በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በደመ ነፍስ የተገኘ አስደናቂ ጥበብ

በደመ ነፍስ የተገኘ አስደናቂ ጥበብ

በደመ ነፍስ የተገኘ አስደናቂ ጥበብ

“እጅግ አስደናቂ ከሆኑት ተፈጥሯዊ ክንውኖች ሁሉ ቀዳሚውን ቦታ የሚይዘው [የወፎች] ፍልሰት ሳይሆን አይቀርም።”—ኮሊንስ አትላስ ኦቭ በርድ ማይግሬሽን

ታኅሣሥ 9, 1967 አንድ የአውሮፕላን አብራሪ፣ 30 የሚሆኑ ኹፐር ስዋን የተባሉ የዳክዬ ዝርያዎች ከመሬት 8,200 ሜትር ከፍ ብለው ወደ አየርላንድ ሲበሩ ተመለከተ። እነዚህ ወፎች የአየሩ ቅዝቃዜ ከዜሮ በታች 40 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ በሆነበት በዚህ ከፍታ ላይ የሚበሩት ለምን ነበር? በዚህ ከፍታ ላይ ሲበሩ፣ በዝቅተኛ ቦታዎች አለማቋረጥ ከሚጥለው የበረዶ ውሽንፍር ማምለጥ የሚችሉ ከመሆኑም በላይ በነፋሱ እየተገፉ በሰዓት 200 ኪሎ ሜትር በሆነ ፍጥነት መጓዝ ይችላሉ። ወፎቹ ከአይስላንድ ተነስተው ወደ አየርላንድ የሚያደርጉትን 1,300 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ጉዞ በ7 ሰዓት ውስጥ እንዳጠናቀቁ ተገምቷል።

በጣም ሩቅ ወደሆነ ቦታ በመፍለስ ረገድ በዓለም ላይ ተወዳዳሪ ያልተገኘላት አርክቲክ ተርን የምትባለው ወፍ እንቁላሎቿን የምትጥለው ከአርክቲክ ክልል በስተ ሰሜን ሲሆን በሰሜናዊው ንፍቀ ክበብ ክረምት በሚሆንበት ጊዜ ግን ወቅቱን የምታሳልፈው በደቡባዊ ንፍቀ ክበብ በሚገኘው በአንታርክቲካ ነው። ይህች ትንሽ የባሕር ወፍ በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ ከ40,000 እስከ 50,000 ኪሎ ሜትር የምትጓዝ ሲሆን ይህም ምድርን ከመዞር ጋር የሚተካከል ነው!

ነጭ ሽመላዎች እንቁላላቸውን የሚጥሉት በሰሜናዊ አውሮፓ ሲሆን የሰሜናዊውን ንፍቀ ክበብ የክረምት ወቅት የሚያሳልፉት በደቡብ አፍሪካ በመሆኑ ደርሶ መልስ 24,000 ኪሎ ሜትር ይጓዛሉ። በበልግና በጸደይ ወቅቶች በሺዎች የሚቆጠሩ ሽመላዎች እስራኤልን አቋርጠው የሚያልፉ ሲሆን ይህ ፕሮግራማቸውም በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን እንኳ የታወቀ ነበር።—ኤርምያስ 8:7

በደመ ነፍስ የሚመሩበትን ይህን ጥበብ በውስጣቸው ያስቀመጠው ማን ነው? ከ3,500 ዓመታት በፊት አምላክ ጻድቁን ኢዮብን “ጭልፊት የሚበረው፣ ክንፎቹንም ወደ ደቡብ የሚዘረጋው፣ በአንተ ጥበብ ነውን? ንስር ወደ ላይ የሚመጥቀው፣ ጎጆውንም በከፍታ ላይ የሚሠራው፣ በአንተ ትእዛዝ ነውን?” በማለት ጠይቆት ነበር። ኢዮብ በሰጠው መልስ ላይ ወፎችም ሆኑ ሌሎች እንስሳት ላላቸው አስደናቂ ጥበብ አምላክን አወድሶታል።—ኢዮብ 39:26, 27፤ 42:2

በደመ ነፍስ ከመመራት እጅግ የሚበልጥ ጥበብ

የአምላክ ምድራዊ ፍጥረት ቁንጮ የሆኑት ሰዎች ግን በዋነኝነት የሚመሩት በደመ ነፍስ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ሕሊናና የማፍቀር ችሎታ እንዲሁም የራሳችንን ምርጫ የማድረግ ነጻነት አለን። (ዘፍጥረት 1:27፤ 1 ዮሐንስ 4:8) እነዚህ ሁሉ ስጦታዎች ስለተሰጡን ፍትሕና ትክክለኛ የሥነ ምግባር አቋም የሚንጸባረቅባቸው ውሳኔዎች ማድረግ የምንችል ሲሆን አንዳንድ ጊዜም ይህን ለማድረግ የላቀ ፍቅርና የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ እናሳያለን።

እርግጥ ነው፣ የአንድ ሰው አመለካከትና ባሕርይ በአብዛኛው የሚመካው ከሕፃንነቱ ጀምሮ ሥነ ምግባራዊ መመሪያዎችና መንፈሳዊ ትምህርቶች በማግኘቱ ወይም ባለማግኘቱ ላይ ነው። በመሆኑም ሰዎች ትክክል ወይም ስህተት፣ ተቀባይነት ያለው ወይም የሌለው እንደሆነ የሚቆጥሩት ነገር ይለያይ ይሆናል። እነዚህ ልዩነቶች በተለይም ደግሞ ባሕል፣ ብሔራዊ ስሜትና ሃይማኖት ከሚያሳድሩት ኃይለኛ ተጽዕኖ ጋር ሲዳመሩ፣ አለመግባባትና አለመቻቻል አልፎ ተርፎም ጥላቻ ሊያስከትሉ ይችላሉ።

መላው ሰብዓዊ ቤተሰብ ጽንፈ ዓለሙን ለሚቆጣጠሩት አንድ ዓይነት ተፈጥሯዊ ሕጎች እንደሚታዘዝ ሁሉ፣ ትክክለኛውን ሥነ ምግባራዊ አቋምና መንፈሳዊ እውነት የሚያንጸባርቁ አንድ ዓይነት መሥፈርቶችን የሚከተል ቢሆን ኖሮ ዓለም ምንኛ የተሻለ በሆነ ነበር! ይሁን እንጂ ዓለም አቀፋዊ የሥነ ምግባር መሥፈርቶችን ለማውጣት ችሎታና እውቀቱ ያለው አካል አለ? ካለ ደግሞ እንዲህ ያሉትን መሥፈርቶች ያወጣ ይሆን? ወይስ ከዚህ ቀደም እነዚህን መሥፈርቶች አውጥቶ ይሆን? እነዚህ ጥያቄዎች በሚቀጥሉት ርዕሰ ትምህርቶች ውስጥ ይብራራሉ።