በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በተስፋ ደስ ይበላችሁ

በተስፋ ደስ ይበላችሁ

በተስፋ ደስ ይበላችሁ

ጆ ለሞት በሚዳርግ የካንሰር በሽታ ተይዟል። ባለቤቱ ኪርሽተንና ጥቂት ጓደኞቹ አልጋው አጠገብ ቁጭ ብለው ያወጋሉ። ኪርሽተን ባሏን ስታየው ጉንጮቹ በእንባ እንደራሱ ተገነዘበች። መጀመሪያ ላይ አሞት መስሏት ነበር። በወቅቱ ሕመም ተሰምቶት የነበረ ሊሆን ቢችልም ያለቀሰው በዚህ ምክንያት እንዳልሆነ ገለጸላት።

ኪርሽተን እንዲህ ብላለች:- “ጆ በዚህ የመከራ ወቅት እርሱን ለመጠየቅ በመጡ የቅርብ ጓደኞቻችን ተከብቦ ነበር። እንዲሁም ድንቅ ተስፋ የነበረው ሲሆን በዚህ ወቅት ከየትኛውም ጊዜ ይበልጥ ይህ ተስፋ እንደሚፈጸምለት እርግጠኛ ሆኖ ነበር፤ ይህንን ተስፋ ማንም ሊቀማው እንደማይችል አውቆ ነበር። በመሆኑም የደስታ እንባ እያነባ እንደሆነ ነገረን። ጆ በዚያው ዕለት ምሽት ላይ ሞተ።”

ጆ በሽታው በተባባሰበት በዚያ ወቅት እንዲበረታ የረዳው የትኛው ተስፋ ነው? ይሖዋ አምላክ ገነት በሆነች ምድር ላይ ከፍጹም ጤንነት ጋር የዘላለም ሕይወት እንደሚሰጥ የተናገረው ተስፋ ነው። (መዝሙር 37:10, 11, 29) ራእይ 21:3, 4 እንዲህ ይላል:- “የእግዚአብሔር ማደሪያ በሰዎች መካከል ነው፤ . . . እንባን ሁሉ ከዐይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት ወይም ሐዘን ወይም ልቅሶ ወይም ሥቃይ አይኖርም፤ [በዛሬው ጊዜ ያሉትን በርካታ ችግሮች ጨምሮ] የቀድሞው ሥርዐት ዐልፎአልና።”

ሙታን እንኳን ያላቸው ተስፋ

ጆ ተስፋው ይፈጸማል ሲባል ከሞት ይነሳል ማለት ነው። ኢየሱስ “በመታሰቢያ መቃብር ውስጥ ያሉ ሁሉ” ማለትም በአምላክ አእምሮ ውስጥ ያሉ ሙታን ከሞት እንደሚነሱ የሰጠው ተስፋ በእርግጥም አጽናንቶት ነበር። (ዮሐንስ 5:28, 29 NW) የቤተሰብህን አባል ወይም ጓደኛህን በሞት በማጣትህ ምክንያት አዝነሃል? ከሆነ አንተም በትንሣኤ ተስፋ መጽናናት ትችላለህ። ይህ ተስፋ የምንወዳቸውን ሰዎች በሞት በማጣታችን ምክንያት የሚሰማንን ጥልቅ ሐዘን ሙሉ በሙሉ ሊያስወግድልን እንደማይችል የተረጋገጠ ነው። ኢየሱስ ራሱ ጓደኛው አልዓዛር በሞተበት ጊዜ ‘እንባውን አፍስሷል።’ ቢሆንም ተስፋችን ሐዘናችንን ቀለል ያደርግልናል።—ዮሐንስ 11:14, 34, 35፤ 1 ተሰሎንቄ 4:13

ኪርሽተን እንዲህ ብላለች:- “ጆ በካንሰር በሽታ በሞተበት ጊዜ እንደ በፊቱ እውነተኛ ደስታ ፈጽሞ ሊኖረኝ እንደማይችል ተሰምቶኝ ነበር። አሁን ጥቂት ዓመታት ያለፉ ቢሆንም በዚህ ሥርዓት ውስጥ በጭራሽ የቀድሞውን ዓይነት ሕይወት መኖር እንደማልችል ተገንዝቤያለሁ። የጆ ሞት ሊደፈን የማይችል ክፍተት ፈጥሯል። እውነቱን ለመናገር ግን የአእምሮ ሰላሜና የነበረኝ የእርካታ ስሜት ተመልሶልኛል።”

ኪርሽተን የሰጠችው አስተያየት፣ ባለንበት ሥርዓት ውስጥ እያንዳንዷን ደቂቃ በደስታ ማሳለፍ እንደማንችል ያስታውሰናል። ሕይወት የራሱ የሆኑ ውጣ ውረዶች አሉት። ስለዚህ የምናዝንበትና መደሰት ፈጽሞ ተገቢ የማይሆንበት ጊዜ አለ። (መክብብ 3:1, 4፤ 7:2-4) እንዲሁም አንዳንዶቻችን በተለያዩ ምክንያቶች ሊፈጠር ከሚችል ጭንቀት ጋር እየታገልን ይሆናል። የሆነ ሆኖ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት ተስፋዎች በጣም ያጽናናሉ፤ እንዲሁም በዚሁ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘው አቻ የሌለው ጥበብ ደስታ ከሚያሳጡ በርካታ ስውር አደጋዎች ይጠብቀናል። አምላክ “የሚያዳምጠኝ ሁሉ ግን በሰላም ይኖራል፤ ክፉን ሳይፈራ ያለ ሥጋት ይቀመጣል” ብሏል።—ምሳሌ 1:33

አዎን፣ ይሖዋ ከልቡ ስለ እኛ ያስባል። ላይ ላዩን ሳይሆን ከልባችን፣ ለጥቂት ዓመታት ብቻ ሳይሆን ለዘላለም ደስተኛ እንድንሆን ይፈልጋል! በመሆኑም ልጁ “ለመንፈሳዊ ፍላጎታቸው ንቁ የሆኑ ደስተኞች ናቸው” የሚሉትን ጊዜ የማይሽራቸው ቃላት ተናግሯል። (ማቴዎስ 5:3 NW) ጥበበኞች ከሆንን እነዚህን ቃላት በተግባር ላይ እናውላቸዋለን።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ደስታ የሚያስገኙ ዘጠኝ ‘ቅመሞች’

1. ለመንፈሳዊ ነገሮች አድናቆት ማዳበር።—ማቴዎስ 5:3 NW

2. ባለህ ነገር መርካትና ‘ከገንዘብ ፍቅር’ መራቅ።—1 ጢሞቴዎስ 6:6-10

3. በመዝናኛ ረገድ ሚዛናዊ መሆን።—2 ጢሞቴዎስ 3:1, 4

4. ለጋስ መሆንና ሌሎችን የሚያስደስት ነገር ለማድረግ መጣር።—የሐዋርያት ሥራ 20:35

5. አመስጋኝ መሆንና የተደረጉልንን መልካም ነገሮች አለመዘንጋት።—ቈላስይስ 3:15

6. የይቅር ባይነት መንፈስ ማዳበር።—ማቴዎስ 6:14

7. ጓደኞችን በጥበብ መምረጥ።—ምሳሌ 13:20

8. አካላዊ ጤንነትን መጠበቅና ከመጥፎ ልማዶች መራቅ።—2 ቆሮንቶስ 7:1

9. መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተገለጸው የወደፊት ‘ተስፋ ደስተኛ መሆን።’—ሮሜ 12:12

[በገጽ 8, 9 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

በአዲስ ዓለም ውስጥ ስለሚገኘው ሕይወት የሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ ትልቅ የመጽናናት ምንጭ ነው