በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

የመጀመሪያው መቶ ዘመን አይሁዳውያን አስከሬንን ለቀብር ያዘጋጁ የነበረው እንዴት ነው?

አይሁዳውያን፣ ሰው ሲሞትባቸው የሚቀብሩት ቶሎ ብለው፣ አብዛኛውን ጊዜ በሞተበት ዕለት ነበር። በአፋጣኝ እንዲቀብሩ የሚያነሳሷቸው ሁለት ምክንያቶች ነበሩ። አንደኛ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ የአየሩ ጠባይ ሞቃታማ ስለሆነ አስከሬን ቶሎ ይበሰብሳል። ሁለተኛ፣ በወቅቱ በነበረው አስተሳሰብ መሠረት አንድ አስከሬን ሳይቀበር የተወሰኑ ቀናት እንዲያልፉ ማድረግ ለሟቹም ሆነ ለቤተሰቡ አክብሮት አለማሳየት ነው።

በወንጌሎችና በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ ሰዎቹ በሞቱበት ዕለት የተከናወኑ ቢያንስ አራት የቀብር ሥነ ሥርዓቶች ተመዝግበዋል። (ማቴዎስ 27:57-60፤ የሐዋርያት ሥራ 5:5-10፤ 7:60 እስከ 8:2) ከብዙ መቶ ዘመናት በፊት የያዕቆብ ሚስት ራሔል የሞተችው ያዕቆብና ቤተሰቡ በጉዞ ላይ እያሉ ነበር። ያዕቆብ አስከሬኗን ወደ ቤተሰቡ የቀብር ቦታ ከመውሰድ ይልቅ ራሔልን “ወደ ኤፍራታ በሚወስደው መንገድ በቤተልሔም” ቀበራት።—ዘፍጥረት 35:19, 20, 27-29

ስለ ቀብር ዝግጅት የሚገልጹ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች እንደሚያሳዩት አይሁዳውያን አስከሬንን ለቀብር ለማዘጋጀት ከፍተኛ ጥንቃቄ ያደርጉ ነበር። ወዳጅ ዘመዶች የሟቹን አስከሬን ካጠቡት በኋላ በቅመምና ጥሩ መዓዛ ባለው ዘይት አሽተው በጨርቅ ይገንዙታል። (ዮሐንስ 19:39, 40፤ የሐዋርያት ሥራ 9:36-41) እንዲሁም ጎረቤቶችና ሌሎች ሰዎች መጥተው ሐዘናቸውን ይገልጻሉ፤ ቤተሰቡንም ያጽናናሉ።—ማርቆስ 5:38, 39

የኢየሱስ አቀባበር የአይሁዳውያንን የቀብር ሥነ ሥርዓት የተከተለ ነበር?

ብዙ አይሁዳውያን ቤተሰቦች የሞቱ ዘመዶቻቸውን የሚቀብሩት በዋሻዎችና በአብዛኞቹ የእስራኤል አካባቢዎች እንደተለመደው ከለስላሳ ዐለት በተፈለፈሉ መቃብሮች ነበር። እንዲህ በማድረግም የቀድሞ አባቶቻቸው የተዉትን የአቀባበር ሥርዓት ይከተሉ ነበር። አብርሃም፣ ሣራ፣ ይስሐቅ፣ ያዕቆብና ሌሎችም የተቀበሩት በኬብሮን አቅራቢያ በሚገኘው በመክፈላ ዋሻ ውስጥ ነው።—ዘፍጥረት 23:19፤ 25:8, 9፤ 49:29-31፤ 50:13

ኢየሱስ የተቀበረው ከዐለት ተፈልፍሎ በተሠራ መቃብር ውስጥ ነው። (ማርቆስ 15:46) እንዲህ ዓይነቱ መቃብር በአብዛኛው ጠባብ በር ነበረው። በውስጡ ያሉት ዐለቱን በመፈልፈል የተሠሩ እንደ መደርደሪያ ያሉ በርካታ ማስቀመጫዎች፣ የሞቱትን የቤተሰብ አባላት አስከሬን ለማስቀመጥ ያገለግላሉ። ኢየሱስ ምድር ሳለ በነበረው ባሕል መሠረት፣ የተቀበረው አስከሬን ከበሰበሰ በኋላ አፅሙ ከድንጋይ በተሠራ የሬሳ ሣጥን ውስጥ ይደረግ ነበር። እንዲህ መደረጉ፣ በአንድ ቤተሰብ ውስጥ ሰው ሲሞት መቅበሪያ ቦታ ለማግኘት ያስችላል።

በሙሴ ሕግ ሥር የነበረው የሰንበት እረፍት አይሁዳውያን በዚያ ቀን የቀብር ሥነ ሥርዓት እንዳያካሂዱ ይከለክል ነበር። ኢየሱስ የሞተው ሰንበት ሊጀምር ሦስት ሰዓት ገደማ ሲቀረው ስለነበረ የአርማትያሱ ዮሴፍና ሌሎች ሰዎች የኢየሱስን አስከሬን የቀበሩት የሚያስፈልገውን ዝግጅት ሳያጠናቅቁ ነው። (ሉቃስ 23:50-56) በዚህም ምክንያት አንዳንድ የኢየሱስ ወዳጆች የአስከሬን አገናነዝ ሥርዓቱን ለማጠናቀቅ በሰንበት ማግስት ወደ መቃብሩ ሄደው ነበር።—ማርቆስ 16:1፤ ሉቃስ 24:1