ወደ አምላክ ቅረብ
“ከትእዛዛት ሁሉ የመጀመሪያው የትኛው ነው?”
አምላክን ማስደሰት የሚቻለው እንዴት ነው? ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ሕጎችና ደንቦች መከተል ይኖርብን ይሆን? ደስ የሚለው ነገር፣ መልሱ አይኖርብንም የሚል ነው። የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ በተናገረው መሠረት አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ነገር በአንድ ቃል ሊጠቃለል ይችላል።—ማርቆስ 12:28-31ን አንብብ።
በመጀመሪያ፣ ኢየሱስ እነዚህን ቃላት የተናገረበትን መቼት ተመልከት። ኢየሱስ ከመሞቱ ከጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ ኒሳን 11 ዕለት በቤተ መቅደስ እያስተማረ ነበር። ጠላቶቹ እሱን ለማጥመድ በማሰብ አንዳንድ አወዛጋቢ ጥያቄዎችን ይጠይቁት ጀመር። በዚህ ጊዜ ለሁሉም ጥያቄዎቻቸው አፋቸውን የሚያስይዝ መልስ ሰጣቸው። በኋላም ኢየሱስ “ከትእዛዛት ሁሉ የመጀመሪያው የትኛው ነው?” የሚል ጥያቄ ቀረበለት።—ቁጥር 28
ይህ ጥያቄ አስቸጋሪ ነበር። አንዳንድ አይሁዳውያን በሙሴ ሕግ ውስጥ ከሚገኙት ከ600 በላይ ሕጎች መካከል የመጀመሪያው ወይም የሚበልጠው የትኛው እንደሆነ ይከራከሩ ነበር። ሌሎቹ ደግሞ ሁሉም ሕጎች እኩል እንደሆኑና ሕጎቹን ማበላለጥ ስህተት እንደሆነ ያምኑ የነበረ ይመስላል። ታዲያ ኢየሱስ ለዚህ ጥያቄ ምን ምላሽ ይሰጥ ይሆን?
ኢየሱስ በሰጠው መልስ ላይ አንድ ሳይሆን ሁለት ትእዛዛትን ጠቀሰ። በመጀመሪያ እንዲህ አለ፦ “አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህ፣ በሙሉ አእምሮህና በሙሉ ኃይልህ ውደድ።” (ቁጥር 30፤ ዘዳግም 6:5) ኢየሱስ “ልብ፣” “አእምሮ፣” “ነፍስ” እና “ኃይል” የሚሉትን ቃላት የተጠቀመው ልዩነታቸውን ለመግለጽ ሳይሆን በመካከላቸው ያለውን ዝምድና ለማመልከት ነው፤ ምክንያቱም ሁሉም የሚያመለክቱት ውስጣዊውን ሰው ነው። * ስለዚህ ኢየሱስ ይህን ሐሳብ ሲናገር ለአምላክ ያለን ፍቅር ሙሉ እንዲሆን የምንችለውን ሁሉ ማድረግ እንዳለብን አበክሮ መግለጹ ነበር። በመሆኑም ይሖዋን መውደድ የአንድን ሰው ሁለንተና ይኸውም ችሎታውንና ኃይሉን በሙሉ የሚያጠቃልል ነው። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ማመሳከሪያ ይህን ጥቅስ “አምላክ ሙሉ በሙሉና በተሟላ መንገድ ሊወደድ ይገባዋል” በማለት አስቀምጦታል። አምላክን ከወደድከው በእያንዳንዱ ዕለት የእሱን ሞገስ በሚያስገኝ መንገድ ለመኖር የቻልከውን ሁሉ ታደርጋለህ።—1 ዮሐንስ 5:3
ሁለተኛ፣ ኢየሱስ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” ብሏል። (ቁጥር 31፤ ዘሌዋውያን 19:18) አምላክን መውደድና ባልንጀራን መውደድ የማይነጣጠሉ ነገሮች ናቸው። ባልንጀራን መውደድ አምላክን በመውደድ የሚገኝ ነገር ነው። (1 ዮሐንስ 4:20, 21) ባልንጀሮቻችንን እንደ ራሳችን አድርገን የምንወዳቸው ከሆነ እኛን እንዲይዙን በምንፈልገው መንገድ እንይዛቸዋለን። (ማቴዎስ 7:12) እንዲህ በማድረግ፣ እኛንም ሆነ እነሱን በአምሳሉ የፈጠረውን አምላክ እንደምንወድ እናሳያለን።—ዘፍጥረት 1:26
ይሖዋ ከአገልጋዮቹ የሚፈልገው ነገር በሙሉ በአንድ ቃል ማለትም በፍቅር ሊጠቃለል ይችላል
አምላክንና ባልንጀራን እንድንወድ የተሰጡት ትእዛዛት ምን ያህል አስፈላጊ ናቸው? ኢየሱስ “ከእነዚህ የሚበልጥ ሌላ ትእዛዝ የለም” ብሏል። (ቁጥር 31) ማቴዎስ ባሰፈረው ተመሳሳይ ዘገባ ላይ ኢየሱስ ሌሎች ትእዛዛት ሁሉ በእነዚህ በሁለቱ ላይ የተመሠረቱ እንደሆኑ ተናግሯል።—ማቴዎስ 22:40
አምላክን ማስደሰት አስቸጋሪ አይደለም። አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ነገር በሙሉ በአንድ ቃል ማለትም በፍቅር ሊጠቃለል ይችላል። ፍቅር ምንጊዜም ይኸውም ቀድሞም ሆነ አሁን እንዲሁም ወደፊት የእውነተኛው አምልኮ መሠረት ነው። ይሁን እንጂ ፍቅር በአንደበት ብቻ የሚገለጽ ወይም የስሜት ጉዳይ ብቻ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ በሥራ መገለጽ ይኖርበታል። (1 ዮሐንስ 3:18) ታዲያ ‘ፍቅር የሆነውን’ ይሖዋ አምላክን መውደድና ለእሱ ያለህን ፍቅር ማዳበር የምትችለው እንዴት እንደሆነ ለምን አትማርም?—1 ዮሐንስ 4:8
በመጋቢት ወር የሚነበብ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል
ከማርቆስ 9-16 እስከ ሉቃስ 1-6
^ አን.6 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ነፍስ” የሚለው ቃል አንድን ሰው ያመለክታል። ስለዚህ “ነፍስ” የሚለው ቃል ‘ልብን፣’ ‘አእምሮን’ እና ‘ኃይልን’ አጠቃሎ ሊይዝ ይችላል።