በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሻርክ ቤይ—አስደናቂ የባሕር ወሽመጥ

ሻርክ ቤይ—አስደናቂ የባሕር ወሽመጥ

ሻርክ ቤይ—አስደናቂ የባሕር ወሽመጥ

አውስትራሊያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

ሻርክ ቤይ በአውስትራሊያ ምዕራባዊ ጠረፍ ከፐርዝ ከተማ በስተ ሰሜን 650 ኪሎ ሜትር ርቆ የሚገኝ ጥልቀት የሌለው ትልቅ የባሕር ወሽመጥ ነው። በ1629 የደች ዜጋ የሆነው ፍራንስዋ ፔልሳርት የተባለ አሳሽ ይህን በረሃማ ቦታ “ሣር ቅጠል የሌለበት የተራቆተና የተረገመ አገር” በማለት ገልጾታል። ከዚያ ወዲህ አካባቢውን ሊጎበኙ የመጡ ሰዎችም “ተስፋ የሌለው የውኃ አካል፣” “ጥቅም የሌለው የባሕር ወሽመጥ፣” እና “ተስፋ አስቆራጭ ቦታ” በማለት ስሜታቸውን በጽሑፍ አስፍረዋል።

ይሁንና በአሁኑ ጊዜ በየዓመቱ ከ120,000 የሚበልጡ ሰዎች ሻርክ ቤይን ለመጎብኘት ይጎርፋሉ። ይህ ርቆ የሚገኝ ቦታ ያሉት መስህቦች በጣም አስደናቂ ከመሆናቸው የተነሳ በ1991 በዓለም ቅርስ መዝገብ ላይ ሰፍሯል። *

ሕያዋን ፍጥረታት የሚርመሰመሱባቸው መስኮች

በሻርክ ቤይ፣ በአጠቃላይ ከ4,000 ካሬ ኪሎ ሜትር በላይ የሚሆን ቦታ የሚሸፍኑና በዓለም ላይ ብዙ ዓይነት ሣር መሰል የባሕር ውስጥ ዕፅዋትን በመያዝም ሆነ በትልቅነታቸው ተወዳዳሪ የሌላቸው መስኮች ይገኛሉ፤ በመሆኑም ፔልሳርት ወደ ውኃው ውስጥ ቢመለከት ኖሮ በሣር የተሸፈነ መስክ ያገኝ ነበር። በሻርክ ቤይ ምሥራቃዊ ክፍል የሚገኘው ዉራሜል የሚባለው የባሕር ውስጥ ሣር ያለበት ዳርቻ ብቻ እንኳን 130 ኪሎ ሜትር ርቀት ይሸፍናል።

የባሕር ውስጥ ሣር ተብለው የሚጠሩት አበባ ያላቸው ዕፅዋት ሲሆኑ እነዚህ ዕፅዋት ዓይነታቸው ለቁጥር የሚያታክት የባሕር ውስጥ ፍጥረታትን ይጠቅማሉ። ገና ታዳጊ የሆኑ ሸርጣኖች፣ ትናንሽ ዓሦችና ቁጥር ሥፍር የሌላቸው ሌሎች የባሕር ውስጥ ፍጥረታት በባሕር ውስጥ ዕፅዋት ቅጠሎች ሥር ይኖራሉ። በተጨማሪም የባሕር ውስጥ መስኩ 10,000 ለሚያህሉ ዱጎንግ ወይም የባሕር ላሞች ተብለው ለሚጠሩ እንስሳት በቂ ምግብ ይሆናቸዋል። እስከ 400 ኪሎ ግራም የሚመዝኑት እነዚህ ገራምና በዙሪያቸው የሚከናወነውን ነገር መመልከት የሚወዱ አጥቢ እንስሳት አንዳንድ ጊዜም ከ100 በላይ ሆነው በውኃው ውስጥ በብዛት የሚገኘውን መስክ በጸጥታ ይግጣሉ። በዓለም ላይ አብዛኞቹ የባሕር ላሞች የሚኖሩት በስተ ምዕራብ ካለው ሻርክ ቤይ አንስቶ በስተ ምሥራቅ እስካለው ሞርተን ቤይ ባለው የአውስትራሊያ ሰሜናዊ ክፍል ሳይሆን አይቀርም። *

ሻርክ ቤይ እንደ ስሙ ከ12 የሚበልጡ የሻርክ ዝርያዎች በብዛት የሚገኙበት ቦታ ነው። ከሻርኮቹ መካከል አስፈሪ የሆነው ታይገር ሻርክ እንዲሁም ከዓሣ ዝርያዎች ሁሉ በዓለም ላይ በትልቅነቱ አንደኛ ቢሆንም ምንም ጉዳት የማያደርሰው ግዙፉ ዌል ሻርክ ይገኛሉ። በዚህ ሥፍራ ዶልፊኖችም የሚኖሩ ሲሆን ይህም ዶልፊኖች ባሉበት ሻርኮች እንደማይገኙ የሚነገረው መሠረተ ቢስ ሐሳብ ሐሰት መሆኑን ያረጋግጣል። እንዲያውም በአካባቢው ካሉት ዶልፊኖች መካከል 70 በመቶ የሚሆኑት ሻርኮች ጥቃት እንደሰነዘሩባቸው የሚያሳይ ጠባሳ በሰውነታቸው ላይ እንደሚገኝ ተመራማሪዎች ደርሰውበታል። በሻርክ ቤይ ካሉት ልዩ ልዩ ዓይነት እንስሳት መካከል በሺዎች የሚቆጠሩ ሃምፕባክ የሚባለው ዓሣ ነባሪ ዝርያዎች የሚገኙ ሲሆን እነዚህ ዓሣ ነባሪዎች በየዓመቱ ወደ ደቡብ በሚፈልሱበት ወቅት በዚህ ሥፍራ ያርፋሉ፤ በባሕሩ ዳር እንቁላሎቻቸውን ለመጣል በየዓመቱ የሚመጡ ይህንኑ የሚያህል ቁጥር ያላቸው የባሕር ዔሊዎችም በሻርክ ቤይ ይገኛሉ።

በእርግጥ ዓለቶች ናቸው?

ከሌሎቹ የሻርክ ቤይ ክፍሎች በተለየ፣ በሻርክ ቤይ ደቡባዊ ጫፍ የሚገኘው ሃመሊን ፑል የሚባለው አካባቢ የተራቆተና ሕይወት አልባ ነው። በዚህ ቦታ የሚገኘው ጥልቀት የሌለው ለብ ያለ ውኃ በጣም ስለሚተን ጨዋማነቱ ከተለመደው የባሕር ውኃ በእጥፍ ይበልጣል። ውኃው ዙሪያውን ፈዘዝ ያለ ግራጫ ቀለም ባላቸው ዓለት መሳይ ነገሮች የተከበበ ነው። ሆኖም እነዚህ “ዓለቶች” በቅርበት ሲታዩ ስትሮማቶላይቶች እንደሆኑ ማወቅ ይቻላል፤ ስትሮማቶላይት እጅብ ብለው የሚኖሩና ሳይኖባክቴሪያ ወይም ወደ አረንጓዴ የሚወስደው ሰማያዊ ቀለም ያላቸው አልጌዎች ተብለው የሚጠሩ ባለ አንድ ሕዋስ ጥቃቅን ነፍሳት የሚሠሩት ነገር ነው። በእያንዳንዱ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ወደ ሦስት ቢሊዮን የሚያህሉ ሳይኖባክቴሪያዎች ይኖራሉ!

እነዚህ ችግር የማይበግራቸው ጥቃቅን ተሕዋስያን ራሳቸው የሚያመነጩትን ዝልግልግ የሚል የሚያጣብቅ ፈሳሽ፣ ከባሕሩ ውኃ ከተወሰዱ ነገሮች ጋር እየቀላቀሉ ሲሚንቶ ከሠሩ በኋላ ይህንን በማነባበር ዓለት የሚመስለውን ቤታቸውን ይገነባሉ። ሂደቱ ከመጠን በላይ አዝጋሚ ነው። አንድ ስትሮማቶላይት 30 ሴንቲ ሜትር ከፍታ ላይ ለመድረስ 1,000 ዓመት ሊፈጅበት ይችላል!

ሃመሊን ፑል፣ በዓለም ላይ በጣም ብዙና ልዩ ልዩ ዓይነት የባሕር ውስጥ ስትሮማቶላይቶች ያሉበት ቦታ ነው። ይህ ብቻም ሳይሆን ስትሮማቶላይቶች እስካሁን ሳይጠፉ የቆዩበት ብቸኛ ሥፍራም ነው።

የሻርክ ቤይ መስህቦች

ሻርክ ቤይ ካሉት መስህቦች ዋነኛው በዴናም ባሕረ ገብ መሬት ጫፍ ላይ በምትገኘው መንኪ ሚያ በተባለች የባሕር ዳርቻ አካባቢ ያለው ቦትልኖዝ የሚባለው ዶልፊን ነው። መንኪ ሚያ፣ ለማዳ ያልሆኑ ዶልፊኖች ከሰዎች ጋር ለመገናኘት ወደ ባሕሩ ዳርቻ አዘውትረው ከሚመጡባቸው በዓለም ላይ ያሉ ጥቂት ቦታዎች አንዷ ናት። ይህ የሰዎችና የዶልፊኖች ግንኙነት መቼ እንደጀመረ በእርግጠኝነት የሚያውቅ ሰው የለም።

አንዳንዶች በ1950ዎቹ ዓመታት ዶልፊኖች ዓሦችን ጥልቀት ወደሌለው ውኃ በመግፋት አንድ ላይ እንዲሰባሰቡ ያደርጉ እንደነበረ ይናገራሉ፤ ዛሬም ቢሆን ዶልፊኖች እንዲህ ሲያደርጉ ይታያል። ሰዎች በዚህ አጋጣሚ ተጠቅመው ዶልፊኖቹን ዓሣ ማብላትና ከእነርሱ ጋር መወዳጀት ጀምረው ሊሆን ይችላል። በ1964 በመንኪ ሚያ ዓሣ ስታጠምድ የነበረች አንዲት የአካባቢው ነዋሪ በጀልባዋ ዙሪያ ሲንቦራጨቅ ለነበረ ብቸኛ ዶልፊን ዓሣ ወረወረችለት። ሰዎች ቻርሊ ብለው ስም ያወጡለት ይህ ዶልፊን በቀጣዩ ምሽት መጣና በቀጥታ ከሴትዮዋ እጅ ላይ ዓሣ ተቀብሎ በላ። ብዙም ሳይቆይ የቻርሊ ጓደኞች የሆኑ ሌሎች ዶልፊኖችም አብረውት መምጣት ጀመሩ።

ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የእነዚህ ዶልፊኖች ልጆችና የልጅ ልጆች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ጎብኚዎችን ሲያዝናኑ እንዲሁም ባዮሎጂስቶችን ሲያስደስቱ ኖረዋል። ከተለያዩ አገሮች የመጡ ከ100 የሚበልጡ ባዮሎጂስቶች በእነዚህ እንስሳት ላይ ጥናት ያካሄዱ ሲሆን በዚህም የተነሳ እነዚህ ዶልፊኖች በዓለም ላይ ከሚገኙት ዶልፊኖች ሁሉ የበለጠ ጥናት ተደርጎባቸዋል።

በአሁኑ ጊዜ ዶልፊኖች ብዙውን ጊዜ ከልጆቻቸው ጋር በመሆን በአብዛኞቹ ቀናት ጠዋት ጠዋት ወደ መንኪ ሚያ የባሕር ዳርቻ ይመጣሉ። ብዙ ጎብኚዎች የዶልፊኖቹን መምጣት በጉጉት የሚጠባበቁ ሲሆን ለዶልፊኖቹ ዓሣ ለመስጠት አጋጣሚ የሚያገኙት ግን በጣም ጥቂቶች ናቸው። ለምን? ምክንያቱም የመናፈሻ ቦታው ጠባቂዎች እንስሳቱ ሰዎች የሚሰጧቸውን ምግብ ብቻ ከመጠበቅ ይልቅ ራሳቸው ምግባቸውን እንዲያገኙ ስለሚፈልጉ ነው። ይሁን እንጂ ለጉብኝት የመጡት ሰዎች በሙሉ ዶልፊኖቹ ከሰው እጅ ላይ ምግብ እየወሰዱ ሲበሉ የማየት አጋጣሚ ያገኛሉ። አንዲት ሴት “ሰዎች ከሁሉም የምድር ፍጥረታት ጋር እንዲህ ዓይነት ቅርርብ ቢኖራቸው እንዴት ጥሩ ነበር!” በማለት ምኞቷን ገልጻለች።

እንዲህ ያለው ምኞት አምላክ መጀመሪያ ሰዎችን ሲፈጥር ከነበረው ዓላማ ጋር ይስማማል፤ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚገልጸው የአምላክ ዓላማ ሁሉም እንስሳት ለሰዎች ሰላማዊ ሆነው እንዲገዙላቸው ነበር። (ዘፍጥረት 1:28) እንስሳትን የምትወድ ከሆነ፣ የአምላክ ዓላማ በኃጢአት የተነሳ ለጊዜው ቢስተጓጎልም እንኳ በኢየሱስ ክርስቶስ የሚመራው የአምላክ መንግሥት ምድርን በሚገዛበት ወቅት ሙሉ በሙሉ እንደሚፈጸም ማወቅ ሊያስደስትህ ይችላል።—ማቴዎስ 6:9, 10፤ ራእይ 11:15

በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር መላዋ ምድር በጤናማ ሰዎች የተሞላችና የተፈጥሮ ውበት የተላበሰች መኖሪያ ትሆናለች። በቅርቡ እንደ ሻርክ ቤይ ያሉ ሥፍራዎች ሊጎበኟቸው ለሚመጡ ሰዎች ከአሁኑ በበለጠ ሁኔታ የሚያሳዩት ተጨማሪ ነገር ይኖራቸዋል።—መዝሙር 145:16፤ ኢሳይያስ 11:6-9

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.4 የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት በዓለም ቅርስ መዝገብ ላይ የሚያሰፍረው የላቀ ባሕላዊ ወይም ተፈጥሯዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ቦታዎች ነው።

^ አን.7 ዱጎንግ ወይም የባሕር ላም፣ ማናቴ ከሚባሉት ቅጠል በል አጥቢ እንስሳት ጋር የሚመሳሰሉ ቢሆኑም ዝርያቸው የተለየ ነው። ማናቴዎች ጅራታቸው ክብ ሲሆን የባሕር ላሞች ግን እንደ ዶልፊኖች ዓይነት ሾል ያለ ጅራት አላቸው።

[በገጽ 15 ላይ የሚገኙ ካርታዎች]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

አውስትራሊያ

ሻርክ ቤይ

[በገጽ 16, 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የመንኪ ሚያ የባሕር ዳርቻ ከአየር ላይ ሆኖ ሲታይ

[በገጽ 16, 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ገራም የሆነው ዱጎንግ ወይም የባሕር ላም

[ምንጭ]

© GBRMPA

[በገጽ 16, 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በቢሊዮን የሚቆጠሩ ጥቃቅን ተሕዋስያን ስትሮማቶላይቶችን ይሠራሉ

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለማዳ ያልሆኑ ዶልፊኖች አዘውትረው ወደ መንኪ ሚያ የባሕር ዳርቻ ይመጣሉ

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

© GBRMPA; satellite map: Jeff Schmaltz, MODIS Rapid Response Team, NASA/GSFC

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ከዱጎንግ በቀር ሁሉም ምስሎች የተገኙት በምዕራብ አውስትራሊያ ቱሪዝም ትብብር ነው