በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በአምላክ መታመንን ተማርኩ

በአምላክ መታመንን ተማርኩ

በአምላክ መታመንን ተማርኩ

ኤላ ቱም እንደተናገረችው

ቤተሰባችን የሚኖረው በደቡብ ኢስቶኒያ፣ ከሩሲያ ድንበር 60 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኝ ኦቴፓ የምትባል ትንሽ ከተማ አቅራቢያ ነበር። በጥቅምት ወር 1944 ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወደ ማብቂያው ሲቃረብ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ካጠናቀቅኩ ብዙም አልቆየሁም ነበር። የሩሲያ ሠራዊት ጀርመኖችን በኢስቶኒያ በኩል እያሳደደ በነበረበት ወቅት ጎረቤቶቻችንን ጨምሮ 20 የምንሆን ሰዎች ከብቶቻችንን ይዘን በጫካ ውስጥ ተደበቅን።

ለሁለት ወራት ያህል በዙሪያችን ቦምብ ሲዘንብ በጦር ሜዳ ውስጥ እንዳለን ያህል ተሰምቶን ነበር። ጫካ ውስጥ አንድ ላይ ተሰባስበን እንቀመጥና እኔ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተለይም የሰቆቃወ ኤርምያስን መጽሐፍ የተወሰኑ ክፍሎች አነባለሁ። መጽሐፍ ቅዱስን ለመጀመሪያ ጊዜ ያነበብኩት በዚህ ወቅት ነው። አንድ ቀን ወደ አንድ ከፍ ያለ ኮረብታ ወጥቼ ተንበረከክሁና “ጦርነቱ ሲያበቃ ሁልጊዜ እሁድ እሁድ ወደ ቤተ ክርስቲያን ለመሄድ ቃል እገባለሁ” ብዬ ጸለይኩ።

ብዙም ሳይቆይ ጦርነቱ ወደ ምዕራብ አቅጣጫ ተሸጋገረ። በመጨረሻም ግንቦት 1945፣ ጀርመን ድል ስትሆን በአውሮፓ የተካሄደው ጦርነት አበቃ። በዚህ መሃል ለአምላክ የገባሁትን ቃል ለመፈጸም በየሳምንቱ ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄድ ጀምሬ ነበር። ይሁን እንጂ ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚሄዱት ጥቂት አረጋውያን ሴቶች ብቻ ስለነበሩ በእነሱ መካከል መገኘት ያሳፍረኝ ነበር። አንድ ሰው ሊጠይቀን ወደ ቤታችን ጎራ ካለ መጽሐፍ ቅዱሴን ጠረጴዛው ሥር እደብቀው ነበር።

ከጥቂት ጊዜ በኋላ በአካባቢው በሚገኝ ትምህርት ቤት አስተማሪ ሆኜ ተቀጠርኩ። በዚህ ጊዜ የኮሚኒስቱ አገዛዝ ሥልጣን ስለያዘ አምላክ የለሽነት ተስፋፍቶ ነበር። እኔ ግን የኮሚኒስት ፓርቲ አባል ለመሆን ፈቃደኛ አልነበርኩም። ለልጆች ባሕላዊ ውዝዋዜ እንደማዘጋጀት ያሉ በርካታ ማኅበራዊ ተግባራትን በማከናወን ራሴን በሥራ አስጠመድኩ።

ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኘሁ

ለልጆቹ የመድረክ አልባሳት ያስፈልጉ ስለነበር በሚያዝያ ወር 1945 ኤሚሊ ሳናሚስ ወደምትባል ጐበዝ ልብስ ሠፊ ሄድኩ። ኤሚሊ ለካስ የይሖዋ ምሥክር ኖራለች፣ “ስለ ዓለም ሁኔታ ምን ታስቢያለሽ?” ብላ ጠየቀችኝ። በወቅቱ በሳንፍራንሲስኮ፣ ዩናይትድ ስቴትስ የሰላም ስብሰባ እየተካሄደ ስለነበር “ይህ መንግሥት በቅርቡ ይወድቃል፤ የሰላም ስብሰባው የሚካሄደው ለዚህ እንደሆነ እርግጠኛ ነኝ” አልኳት።

ኤሚሊ የሰላም ስብሰባው ምንም ዓይነት ዘላቂ ጥቅም እንደማያስገኝ ነገረችኝ፤ ይህንንም ከመጽሐፍ ቅዱስ ልታሳየኝ እንደምትችል ሐሳብ አቀረበችልኝ። እኔ ግን በመካከለኛ ዕድሜ ላይ የምትገኘው ይህች ደግና ትሑት ሴት ያቀረበችልኝን ሐሳብ ልቀበል አልፈለግሁም፤ ልሄድ ስል “አምላክ አዳምንና ሔዋንን የት እንዲኖሩ እንደፈጠራቸው ታውቂያለሽ?” ብላ ጠየቀችኝ። የዚህን ጥያቄ መልስ ስላላወቅሁት “አባትሽን ጠይቂው” አለችኝ።

እቤት ስደርስ አባቴን ጠየቅሁት። እሱ ግን መልሱን ሊሰጠኝ አልቻለም፤ እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስን የማወቅ ጉዳይ ሊያሳስበን እንደማይገባና እንዲሁ ማመን ብቻ እንዳለብን ተናገረ። አልባሳቱን ለመውሰድ ወደ ኤሚሊ ስመለስ አባቴ የጠየቀችኝን ጥያቄ መልስ እንዳላወቀው ነገርኳት። እሷና እህቷ መጽሐፍ ቅዱሳቸውን ገልጠው አምላክ ለአዳምና ለሔዋን የሰጣቸው ትእዛዝ ገነት የሆነች መኖሪያቸውን እንዲንከባከቧትና በደስታ ለዘላለም እንዲኖሩባት መሆኑን አነበቡልኝ። የአምላክ ዓላማ አዳምና ሔዋን ልጆች እንዲወልዱና ምድርን በሙሉ ገነት እንዲያደርጓት እንደነበረ ከመጽሐፍ ቅዱስ አሳዩኝ። ከመጽሐፍ ቅዱስ ያሳዩኝ ማስረጃ ማረከኝ!—ዘፍጥረት 1:28፤ 2:8, 9, 15፤ መዝሙር 37:29፤ ኢሳይያስ 45:18፤ ራእይ 21:3, 4

መጀመሪያ የተገኘሁበት ክርስቲያናዊ ስብሰባ

በ1945 በአውሮፓ የበጋ ወራት የሦስት ወር የመምህራን ኮርስ ለመካፈል ወደ ታርቱ ከተማ መሄድ ስለነበረብኝ ኤሚሊ በዚያ ከተማ የምትኖር የአንዲት የይሖዋ ምሥክር አድራሻ ሰጠችኝ። በተጨማሪም ኤሚሊ ፍጥረት የተሰኘ መጽሐፍ ሰጥታኝ ነበር፤ መጽሐፉ መሠረታዊ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን ግልጽ አድርጎ የሚያቀርብ መሆኑ ማረከኝ። ስለዚህ ነሐሴ 4, 1945 ወደተሰጠኝ አድራሻ ሄድኩ።

በሩን ሳንኳኳ የሚከፍት ሰው ስላጣሁ በኃይል አንኳኳሁ፤ በዚህ ጊዜ ከጎረቤት አንድ ሰው ወጣና 56 ሳልሜ ጎዳና ላይ የሚገኝ ሌላ አድራሻ ሰጠኝ። እዚያ እንደደረስኩ አንዲት ሴት በኩሽናዋ ውስጥ ሆና ድንች ስትልጥ አገኘሁና “እዚህ ቤት ሃይማኖታዊ ስብሰባ ይካሄዳል?” ብዬ ጠየቅኋት። እሷም በስብሰባው ላይ ያልተጋበዘ ሰው መገኘት ስለማይችል ተመልሼ እንድሄድ በቁጣ ነገረችኝ። እኔ ግን እንድታስገባኝ ስለወተወትኳት ፎቁን ወጥቼ መጽሐፍ ቅዱስን ከሚያጠኑት ሰዎች ጋር እንድሰበሰብ ፈቀደችልኝ። ብዙም ሳይቆይ የምሳ እረፍት ስለደረሰ ለመሄድ ተነሳሁ። እነሱ ግን እንድቆይ አደረጉኝ።

በምሳ እረፍቱ ወቅት በክፍሉ ውስጥ ዙሪያዬን ሳማትር በመስኮቱ ጥግ በጣም የገረጡና የከሱ ሁለት ወጣቶች ተቀምጠው አየሁ። በኋላ ላይ በጦርነቱ ዘመን ተይዘው እንዳይታሰሩ በመፍራት በተለያየ ቦታ ከአንድ ዓመት በላይ ተደብቀው ማሳለፋቸውን ሰማሁ። * በከሰዓት በኋላው ስብሰባ ፍሬድሪክ አልትፔሬ የሚባል ወንድም በንግግሩ ላይ “አርማጌዶን” የሚለውን ቃል ተጠቅሞ ነበር። ቃሉ ለእኔ አዲስ በመሆኑ ከስብሰባው በኋላ ስለ አርማጌዶን እንዲነግረኝ ጠየቅሁት። እሱም ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አሳየኝ። (ራእይ 16:16) ይህን ቃል መጽሐፍ ቅዱስ ላይ በማግኘቴ መደነቄን ሲያይ እንዴት አዲስ ሊሆንብኝ እንደቻለ ገረመው።

ይህ ስብሰባ ለሚታወቁና እምነት ለሚጣልባቸው የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ የተዘጋጀ መሆኑን ተረዳሁ። ይህ ስብሰባ ከጦርነቱ በኋላ የተደረገ የመጀመሪያው ስብሰባ እንደነበረም ከጊዜ በኋላ ተገነዘብኩ! ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በአምላክ መተማመን ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ተገነዘብኩ። (ምሳሌ 3:5, 6) ከአንድ ዓመት በኋላ በነሐሴ 1946፣ በ20 ዓመቴ ራሴን ለእውነተኛው አምላክ ለይሖዋ መወሰኔን በጥምቀት አሳየሁ።

የቤተሰብን ተቃውሞ መቋቋም

መንግሥት በትምህርት ቤት ለተማሪዎች አምላክ የለም የሚለውን ጽንሰ ሐሳብ ማስተማር እንደሚገባ በተደጋጋሚ ስላስታወቀ ይህ ጉዳይ በመጽሐፍ ቅዱስ ለሠለጠነው ሕሊናዬ ፈተና ሆነ። ሥራዬን መቀየር ፈለግሁ። ይህን ለእናቴ ስነግራት በንዴት ፀጉሬን እየነጨች ደበደበችኝ። በዚህ ጊዜ ቤቱን ለቅቄ ለመውጣት ወሰንኩ። ይሁን እንጂ አባቴ እንድጸና ያበረታታኝ ከመሆኑም በላይ እንደሚረዳኝ ነገረኝ።

ወንድሜ አንትስ ከእናቴ ጋር ሆኖ ይቃወመኝ ጀመር። ከዚያም አንድ ቀን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ጽሑፍ እንድሰጠው ጠየቀኝና ካነበበው በኋላ በጣም ወደደው። እናቴ በጣም ተናደደች። አንትስ በትምህርት ቤትም ሳይቀር ስለ አምላክ መናገር ጀምሮ የነበረ ቢሆንም ስደት ሲደርስበት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር የነበረውን ግንኙነት አቆመ። ከዚያም ጥቂት ጊዜ ቆይቶ በመዋኘት ላይ እያለ ውኃ ውስጥ ዘሎ ሲገባ ጭንቅላቱ ላይ ጉዳት ደረሰበት። ሽባ ሆኖ ከተኛበት መንቀሳቀስ ባይችልም የማሰብ ችሎታው ግን አልተዛባም ነበር። “ይሖዋ ይቅር ይለኛል?” ብሎ ጠየቀኝ። “አዎን” አልኩት። አንትስ ከጥቂት ቀናት በኋላ በ17 ዓመቱ ሞተ።

መስከረም 1947 በትምህርት ቤት የነበረኝን ሥራ ለቀቅሁ። እናቴ እኔን መቃወሟን ቀጠለች። ልብሴን በሙሉ ከቤት አውጥታ ስትጥል ቤቱን ለቅቄ ከኤሚሊና ከእህቷ ጋር መኖር ጀመርኩ። ኤሚሊና እህቷ፣ ይሖዋ አገልጋዮቹን ፈጽሞ እንደማይተዋቸው በመንገር ያበረታቱኝ ነበር።

ከጦርነቱ በኋላ በኢስቶኒያ የደረሰብኝ ፈተና

ኤሚሊና እህቷ ከእነሱ ጋር ሆኜ ለገበሬዎች ቤተሰቦች የሚሆን ልብስ እንድሰፋ ፈቀዱልኝ። ብዙውን ጊዜ ለእነዚህ ቤተሰቦች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ማካፈል እንችል ነበር። ከእነርሱ ጋር በቆየሁበት ወቅት ልብስ ስፌት ከመማሬም በላይ በክርስቲያናዊ አገልግሎት የበለጠ ተሞክሮ ማካበት ስለቻልኩ አስደሳች ጊዜ ነበር። ልብስ ከመስፋት በተጨማሪ በሒሳብ አስተማሪነት ተቀጠርኩ። ይሁን እንጂ በ1948 ባለ ሥልጣናቱ የይሖዋ ምሥክሮችን እየያዙ ማሰር ጀመሩ።

በቀጣዩ ዓመት ጥቅምት ወር ላይ በአንድ የእርሻ ቦታ በመሥራት ላይ እንዳለሁ ባለ ሥልጣናቱ እኔን ለማሰር ወደ ኤሚሊና እህቷ መኖሪያ ቤት መሄዳቸውን ሰማሁ። በወንድም ሁጎ ሱሴ የእርሻ ቦታ ለመደበቅ ስሄድ እሱም በዚያን ጊዜ ተይዞ መታሰሩ ተነገረኝ። ልብስ የሰፋሁላት አንዲት ሴት ከእሷ ጋር እንድኖር ፈቀደችልኝ። በኋላም ከአንዱ የእርሻ ቦታ ወደ ሌላው እየተዘዋወርኩ ልብስ መስፋትና መስበኬን ቀጠልኩ።

የበረዶው ወራት ሲጀምር በታርቱ ከተማ ከእኔ በዕድሜ ጥቂት ዓመታት በምትበልጥ ሊንዳ ሜቴግ የተባለች ቀናተኛ ወጣት እህት ቤት ሳለሁ የሶቪዬት መንግሥት የደኅንነት ኮሚቴ (ኬጂቢ) አባላት አገኙኝ። ተይዤ ለጥያቄ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ተወሰድኩ። እዚያም አፍጥጠው በሚመለከቱኝ ወጣት የፖሊስ መኮንኖች ፊት ልብሴን በሙሉ እንዳወልቅ ስላስገደዱኝ እንደተዋረድኩ ተሰማኝ። ሆኖም ወደ ይሖዋ ከጸለይኩ በኋላ ውስጣዊ ሰላምና መረጋጋት አገኘሁ።

ቀጥሎም ለመተኛት እንኳ በቂ ቦታ በሌላት በጣም ጠባብ ክፍል ውስጥ አስገብተው ዘጉብኝ። ከዚያ የምወጣው ለጥያቄ ሲወስዱኝ ብቻ ነበር። የፖሊስ መኮንኖቹ “የአምላክን መኖር ካጂ አላልንሽም፤ ግን ይህን የማይረባ ስብከትሽን ብቻ ተይ! በዚህ ከተስማማሽ ለወደፊቱ አስደሳች ጊዜ ይጠብቅሻል” ይሉኝ ነበር። ደግሞም “የምትፈልጊው መኖር ነው ወይስ በሳይቤሪያ ምድር ከአምላክሽ ጋር መሞት?” እያሉ ያስፈራሩኝ ነበር።

ለሦስት ቀናት ተደጋጋሚ ምርመራ ያደርጉብኝ ስለነበር እንቅልፍ ነሱኝ። በዚህ ጊዜ ለመጽናት የረዳኝ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ ማሰላሰሌ ነበር። በመጨረሻም አንድ መርማሪ መስበኬን እንደምተው የሚገልጽ ሰነድ ላይ እንድፈርም ጠየቀኝ። እኔም “ይህን ጉዳይ ብዙ አስቤበታለሁ። የአምላክን ሞገስ አጥቼ ነፃ ሆኜ ከመኖር ከአምላክ ጋር ያለኝን ዝምድና እንደያዝኩ በእስር ቤት መቆየት እመርጣለሁ” አልኩት። በዚህ ጊዜ መርማሪው “ጅል! ሁላችሁም ታስራችሁ ወደ ሳይቤሪያ ትላካላችሁ!” ብሎ ጮኸብኝ።

ሳይታሰብ በነፃ ተለቀቅሁ

የሚገርመው ነገር እኩለ ሌሊት ገደማ መርማሪዎቹ ዕቃዬን ይዤ እንድሄድ ነገሩኝ። እንደሚከታተሉኝ ስላወቅሁ የእምነት ባልንጀሮቼ ወደሆኑት ክርስቲያኖች አልሄድኩም፤ ወደ ወንድሞች ቤት ብሄድ እነሱን ለፖሊስ አሳልፎ መስጠት ይሆናል። በጎዳናው ላይ ስሄድ እንደፈራሁት ሦስት ሰዎች ተከተሉኝ። ይሖዋ እንዲመራኝ ከጸለይኩ በኋላ ጨለማ ወደሆነ መንገድ ተጠመዘዝኩና ሮጬ ወደ አንድ የአትክልት ሥፍራ ገባሁ። መሬት ላይ ተኝቼ በቅጠሎች ተሸፈንኩ። ሰዎቹ እያንኮሻኮሹ ሲሄዱ እሰማቸው ነበር፤ እንዲሁም የባትሪያቸው መብራት ይታየኝ ነበር።

በአትክልቱ ሥፍራ ተኝቼ ብዙ ሰዓታት ካሳለፍኩ በኋላ አጥንቶቼ በቅዝቃዜ ደነዘዙ። በመጨረሻም ጫማዬ ድምፅ እንዳያሰማ አውልቄ ያዝኩትና ድንጋይ በተነጠፈበት መንገድ ላይ መሄድ ጀመርኩ። ከከተማዋ ስወጣ በአውራ ጎዳናው ዳር በተቆፈረው ቦይ ውስጥ ጉዞዬን ቀጠልኩ። መኪና ሲመጣ ቦዩ ውስጥ ተኝቼ እደበቃለሁ። ከንጋቱ አሥራ አንድ ሰዓት ሲሆን ከታርቱ ከተማ ብዙም ሳይርቅ ወደሚገኘው የዩኤሬ እና የሜኤታ ቶሜል ቤት ደረስኩ።

ሜኤታ እንዲሞቀኝ ብላ ወዲያውኑ ሳውና አሞቀችልኝ። በቀጣዩ ቀን ወደ ታርቱ ሄዳ ሊንዳ ሜቴግን ይዛት መጣች። ሊንዳ “አሁኑኑ መስበክ እንጀምርና ምሥራቹን በመላው ኢስቶኒያ እናዳርስ” ስትል አበረታታችኝ። የፀጉሬን አበጣጠር በመቀየርና ፊቴን በመቀባባት እንዲሁም መነጽር በማድረግ መልኬን ከለወጥኩ በኋላ ስብከታችንን ጀመርን። በቀጣዮቹ ወራት በብስክሌት እየተጓዝን ርቀው በሚገኙ ክልሎች ሰበክን። በመንገዳችን ላይ በእርሻ ቦታቸው የሚኖሩ የእምነት አጋሮቻችንንም አበረታታን።

ወንድሞች ሐምሌ 24, 1950 በኦቴፓ አቅራቢያ የሚኖር የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ንብረት በሆነ በአንድ ሠፊ የድርቆሽ መጋዘን ውስጥ ትልቅ ስብሰባ ለማካሄድ ዝግጅት አደረጉ። የስብሰባው ሐሳብ በኬጂቢ እንደተደረሰበት ስንሰማ ወደ ስብሰባው ሲሄዱ የነበሩትን አብዛኞቹን ወንድሞች ማስጠንቀቅ ቻልን። ስብሰባው በቀጣዩ ቀን በሌላ ሥፍራ እንዲካሄድ ዝግጅት ተደረገና 115 ተሰብሳቢዎች ተገኙ። ከዚህ ስብሰባ በኋላ ሁላችንም ወደ ቤታችን ስንመለስ ልባችን በደስታ ተሞልቶና የሚደርስብንን ፈተና በታማኝነት ለመወጣት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ተጠናክረን ነበር። *

ከዚያ በኋላ እኔና ሊንዳ መስበካችንንና የእምነት ባልንጀሮቻችንን ማበረታታት ቀጠልን። በዚያው ዓመት ትንሽ ቆየት ብሎ፣ የደረሰ ድንች በመሰብሰብ ሥራ የተሳተፍን ሲሆን አብረውን ለሚሠሩ ሰዎች የመንግሥቱን መልእክት ማካፈል ችለናል። የአንድ እርሻ ባለቤት የሆነ ሰው ሥራውን አቁሞ ለአንድ ሰዓት ያዳመጠን ሲሆን “ይህ ልዩ ዜና ነው!” በማለት አድናቆቱን ገልጾልናል።

እኔና ሊንዳ ወደ ታርቱ ስንመለስ የሊንዳን እናት ጨምሮ ሌሎች ተጨማሪ ወንድሞችና እህቶች መታሰራቸውን ሰማን። በዚህ ጊዜ ኤሚሊንና እህቷን ጨምሮ አብዛኞቹ ወዳጆቻችን ታስረው ነበር። ኬጂቢ እኛንም እየፈለገን መሆኑን ስላወቅን ለየራሳችን ብስክሌት ይዘን ከታርቱ ውጪ መስበካችንን ቀጠልን። አንድ ቀን ማታ በቅርቡ በተጠመቀች አልማ ቫርድጃ በምትባል እህት ቤት ሳለሁ ኬጂቢዎች አገኙኝ። ከመካከላቸው አንዱ ፓስፖርቴን ከተመለከተ በኋላ “ኤላ! አንቺን ለማግኘት ያልፈለግንበት ቦታ የለም!” አለኝ። ይህ የሆነው ታኅሣሥ 27, 1950 ነበር።

እስርና ወደ ሳይቤሪያ መጋዝ

አልማና እኔ በተረጋጋ ሁኔታ ጓዛችንን ከጠቀለልን በኋላ ቁጭ ብለን ትንሽ ነገር መብላት ጀመርን። የኬጂቢ ወኪሎች በሁኔታው ተገርመው “እናንተ፣ ማልቀስ ሲገባችሁ ጭራሽ ቁጭ ብላችሁ ትበላላችሁ?” አሉን። እኛም “ወደ አዲሱ ምድባችን ልንሄድ ነው። ከዚህ በኋላ የምንበላው መቼ እንደሆነ ስለማናውቅ መብላት አለብን” ብለን መለስንላቸው። ይዘውን ሲሄዱ ብርድ ልብስ ይዤ ስለነበር ከጊዜ በኋላ ጠርዙን ቀድጄ ካልሲና ጓንት ሰፋሁ። ለብዙ ወራት ከታሰርኩ በኋላ በነሐሴ 1951 በኢስቶኒያ ከነበሩ ሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች ጋር በግዞት ተወሰድኩ። *

ከኢስቶኒያ ደግሞ ሩሲያ ወደሚገኘው ሌኒንግራድ (አሁን ሴይንት ፒተርስበርግ ተብሏል) በባቡር ተላክን፤ ከዚያም ከአርክቲክ ክልል በላይ በኮሜ ሪፑብሊክ ወደሚገኘው ከባድ የጉልበት ሥራ የሚሠራበት ቮርኩታ የተባለ በአስከፊነቱ የታወቀ ካምፕ ተወሰድን። በቡድኑ ውስጥ ሦስት የይሖዋ ምሥክር ሴቶች ነበርን። በትምህርት ቤት ሳለሁ የሩሲያ ቋንቋ ተምሬ ስለነበር ከታሰርኩበት ጊዜ ጀምሮ እየተለማመድኩ ነበር። ስለዚህ ወደ ካምፑ ስንደርስ የሩሲያ ቋንቋ በደንብ መናገር ችዬ ነበር።

ቮርኩታ ሳለን ፖላንድ ውስጥ በናዚ ማጎሪያ ካምፕ በታሰረችበት ጊዜ እውነትን ከተቀበለች አንዲት የዩክሬን ተወላጅ የሆነች ወጣት እህት ጋር ተገናኘን። በ1945 ጀርመኖች በባልቲክ ባሕር ውስጥ እንዲሰጥም ለማድረግ ባሰቡት መርከብ ላይ እሷና ሌሎች 14 የይሖዋ ምሥክሮች ተጭነው ነበር። ይሁን እንጂ መርከቡ በደህና ዴንማርክ ደረሰ። ይህች እህት ወደ ሩሲያ ከተመለሰች በኋላ ስትሰብክ በመገኘቷ ታሰረችና እኛ ወዳለንበት ወደ ቮርኩታ መጣች፤ የእርሷ መምጣት ለእኛ የብርታት ምንጭ ሆኖልናል።

በተጨማሪም ከሁለት ሴቶች ጋር የተገናኘን ሲሆን እነርሱም በዩክሬን ቋንቋ “እዚህ የይሖዋ ምሥክር የሆነ አለ?” ብለው ጠየቁን። ወዲያው እነዚህ ሴቶች ክርስቲያን እህቶቻችን መሆናቸውን ተገነዘብን! እነዚህ እህቶች እኛን አበረታተውናል፤ እንዲሁም ተንከባክበውናል። ሌሎች እስረኞች እንደተናገሩት ሊቀበሉን ይጠባበቁ ከነበሩ ቤተሰቦቻችን ጋር የተገናኘን ይመስል ነበር።

በሞርዶቪያ ወደሚገኙ ካምፖች መዛወር

በ1951 ታኅሣሥ ወር ላይ ባደረግሁት የሕክምና ምርመራ ከታይሮይድ እጢ ጋር በተያያዘ ሕመም እንዳለብኝ ስለተረጋገጠ ከሞስኮ በስተ ደቡብ ምሥራቅ 400 ኪሎ ሜትር፣ ከነበርኩበት ቦታ ደግሞ በስተ ደቡብ ምዕራብ 1,500 ኪሎ ሜትር ርቆ ወደሚገኝ አንድ ትልቅ የሞርዶቪያ እስር ቤት እንድዛወር ተደረገ። እዚያ በቆየሁባቸው በቀጣዮቹ ዓመታትም በነበርኩበት የሴቶች እስር ቤት ውስጥ ከጀርመን፣ ከሃንጋሪ፣ ከፖላንድና ከዩክሬን የመጡ የይሖዋ ምሥክሮችን አግኝቻለሁ። በተጨማሪም ማይሙ ከምትባል ከኢስቶኒያ የመጣች የፖለቲካ እስረኛ ጋር ተገናኘሁ።

ማይሙ በኢስቶኒያ ታስራ ሳለች የወለደቻትን ልጅ አንዲት ደግ የእስር ቤት ዘበኛ ለእናቷ ሰጥታላት ነበር። ማይሙን በሞርዶቪያ እስር ቤት መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠናኋት ሲሆን እሷም የተማረችውን አመነችበት። ለእናቷም ደብዳቤ ጻፈችላቸውና እሳቸውም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ተቀበሉ፤ ለማይሙ ልጅ ለካሪንም አስተማሯት። ከስድስት ዓመት በኋላ ማይሙ ከእስር ቤት ተለቃ ከሴት ልጅዋ ጋር ተገናኘች። ካሪን አድጋ የይሖዋ ምሥክር የሆነ የእምነት ባልንጀራዋን አገባች። ካሪንና ባሏ ላለፉት 11 ዓመታት በታሊን፣ ኢስቶኒያ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ሲያገለግሉ ቆይተዋል።

ግዙፍ በሆነው የሞርዶቪያ እስር ቤት ውስጥ የሚገኝ ዋሻው ተብሎ የሚጠራ ቦታ ነበር፤ ይህም በቅጥር ግቢው ውስጥ የሚገኙ ጥብቅ ቁጥጥር የሚደረግባቸው ትናንሽ ክፍሎችን የያዘ ነበር። እኔና ሌሎች ስድስት እህቶች በክርስቲያናዊ እንቅስቃሴያችን ምክንያት በእነዚያ ክፍሎች ውስጥ ታስረናል። ይሁን እንጂ እዚያ እያለንም ቢሆን የመጠበቂያ ግንብ ርዕሶችን በእጃችን ገልብጠን ትናንሽ ቅጂዎች በማዘጋጀት በአቅራቢያው ወደሚገኙ እስር ቤቶች በድብቅ እንዲገቡ እናደርግ ነበር። ከምንጠቀምባቸው ዘዴዎች አንዱ ትልቅ ሣሙና ወስደን ውስጡን በመቦርቦር ቀዳዳ ካበጀን በኋላ አንድ የመጠበቂያ ግንብ ርዕስ በውስጡ በመክተት ሣሙናውን መልሰን ማሸግ ነበር።

በሞርዶቪያ ካምፕ በነበርኩባቸው ዓመታት ከአሥር የሚበልጡ ሴቶች እውነተኛውን አምላክ እንዲያመልኩ መርዳት ችዬአለሁ። በመጨረሻም ግንቦት 4, 1956 “ይሖዋ አምላክሽን በነፃነት ማምለክ ትችያለሽ” ተባልኩ። በዚያው በግንቦት ወር በኢስቶኒያ ወደሚገኘው የትውልድ ሥፍራዬ ተጓዝኩ።

ወደ ትውልድ ሥፍራዬ ከተመለስኩ በኋላ ያሳለፍኳቸው ወደ 50 የሚጠጉ ዓመታት

ከእስር ቤት ተለቅቄ ስመለስ ሥራ፣ ገንዘብም ሆነ ቤት አልነበረኝም። ይሁን እንጂ ኢስቶኒያ በደረስኩ በጥቂት ቀናት ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስን ለመማር ፍላጎት ያላት አንዲት ሴት አገኘሁ። ለጊዜው ከእሷና ከባሏ ጋር በባለ አንድ ክፍል አፓርታማ ቤታቸው ውስጥ እንድኖር ፈቀደችልኝ። በብድር ባገኘሁት ገንዘብ ሱፍ ክር ገዛሁና ሹራብ ሠርቼ ሸጥኩ። በኋላም ለቀጣዮቹ ሰባት ዓመታት በታርቱ የካንሰር ሆስፒታል ውስጥ ተቀጥሬ የተለያዩ ሥራዎችን ሠራሁ። በመሃሉ ሌምቢት ቱም በሳይቤሪያ ከነበረበት ግዞት ተመልሶ ስለነበር በ1957 ኅዳር ወር ተጋባን።

የስብከት ሥራችን ገና በእገዳ ሥር ስለነበረ ኬጂቢ እየተከታተለ እረፍት ነሳን። ሆኖም እምነታችንን ለማካፈል የቻልነውን ሁሉ አድርገናል። ሌምቢት የስብከት ሥራችን ምን ይመስል እንደነበረ በየካቲት 22, 1999 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ላይ ገልጾታል። በ1950ዎቹ ዓመታት ማብቂያ እንዲሁም በ1960ዎቹና 1970ዎቹ፣ በግዞት የተወሰዱ የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ትውልድ ሥፍራቸው እየተመለሱ ነበር። በ1980ዎቹ ዓመታት ማብቂያ ላይ በኢስቶኒያ ከ700 የሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮች ነበሩ። በ1991 ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴያችን ሕጋዊ ሆነ። ከዚያ ጊዜ ወዲህ በኢስቶኒያ ያለነው የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥር ወደ 4,100 ከፍ ብሎአል!

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በኢስቶኒያ ለመጀመሪያ ጊዜ በምስጢር በተደረገው የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ ከተገኘሁ አሁን 60 ዓመት አልፏል። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ቁርጥ ውሳኔዬ “በእግዚአብሔር ታመን፤ መልካምንም አድርግ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር መከተል ነበር። በይሖዋ ከታመንን ‘የልባችንን መሻት’ እንደምናገኝ ተምሬያለሁ።—መዝሙር 37:3, 4

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.14 ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዱ ሌምቢት ቱም ሲሆን ራሱ የተናገረው የሕይወት ታሪኩ በየካቲት 22, 1999 የንቁ! እትም (እንግሊዝኛ) ላይ ወጥቷል።

^ አን.30 ስለዚህ ስብሰባ ዝርዝር መግለጫ ለማግኘት የየካቲት 22, 1999 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ገጽ 12, 13ን ተመልከት።

^ አን.34 በኢስቶኒያ የነበሩት አብዛኞቹ የይሖዋ ምሥክሮች የተጋዙት በ1951 በሚያዝያ ወር መጀመሪያ ላይ ነበር። የሚያዝያ 22, 2001 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ገጽ ከ6-8ን እና በሶቪዬት ሕብረት ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች በፈተና ወቅት ያሳዩት ጽናት የተሰኘውን የቪዲዮ ፊልም ተመልከት።

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“አሁኑኑ መስበክ እንጀምርና ምሥራቹን በመላው ኢስቶኒያ እናዳርስ።”—ሊንዳ ሜቴግ

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሞርዶቪያ እስር ቤት ውስጥ ከሌሎች ዘጠኝ የይሖዋ ምሥክሮች ጋር

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በአሁኑ ጊዜ ከባለቤቴ ከሌምቢት ጋር