ዘፀአት 1:1-22

  • እስራኤላውያን በግብፅ እየበዙ ሄዱ (1-7)

  • ፈርዖን እስራኤላውያንን ጨቆናቸው (8-14)

  • ፈሪሃ አምላክ ያላቸው አዋላጆች ወንዶቹን ልጆች ሳይገድሏቸው ቀሩ (15-22)

1  ቤተሰባቸውን ይዘው ከያዕቆብ ጋር ወደ ግብፅ የመጡት የእስራኤል ወንዶች ልጆች ስም የሚከተለው ነው፦+  ሮቤል፣ ስምዖን፣ ሌዊ፣ ይሁዳ፣+  ይሳኮር፣ ዛብሎን፣ ቢንያም፣  ዳን፣ ንፍታሌም፣ ጋድና አሴር።+  ከያዕቆብ አብራክ የወጡት* በጠቅላላ 70* ነበሩ፤ ዮሴፍ ግን ቀድሞውኑም እዚያው ግብፅ ነበር።+  ከጊዜ በኋላ ዮሴፍ ሞተ፤+ ወንድሞቹም ሁሉ ሞቱ፤ ያም ትውልድ በሙሉ ሞተ።  እስራኤላውያንም* ተዋለዱ፤ በጣም ብዙ ሆኑ፤ ቁጥራቸውም በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረና ኃያል እየሆኑ ሄዱ፤ ከዚህም የተነሳ ምድሪቱን ሞሏት።+  ከጊዜ በኋላ ዮሴፍን የማያውቅ አዲስ ንጉሥ በግብፅ ተነሳ።  እሱም ሕዝቦቹን እንዲህ አላቸው፦ “ይኸው እንደምታዩት የእስራኤል ሕዝብ ከእኛ ይልቅ እጅግ ብዙና ኃያል ነው።+ 10  እንግዲህ እነሱን በተመለከተ አንድ መላ እንፍጠር። ካልሆነ ግን ቁጥራቸው እየበዛ ይሄዳል፤ ደግሞም ጦርነት ከተነሳ ከጠላቶቻችን ጋር ወግነው እኛን መውጋታቸውና አገሪቱን ጥለው መኮብለላቸው አይቀርም።” 11  በመሆኑም ከባድ ሥራ በማሠራት እንዲያስጨንቋቸው የግዳጅ ሥራ የሚያሠሩ አለቆችን ሾሙባቸው፤+ እነሱም ጲቶም እና ራምሴስ+ የተባሉ ለማከማቻ የሚሆኑ ከተሞችን ለፈርዖን ገነቡ። 12  ሆኖም ይበልጥ በጨቆኗቸው መጠን ይበልጥ እየበዙና በምድሩ ላይ ይበልጥ እየተስፋፉ ስለሄዱ ግብፃውያን በእስራኤላውያን የተነሳ ከፍተኛ ፍርሃት አደረባቸው።+ 13  በመሆኑም ግብፃውያን እስራኤላውያንን ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ በባርነት ይገዟቸው ጀመር።+ 14  የሸክላ ጭቃ በማስቦካት፣ ጡብ በማሠራትና በእርሻ ላይ ማንኛውንም ዓይነት የባርነት ሥራ እንዲሠሩ በማድረግ ሕይወታቸውን መራራ አደረጉባቸው። አዎ፣ ማንኛውንም ዓይነት የባርነት ሥራ በማሠራት በጭካኔ ያንገላቷቸው ነበር።+ 15  በኋላም የግብፅ ንጉሥ፣ ሺፍራ እና ፑሃ የተባሉትን ዕብራውያን አዋላጆች አነጋገራቸው፤ 16  እንዲህም አላቸው፦ “ዕብራውያን ሴቶችን በምታዋልዱበት ጊዜ+ በማዋለጃው ዱካ ላይ ተቀምጠው ስታዩ የሚወለደው ልጅ ወንድ ከሆነ ግደሉት፤ ሴት ከሆነች ግን በሕይወት ትኑር።” 17  ይሁን እንጂ አዋላጆቹ እውነተኛውን አምላክ ስለፈሩ የግብፅ ንጉሥ ያላቸውን አላደረጉም። ከዚህ ይልቅ ወንዶቹን ልጆች በሕይወት እንዲኖሩ ይተዉአቸው ነበር።+ 18  ከጊዜ በኋላም የግብፅ ንጉሥ አዋላጆቹን ጠርቶ “ወንዶቹን ልጆች በሕይወት እንዲኖሩ የተዋችኋቸው ለምንድን ነው?” አላቸው። 19  አዋላጆቹም ፈርዖንን “ዕብራውያን ሴቶች እንደ ግብፃውያን ሴቶች አይደሉም። እነሱ ብርቱዎች ስለሆኑ አዋላጇ ከመድረሷ በፊት በራሳቸው ይወልዳሉ” አሉት። 20  ስለሆነም አምላክ ለአዋላጆቹ መልካም ነገር አደረገላቸው፤ ሕዝቡም እየበዛና እጅግ ኃያል እየሆነ ሄደ። 21  አዋላጆቹ እውነተኛውን አምላክ በመፍራታቸው፣ አምላክ ከጊዜ በኋላ ቤተሰብ ሰጣቸው። 22  በመጨረሻም ፈርዖን ሕዝቡን ሁሉ “አዲስ የሚወለዱትን የዕብራውያንን ወንዶች ልጆች ሁሉ አባይ ወንዝ ውስጥ ጣሏቸው፤ ሴቶቹን ልጆች ሁሉ ግን በሕይወት እንዲኖሩ ተዉአቸው” ሲል አዘዘ።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “የወጡት ነፍሳት።”
ወይም “70 ነፍስ።”
ቃል በቃል “የእስራኤል ወንዶች ልጆችም።”