በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ጥሩ ሰው መሆን” ብቻውን በቂ ነው?

“ጥሩ ሰው መሆን” ብቻውን በቂ ነው?

የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት

“ጥሩ ሰው መሆን” ብቻውን በቂ ነው?

አሊሰን የተባለች አንዲት ወጣት “በተቻለኝ መጠን ሕይወቴን በተሻለ መንገድ እመራለሁ እንዲሁም ጥሩ ሰው ለመሆን እሞክራለሁ” ብላለች። እንደዚህች ወጣት ሁሉ ብዙዎች አምላክ የሚፈልገው እንዲህ ዓይነቱን ሕይወት መምራት ነው ብለው ያምናሉ።

ሌሎች ደግሞ ከባድ ኃጢአት ቢፈጽሙም እንኳ አኗኗራቸው በጥቅሉ ሲታይ ጨዋነት የሚንጸባረቅበት እስከሆነ ድረስ አምላክ ግድ እንደማይሰጠው ይሰማቸዋል። አምላክ ይበልጥ የሚያዘነብለው ወደ መቅጣት ሳይሆን ይቅር ወደ ማለት ነው የሚል እምነት አላቸው።

እርግጥ ነው፣ “ጥሩ ሰው” ለሚለው አባባል የሚሰጠው ፍቺ ከሰው ወደ ሰው ይለያያል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይላል? በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ምን ማድረግ ይኖርብናል? በአምላክ ዓይን ጥሩ ሰው መሆን ሲባል ምን ማለት ነው?

የፈጣሪያችንን መመሪያ መቀበል

ይሖዋ አምላክ ፈጣሪያችን እንደመሆኑ መጠን ለእኛ የሥነ ምግባር መመሪያ የመስጠት መብት አለው። (ራእይ 4:11) አምላክ አኗኗራችንንና አምልኳችንን በተመለከተ መመሪያ ሆነው የሚያገለግሉ ሕጎችንና መሠረታዊ ሥርዓቶችን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አስፍሮልናል። ሕዝቦቹን “ቃሌን ስሙ፣ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ አድርጉ፤ እንዲሁም እናንተ ሕዝብ ትሆኑኛላችሁ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ” ብሏቸው ነበር።—ኤርምያስ 11:4 የ1954 ትርጉም

በመሆኑም በአምላክ አመለካከት “ጥሩ ሰው መሆን” የእርሱን ሕጎች መማርንና በእነዚህ መሠረት ለመኖር አኗኗራችንን ማስተካከልን ይጠይቃል። የአንድ ሰው ወዳጅ ለመሆን ፈለግህ እንበል። ወዳጅህ እንዲሆን የፈለግኸው ሰው መያዝ የሚፈልገው እንዴት እንደሆነ ማወቅ እንደምትፈልግ ብሎም እርሱን የሚያስደስተውን ነገር እንደምታደርግ ግልጽ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንደ አብርሃም ሁሉ እኛም የይሖዋ ወዳጆች ማለትም አምላክ በሞገሱ የሚመለከተን ሰዎች መሆን እንደምንችል ይጠቁማል። (ያዕቆብ 2:23) ደግሞም አምላክ ከእኛ ከሰዎች ላቅ ያሉ መሥፈርቶች ስላሉት ከሁኔታችን ጋር የሚስማማ ለውጥ እንዲያደርግ ልንጠብቅበት አንችልም።—ኢሳይያስ 55:8, 9

የመታዘዝ አስፈላጊነት

“ጥቃቅን” የሚመስሉ ትእዛዛትን ችላ ማለታችን በእርግጥ በአምላክ ዘንድ ያለንን ተቀባይነት ያሳጣናል? አንዳንድ ሰዎች ከፍተኛ ግምት የማይሰጣቸው የሚመስሉ ሕጎችን መታዘዝ ያን ያህል አስፈላጊ እንዳልሆነ ያስባሉ። ይሁንና አምላክ ያወጣው የትኛውም ሕግ ዝቅተኛ ግምት ሊሰጠው አይገባም። መጽሐፍ ቅዱስ በ1 ዮሐንስ 5:3 ላይ “እግዚአብሔርን መውደድ ትእዛዛቱን መፈጸም ነው” ሲል የአምላክን ሕግ መታዘዝን በተመለከተ ምንም ዓይነት ልዩነት እንዳላስቀመጠ ልብ በል። የአምላክን ሕጎች በሙሉ ለመታዘዝ ጥረት በማድረግ ለእርሱ ከራስ ወዳድነት ነጻ የሆነ ፍቅር እንዳለን ማረጋገጥ እንችላለን።—ማቴዎስ 22:37

ይሖዋ ከሰዎች ፍጽምናን አይጠብቅም። በሠራናቸው ስህተቶች ከልብ የምናዝንና እነዚህን ስህተቶች ላለመድገም ከፍተኛ ጥረት የምናደርግ ከሆነ ይሖዋ በደስታ ይቅር ይለናል። (መዝሙር 103:12-14፤ የሐዋርያት ሥራ 3:19) ይሁን እንጂ በሌሎች ጉዳዮች ባለን ታዛዥነት ይካካሳል ብለን በማሰብ አንዳንድ ሕጎችን ሆን ብለን ችላ ማለት እንችላለን? አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ እንዲህ ያለው አመለካከት ተቀባይነት እንደሌለው ያሳያል።

የእስራኤል ንጉሥ የነበረው ሳኦል አምላክ ከሰጠው ትእዛዝ ውስጥ የሚታዘዘው ለእርሱ ደስ የሚሉትን ብቻ ነበር። ከአማሌቃውያን ጋር በተዋጋበት ወቅት ከብቶቻቸውን አንድም ሳያስቀር ‘እንዲገድል’ ትእዛዝ ተሰጥቶት ነበር። ምንም እንኳ ሳኦል አንዳንድ መመሪያዎችን ቢከተልም “ምርጥ ምርጡን በግና የቀንድ ከብት” ባለመግደል አምላክን ሳይታዘዝ ቀረ። ለምን? እርሱና አብረውት የነበሩት ሰዎች በጎቹንና ከብቶቹን ለራሳቸው ፈልገዋቸው ስለነበር ነው።—1 ሳሙኤል 15:2-9

ነቢዩ ሳሙኤል፣ ሳኦል የአምላክን ትእዛዝ ሳይፈጽም የቀረው ለምን እንደሆነ ሲጠይቀው ሙሉ በሙሉ መታዘዙን ተናገረ። እንዲያውም ለአምላክ ያቀረቧቸውን መሥዋዕቶች ጨምሮ እርሱና ሕዝቡ ያከናወኗቸውን መልካም ሥራዎች ሁሉ ዘረዘረ። ሳሙኤል እንዲህ ሲል ጠየቀው:- “ለእግዚአብሔር ቃል በመታዘዝ ደስ የሚለውን ያህል፣ እግዚአብሔር በሚቃጠል ቍርባንና መሥዋዕት ደስ ይለዋልን? እነሆ! መታዘዝ ከመሥዋዕት፣ ማዳመጥም ከአውራ በግ ሥብ ይበልጣል።” (1 ሳሙኤል 15:17-22) በመሆኑም መሥዋዕቶችን በማቅረብ አሊያም ሌሎች ጥሩ ሥራዎችን በማከናወን፣ ሳንታዘዝ የቀረንባቸውን አጋጣሚዎች ማካካስ አንችልም።

አምላክ ያወጣቸው መሥፈርቶች የፍቅሩ መግለጫ ናቸው

ይሖዋ አፍቃሪ ስለሆነ እርሱን ማስደሰት የምንችለው ምን ብናደርግ እንደሆነ በግምት እንድንደርስበት አይጠብቅብንም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ የተቀመጡ የሥነ ምግባር መመሪያዎችን የሰጠን ሲሆን ይህንንም ማድረጉ “መንገዱ ይህ ነው፤ በእርሱ ሂድ” ያለ ያህል ነው። (ኢሳይያስ 30:21) የእርሱን መመሪያ መከተላችን ከብስጭት እንዲሁም ሰዎች ሥነ ምግባርን በሚመለከት ካላቸው እርስ በርሱ የሚጋጭ ሐሳብ ውስጥ የተሻለውን መምረጥ ከሚያስከትለው ግራ መጋባት ያድነናል። በተጨማሪም አምላክ ምንጊዜም መመሪያ የሚሰጠን ለጥቅማችን ይኸውም ‘የሚበጀን ምን እንደሆነ ለማስተማር’ እንደሆነ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ኢሳይያስ 48:17, 18

በእኛ አመለካከት ጥሩ መስሎ የሚታየንን መምረጥ ምን አደጋ አለው? ሁላችንም የራስ ወዳድነትን ዝንባሌ ወርሰናል። በመሆኑም ልባችን ሊያታልለን ይችላል። (ኤርምያስ 17:9) ከባድና የማያፈናፍኑ ናቸው ብለን ያሰብናቸውን ሕጎች አስፈላጊነት አቅልለን ልንመለከት እንችላለን።

ለምሳሌ ያህል፣ ሁለት ያልተጋቡ ሰዎች የጾታ ግንኙነት ቢፈጽሙ ይህ ድርጊት የግል ጉዳያቸው ስለሆነ ማንንም እንደማይነካ ይሰማቸው ይሆናል። ይህ ድርጊታቸው ከመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርቶች ጋር እንደሚጋጭ ቢገነዘቡም “ማንም እስካልተጎዳ” ድረስ አምላክ በሁኔታው አያዝንም የሚል ድምዳሜ ላይ ይደርሱ ይሆናል። የእነዚህ ሰዎች ፍላጎት የድርጊቱን ክብደትና የሚያስከትላቸውን መዘዞች እንዳያስተውሉ ሊጋርዳቸው ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ “ለሰው ቀና መስሎ የሚታይ መንገድ አለ፤ በመጨረሻ ግን ወደ ሞት ያደርሳል” በማለት ያስጠነቅቃል።—ምሳሌ 14:12

የይሖዋ ሕጎች በሙሉ እርሱ ለሰዎች ያለውን ፍቅር ብሎም ከችግር ነጻ የሆነ ሕይወት እንድንመራ ያለውን ፍላጎት የሚያንጸባርቁ ናቸው። ሰዎች፣ አምላክ የጾታ ሥነ ምግባርንም ሆነ ሌሎች ጉዳዮችን አስመልክቶ ያወጣቸውን ሕጎች መጣሳቸው የተሻለ ደስታ እንዲያገኙና ስኬታማ ሕይወት እንዲመሩ አላደረጋቸውም። እንዲያውም ብዙዎቹን ለከባድ ችግር ዳርጓቸዋል። በሌላ በኩል ግን የአምላክን ሕጎች መከተላችን ጥሩ ሕይወት እንድንመራ ይረዳናል እንዲሁም በእኛም ሆነ በሌሎች ላይ አላስፈላጊ ጉዳት እንዳናደርስ ይጠብቀናል።—መዝሙር 19:7-11

በአምላክ ዘንድ ጥሩ ሰው ሆነህ ለመገኘት ልባዊ ፍላጎት ካለህ መመሪያዎቹን ለመከተል ከፍተኛ ጥረት አድርግ። እንዲህ ካደረግህ የይሖዋ ‘ትእዛዛት ከባድ አይሆኑብህም።’—1 ዮሐንስ 5:3

ይህን አስተውለኸዋል?

▪ የፈጣሪያችንን መመሪያ መቀበል ያለብን ለምንድን ነው?—ራእይ 4:11

▪ የአምላክን ትእዛዛት በሙሉ መታዘዝ ይኖርብናል?—1 ዮሐንስ 5:3

▪ የራሳችንን የሥነ ምግባር መመሪያዎች ማውጣታችን ጥበብ ያልሆነው ለምንድን ነው?—ምሳሌ 14:12፤ ኤርምያስ 17:9

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አምላክ ለሥነ ምግባር ያለው ዓይነት አመለካከት አለህ?