በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ልዩ ትኩረት የሚያሻቸውን ልጆች ማሳደግ

ልዩ ትኩረት የሚያሻቸውን ልጆች ማሳደግ

ልዩ ትኩረት የሚያሻቸውን ልጆች ማሳደግ

ፊንላንድ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

በፎቶግራፉ ላይ (በስተ ግራ) የሚታየው ማርከስ 20 ዓመቱ ቢሆንም የሚረዳው ሰው ሳይኖር መብላት፣ መጠጣት ወይም ሰውነቱን መታጠብ አይችልም። ጥሩ እንቅልፍ የማይወስደው ከመሆኑም በላይ ሌሊቱን በሙሉ ክትትል ያስፈልገዋል። አደጋ ስለማያጣው ዘወትር የመጀመሪያ ሕክምና እርዳታ ያስፈልገዋል። ያም ሆኖ ግን የማርከስ ወላጆች በጣም ይወዱታል። ገራገር፣ ደግና ሰው ወዳድ በመሆኑ ያደንቁታል። ልጃቸው ማርከስ የጤና እክል ቢኖርበትም ይኮሩበታል።

የዓለም የጤና ድርጅት እንደሚገምተው ከዓለም ሕዝብ ውስጥ 3 በመቶ ያህሉ አንድ ዓይነት የአእምሮ ዝግመት አለባቸው። ደካማ የአእምሮ ችሎታ የሚመጣው ከዘር በተወረሱ ችግሮች፣ በወሊድ ጊዜ በሚደርሱ ጉዳቶች፣ ገና በጨቅላነት በሚያጋጥሙ የአእምሮ ሕመሞችና በምግብ እጥረት እንዲሁም በአደገኛ መድኃኒቶችና ዕፆች፣ በአልኮል ወይም ለኬሚካል በመጋለጥ የተነሳ ሊሆን ይችላል። አብዛኛው የአእምሮ ዘገምተኝነት መንስኤው አይታወቅም። ታዲያ፣ ልዩ ትኩረት የሚያስፈልገው ልጅ ያላቸው ወላጆች ሕይወታቸው ምን ይመስላል? እንደዚህ ያሉትን ወላጆች ማበረታታት የሚቻለው እንዴት ነው?

አሳዛኙን ዜና መስማት

ፈተናው የሚጀምረው ወላጆች ልጃቸው የአእምሮ ዝግመት እንዳለበት ከተገነዘቡበት ጊዜ እንስቶ ነው። ሲርካ “ባለቤቴና እኔ ሴት ልጃችን ዳውን ሲንድሮም የሚባለው የአእምሮ ዘገምተኝነት በሽታ እንዳለባት በተገነዘብን ጊዜ ሰማይ እንደተደፋብን ሆኖ ተሰምቶን ነበር” በማለት ታስታውሳለች። አን የምትባለው የማርከስ እናት ደግሞ “ልጄ የአእምሮ ዘገምተኛ እንደሚሆን በተነገረኝ ጊዜ ሌሎች እንዴት ይመለከቱታል የሚለው ነገር አሳስቦኝ ነበር። ብዙም ሳይቆይ ግን ስለ ሌሎች አመለካከት መጨነቁን ትቼ ለልጄ በሚያስፈልጉትና እኔ ላደርግለት በምችላቸው ነገሮች ላይ አተኮርኩ” ትላለች። ኤርምጋርድ የምትባል እናትም ተመሳሳይ ስሜት ነበራት። እንዲህ ብላለች:- “ሐኪሞቹ ሴት ልጃችን ኤውንቄ ስላለባት የጤና እክል በነገሩን ጊዜ እኔን ያሳሰበኝ ትንሿን ልጄን እንዴት ልረዳት እችላለሁ የሚለው ጥያቄ ነበር።” እንደ ሲርካ፣ አን እና ኤርምጋርድ ያሉት ወላጆች የምርመራው ውጤት ከተነገራቸው በኋላ የሚኖሯቸው አማራጮች ምንድን ናቸው?

የጤና እክል ካለባቸው ልጆች ጋር በተያያዘ የሚሠራው የዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ የመረጃ ስርጭት የሚከተለውን ምክር ይሰጣል:- “በመጀመሪያ ማድረግ ያለባችሁ ነገር መረጃ መሰብሰብ ነው። ስለ ልጃችሁ ሕመም፣ ልታገኙ ስለምትችሉት እርዳታና ልጃችሁ በአካልም ሆነ በአእምሮ የሚችለውን ያህል እንዲያድግ ለመርዳት ልታደርጉ ስለምትችሏቸው ተጨባጭ ነገሮች መረጃ ያስፈልጋችኋል።” ልጃችሁን በምትንከባከቡበት ጊዜ ባገኛችሁት መረጃ መጠቀማችሁ ዓላማ እንዲኖራችሁና በየትኛው አቅጣጫ መጓዝ እንዳለባችሁ እንድትገነዘቡ ይረዳችኋል። ለልጃችሁ የምታደርጉት እንክብካቤ በጉዞ ላይ ሆናችሁ የተጓዛችሁትን ርቀትና የደረሳችሁበትን ቦታ በካርታ ላይ ምልክት ከማድረግ ጋር ይመሳሰላል።

ምን ቢጠቁር ጉም ብርሃን አያጣም

የልጅነት የአእምሮ ዘገምተኝነት እንደ ጥቁር ደመና የሚያጠላ ተፈታታኝ ችግር ቢኖረውም ብሩህ ገጽታም አለው። እንዴት?

አንደኛ ነገር፣ ወላጆች የአእምሮ ዘገምተኛ ከሆኑት ልጆች አብዛኞቹ ሥቃይ እንደማይሰማቸው ሲያውቁ ሊጽናኑ ይችላሉ። ዶክተር ሮበርት ኢዛክሰን ዘ ሪታርድድ ቻይልድ በተሰኘ መጽሐፋቸው ላይ “አብዛኞቹ [የአእምሮ ዘገምተኛ ልጆች] መደሰት ይችላሉ፤ ከሌሎች ጋር ጊዜ ማሳለፍ፣ ሙዚቃ ማዳመጥ፣ በአንዳንድ ስፖርቶች መካፈል፣ ጣፋጭ ምግቦችን መብላትና ጓደኞች ማፍራት ያስደስታቸዋል” ሲሉ ጽፈዋል። ከጤነኞቹ ልጆች ጋር ሲነጻጸሩ መሥራት የሚችሉት ነገር አነስተኛ ከመሆኑም በላይ በዙሪያቸው ካለው ዓለም ጋር ብዙም ላይቀራረቡ ይችላሉ። ይሁንና አብዛኛውን ጊዜ ከጤነኞቹ ልጆች ይልቅ ‘በራሳቸው ትንሽ ዓለም’ ደስ ብሏቸው ይኖራሉ።

ሁለተኛ ነገር፣ ወላጆች ልጃቸው በከፍተኛ ጥረት ባገኘው ውጤት ኩራት ሊሰማቸው ይችላል። ልጁ የሚማረው እያንዳንዱ አዲስ ተግባር አንድ ትልቅ ተራራ እንደመውጣት የሚቆጠር ሲሆን ከተራራው አናት ላይ ሆኖ ውጤቱን መቃኘት ለወላጆችም ሆነ ለልጁ የሚያረካ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ብራያን ማዕከላዊውን የነርቭ ሥርዓት የሚያጠቃ ቲዩበረስ ስክሎሮሲስ የተባለ ሕመምና የሚጥል በሽታ እንዲሁም የመናገርና ከሰዎች ጋር የመግባባት ችግር አለበት። ብራያን የማሰብ ችሎታው ጥሩ ቢሆንም መናገርና እጆቹን እንደልቡ ማዘዝ አይችልም። ሆኖም ጎደል ያለ ኩባያ በእጁ ይዞ ሳያንጠባጥብ መጠጣትን ቀስ በቀስ ተምሯል። ብራያን አእምሮውንና አካሉን አንድ ላይ ማሠራት በመቻሉ የሚወደውን ወተት ያለ ረዳት በእጁ ይዞ መጠጣት ችሏል።

የብራያን አባትና እናት ልጃቸው ይህን ማድረግ በመቻሉ በሕመሙ ላይ በትንሹም ቢሆን ድል እንደተቀዳጀ ይሰማቸዋል። “ልጃችንን የምንመለከተው በጫካ ውስጥ እንዳለ ምርጥ እንጨት የሚወጣው ጠንካራ ዛፍ አድርገን ነው” ትላለች እናቱ ሎሬ። “እንዲህ ዓይነቱ ዛፍ እንደ ሌሎቹ ዛፎች በፍጥነት ባያድግም ከፍተኛ ዋጋ ያለው እንጨት ያስገኛል። በተመሳሳይም ዘገምተኛ አእምሮ ያላቸው ሕፃናት እድገታቸው ፈጣን ባይሆንም ወላጆቻቸው ዘላቂ ጥንካሬ እንዳላቸው ትንንሽ . . . ዛፎች አድርገው ይመለከቷቸዋል።”

ሦስተኛ፣ ብዙ ወላጆች ልጆቻቸው አፍቃሪ በመሆናቸው በጣም ይደሰታሉ። ኤርምጋርድ እንዲህ ትላለች:- “ኤውንቄ በጊዜ መተኛት የምትወድ ሲሆን ሁልጊዜ ወደ መኝታዋ ከመሄዷ በፊት እያንዳንዱን የቤተሰብ አባል ትስማለች። ቤት ከመግባታችን በፊት የምትተኛ ከሆነ እስክንመጣ ባለመጠበቋ ይቅርታ በመጠየቅ አጠር ያለ ማስታወሻ ትጽፋለች። በማስታወሻውም ላይ እንደምትወደንና ሲነጋ ልታየን እንደምትናፍቅ የሚገልጽ ሐሳብ ታክላለች።”

ማርከስ መናገር አይችልም፤ ሆኖም ከፍተኛ ጥረት አድርጎ ወላጆቹን እንደሚወዳቸው ለመናገር የሚያስችሉ ጥቂት የምልክት ቋንቋ ቃላትን ተማረ። ቴአ እያደገች ስትሄድ የአእምሮ ዘገምተኛ እየሆነች ነው፤ ወላጆቿ ስለ እርሷ ሲናገሩ “ፍቅሯን በማቀፍና በመሳም ስለምትገልጽልን በሕይወታችን ደስተኞች እንድንሆን አድርጋናለች” ይላሉ። ወላጆችም ቢሆኑ እንደዚህ ላሉት ልጆቻቸው ያላቸውን ፍቅር በቃልም ሆነ አካላዊ በሆነ መንገድ አዘውትረው ሊገልጹላቸው እንደሚያስፈልግ እሙን ነው።

አራተኛ፣ ክርስቲያን ወላጆች ልጆቻቸው በአምላክ ላይ እምነት እንዳላቸው ሲገልጹ በመስማት ጥልቅ እርካታ ያገኛሉ። በዚህ ረገድ ተስማሚ ምሳሌ የሚሆነን ጁሃ የተባለው ልጅ ነው። ጁሃ አባቱ በሚቀበርበት ጊዜ በሕዝቡ ፊት ጸሎት ለማቅረብ እንዲፈቀድለት ሲጠይቅ ሁሉንም አስገረማቸው። ጁሃ ባቀረበው አጭር ጸሎት ላይ አምላክ አባቱን እንደሚያስታውሰውና ጊዜው ሲደርስም እንደሚያስነሳው ያለውን እምነት ገለጸ። ከዚያም እያንዳንዱን የቤተሰብ አባል በስም እየጠቀሰ አምላክ እንዲረዳቸው ጠየቀ።

በተመሳሳይም ኤውንቄ በአምላክ ላይ ያላት እምነት ወላጆቿን ያስደስታቸዋል። ኤውንቄ የምትማረውን ነገር ሁሉ መረዳት አትችልም። አንድ የተሟላ ምስል ከሚያስገኙ የሥዕል ቁርጥራጮች ውስጥ ግማሹን ወስደው ቢገጣጥሟቸው ሙሉ ምስል እንደማያስገኙ ሁሉ ኤውንቄም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጹ ብዙ ሰዎችን ብታውቅም ከታሪካቸው ጋር ማያያዝ ግን አትችልም። ይሁን እንጂ ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ አንድ ቀን ምድርን ከችግር ነፃ እንደሚያደርጋት ትገነዘባለች። ኤውንቄ የተሟላ የአእምሮ ጤንነት በምታገኝበት አምላክ ቃል በገባው አዲስ ዓለም ውስጥ ለመኖር በጉጉት ትጠባበቃለች።

ራሳቸውን እንዲችሉ ማበረታታት

የአእምሮ ዘገምተኛ የሆኑ ልጆች ልጅ እንደሆኑ አይቀሩም፤ አድገው የአእምሮ ዘገምተኛ የሆኑ አዋቂዎች ይሆናሉ። ስለዚህ ወላጆች የተለየ ትኩረት የሚያሻቸው ልጆቻቸው ከሚያስፈልገው በላይ የሌሎችን እርዳታ እንዳይለምዱ ሊረዷቸው ይገባል። የማርከስ እናት አን እንዲህ ትላለች:- “ማርከስ የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ ራሳችን ብናደርግለት ቀላል ከመሆኑም በላይ ጊዜ ይቆጥባል። ይሁን እንጂ በተቻለ መጠን ራሱን እንዲችል ለማድረግ የቻልነውን ሁሉ ጥረናል።” የኤውንቄ እናትም አክላ “ኤውንቄ ብዙ አስደሳች ባሕርያት ያሏት ቢሆንም አንዳንድ ጊዜ አስቸጋሪ ትሆናለች። እሷ ሳትፈልግ አንድ ነገር እንድታከናውን ከጠየቅናት ሥራውን የምትሠራው እኛን ለማስደሰት ስለምትፈልግ እንደሆነ በማስታወስ ደጋግመን መጎትጎት አለብን። ለመሥራት ከተስማማች በኋላም እንኳን እየተከታተልን እንድትጨርሰው ማበረታታት አለብን።”

የብራያን እናት ሎሬ የልጅዋን ሕይወት ይበልጥ አስደሳች ለማድረግ ሁልጊዜ ጥረት ታደርጋለች። ሎሬ እና ባሏ፣ ብራያን በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ በኮምፒውተር መጻፍ እንዲችል ረዱት። ብራያን አሁን በጣም ደስ እያለው ለጓደኞቹና ለቤተሰቡ የኢ-ሜይል መልእክቶችን ይልካል። ይሁን እንጂ በሚጽፍበት ጊዜ የእጁን አንጓ ደግፎ የሚይዝለት ሰው ያስፈልገዋል። ወላጆቹ ክርኑን ብቻ መደገፍ የሚያስፈልግበት ደረጃ ላይ እስኪደርስ ድረስ እየረዱት ነው። ይህ ለውጥ ጥቂት መስሎ ቢታይም ራሱን በመቻል ረገድ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው እርምጃ እንደሆነ ያውቃሉ።

ያም ሆኖ ወላጆች ከልጆቻቸው ብዙ መጠበቅ ወይም ከአቅማቸው በላይ እንዲጣጣሩ ግፊት ማድረግ አይኖርባቸውም። እያንዳንዱ ልጅ ችሎታው ይለያያል። ዘ ስፔሻል ቻይልድ የተሰኘው መጽሐፍ “ራሳቸውን እንዲችሉ በማበረታታትና ተስፋ እንዳይቆርጡ ለማድረግ የሚያስፈልጋቸውን ያህል እርዳታ በመስጠት ረገድ ሚዛናዊ መሆን ጠቃሚ ነው” የሚል ሐሳብ ይሰጣል።

ታላቁ የእርዳታ ምንጭ

የአእምሮ ዘገምተኛ የሆኑ ልጆች ያሏቸው ወላጆች ከፍተኛ ትዕግሥትና ጽናት ያስፈልጋቸዋል። ብዙ ወላጆች ችግር ሲደራረብባቸው ተስፋ የሚቆርጡበት ጊዜ ይኖራል። ድካም ደግሞ ብዙውን ጊዜ ጎጂ ውጤት አለው። ወላጆች ሊያለቅሱና አንዳንድ ጊዜም ሊማረሩ ይችላሉ። በዚህ ጊዜ ምን ማድረግ ይቻላል?

ወላጆች ‘ጸሎት ሰሚ’ ከሆነው አምላክ እርዳታ ሊጠይቁ ይችላሉ። (መዝሙር 65:2) እሱ ለመጽናት የሚያስፈልጋቸውን ብርታት፣ ተስፋና ጥንካሬ ይሰጣቸዋል። (1 ዜና መዋዕል 29:12፤ መዝሙር 27:14) አምላክ በሐዘን የተሰበረውን ልባችንን የሚያጽናናልን ከመሆኑም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ በሚሰጠው ‘ተስፋ እንድንደሰት’ ይፈልጋል። (ሮሜ 12:12፤ 15:4, 5፤ 2 ቆሮንቶስ 1:3, 4) በአምላክ የሚተማመኑ ወላጆች ወደፊት ‘ዕውሮች የሚያዩበት፣ ደንቈሮዎች የሚሰሙበት፣ አንካሶች መሄድ የሚችሉበትና ድዳዎች በደስታ የሚዘምሩበት’ ጊዜ ሲመጣ የሚወዱት ልጃቸውም ፍጹም የሆነ አእምሯዊና አካላዊ ጤንነት እንደሚያገኝ እርግጠኞች ሊሆኑ ይችላሉ።—ኢሳይያስ 35:5, 6፤ መዝሙር 103: 2, 3

ወላጆች ምን ማድረግ ይችላሉ?

ስለ ልጃችሁ የጤና እክል ለማወቅና መረጃ ለማግኘት ጥረት አድርጉ

አዎንታዊ አመለካከት ለመያዝ ጣሩ

ልጃችሁ በተቻለ መጠን ራሱን እንዲችል ወይም ራሷን እንድትችል እርዱት/ዷት

አምላክ ብርታት፣ ተስፋና ጥንካሬ እንዲሰጣችሁ ጠይቁት

ሌሎች ምን ማድረግ ይችላሉ?

ከአእምሮ ዘገምተኛው ልጅ ጋር በምትነጋገሩበት ጊዜ በሕፃናት ቋንቋ ከመጠቀም ይልቅ የልጁን ዕድሜ ከግምት በማስገባት ከልባችሁ አነጋግሩት

ከወላጆቹ ጋር ስለ ልጃቸው አውሩ፣ እንዲሁም አመስግኗቸው

የወላጆቹን ስሜት ተረዱላቸው፤ አሳቢነትም አሳዩአቸው

የተለየ ትኩረት የሚያስፈልገው ልጅ ካላቸው ወላጆችና ከቤተሰባቸው ጋር አንዳንድ ሥራዎችን አብራችሁ ሥሩ

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ሌሎች እርዳታ ማበርከት የሚችሉት እንዴት ነው?

የማራቶን ሯጮች ጽናት ተመልካቾችን እንደሚያስደንቃቸው ሁሉ አእምሮው ዘገምተኛ የሆነ ልጅ ያላቸው ወላጆች ቀን ከሌሊት እንዲሁም ከሳምንት እስከ ሳምንት ልጃቸውን ሲንከባከቡ ስታይ ባላቸው ብርታት ትደነቅ ይሆናል። የማራቶን ሩጫ በሚካሄድበት መንገድ ዳር የሚቆሙ ተመልካቾች ለሯጮቹ ኃይላቸውን የሚያድስ ውኃ በጠርሙስ ማቅረባቸው የተለመደ ነው። አንተም የተለየ ትኩረት ለሚያስፈልገው ልጅ የዕድሜ ልክ እንክብካቤ በማድረግ ሥራ ለተጠመዱ ወላጆች ኃይል የሚያድስ ማበረታቻና ድጋፍ ልትሰጥ ትችላለህ?

እርዳታ ልታበረክት የምትችልበት አንዱ መንገድ ከልጃቸው ጋር በማውራት ነው። መጀመሪያ ላይ ልጁ ስታናግረው ብዙም ላይመልስልህ ወይም እስከ ጭራሹ ዝም ሊልህ ስለሚችል ትንሽ ግር ይልህ ይሆናል። ይሁን እንጂ እንደዚህ ካሉት ልጆች አብዛኞቹ ማዳመጥ ደስ እንደሚላቸውና ስለምትናገረው ነገር በጥልቅ ማሰብ እንደሚችሉ አስታውስ። እርግጥ አንዳንድ ጊዜ ሙሉ በሙሉ ከውኃ በታች ሆኖ ጫፉ ብቻ ብቅ እንዳለ የበረዶ ግግር፣ በአእምሯቸው ውስጥ ያለው ጥልቅ ስሜት በፊታቸው ላይ ላይነበብ ይችላል። *

የሕፃናት የነርቭ ሐኪም የሆኑት ዶክተር አኒኬ ኮይስቲኔን፣ ከአእምሮ ዘገምተኛ ልጆች ጋር በቀላሉ ማውራት የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ሲገልጹ የሚከተለውን ሐሳብ ያቀርባሉ:- “መጀመሪያ ላይ ስለ ቤተሰባቸው ወይም የእረፍት ጊዜያቸውን እንዴት እንደሚያሳልፉ መጠየቅ ትችላላችሁ። ከሕፃን ልጅ ጋር እንደምታወሩ አድርጋችሁ ሳይሆን እንደ ዕድሜያቸው አነጋግሯቸው። አጫጭር ዓረፍተ ነገሮችን በመጠቀም በአንድ ጊዜ ስለ አንድ ርዕሰ ጉዳይ ብቻ አውሩ። ስለምትናገሩት ነገር ማሰብ እንዲችሉ ጊዜ ስጧቸው።”

ወላጆቻቸውንም ቢሆን ልታዋሯቸው ያስፈልጋል። የሚያጋጥማቸውን ስሜታዊ ትግል በተረዳችሁላቸው መጠን ችግራቸውን በእነሱ ቦታ ሆናችሁ ማየት ትችላላችሁ። ለምሳሌ ያህል፣ የማርከስ እናት አን የምትወደውን ልጅዋን ይበልጥ ለማወቅ ትጓጓለች። መናገር ባለመቻሉና የሚያስበውን ነገር ገልጾ ማስረዳት ስለሚከብደው ታዝናለች። በተጨማሪም እሷ አንድ ነገር ሆና ያለ እናት እንዳይቀር ትጨነቃለች።

ወላጆች የአእምሮ ዘገምተኛ ልጃቸውን ለመንከባከብ የቱንም ያህል ቢደክሙም አብዛኛውን ጊዜ ገና ብዙ እንደሚቀራቸው ይሰማቸዋል። የብራያን እናት ሎሬ ልጅዋን በምትንከባከብበት ጊዜ ለምትፈጽመው ጥቃቅን ስህተት ሁሉ ራሷን ትወቅሳለች። በተጨማሪም ለሌሎቹ ልጆቿ ተጨማሪ ትኩረት መስጠት ባለመቻሏ የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማታል። እንደዚህ ላሉት ወላጆች ትኩረት መስጠታችሁና ስሜታቸውን የምታከብሩላቸው መሆኑ እነርሱንም ሆነ ልጆቻቸውን የሚያበረታታቸው ከመሆኑም በላይ እገዛ ያደርግላቸዋል። ኤርምጋርድ “የአእምሮ ዘገምተኛ ስለሆነችው ልጄ ሲያዋሩኝ ደስ ይለኛል። ከኤውንቄ ጋር ስኖር የሚያጋጥመኝን ደስታም ሆነ ሐዘን ሊጋሩኝ ፈቃደኛ የሆኑትን ሁሉ እወዳቸዋለሁ” ትላለች።

እርዳታ ማበርከት የምትችሉባቸው ሌሎች ትናንሽም ሆኑ ትላልቅ መንገዶች አሉ። ምናልባት ወላጆቹንም ሆነ ልጆቻቸውን ቤታችሁ ልትጋብዟቸው ወይም ቤተሰባችሁ በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች እንዲካፈሉ ልትጠይቋቸው ትችላላችሁ። በተጨማሪም ወላጆቹ እረፍት በሚያደርጉበት ጊዜ ልጃቸውን ለጥቂት ሰዓታት ልትጠብቁላቸው ትችሉ ይሆናል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.37 የሐምሌ 2000 ንቁ! መጽሔት ላይ የወጣውን “ሎይዳ የሐሳብ ግንኙነት ለመፍጠር ያደረገችው ትግል” የሚል ርዕስ ተመልከት።

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ልባዊ አሳቢነት ማሳየት ለወላጆቹና ለልጁ አክብሮት እንዳላችሁ ይጠቁማል

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እንደ ኤውንቄ ሁሉ የአእምሮ ዘገምተኛ የሆኑ ልጆች እያደጉ ሲሄዱም ቢሆን ፍቅር ማግኘት ያስፈልጋቸዋል

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሎሬ ልጅዋ ብራያን ራሱን እንዲችል ለማበረታታት በኮምፒውተር መጻፍ እንዲችል ረድታዋለች