በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ይሖዋ እባክህ እንዳገለግልህ ፍቀድልኝ’

‘ይሖዋ እባክህ እንዳገለግልህ ፍቀድልኝ’

‘ይሖዋ እባክህ እንዳገለግልህ ፍቀድልኝ’

ዳንዬል ሆል እንደተናገረችው

ትንሽ ልጅ ሳለሁ ጎረቤታችን ወደነበረችው ወደ አያቴ ቤት መሄድ ደስ ይለኝ ነበር። አያቴ ቀትር ላይ ትንሽ የመተኛት ልማድ ነበራት። ተኝታ እያለ ከደረስኩ እዚያው አልጋ ላይ ቁጭ ብለን የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን ታነብልኛለች። በተደጋጋሚ ጊዜ “መቼም ቢሆን ይሖዋ እንደሚወድሽ አትርሺ። አንቺም የምትወጂው ከሆነ ምንጊዜም ይንከባከብሻል” ትለኝ ነበር። እነዚህ ቃላት በአእምሮዬና በልቤ ላይ ተቀርጸዋል።

አያቴ በ1977 የአራት ዓመት ልጅ ሳለሁ ሞተች። የትውልድ ከተማችን በሆነችው በሞኢ፣ አውስትራሊያ እንደሚኖሩት የአባቴ ዘመዶች ሁሉ እርሷም የይሖዋ ምሥክር ነበረች። ወላጆቼ የይሖዋ ምሥክሮች ባይሆኑም አባቴ ግን ለእነርሱ ጥሩ አመለካከት ነበረው። ከጊዜ በኋላ ቤተሰባችን ኒው ሳውዝ ዌልስ አቅራቢያ ወደምትገኘው ቲንተንባር የተባለች አነስተኛ ከተማ ተዛወረ። እዚያም እያለን እኔና ታላቅ ወንድሜ ጄሚ ከአባታችን ጋር አልፎ አልፎ በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ እንገኝ ነበር።

የስምንት ዓመት ልጅ ሳለሁ ወላጆቼ ተለያዩ። በዚህ ጊዜ አባታችን ወደ ሞኢ ሲመለስ እኔና ጄሚ ከእናታችን ጋር መኖራችንን ቀጠልን። እናታችን ለመጽሐፍ ቅዱስ ግድ ስለሌላት በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ እንድንገኝ አትፈልግም ነበር። ይህ ሁኔታ በጣም ያሳዝነኝ ነበር። አያቴ ትነግረኝ የነበሩት ቃላት ፈጽሞ ከልቤ አልጠፉም። ለይሖዋ ፍቅር እንደነበረኝ አውቃለሁ! እርሱንም ማገልገል እፈልጋለሁ። በመሆኑም የእርሱ ምሥክር መሆን እንደምፈልግ ለይሖዋ በጸሎት ነገርኩት። ጄሚም ቢሆን እንዲህ ይሰማው ነበር።

በትምህርት ቤት የገጠመን ፈተና

ብዙም ሳይቆይ አንድ አስተማሪ በክፍላችን ውስጥ ያሉ ተማሪዎችን ሃይማኖት ለመመዝገብ ፈልጎ እያንዳንዳችን ሃይማኖታችንን ጮክ ብለን እንድንነግረው ጠየቀን። የጄሚ ተራ ሲደርስ ድምጹን ከፍ አድርጎ “የይሖዋ ምሥክር” በማለት ተናገረ። አስተማሪው መጻፉን አቋርጦ ምን እንዳለ እንዲደግምለት ጠየቀው። እርሱም በድጋሚ ነገረው። አስተማሪውም “አይመስለኝም፤ እስቲ ያንተን በኋላ እመለስበታለሁ” አለው። እኔም ተራዬ ሲደርስ ጮክ ብዬ “የይሖዋ ምሥክር” በማለት ተናገርኩ። አስተማሪው በጣም ተበሳጭቶ የትምህርት ቤቱን ዳይሬክተር አስጠራው።

ዳይሬክተሩም “ይኸው የተመዘገባችሁበት ወረቀት አለኝ፤ ወላጆቻችሁ የይሖዋ ምሥክሮች ብለው አላስመዘገቧችሁም” በማለት ኮስተር ብሎ ተናገረ። እኔና ጄሚም “እኛ የምንከተለው ሃይማኖት ግን ይህ ነው” ብለን በአክብሮት መለስንለት። ከዚያ በኋላ እርሱም ሆነ አስተማሪው ስለዚህ ጉዳይ አንስተው አያውቁም።

ትምህርት ቤት ሳለሁ ያለኝን አነስተኛ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ለሌሎች ለማካፈል ጥረት አደርግ ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ የተባለውን ጽሑፍ ይዤ በመሄድ በአምላክ መኖር ለምታምን አንዲት ልጅ አነብላታለሁ። * በክርስቲያናዊ ሕጎች ለመመራት ጥረት አደርግ ስለነበር ተማሪዎች ብዙም አይቀርቡኝም። አንዳንድ ጊዜ ብቸኝነት ይሰማኝ ነበር።

ይሖዋ የቅርብ ወዳጄ እንዲሆን በተደጋጋሚ ጊዜያት አጥብቄ እጸልይ ነበር። ሁልጊዜ ከትምህርት ቤት ስመለስ አልጋዬ ላይ ቁጭ ብዬ የቀኑን ውሎዬን በዝርዝር እነግረዋለሁ። ብዙ ጊዜም አለቅስ ነበር። እንባዬ ጉንጬ ላይ እየወረደ “ይሖዋ እባክህ ከሕዝቦችህ ጋር እንዳገለግልህ ፍቀድልኝ” እያልኩ እለምነዋለሁ። ከጸለይኩ በኋላ ሁልጊዜ ጥሩ ስሜት ይሰማኛል።

አበረታች ደብዳቤ

የአሥር ዓመት ልጅ ሳለሁ ጄሚ ወደ ሞኢ ተመልሶ ከአባቴ ጋር መኖር ጀመረ። በዚህ ጊዜ ስለ መንፈሳዊ ነገሮች የማነጋግረው ሰው አጣሁ። አንድ ቀን ጎረቤት ሄጄ ሳለሁ በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጁ አንዳንድ መጽሔቶችን አየሁ። የምኖርበትን አገር ቅርንጫፍ ቢሮ አድራሻ በአእምሮዬ ይዤ ሳልረሳው ለመጻፍ በፍጥነት ወደ ቤት ሄድኩ። ከዚያም ያለሁበትን ሁኔታ በመግለጽ መንፈሳዊ እርዳታ እንዲደረግልኝ የሚጠይቅ ደብዳቤ ለቅርንጫፍ ቢሮው ጻፍኩ። በቀጥታ ለእኔ የተጻፈ ልብ የሚነካ ሁለት ገጽ ደብዳቤ ሲደርሰኝ ዓይኔ በእንባ ተሞላ። ይህ በእርግጥ ይሖዋ እንደ ውድ አድርጎ እንደሚመለከተኝ የሚያሳይ ማስረጃ ነው!

ደብዳቤው በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የሶርያ ሰራዊት አዛዥ የነበረው የንዕማን አገልጋይ የነበረችውን የትንሿን እስራኤላዊት ልጃገረድ እምነት እንድኮርጅ የሚያበረታታ ነበር። ይህች ልጅ በምርኮ የተወሰደችና ከትውልድ አገሯ ርቆ በሚገኝ ቦታ ላይ የምትኖር ቢሆንም ይሖዋ አምላክን ፈጽሞ አልረሳችም ነበር። ስለ እምነቷ በድፍረት በመናገር የእርሱ እውነተኛ ምሥክር መሆኗን አሳይታለች።—2 ነገሥት 5:1-4

ከቅርንጫፍ ቢሮው የደረሰኝ ደብዳቤ አክሎ እንዲህ ይላል:- “ትንሽ ልጅ እንደመሆንሽ መጠን ለወላጆችሽ ታዛዥ በመሆንና ትምህርትሽን ተግተሽ በመማር ይሖዋን ልታገለግዪው ይገባል። እንዲሁም በጸሎትና በጥናት አማካኝነት ይበልጥ ወደ ይሖዋ መቅረብ ይኖርብሻል።” ደብዳቤው በመደምደሚያው ላይ “ዳንዬል፣ የምንኖረው የትም ይሁን የት ይሖዋ ምንጊዜም ከእኛ ጋር እንደሆነ አትርሺ፤ ይህንን ደግሞ እንደምታምኚበት ይሰማናል” ይላል። (ሮሜ 8:35-39) ይህ ደብዳቤ ያረጀና የነተበ ቢሆንም እስካሁን ድረስ በመጽሐፍ ቅዱሴ ውስጥ አስቀምጬዋለሁ። ለብዙ ዓመታት በተደጋጋሚ አንብቤዋለሁ። ሆኖም ሳነበው ያላለቀስኩበት ጊዜ የለም።

ከዚያ ብዙም ሳይቆይ አባቴ፣ መጠበቂያ ግንብና ንቁ! መጽሔቶች በፖስታ ቤት እንዲደርሱኝ አስፈላጊውን ዝግጅት እንዳደረገልኝ የሚገልጽ ደብዳቤ ደረሰኝ። በዚህ ጊዜ በጣም ተደሰትኩ! ከዚህ ጊዜ አንስቶ መንፈሳዊ ምግብ በየጊዜው አገኝ ጀመር። እያንዳንዱ እትም እንደደረሰኝ ከዳር እስከ ዳር አነበዋለሁ። መጀመሪያ ላይ የደረሱኝ እነዚያ የሚያማምሩ መጽሔቶች እስካሁን ድረስ አሉኝ። በዚህ ጊዜ አካባቢ በአቅራቢያችን ያለ የአንድ ጉባኤ ሽማግሌ እየመጣ ይጠይቀኝ ጀመር። ምንም እንኳ ወንድም የሚቆየው ለአጭር ጊዜ ቢሆንም የምናደርገው ጭውውት አበረታች ነበር።

የሁኔታዎች መለወጥ እድገት እንዳደርግ ረዳኝ

ያለሁበት መንፈሳዊ ሁኔታ የተሻሻለ ቢሆንም ይሖዋን በነጻነት የማመልክበትን ጊዜ እናፍቅ ነበር። 13 ዓመት ሲሆነኝ ከአባቴ ጋር መኖር እችል እንደሆነ እናቴን ጠየቅኋት። እናቴ እንደምትወደኝ ሁሉ እኔም በጣም እወዳት ነበር፤ ሆኖም ይሖዋን ለማገልገል ቆርጬ ነበር። እናቴም በሐሳቤ ስትስማማ ወደ ሞኢ ተመልሼ በዚያ አካባቢ በሚገኘው ጉባኤ ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመርኩ። አባታችን ስለፈቀደልን እኔና ጄሚ በሁሉም የጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመርን። በዚያ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች እኛን ለመርዳት ከፍተኛ ጥረት ያደርጉ ነበር። እኔና ጄሚ ፈጣን መንፈሳዊ እድገት አድርገን በጥቂት ወራት ልዩነት ተጠመቅን። አዎን፣ ልጅ ሳለሁ ላቀረብኩት ጸሎት መልስ አገኘሁ። ከሕዝቡ ጋር ሆኜ ይሖዋን ማገልገል ጀመርኩ!

ከጊዜ በኋላ በሞኢ ጉባኤ ከሚገኙት ፊሊፕ ከተባለው አጎቴና ሎሬን ከምትባለው አክስቴ ጋር በጣም ተቀራረብን። እንዲያውም ልክ እንደ ልጃቸው ነበር የሚያዩኝ። የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ሄደው ለማገልገል ሲሉ በፓፑዋ ኒው ጊኒ ወደምትገኘው ቡገንቪል ደሴት በተዛወሩ ጊዜ አብሬያቸው እንድሄድ ሲጠይቁኝ ያለምንም ማመንታት ለመሄድ ተስማማሁ። በወቅቱ የ15 ዓመት ልጅ የነበርኩ ቢሆንም አባቴና እናቴ እንድሄድ ፈቀዱልኝ።

ቡገንቪል እያለሁ ትምህርቴን በተልእኮ መማር ቀጠልኩ። ከትምህርት ሰዓት ውጭ አብዛኛውን ጊዜ የማሳልፈው በስብከቱ ሥራ ነበር። ከሚስዮናውያንና ከአቅኚዎች ጋር ማገልገል ምንኛ ያስደስታል! በዚህ አካባቢ እንዳሉ ሰዎች ትሑት ሕዝብ አይቼ አላውቅም። ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው።

ከጊዜ በኋላ የፖለቲካ ብጥብጥ ስለተነሳ እዚያ መቆየት አስቸጋሪ ሆነብኝ። ያቺን ትንሽ ደሴትና የሚያማምሩ ሕዝቦቿን ትቶ መሄድ የሚያሳዝን ነው። የተሳፈርኩባት ትንሽ አውሮፕላን መሬት ለቅቃ ስትነሳ አጎቴ ፊሊፕ እጁን ሲያውለበልብ ተመለከትኩት። ስቅስቅ ብዬ እያለቀስኩ፣ ይሖዋ አንድ ቀን በውጭ አገር ሚስዮናዊ ሆኜ እንዳገለግል እንዲፈቅድልኝ በውስጤ ለመንኩት።

ለጸሎቶቼ መልስ አገኘሁ

ወደ አውስትራሊያ ተመልሼ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ካጠናቀቅኩ በኋላ ሕግ ነክ ጉዳዮችን በሚከታተል አንድ ድርጅት ውስጥ በተለማማጅነት መሥራት ጀመርኩ። በዚህ መሃል አባቴ እንደገና አግብቶ ትልቅ ቤተሰብ መሥርቶ ነበር። ጄሚ ከእናታችን ጋር ይኖር የነበረ ሲሆን እኔ ደግሞ ለተወሰኑ ጊዜያት አንዴ ከእናቴ ጋር ሌላ ጊዜ ደግሞ ከአባቴ ጋር እኖር ነበር። ሕይወት የተመሰቃቀለብኝ መሰለኝ። ኑሮዬን ቀላል በማድረግ በመንፈሳዊ ግቦቼ ላይ ለማተኮር ስለፈለግሁ በ1994 በሞኢ አቅኚ ሆኜ በማገልገል የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ጀመርኩ።

እንደገና ደስተኛ ሕይወት መምራት ጀመርኩ። በጉባኤ ውስጥ የምቀራረበው መንፈሳዊ ዝንባሌ ካላቸው ወጣቶች ጋር ነበር። እነዚህ ጓደኞቼ ትልቅ ድጋፍ ሆነውልኛል። ከእነርሱም መካከል ረጋ ያለ፣ ደግና ትሑት የሆነውን ዊል የተባለ ወንድም በ1996 አገባሁ። ዊል በእውነትም ከይሖዋ የተገኘ ስጦታ ነው።

እኔና ዊል የተረጋጋ የትዳር ሕይወት የነበረን ሲሆን በጣም ደስተኞች ነበርን። አንድ ቀን ዊል ጉባኤያችንን ይጎበኝ ከነበረው ተጓዥ የበላይ ተመልካች ጋር ሲያገለግል ቆይቶ ወደ ቤት ተመለሰ። እንድቀመጥ ከነገረኝ በኋላ “ለእርዳታ ወደ ሌላ ጉባኤ ለመሄድ ፈቃደኛ ትሆኛለሽ?” ሲል ጠየቀኝ። እኔም በውስጤ አዎን ብዬ የመለስኩ ቢሆንም ለቀልድ ያህል “የት? ቫንዋቱ? ፊጂ?” ብዬ ጠየቅሁት። ዊልም “ሞርዌል” በማለት ሲመልስልኝ “ውይ እሱማ እዚሁ አይደለም እንዴ!” አልኩት። ሁለታችንም ተሳስቀን በጎረቤት ጉባኤ ውስጥ በአቅኚነት ለማገልገል ተስማማን።

በሞርዌል ያሳለፍናቸው ቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት አስደሳችና ፍሬያማ ነበሩ። ከዚያም አንድ ያልጠበቅነው ነገር አጋጠመን። አውስትራሊያ ከሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ልዩ አቅኚዎች ሆነን እንድናገለግል የተጋበዝን መሆናችንን የሚገልጽ ደብዳቤ ደረሰን። የተመደብነው ከኢንዶኔዥያ ተጎራባች ደሴቶች ምሥራቃዊ ጫፍ ላይ በምትገኘው ምሥራቅ ቲሞር በምትባለው ትንሽ አገር ነው። * በዚህ ወቅት ዓይኖቼ እንባ አቀረሩ። ይሖዋ ጸሎቶቼን ሁሉ ስለሰማልኝ አመሰገንኩት። ይሖዋ አገልጋዩ እንድሆን ብቻ ሳይሆን ከባለቤቴ ጋር በውጭ አገር ማገልገል እንድችል አጋጣሚ ሰጥቶኛል።

በባሕር ማዶ ማገልገል

ሐምሌ 2003 የምሥራቅ ቲሞር ዋና ከተማ ወደሆነችው ዲሊ ደረስን። የዲሊ ጉባኤ በአገሪቱ የሚገኝ ብቸኛ ጉባኤ ሲሆን ከአውስትራሊያ የመጡ 13 ልዩ አቅኚዎችና የአገሬው ተወላጅ የሆኑ ጥቂት የይሖዋ ምሥክሮችን ያቀፈ ነው። በቲሞር የሚገኙት ወንድሞችና እህቶች በጣም ድሆች ነበሩ። ብዙዎቹ ለ24 ዓመታት በዘለቀውና በ1999 ባበቃው የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት ንብረቶቻቸውንና የቤተሰባቸውን አባላት አጥተዋል። አብዛኞቹም በአዲሱ እምነታቸው የተነሳ የሚደርስባቸውን ከባድ የቤተሰብ ተቃውሞ መቋቋም አስፈልጓቸዋል። ምንም እንኳ ብዙ መከራ ያሳለፉ እንዲሁም ድሆች ቢሆኑም በመንፈሳዊ ሀብታምና ደስተኞች ናቸው።—ራእይ 2:8, 9

አብዛኞቹ ቲሞራውያን አምላክን የሚፈሩና ለመጽሐፍ ቅዱስ አክብሮት ያላቸው ናቸው። እንዲያውም በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ከማግኘታችን የተነሳ ማስጠናት ከአቅማችን በላይ ሆኖብን ነበር! መጀመሪያ አካባቢ ካገኘናቸው ጥናቶች መካከል አንዳንዶቹ የተጠመቁ ወንድሞችና እህቶች ሆነው አብረውን ይሖዋ ማገልገል ጀምረዋል። ጥናቶቻችን መንፈሳዊ እድገት ሲያደርጉ ማየት ከፍተኛ ደስታ አስገኝቶልናል።

ከዚያም በ2006 ዲሊ ውስጥ እንደገና ብጥብጥ ተቀሰቀሰ። በተለያዩ ትንንሽ ጎሳዎች መካከል የተፈጠረው ግጭት ተባብሶ ወደ ከፍተኛ ደረጃ ደረሰ። በርካታ ቤቶች በመዘረፋቸው ወይም በእሳት በመጋየታቸው ምክንያት በአካባቢው የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች በልዩ አቅኚዎች ቤት መጠለል ግድ ሆኖባቸዋል። በወቅቱ ቤታችንና ግቢያችን ጊዜያዊ መጠለያ ካምፕ ሆኖ አገልግሏል። እንዲያውም በአንድ ወቅት ወደ መቶ የሚጠጉ ሰዎች ቤታችን አርፈው ነበር! ለመኪና ማቆሚያነት የምንጠቀምበት ሰፊ ቦታ ኩሽና፣ ምግብ ቤትና ጊዜያዊ የመንግሥት አዳራሽ ሆኖ ነበር።

ምንም እንኳ በአቅራቢያችን ተኩስና የቦምብ ፍንዳታ ቢኖርም ቤታችን ሰላም የሰፈነበት ነበር። ሁላችንም የይሖዋ ጥበቃ እንዳልተለየን ተሰምቶናል። የዕለቱን እንቅስቃሴያችንን የምንጀምረው በአንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ላይ ውይይት በማድረግ ነበር። እንደወትሮው ሁሉ ስብሰባዎችን እናደርግ የነበረ ሲሆን ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችንም መጽሐፍ ቅዱስ እናስጠናለን።

ሳምንታት እያለፉ ሲሄዱ በአገሪቱ ምሥራቃዊ ክፍል የተወለዱ ወንድሞች በዲሊ መቆየታቸው አደገኛ መሆኑ ግልጽ እየሆነ መጣ። ስለዚህ ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች ከዲሊ በስተ ምሥራቅ ከሦስት ሰዓት ጉዞ በኋላ በምትገኘውና በስፋቷ ሁለተኛውን ደረጃ በምትይዘው በባውካው አዲስ ቡድን እንዲቋቋም ወሰኑ። እኔና ዊል እዚያ እንድናገለግል የተመደብነውም ለዚህ ነው።

ምሥራቅ ቲሞር ከደረስን ከሦስት ዓመት በኋላ ማለትም ሐምሌ 2006 ወደ ባውካው መጣን። አዲሱ ቡድናችን አራት ልዩ አቅኚዎችንና ስድስት ቲሞራውያን የይሖዋ ምሥክሮችን ያቀፈ ነበር። ምንም እንኳ የአካባቢው ወንድሞችና እህቶች በዲሊ የነበራቸውን ንብረት ሁሉ ቢያጡም ፈገግታ ከፊታቸው አልተለያቸውም ነበር። የእነዚህን ወንድሞች ታማኝነትና የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ ከልብ እናደንቃለን!

እኔና ዊል አሁንም በባውካው በማገልገል ላይ እንገኛለን። የተሰጠንን የአገልግሎት ምድብ የምንወደው ከመሆኑም በላይ ከይሖዋ ያገኘነው ተጨማሪ በረከት እንደሆነ አድርገን እንቆጥረዋለን። ወደኋላ መለስ ብዬ ሳስብ አያቴ ትክክል እንደነበረች ይሰማኛል። ይሖዋ በእነዚህ ሁሉ ዓመታት ተንከባክቦኛል። ይሖዋ ከሕዝቦቹ ጋር እንዳገለግለው ስለፈቀደልኝ ሁልጊዜ አመሰግነዋለሁ። አያቴ ከሞት ተነስታ የምንገናኝበትን ጊዜ በናፍቆት እጠባበቃለሁ። በዚያን ጊዜ ሕይወቴ አስደሳችና አርኪ እንዲሆን ምን ማድረግ እንዳለብኝ ስለነገረችኝ አመሰግናታለሁ።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.9 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።

^ አን.25 ኢስት ቲሞር (ምሥራቅ ቲሞር) የሚለውን ስያሜ የሰጧት እንግሊዝኛ ተናጋሪዎች ሲሆኑ ቲሞር ሌስተ ተብላም ትጠራለች።

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከአያቴ ጋር

[በገጽ 28, 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከባለቤቴ ከዊል ጋር