በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 አንባቢያን የሚያነሱት ጥያቄ . . .

ኢየሱስ አብሮት ለተሰቀለው ወንጀለኛ በሰማይ እንደሚኖር ቃል ገብቶለት ነበር?

ኢየሱስ አብሮት ለተሰቀለው ወንጀለኛ በሰማይ እንደሚኖር ቃል ገብቶለት ነበር?

ይህ ጥያቄ የሚነሳው ኢየሱስ ከጎኑ ለተሰቀለው ወንጀለኛ ወደፊት በገነት እንደሚኖር ቃል ገብቶለት ስለነበረ ነው። ኢየሱስ “እውነት እልሃለሁ ዛሬ፣ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” ብሎታል። (ሉቃስ 23:43) እዚህ ላይ ኢየሱስ ይህ ገነት የት እንደሚገኝ አለመናገሩን ልብ በል። ታዲያ ኢየሱስ ወንጀለኛው ከእሱ ጋር በሰማይ እንደሚሆን እየተናገረ ነበር?

በመጀመሪያ፣ ወንጀለኛው በሰማይ ለመኖር የሚያስፈልጉትን ብቃቶች ያሟላ እንደሆነና እንዳልሆነ እንመልከት። ወደ ሰማይ የመሄድ ተስፋ ያላቸው ሰዎች በመንፈስ የተወለዱ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ሲሆኑ በውኃና በመንፈስ ቅዱስ ተጠምቀዋል። (ዮሐንስ 3:3, 5) በሌላ በኩል ደግሞ ከአምላክ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ጋር ተስማምተው መኖር እንዲሁም እንደ ሐቀኝነት፣ ታማኝነትና ርኅራኄ የመሳሰሉትን ባሕርያት ማሳየት ይኖርባቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 6:9-11) በተጨማሪም ምድራዊ ሕይወታቸውን እስኪያጠናቅቁ ድረስ ለአምላክና ለክርስቶስ ታማኝ መሆን አለባቸው። (ሉቃስ 22:28-30፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:12) ከሞት የሚነሱትና በሰማይ ለሚጠብቃቸው ከባድ ኃላፊነት ማለትም ከክርስቶስ ጋር ለሺህ ዓመት ካህናትና ነገሥታት ሆነው ሰዎችን ለማገልገል ብቃት እንዳላቸው የሚያስመሠክሩት እነዚህን መሥፈርቶች ካሟሉ ብቻ ነው።—ራእይ 20:6

ከኢየሱስ ጎን የተሰቀለው ሰው ግን ወንጀለኛ ሲሆን የሞተውም ቢሆን ወንጀለኛ እንደሆነ ነው። (ሉቃስ 23:32, 39-41) እርግጥ ነው፣ “ወደ መንግሥትህ ስትመጣ አስበኝ” ብሎ ሲናገር ለኢየሱስ አክብሮት እንዳለው አሳይቷል። (ሉቃስ 23:42) ይሁን እንጂ የተጠመቀና በመንፈስ የተወለደ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር አልነበረም፤ ከዚህም በላይ ጥሩ ምግባር ይዞ በመኖርና በታማኝነት በመጽናት ረገድ ያስመዘገበው ታሪክ የለውም። ታዲያ ኢየሱስ ንጹሕ አቋማቸውን ከጠበቁት ታማኝ ተከታዮቹ ጋር አብሮ በሰማይ እንዲነግሥ ለዚህ ሰው ቃል ይገባለታል ብሎ ማሰቡ ምክንያታዊ ነው?—ሮም 2:6, 7

ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ ገንዘብ የሰረቀህ አንድ ሰው ይቅርታ ቢጠይቅህ በዚህ ግለሰብ ላይ ክስ ላለመመሥረት ትወስን ይሆናል። ይሁን እንጂ በዚህ ሰው ላይ እምነት ጥለህ ንግድህን እንዲቆጣጠርልህ ወይም ቤተሰብህን እንዲንከባከብልህ ታደርጋለህ? እንዲህ ዓይነቱን ኃላፊነት የምትሰጠው በጣም ለምታምነው ሰው ብቻ እንደሚሆን የተረጋገጠ ነው። በተመሳሳይም በሰማይ የመኖር ተስፋ የተሰጣቸው ሰዎች፣ የሰውን ዘር በሚገዙበት ጊዜ የአምላክን የጽድቅ መሥፈርቶች ማስከበር እንደሚችሉ በግልጽ መታየት አለበት። (ራእይ 2:10) ወንጀለኛው ባለቀ ሰዓት ላይ ከልቡ ንስሐ ቢገባም በሰማይ ለመኖር ብቁ የሚያደርገውን ተግባር አላከናወነም።

ይሁን እንጂ ኢየሱስ ለወንጀለኛው በዚያን ዕለት በሰማይ አብሮት እንደሚሆን ቃል ገብቶለት የለም? ይህ ሊሆን አይችልም፤ ምክንያቱም ኢየሱስ ራሱ በዚያን ቀን ወደ ሰማይ አልሄደም። ከዚህ ይልቅ ለሦስት ቀናት የቆየው “በምድር ልብ” ማለትም በመቃብር ውስጥ ነው። (ማቴዎስ 12:40፤ ማርቆስ 10:34) ከትንሣኤው በኋላም እንኳ ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት በምድር ላይ ለ40 ቀናት ቆይቷል። (የሐዋርያት ሥራ 1:3, 9) በመሆኑም ወንጀለኛው በዚያን ዕለት ከኢየሱስ ጋር በሰማይ መሆን አይችልም ነበር።

ታዲያ ይህ ወንጀለኛ የሚገባው ወደ የትኛው ገነት ነው? ይህ ሰው ከሞት ከተነሳ በኋላ፣ ኢየሱስ በሚገዛው ምድራዊ ገነት ውስጥ ይኖራል። (የሐዋርያት ሥራ 24:15፤ ራእይ 21:3, 4) ስለዚህ ገነትና በዚህ ገነት ውስጥ ለመኖር ስለሚያስፈልጉት ብቃቶች ይበልጥ ለማወቅ አንድ ይሖዋ ምሥክር ልታነጋግር ትችላለህ።