በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እርሳስ ያለው አለ?

እርሳስ ያለው አለ?

እርሳስ ያለው አለ?

ብሪታንያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

ርካሽ፣ ጥቅም ላይ ለማዋል ውጣ ውረድ የማይጠይቅና ክብደት የሌለው መሣሪያ ነው። በቀላሉ በኪስ ሊያዝ የሚችል ሲሆን ለመሥራት የኤሌክትሪክ ኃይል አያስፈልገውም፤ ቀለም የማይተፋ ከመሆኑም በላይ በእርሱ የተጻፈውን ነገር በቀላሉ ማጥፋት ይቻላል። ልጆች መጻፍ የሚለማመዱት፣ እውቅ ሠዓሊዎች ድንቅ የሥዕል ሥራዎችን የሚሠሩት በእርሱ ነው። ብዙዎቻችን ለማስታወሻ መያዣነት ስለምንፈልገው ከኪሳችን አንለየውም። አዎን፣ በየትኛውም ቦታ እንደ ልብ የሚገኘው እርሳስ በዓለም ላይ ማንም ሰው በቀላሉ ሊገዛው የሚችልና በሰፊው ጥቅም ላይ የዋለ የጽሕፈት መሣሪያ ነው። እርሳስ የተፈለሰፈበትንም ሆነ እየተሻሻለ የመጣበትን መንገድ በተመለከተ የሚነገረው አስደናቂ ታሪክ የሚጀምረው እንግሊዝ ውስጥ ባለ ገጠራማ ቦታ ድንገት በተገኘ አንድ ግኝት ነው።

ጥቁር ሊድ

በ16ኛው መቶ ዘመን በሰሜናዊው እንግሊዝ፣ ሌክ ዲስትሪክት ውስጥ ባለው ሸለቆ በሚገኝ ቦሮውዴል በሚባል ኮረብታ ግርጌ ምንነታቸው በውል የማይታወቅ ጥቋቁር ጓሎች ተገኙ። ሰዎች ይህን ማዕድን ሲያዩት ከሰል ቢመስላቸውም ሊያነዱት ሲሞክሩ ሊነድ አልቻለም፤ በሌላ በኩል ግን ለመጻፊያነት በሚያገለግሉ ነገሮች ላይ ሲጭሩት በቀላሉ የሚጠፋ የሚያብረቀርቅ ጥቁር ምልክት ይተዋል። መጀመሪያ ላይ ይህ ንጥረ ነገር ጥቁር ሊድ የሚል ስም ተሰጥቶት ነበር። በነካው ነገር ላይ የመላከክ ባሕርይ ስለነበረው ሰዎች ቁርጥራጮቹን በበግ ቆዳ ወይም በሲባጎ ይጠቀልሏቸው ነበር። ሊዱን እንጨት ውስጥ አስገብቶ የመያዙን ሐሳብ ለመጀመሪያ ጊዜ ያፈለቀው ማን እንደሆነ በውል አይታወቅም። ይሁን እንጂ በ1560ዎቹ ዓመታት ጥንታዊው እርሳስ አውሮፓ አሕጉር ደርሶ ነበር።

ብዙም ሳይቆይ ጥቁር ሊድ ተቆፍሮ እየወጣ የሠዓሊዎችን ፍላጎት ለማሟላት ሲባል ወደ ውጭ አገር ይላክ ጀመር። በ17ኛው መቶ ዘመን ደግሞ በሁሉም ቦታ ጥቅም ላይ ውሎ ነበር። ይህ በእንዲህ እንዳለ የእርሳስ አምራቾች የተሻለ የጽሕፈት መሣሪያ ለመሥራት ጥቁር ሊድ ብለው በጠሩት በዚህ ንጥረ ነገር ላይ ምርምር ያካሂዱ ጀመር። ንጹሕ የሆነውና በቀላሉ ከመሬት ማውጣት የሚቻለው ቦሮውዴል የተባለ ምርት የሌቦችና የሕገ ወጥ ነጋዴዎች ዒላማ ሆነ። በዚህም ምክንያት የብሪታንያ ፓርላማ በ1752 ጥቁር ሊድ መስረቅ በእስራት ወይም በግዞት የሚያስቀጣ ወንጀል መሆኑን የሚገልጽ ሕግ አጸደቀ።

በ1779 ስዊድናዊው የኬሚስትሪ ሊቅ ካርል ሼለ ጥቁር ሊድ እንደታሰበው ሊድ የተባለው ማዕድን ሳይሆን ለስላሳነት ያለው የንጹሕ ካርቦን ዓይነት መሆኑን በምርምር ደረሰበት። ይህ ከሆነ ከአሥር ዓመታት በኋላ ጀርመናዊው ጂኦሎጂስት አብርሃም ቨርነር ይህን ንጥረ ነገር ግራፋይት በማለት ሰየመው፤ ቃሉ ግራፌን ከሚል የግሪክኛ ቃል የተወረሰ ሲሆን “መጻፍ” የሚል ትርጉም አለው። በእርግጥም እርሳሶች ሊድ የሚባል ነገር የለባቸውም!

እርሳስ እየተሻሻለ የመጣበት መንገድ

የእንግሊዙ ግራፋይት ንጹሕና ምንም ዓይነት ተጨማሪ ሂደት የማይጠይቅ በመሆኑ ለበርካታ ዓመታት የእርሳስ ኢንዱስትሪውን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሮት ነበር። በአውሮፓ ያለው ግራፋይት ጥራቱ አነስተኛ በመሆኑ በዚያ የነበሩት አምራቾች የእርሳሱን ጥራት ማሻሻል የሚቻልበትን መንገድ ለማግኘት ምርምር ማድረግ ጀመሩ። ፈረንሳዊው ኢንጂነር ኒኮላ ዣክ ኮንታ ግራፋይትን ከሸክላ ጋር አብኩቶ ቀጫጭን እርሳሶችን ከሠራ በኋላ ምድጃ ላይ አድርጎ በእሳት ተኮሳቸው። ይህ ሰው በሸክላው ውስጥ የሚገባውን የግራፋይት መጠን በመጨመርና በመቀነስ የተለያየ የጥቁረት ደረጃ ያላቸውን እርሳሶች መሥራት ችሏል። ይህ ዘዴ አሁንም ድረስ እየተሠራበት ነው። ኮንታ የፈጠራ ባለቤትነት መብቱን በ1795 አስከብሯል።

በ19ኛው መቶ ዘመን እርሳስ ማምረት ትልቅ ንግድ ሆነ። ግራፋይት ሳይቤሪያን፣ ጀርመንንና የአሁኗን ቼክ ሪፑብሊክ ጨምሮ በተለያዩ ቦታዎች ተገኘ። በመጀመሪያ በጀርመን ከዚያም በኋላ በዩናይትድ ስቴትስ በርካታ ፋብሪካዎች ተከፈቱ። እርሳስ በማሽኖች አማካኝነት በብዛት መመረቱ ዋጋውን ያወረደው ሲሆን 20ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ ትምህርት የጀመሩ ልጆች እንኳ ሳይቀሩ እርሳስ ተጠቃሚ ሆነው ነበር።

ዘመናዊው እርሳስ

በዓለም ዙሪያ በየዓመቱ በብዙ ቢሊዮኖች የሚመረተው እርሳስ ለጽሑፍም ሆነ ለሥዕል ሁለገብ አገልግሎት የሚሰጥ ጥራት ያለው የጽሕፈት መሣሪያ ሆነ። አንድን የእንጨት እርሳስ እንደ ምሳሌ ብንወስድ 56 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው መሥመርና 45,000 ቃላትን መጻፍ ይችላል። ከብረት ወይም ከፕላስቲክ በተሠሩ እስክርቢቶ መሰል መያዣዎች ውስጥ የሚገቡ ቀጫጭን እርሳሶች ፈጽሞ ስለማይዶለዱሙ መቀረጽ አያስፈልጋቸውም። ባለ ቀለም እርሳሶች በግራፋይት ፋንታ የተለያየ ዓይነት መልክ ያላቸውን ቀለማት ይጠቀማሉ።

ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያለው፣ ጠንካራ፣ ቀላልና ውጤታማ የሆነው እርሳስ በሌላ ነገር ተተክቶ ከአገልግሎት ውጪ እንደሚሆን የሚያሳይ አዝማሚያ አይታይም። በመሆኑም በመጪዎቹም ዓመታት በቤትም ይሁን በሥራ ቦታ አንድ ሰው “እርሳስ ያለው አለ?” ብሎ ሲጠይቅ መስማትህ አይቀርም።

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

እርሳሱ እንጨቱ ውስጥ የሚገባው እንዴት ነው?

የተፈጨ ግራፋይትና ሸክላ በውኃ ከተቦካ በኋላ በጣም ቀጭን ቀዳዳ ባለው የብረት ቱቦ ውስጥ በኃይል ተገፍቶ ሲያልፍ ረዥም ፓስታ የሚመስል ቅርጽ ይዞ ይወጣል። እርሳሱ ከደረቀ በኋላ ተቆራርጦ በጡብ መጥበሻ ላይ ተደርጎ ይጠበስና በትኩስ ዘይትና ሰም ውስጥ ይጨመራል። በቀላሉ የሚቀረጽ እንጨት (ብዙውን ጊዜ ለዚህ ዓላማ የሚውለው የጥድ እንጨት ነው) በቀጫጭኑ ከተሰነጣጠቀ በኋላ ይላግና እርሳሱን በግማሹ መያዝ እንዲችል ተደርጎ ይቦረቦራል። ከዚያም እርሳሱ በተቦረቦረው ቦታ ይገባና በተመሳሳይ ሁኔታ የተዘጋጀ ሌላ እንጨት ሙጫ ተደርጎለት ከመጀመሪያው እንጨት ጋር ይጣበቃል። ሙጫው ሲደርቅ በሚፈለገው መጠን ይቆራረጣል። እንጨቶቹ ቅርጽ ከወጣላቸው፣ በብርጭቆ ወረቀት ከለሰለሱና ቀለም ከተቀቡ በኋላ የአምራቹ የንግድ ምልክት ይታተምባቸዋል፤ ከዚህ በኋላ ከአንድ ወጥ እንጨት የተሠሩ የሚመስሉት እርሳሶች አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ ይሆናሉ። እርሳሱ አንዳንድ ጊዜ በአንዱ ጫፍ ላይ ላጲስ ይገጠምለታል።

[ምንጭ]

Faber-Castell AG

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የትኛውን እርሳስ ብጠቀም ይሻላል?

የምትፈልገውን የእርሳስ ዓይነት ለመምረጥ በእርሳሱ ጎን ላይ የተጻፉትን ፊደላት ወይም ቁጥሮች ልብ ብለህ ተመልከት። እነዚህ ፊደላት ወይም ቁጥሮች የእርሳሱን የጥንካሬ አሊያም የልስላሴ መጠን የሚያመለክቱ ናቸው። ለስላሳ እርሳሶች ደማቅ ቀለም ይኖራቸዋል።

ኤችቢ (HB) ሁለገብ ሲሆን በመካከለኛ ደረጃ ላይ የሚመደብ እርሳስ አለው።

(B) የሚል ምልክት ያላቸው ደግሞ ለስላሳ እርሳሶች ናቸው። እንደ 2B ወይም 6B ያሉት ምልክቶች የእርሳሱን የልስላሴ መጠን የሚያመለክቱ ሲሆኑ ቁጥሩ ከፍ ባለ መጠን የእርሳሱ ልስላሴም የዚያኑ ያህል ይጨምራል።

ኤች (H) የሚያመለክተው ጠንካራ እርሳስን ነው። ቁጥሩ 2H፣ 4H፣ 6H እና ወዘተ እያለ ከፍ ባለ መጠን፣ የእርሳሱ ጥንካሬም የዚያኑ ያህል ይጨምራል።

ኤፍ (F) የሚለው ምልክት የእርሳሱ የጥንካሬ ደረጃ በH እና በHB መካከል መሆኑን ያመለክታል።

አንዳንድ አገሮች ከላይ ከተጠቀሱት የተለዩ መለኪያዎችን ይጠቀማሉ። ለምሳሌ ያህል በዩናይትድ ስቴትስ 2 የሚል ምልክት ያለው እርሳስ ደረጃው ከHB ጋር ተመጣጣኝ ነው። በዚህ መሠረት ቁጥሩ ከፍ ባለ መጠን የእርሳሱም ጥንካሬ እየጨመረ ይሄዳል።