በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የትምህርት ቤት ጓደኝነት ገደቡ እስከ ምን ድረስ መሆን አለበት?

የትምህርት ቤት ጓደኝነት ገደቡ እስከ ምን ድረስ መሆን አለበት?

የወጣቶች ጥያቄ . . .

የትምህርት ቤት ጓደኝነት ገደቡ እስከ ምን ድረስ መሆን አለበት?

“አብረውኝ የሚማሩ ልጆች ቅዳሜና እሁድ አብረው ስላሳለፉት ጥሩ ጊዜ ሲያወሩ ስሰማ እንደተገለልኩ ሆኖ ይሰማኛል።”—ሚሼል *

“አንዳንድ ጊዜ የተወሰኑ ልጆች አንድ ላይ ሆነው በማይበት ጊዜ እንዴት ደስ የሚሉ ጓደኛሞች ናቸው ብዬ አስባለሁ። እኔም የእነሱ ጓደኛ ለመሆን እመኛለሁ።”—ጆ

“በትምህርት ቤት ውስጥ ወዳጆች በማፍራት በኩል ምንም ችግር የለብኝም። ከሌሎች ጋር በቀላሉ መቀራረብ እችላለሁ። ሆኖም ይህ ችግር አስከትሎብኛል።”—ማሪያ

ውሏችሁን በአብዛኛው የምታሳልፉት አብረዋችሁ ከሚማሩ ልጆች ጋር ነው። የሚያጋጥሟችሁ ፈታኝ ሁኔታዎች፣ የሚያበሳጯችሁ ነገሮችም ሆኑ የምትደርሱባቸው ስኬቶች ብዙውን ጊዜ ተመሳሳይ ናቸው። ከወላጆቻችሁ፣ ከወንድሞቻችሁና ከእህቶቻችሁ ወይም ከክርስቲያን ባልንጀሮቻችሁ ይልቅ አብረዋችሁ የሚማሩት ልጆች ከእናንተ ጋር አንድ የሚያደርጋቸው የጋራ ባሕርይ እንዳላቸው ሆኖ ሊሰማችሁ ይችላል። ከእነሱ ጋር ጓደኝነት ለመመሥረት ልትገፋፉ እንደምትችሉ የታወቀ ነው። ይህ ታዲያ ስህተት ነው? እንደዚህ ዓይነት ጓደኝነት አደጋ አለው? የትምህርት ቤት ጓደኝነት እስከ ምን ድረስ መሆን አለበት? ገደቡ የት ድረስ መሆን አለበት?

ጓደኞች ያስፈልጓችኋል

እያንዳንዱ ሰው ደስታውንም ሆነ ሐዘኑን ሊጋሩት የሚችሉ ጓደኞች ያስፈልጉታል። ኢየሱስ ጓደኞች የነበሩት ሲሆን ከእነርሱ ጋር በሚሆንበት ጊዜ ይደሰት ነበር። (ዮሐንስ 15:15) በመከራ እንጨት ላይ ተሰቅሎ ሊሞት በተቃረበበት ጊዜም የኢየሱስ የቅርብ ጓደኛ የነበረውና ‘[በጣም] የሚወደው ደቀ መዝሙሩ’ ዮሐንስ አጠገቡ ነበር። (ዮሐንስ 19:25-27፤ 21:20) እናንተም ብትሆኑ በአስቸጋሪ ጊዜያት ከአጠገባችሁ የማይርቁ ልክ እንደ ዮሐንስ ዓይነት ጓደኞች ያስፈልጓችኋል። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “ወዳጅ ምንጊዜም ወዳጅ ነው፤ ወንድምም ለክፉ ቀን ይወለዳል” ይላል።—ምሳሌ 17:17

ምናልባት በትምህርት ቤት አብረዋችሁ ከሚማሩ ልጆች መካከል በቀላሉ የምትግባቡት እንዲህ ዓይነት ጓደኛ እንዳገኛችሁ ሆኖ ሊሰማችሁ ይችላል። ተመሳሳይ ፍላጎቶች ሊኖሯችሁ ስለሚችል አንድ ላይ ማውራት ያስደስታችሁ ይሆናል። ግለሰቡ የእምነት ባልደረባችሁ ባይሆንም በእናንተ አመለካከት ‘ከመጥፎ ጓደኞች’ መካከል የማይፈረጅ ሊሆን ይችላል። (1 ቆሮንቶስ 15:33) በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተውን እምነታችሁን የማይጋሩ አንዳንድ ወጣቶች ጥሩ የሥነ ምግባር መመሪያዎችን ይከተሉ ይሆናል። (ሮሜ 2:14, 15) እንዲህ ሲባል ግን ከእነርሱ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት መመሥረት አለባችሁ ማለት ነው?

ክርስቲያኖች ሌሎች ሰዎችን አያገልሉም

እውነተኛ ክርስቲያኖች የእምነት አጋሮቻቸው ያልሆኑ ሰዎችን እንዲሁ አይርቋቸውም። እንዲያውም ክርስቲያኖች የትኛውንም ዘር፣ ሃይማኖትና ባሕል ሳይለዩ ሁሉንም ዓይነት ወንዶችና ሴቶች በማናገር ‘ሕዝቦችን ሁሉ ደቀ መዛሙርት የማድረጉን’ ተልእኳቸውን ይፈጽማሉ። (ማቴዎስ 28:19) ጎረቤቶቻቸውን፣ የሥራ ባልደረቦቻቸውንም ሆነ አብረዋቸው የሚማሩትን ልጆች አያገልሉም። ከዚህ ይልቅ ክርስቲያኖች ለሌሎች ልባዊ አሳቢነት ያሳያሉ።

በዚህ ረገድ ሐዋርያው ጳውሎስ ግሩም ምሳሌ ይሆናል። እምነቱን የማይጋሩት ቢሆኑም እንኳ ‘ከሁሉም ዓይነት ሰዎች ጋር’ እንዴት መነጋገር እንዳለበት ያውቅ ነበር። እርግጥ ነው የጳውሎስ ዓላማ ከእነርሱ ጋር መወዳጀት አልነበረም። ከዚህ ይልቅ “ይህን ሁሉ የማደርገው፣ ከወንጌል በረከት እካፈል ዘንድ፣ ስለ ወንጌል ብዬ ነው” ብሏል።—1 ቆሮንቶስ 9:22, 23

እናንተም ብትሆኑ የጳውሎስን ምሳሌ መከተል ትችላላችሁ። ከእኩዮቻችሁ ጋር በምትሆኑበት ጊዜ ወዳጃዊ ስሜት ለማሳየት ጣሩ። ከእነርሱ ጋር በጥሩ ሁኔታ ሐሳብ መለዋወጥ የምትችሉበትን መንገድ ተማሩ። ምናልባት አብረዋችሁ ከሚማሩት መካከል አንዳንዶቹ የያዛችሁትን የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ መስማት ይፈልጉ ይሆናል። ጃኔት የተባለች አንዲት ክርስቲያን ወጣት የገጠማትን ሁኔታ እንመልከት። እሷና አብረዋት የሚማሩ ልጆች ስለ እያንዳንዱ የክፍላቸው ተማሪ አጭር አስተያየት እንዲጽፉ ተነገራቸው፤ ከዚያም እያንዳንዱ ተማሪ ስለ ራሱ ወይም ስለ ራሷ የተጻፉትን አስተያየቶች እንዲያነብ ተደረገ። ጃኔት ከተሰጧት አስተያየቶች አንዱ “ሁልጊዜ በጣም ደስተኛ ልጅ ትመስያለሽ። ለምን እንደሆነ እባክሽ ንገሪን!” የሚል ነበር።

ይህ ተሞክሮ እንደሚያሳየው አብረዋችሁ የሚማሩ አንዳንድ ልጆች ስለ እምነታችሁ ለማወቅ ይፈልጉ ይሆናል። ለእንደነዚህ ዓይነቶቹ ልጆች ወዳጃዊ ስሜት ማሳየታችሁ ጠቀሜታ እንዳለው አይካድም። ይህ ደግሞ ስለ እምነታችሁ ለማስረዳት አጋጣሚ እንደሚሰጣችሁ ምንም ጥርጥር የለውም። አብረዋችሁ የሚማሩት ልጆች አመለካከታቸውን እንዲገልጹ ፍቀዱላቸው፤ እንዲሁም ሲናገሩ በጥሞና አዳምጧቸው። ወደፊት በሥራ ቦታ ተመሳሳይ ሁኔታ ሊያጋጥማችሁ ስለሚችል ከእኩዮቻችሁ ጋር በምታደርጉት ውይይት ጥሩ ተሞክሮ ልታገኙ ትችላላችሁ። በትምህርት ቤትም ሆነ በሥራ ቦታ ወዳጃዊ ስሜት የምታሳዩ ከሆነ ‘በሁሉም መንገድ የአዳኛችን የእግዚአብሔር ትምህርት እንዲወደድ’ ማድረግ ትችላላችሁ።—ቲቶ 2:10

“አግባብ ባልሆነ መንገድ” የሚመሠረት ጓደኝነት

እርግጥ አብሯችሁ ለሚማር ልጅ ወዳጃዊ ስሜት ማሳየትና ከዚያ ልጅ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት መመሥረት ትልቅ ልዩነት አላቸው። ጳውሎስ “ከማያምኑ ሰዎች ጋር አግባብ ባልሆነ መንገድ አትጠመዱ” በማለት ጽፏል። (2 ቆሮንቶስ 6:14) ከአንድ ሰው ጋር የተቀራረበ ጓደኝነት መመሥረት የምትችሉት ከዚያ ሰው ጋር የሚጣጣም የሥነ ምግባር መሥፈርትና አመለካከት እንዲሁም ግብ ሲኖራችሁ ነው። የእናንተን ቅዱስ ጽሑፋዊ እምነትም ሆነ አቋም ከማይከተል ሰው ጋር እንዲህ ያለ ወዳጅነት መመሥረት የማይቻል ነገር ነው። ከማያምኑ የክፍላችሁ ልጆች ጋር አግባብ ባልሆነ መንገድ መጠመድ መጥፎ ድርጊቶችን እንድትፈጽሙ ሊገፋፋችሁ አሊያም መልካሙን ጠባያችሁን ሊያበላሽባችሁ ይችላል።

ማሪያ ይህን የተገነዘበችው ከባድ ችግር ውስጥ ከገባች በኋላ ነበር። ተግባቢ መሆኗ በርካታ ጓደኞችን ለማፍራት ያስቻላት ሲሆን የት ላይ ገደብ ማበጀት እንዳለባት ግን አላወቀችም ነበር። ማሪያ እንዲህ ትላለች:- “በወንዶችም ሆነ በሴቶች ልጆች ዘንድ ተወዳጅ መሆን ያስደስተኝ ነበር። በዚህም ምክንያት ልክ በሚያሰጥም አሸዋ ላይ እንደቆምኩ ያህል በዚህ ዓለም ውስጥ እየሰጠምኩ ሄድኩ።”

ልክ እንደ ማሪያ ሁሉ እናንተም እምነታችሁን ከማይጋሩ ሰዎች ጋር ያላችሁ ወዳጅነት ገደቡን ያለፈ መሆን አለመሆኑን ለመረዳት ትቸገሩ ይሆናል። ሆኖም ተራ በሆነ ትውውቅና የጠበቀ ጓደኝነት በመመሥረት መካከል ግልጽ የሆነ ገደብ በማበጀት ራሳችሁን ከሐዘንና ከጸጸት መጠበቅ ትችላላችሁ። ታዲያ እንዲህ ማድረግ የምትችሉት እንዴት ነው?

ጥሩ ጓደኞች መምረጥ የሚቻለው እንዴት ነው?

ቀደም ብሎ እንደተገለጸው ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ የቅርብ ወዳጆች ነበሩት። ኢየሱስ እንዲህ ዓይነት ወዳጅነት መመሥረት የቻለው የሚያስከብር አኗኗር በመኖርና ስለ መንፈሳዊ ነገሮች በመናገር ነበር። ሰዎች ትምህርቱንና አኗኗሩን በሚቀበሉበት ጊዜ ከእሱ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ይመሠርቱ ነበር። (ዮሐንስ 15:14) ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ ሲናገር ያዳምጡ የነበሩ አራት ሰዎች ስሜታቸው በጣም ስለተነካ ‘ሁሉን ትተው ተከትለውታል።’ እነዚህ ሰዎች ማለትም ጴጥሮስ፣ እንድርያስ፣ ያዕቆብና ዮሐንስ የኢየሱስ የቅርብ ጓደኞች ሆነዋል።—ሉቃስ 5:1-11፤ ማቴዎስ 4:18-22

ኢየሱስ ለሚያምንበት ነገር ጥብቅ ከመሆኑም ሌላ ጽኑ አቋም እንደነበረው በንግግሩና በድርጊቱ በግልጽ አሳይቷል። ኢየሱስንና ትምህርቱን ያልተቀበሉ ሰዎች ትተውት የሄዱ ሲሆን እሱም ቢሆን እንዲሄዱ ፈቅዶላቸዋል።—ዮሐንስ 6:60-66

ለምሳሌ የአንድ ወጣት ሰው ቅንነት የኢየሱስን ልብ በጥልቅ ነክቶት ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ “ኢየሱስም ተመለከተውና ወደደው” ይላል። ሆኖም ሰውየው ኢየሱስ ከጓደኞቹ ምን እንደሚጠብቅ ሲያውቅ “ሄደ።” ሰውየው ጥሩ ሰው ይመስል ነበር፤ ኢየሱስ ‘የወደደውም’ በዚህ ምክንያት ነበር። ይሁን እንጂ ኢየሱስ፣ ከጓደኞቹ የበለጠ ነገር ይጠብቅባቸው ነበር። (ማርቆስ 10:17-22፤ ማቴዎስ 19:16-22) እናንተስ?

አብሯችሁ ከሚማር አንድ ግለሰብ ጋር ወዳጅነት ትመሠርቱ ይሆናል። ሆኖም ራሳችሁን እንዲህ እያላችሁ ጠይቁ:- ‘ይህ ግለሰብ ኢየሱስ ያዘዘውን ነገር ለማድረግ ፈቃደኛ ነው? ኢየሱስ እንድናመልከው ስላስተማረን ስለ ይሖዋ ለማወቅ ይፈልጋል?’ (ማቴዎስ 4:10) አብረዋችሁ ከሚማሩት ልጆች ጋር በምትወያዩበት ጊዜና ከመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ጋር ተስማምታችሁ ስትኖሩ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ታገኛላችሁ።

ኢየሱስ ለሁሉም ዓይነት ሰዎች የወዳጅነት መንፈስ ያሳይ እንደነበረ ሁሉ አብረዋችሁ ለሚማሩ ልጆች ወዳጃዊ ስሜት ማሳየታችሁ ተገቢ ነው። ሆኖም ኢየሱስ የጠበቀ ወዳጅነት የመሠረተው በሰማይ የሚኖረውን አባቱን ይሖዋን ከሚወዱ ሰዎች ጋር ነው። እናንተም ብትሆኑ እንዲሁ ማድረግ ትችላላችሁ። ስለ እምነታችሁ ለሌሎች በዘዴ በመናገር በትምህርት ቤት ውስጥ “በመልካም ሕይወት ኑሩ።” ከሁሉም በላይ ደግሞ የተሻሉ ጓደኞች ምረጡ።—1 ጴጥሮስ 2:12

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.3 አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች

▪ ከትምህርት ሰዓት ውጭ ትርፍ ጊዜያችሁን አብሯችሁ ከሚማር የማያምን ሰው ጋር ማሳለፍ ምን አደጋዎች አሉት? እንዲህ ማድረጉ ምክንያታዊ ይመስላችኋል?

▪ ይህንን ጽሑፍ ካነበባችሁ በኋላ አብረዋችሁ ከሚማሩ ልጆች ጋር ያላችሁ ጓደኝነት ገደቡን ያለፈ እንደሆነ ተሰምቷችኋል? ከሆነ ምን ልታደርጉ ትችላላችሁ?

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

እውነተኛ ጓደኞች ማፍራት የምችለው እንዴት ነው?

ይህ ቪዲዮ በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ ሲሆን በዩናይትድ ስቴትስ፣ በጣሊያን፣ በፈረንሳይና በስፔን የሚገኙ ወጣቶች ቃለ መጠይቅ ሲደረግላቸው ያሳያል፤ በ36 ቋንቋዎችም ይገኛል።

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አብረዋችሁ ከሚማሩ ልጆች መካከል አንዳንዶቹ ስለ እምነታችሁ ለማወቅ ይጓጉ ይሆናል