

ዮከሃማ

ኪዮቶ

ኦሳካ

[በገጽ 12, 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቶኪዮ በአሁኑ ጊዜ

[ምንጭ]

Ken Usami/photodisc/age fotostock

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

© The Bridgeman Art Library

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

The Mainichi Newspapers