በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ልጆቻችሁን አስተምሩ

ጴጥሮስና ሐናንያ ዋሹ—ከዚህ ምን እንማራለን?

ጴጥሮስና ሐናንያ ዋሹ—ከዚህ ምን እንማራለን?

እንደምታውቀው መዋሸት ማለት እውነት ያልሆነ ነገር መናገር ማለት ነው። ውሸት ተናግረህ ታውቃለህ? * አምላክን የሚወዱ አንዳንድ ትላልቅ ሰዎች እንኳ ውሸት ተናግረው ያውቃሉ። ምናልባት አንተም ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ውስጥ አምላክን የሚወዱ ሆኖም ውሸት የተናገሩ ሰዎችን ታውቅ ይሆናል። ከእነዚህ አንዱ ጴጥሮስ ሲሆን ይህ ሰው ከ12ቱ የኢየሱስ ሐዋርያት አንዱ ነበር። ውሸት የተናገረው ለምን እንደነበረ ታሪኩን እንመርምር።

ኢየሱስ ከተያዘ በኋላ ወደ ሊቀ ካህናቱ ቤት ተወሰደ። በዚህ ጊዜ እኩለ ሌሊት አልፏል። ጴጥሮስም ሳይታወቅ ወደ ካህኑ ግቢ ሹልክ ብሎ ገባ። ለጴጥሮስ በር የከፈተችለት የሊቀ ካህናቱ አገልጋይ በእሳቱ ብርሃን ስታየው አወቀችው። እሷም “አንተም ከገሊላው ኢየሱስ ጋር ነበርክ” አለችው። ጴጥሮስ ግን ፈርቶ ከኢየሱስ ጋር እንዳልነበረ ተናገረ።

ቆየት ብሎም ‘ሌላ ሴት እንዳየችው’ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። እሷም “ይህ ሰው ከናዝሬቱ ኢየሱስ ጋር ነበር” አለች። ጴጥሮስ አሁንም ካደ። ጥቂት ቆይቶ ሌሎች ሰዎች ወደ ጴጥሮስ ቀርበው “በእርግጥ አንተም ከእነሱ አንዱ ነህ!” አሉት።

ጴጥሮስ በጣም ፈራ። ስለዚህ ለሦስተኛ ጊዜ “ሰውየውን አላውቀውም!” ብሎ ዋሸ። በዚህ ጊዜ ዶሮ ጮኸ። ኢየሱስ ጴጥሮስን ተመለከተው፤ ይሄን ጊዜ ጴጥሮስ ከጥቂት ሰዓታት በፊት ኢየሱስ “ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” ያለው ትዝ አለው። ጴጥሮስ በጣም ስላዘነ ምርር ብሎ አለቀሰ!

ታዲያ በአንተ ላይ እንዲህ ዓይነት ነገር ሊደርስ ይችላል?— ትምህርት ቤት ውስጥ ተማሪዎች ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ሲያወሩ ሰማህ እንበል። አንዱ ልጅ “ለባንዲራ ሰላምታ አይሰጡም” ይላል። ሌላው ደግሞ “ለአገራቸው አይዋጉም” ይላል። ሦስተኛው ልጅ ደግሞ “ገናን ስለማያከብሩ ክርስቲያኖች አይደሉም” ብሎ ይናገራል። ከዚያም አንዱ ልጅ ወደ አንተ ዞር ብሎ “የይሖዋ ምሥክር ነህ አይደል?” ብሎ ይጠይቅሃል። በዚህ ጊዜ ምን ትለዋለህ?

እንዲህ ዓይነት ነገር ሲያጋጥምህ ጥሩ መልስ መስጠት እንድትችል አስቀድመህ መዘጋጀት ያስፈልግሃል። ጴጥሮስ አልተዘጋጀም ነበር። በመሆኑም ድንገት ከባድ ተጽዕኖ ሲያጋጥመው ዋሸ! ሆኖም ባደረገው ነገር በጣም ስለተጸጸተ አምላክ ይቅር ብሎታል።

በጥንት ጊዜ ይኖር የነበረ ሐናንያ የተባለ አንድ የኢየሱስ ተከታይም ዋሽቷል። ይሁን እንጂ አምላክ ለእሱም ሆነ ለሚስቱ ለሰጲራ ይቅርታ አላደረገላቸውም። ሰጲራ ውሸት ለመናገር ከባሏ ጋር ተስማምታ ነበር። አምላክ ለሐናንያም ሆነ ለሰጲራ ይቅርታ ያላደረገላቸው ለምን እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

ኢየሱስ ሐዋርያቱን ተሰናብቶ ወደ ሰማይ ከሄደ ከአሥር ቀን በኋላ 3,000 የሚያህሉ ሰዎች በኢየሩሳሌም ተጠምቀው ደቀ መዛሙርት ሆኑ። አብዛኞቹ የጴንጤቆስጤን በዓል ለማክበር ከሩቅ አገሮች የመጡ ሲሆኑ የኢየሱስ ተከታዮች ከሆኑ በኋላ ደግሞ ስለ አዲሱ እምነታቸው ተጨማሪ ነገር ለማወቅ ለጥቂት ቀናት እዚያው ኢየሩሳሌም መቆየት ፈለጉ። ስለዚህ አንዳንዶቹ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ገንዘባቸውን እነዚህን ክርስቲያኖች ለማስተናገድ ተጠቀሙበት።

ሐናንያና ሚስቱ አዲስ የተጠመቁትን ደቀ መዛሙርት ለመርዳት ሲሉ መሬታቸውን ሸጡ። ሐናንያ ገንዘቡን ወደ ሐዋርያት በወሰደ ጊዜ ከሽያጩ ያገኘውን ገንዘብ በሙሉ እንዳመጣ ተናገረ። ይህ ግን እውነት አይደለም! የተወሰነውን ገንዘብ ለራሱ አስቀርቷል! አምላክ ይህን ጉዳይ ለጴጥሮስ ስላሳወቀው ሐናንያን “ያታለልከው ሰውን ሳይሆን አምላክን ነው” አለው። ወዲያውኑ ሐናንያ ወድቆ ሞተ! ከሦስት ሰዓት በኋላ ሚስቱ መጣች። ሰጲራም በባሏ ላይ የደረሰውን ነገር ስላላወቀች ዋሸች፤ በዚህ ጊዜ እሷም ወድቃ ሞተች።

እውነቱን መናገር በጣም አስፈላጊ እንደሆነ የሚያስገነዝብ እንዴት ያለ ጠቃሚ ትምህርት ነው! አዎን፣ ሁላችንም ከእነዚህ ታሪኮች ትምህርት ማግኘት ይኖርብናል! ሆኖም ሁላችንም በተለይ ትናንሽ ልጆች ሳለን ስህተት መሥራታችን አይቀርም። ይሖዋ እንደሚወድህና እንደ ጴጥሮስ ሁሉ አንተንም ይቅር እንደሚልህ ማወቅህ አያስደስትህም?— ቢሆንም እውነት መናገር እንደሚያስፈልገን አትዘንጋ። እንዲሁም በመዋሸት ትልቅ ስህተት ከሠራን ይቅርታ እንዲያደርግልን አምላክን መለመን ያስፈልገናል። ጴጥሮስ ያደረገው ይህንኑ መሆን አለበት፤ ምክንያቱም ይቅርታ ተደርጎለታል። ከእንግዲህ ላለመዋሸት ከልብ ጥረት ካደረግን አምላክ ለእኛም ይቅርታ ያደርግልናል!

ከመጽሐፍ ቅዱስህ ላይ

^ አን.3 ይህን ርዕስ የምታነበው ከትንሽ ልጅ ጋር ከሆነ፣ ይህ ሰረዝ ቆም ብለህ ልጁ ሐሳቡን እንዲገልጽ እንድታበረታታው ለማስታወስ ተብሎ የተደረገ ነው።