በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በአውስትራሊያ በስተ ሰሜን ርቀው በሚገኙ ደሴቶች ‘ምሥራቹ’ ተሰበከ

በአውስትራሊያ በስተ ሰሜን ርቀው በሚገኙ ደሴቶች ‘ምሥራቹ’ ተሰበከ

በአውስትራሊያ በስተ ሰሜን ርቀው በሚገኙ ደሴቶች ‘ምሥራቹ’ ተሰበከ

ኢየሱስ “ይህ የመንግሥቱ ምሥራች . . . በመላው ምድር ይሰበካል” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:14) የይሖዋ ምሥክሮች ኢየሱስ የሰጣቸውን ይህን ትእዛዝ በመከተል የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ሰዎች በሚገኙበት ቦታ ሁሉ ለማድረስ ይጥራሉ። (ማቴዎስ 28:19, 20) ይህ ሥራ አንዳንድ ጊዜ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን መጋፈጥ እንዲሁም ወጪ የሚጠይቅ ቢሆንም ሥራው የሚከናወነው በፈቃደኝነት ነው።

ለምሳሌ ያህል፣ ኔተን እና ካርሊ ርቀው ወደሚገኙት የቶሪስ ስትሪት ደሴቶች ሄደው ለመስበክ ሁኔታቸውን አስተካክለዋል። በ2003 በአውስትራሊያ የሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ተወካይ እነዚህ ባልና ሚስት ወደ ተርዝዴይ ደሴት ሄደው እዚያ ካለው ጉባኤ ጋር እንዲያገለግሉ ጋበዛቸው። ይህ ደሴት በአውስትራሊያና በኒው ጊኒ መካከል በተንጣለለው ሰማያዊው የፓስፊክ ውቅያኖስ ላይ እንደ አረንጓዴ ፈርጥ ጣል ጣል ካሉት ደሴቶች አንዱ ነው።

ቤተሰቡ በ2007 ታይሳንዋይ ተብላ የምትጠራ ዕንቁ ለማውጣት ታገለግል የነበረች አንዲት አሮጌ የእንጨት መርከብ ገዛ። መርከቧን በራሳቸው ወጪ ካደሱ በኋላ መኖሪያቸውን ተርዝዴይ ደሴት በማድረግ ራቅ ብለው ወደሚገኙት አሥር ደሴቶች ለመስበክ መጓዝ ጀመሩ። ከዚህ ቀጥሎ የቀረበው ዘገባ “ካፒቴኑ” ከተደረጉት ጉዞዎች መካከል አንዳንዶቹን በሚመለከት ካሰፈረው “ማስታወሻ” የተወሰደ ነው።

ጥር 2008፦ ዛሬ ስድስት የይሖዋ ምሥክሮችን ለማምጣት ደርሶ መልስ 80 ኪሎ ሜትር ወደሚፈጀው ወደ ባመገ በአነስተኛ ጀልባ ሄድኩ። አሁን የምንገኘው በታይሳንዋይ መርከብ ላይ ሲሆን ወደ ዋረበርና ፐሩመ ደሴቶች እየተጓዝን ነው። አንድ ሊትር በ2.00 የአውስትራሊያ ዶላር ሒሳብ፣ በአጠቃላይ 5,500 ሊትር ነዳጅ ስለቀዳን ታንከሮቻችን ሙሉ ናቸው። መርከባችን በሰዓት 10 ኪሎ ሜትር ብቻ ስለምትጓዝ በጣም ቀርፋፋ ነች። አነስተኛ ሞገድ ከመኖሩ ውጪ የአየሩ ጠባይ በጣም ደስ ይላል።

እዚያ ስንደርስ ባሕሩ ዳርቻ ላይ መልሕቃችንን ከጣልን በኋላ ዋረበር በሚባለው ደሴት ዘመድ ያላቸው የተወሰኑ የቡድናችን አባላት በጀልባ ላይ እንዲሳፈሩ ካደረግን በኋላ ለመስበክ ፈቃድ እንዲሰጠን ወደ ደሴቲቱ ባለ ሥልጣን ሄዱ። ይህ ባለ ሥልጣን በአካባቢው የሚገኝ የአንድ ቤተ ክርስቲያን ፓስተር ቢሆንም ነዋሪዎቹን እንድናነጋግር ፈቀደልን። ፐሩመም ስንደርስ ተመሳሳይ ነገር ያደረግን ሲሆን እዚያም እንድንሰብክ ተፈቀደልን። ሰዎቹ የሚቀረቡ ሲሆኑ ጽሑፎቻችንን የማንበብ ጉጉት ነበራቸው። ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን አስጀምረናል።

ሚያዝያ 2008፦ በፓፑዋ ኒው ጊኒ ድንበር አቅራቢያ ወደሚገኙ በጣም ሩቅ ወደሆኑት ሦስት ደሴቶች ይኸውም ወደ ዱወርን፣ ሳይባይና ቦይጉ የመሄድ ሐሳብ ነበረን። የአየሩ ንብረት መጥፎ ስለሆነብን ወደ መቢኦግ ደሴት አመራን። መቢኦግ ካለንበት አካባቢ 70 ኪሎ ሜትር ብቻ ርቆ የሚገኝ ደሴት ቢሆንም በየቦታው በሚገኙት በርካታ ዓለቶች ምክንያት ጠመዝማዛ መንገድ የምንሄድ በመሆኑ እዚያ ለመድረስ 140 ኪሎ ሜትር መጓዝ ይኖርብናል።

ጀልባዋ በኃይለኛው ማዕበል የተነሳ ከታይሳንዋይ መርከብ ተገነጠለች። እንደ ግድግዳ በቆመው ማዕበል ውስጥ መርከቧን አዙረን ጀልባዋን አመጣናት። በዚህም ምክንያት በመርከቧ ላይ ከተሳፈሩት ሰዎች መካከል አብዛኞቹ አስመለሳቸው።

በመቢኦግ ደሴት እንድንሰብክ ፈቃድ አገኘን፤ የአካባቢው ሰዎች ሞቅ ያለ አቀባበል ሲያደርጉልን የደረሰብንን መንገላታት ረሳነው። አንዲት ሴት መልእክታችንን ስትሰማ በጣም የተደሰተች ከመሆኑም በላይ በምትሠራበት ቤተ መጻሕፍት ውስጥ ለማስቀመጥ ተጨማሪ ጽሑፎችን ወሰደች።

ከግንቦት እስከ ጥቅምት 2008፦ በአየሩ ንብረት ምክንያት ወደ ደሴቶቹ መጓዝ አልቻልንም። ይህን ጊዜ ባለንበት አካባቢ ለመስበክ፣ ሥራ ለመሥራትና መርከቧን ለመጠገን ተጠቀምንበት።

መርከቧ ከፍተኛ ጥገና ያስፈልጋት ስለነበር ወደ ዋናው ወደብ ወደ ዊፐ ከተጓዝን በኋላ መርከቧን በትልቅ መጎተቻ ተጠቅመን ከውኃ ውስጥ አወጣናት። ሲናገሩት ቀላል ቢመስልም ሥራው ግን በጣም ከባድ ነበር! በአካባቢው ባለው ጉባኤ ውስጥ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች በቧንቧ ጥገና፣ ቀለም በመቀባትና በእንጨት ሥራ በፈቃደኝነት ተካፍለዋል። አንዳንዶች ምግብ ይዘው መጥተዋል። ሌሎች ደግሞ ለሚቀጥለው የስብከት ጉዟችን የሚያስፈልጉንን አንዳንድ ዕቃዎችን ሰጥተውናል። ያሳዩንን የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስና ያደረጉልንን እርዳታ በቃላት መግለጽ ያስቸግረናል።

ታኅሣሥ 2008፦ ድወርን፣ ሳይባይ እና ቦይጉ ወደተባሉ ደሴቶች ለመሄድ ጉዞ ጀመርን። ራዳር በመጠቀም ማዕበሉን ያለፍን ሲሆን አቅጣጫ ጠቋሚ መሣሪያ ተጠቅመን ደግሞ ዓለቶቹን በዘዴ ማለፍ ቻልን። ድወርን ለመድረስ 12 ሰዓት ፈጀብን፤ ደሴቱ እስከ ዛሬ ካየናቸው ደሴቶች ሁሉ በጣም ውብ ነው። ረጃጅሞቹ ዓለታማ ኮረብቶች በደመና ተሸፍነዋል። የድወርን ነዋሪዎች መልእክታችንን በጉጉት ያዳመጡ ሲሆን ወደ ቤት ከተመለስን በኋላ ከእነዚህ ሰዎች ጋር የጀመርነውን የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት በስልክ ለመቀጠል ዝግጅት አደረግን።

ለቲ የተባለች አንዲት የደሴቲቱ ነዋሪ በሆነ መንገድ መጽሔቶቻችን ደርሰዋት ስለነበር ተጨማሪ ጽሑፎች ለማግኘት ኩፖኖችን ልካ ነበር። በአውስትራሊያ የሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ ጽሑፎችን የላከላት ሲሆን ከተቻለ እሷን በአካል እንድናገኛት ለጉባኤያችን ደብዳቤ ጻፈ። በመጨረሻም ለቲን አገኘናት፤ ያላትን መንፈሳዊ ፍላጎት በጥቂቱም ቢሆን ማርካት በመቻላችን ደስ ብሎናል።

በሳይባይ ደሴት ላይ ባለ ሥልጣኑ በደሴቲቱ ውስጥ እንድንሰብክ አልፈቀደልንም። ይሁንና በደሴቲቱ ውስጥ ዘመዶች ያሏቸው የቡድናችን አባላት ሄደው ዘመዶቻቸውን እንዲጠይቋቸውና እንዲያነጋግሯቸው ፈቀደ። በሳይባይ ከመንግሥት ኮንትራት ወስጄ ቤቶችን ቀለም መቀባቴ አንዳንድ ወጪዎቻችንን ለመሸፈን አስችሎኛል።

ታሲ የተባለች አንዲት እህታችን የምትኖረው ከሳይባይ 4 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው በአንዲት የፓፑዋ ኒው ጊኒ መንደር ነበር። ከአውስትራሊያ መንግሥት ጋር በተደረገው ስምምነት መሠረት የፓፑዋ ኒው ጊኒ ነዋሪዎች ሳይባይ ሄደው መነገድ ይችላሉ። ታሲ ከመንደሯ የመጡ በርካታ ሰዎችን ማግኘት ብትችልም ለሁሉም የሚሆን በቂ መጽሔት አልነበራትም። ታሲ የይሖዋ ምሥክር ከሆነች በኋላ የመንደሯን ነዋሪዎች ስታገኝ ይህ የመጀመሪያ ጊዜዋ ነበር። ወደ መርከቡ ተመልሰን በመሄድ አንድ ካርቶን ጽሑፎች አመጣንላት፤ አብዛኞቹ ጽሑፎች የተዘጋጁት ቶክ ፒሰን በሚባል የፓፑዋ ኒው ጊኒ ቋንቋ ነበር። ታሲ ከፓፑዋ ኒው ጊኒ ለመጡ ከ30 የሚበልጡ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ነገረቻቸው፤ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች በካርቶኑ ውስጥ የነበረውን ጽሑፍ አንድም ሳይቀር ወሰዱ። ወደሚኖሩበት መንደር መሄድ የሚቻለው በመርከብ ብቻ ስለነበር ከዚያ ቀደም የይሖዋ ምሥክሮች ወደዚያ አካባቢ ሄደው አያውቁም ነበር።

የመጨረሻዋ ደሴት ወደሆነችው ወደ ቦይጉ መድረስ አስቸጋሪ ነበር። ወደ ባሕር ዳርቻው ለመድረስ 4 ኪሎ ሜትር ሲቀረን የውኃው ጥልቀት 2.5 ሜትር ብቻ ነበር። መርከቧ ደግሞ ከውኃ በታች 1.8 ሜትር ገባ ያለች ነበር። እኔና የቡድኑ አንድ አባል ወደ ደሴቲቱ ለመድረስ የሚያስችል መንገድ ለመፈለግ በጀልባ የሄድን ሲሆን ኃይለኛ ዝናብ እየዘነበ ስለነበር በሰበስን! መንገድ ለማግኘት ሁለት ሰዓት ፈጀብን።

እዚያ ስንደርስ የደሴቲቱ ነዋሪዎች የያዝኩት አቅጣጫ ጠቋሚ መሣሪያ የተሳሳተ መረጃ እንደሰጠኝ ሌላው ቀርቶ የድንበር ጠባቂዎችና ባሕር ኃይሎች እንኳ ወደዚህ አካባቢ እንደማይመጡ በጣም ተገርመው ነገሩኝ። የደሴቲቱ ባለ ሥልጣን በዚያ አካባቢ መስበክ እንደማንችል ነገረን፤ ይሁንና በደሴቲቱ ውስጥ ዘመዶች ያሏቸው የቡድናችን አባላት ሄደው ዘመዶቻቸውን እንዲጠይቋቸውና እንዲሰብኩላቸው ፈቀደ። የባለ ሥልጣኑን ትእዛዝ በማክበር ዘመዶቻቸውን ብቻ ጠየቅን። አንድ ሰው ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? * የተባለውን መጽሐፍ ተቀብሎ ወዲያውኑ ማንበብና በመጽሐፍ ቅዱሱ ጀርባ ጥያቄዎችን መጻፍ ጀመረ። ይህ ሰው ወደ ተርዝዴይ ደሴት በመጣበት ጊዜ አግኝተነው ነበር።

ጥር 2009፦ ለመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን በድጋሚ ለማነጋገር ወደ ሞኧ እና መቢኦግ ወደተባሉ ደሴቶች ተመለስን። በሁለቱም ደሴቶች ሞቅ ያለ አቀባበል ተደረገልን። በሞኧ ደሴት፣ በሴይንት ፖል መንደር ያወያየናቸው በርካታ ሰዎች በሚቀጥለው ይህን ያህል ረጅም ጊዜ እንዳንቆይ ነገሩን። የደሴቲቱ ባለ ሥልጣንም በፈለግነው ጊዜ መጥተን መስበክ እንደምንችል ገለጸልን።

በቶሪስ ስትሪት ሰዎች የሚኖሩባቸው 17 ደሴቶች አሉ። በደሴቶቹ ውስጥ የሚኖረውን እያንዳንዱን ሰው የማነጋገር አጋጣሚ ይኑረን አይኑረን እርግጠኞች አይደለንም። ይሁንና በአውስትራሊያ በስተ ሰሜን ርቀው በሚገኙ ደሴቶች ባለው ጉባኤ ውስጥ ያለነው ክርስቲያኖች ለታላቁ ፈጣሪያችን ለይሖዋ ውዳሴ ለማምጣት አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ለማድረግ ፈቃደኞች ነን።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.17 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

አውስትራሊያ

ዊፐ

ባመገ

ቶሪስ ስትሪት ደሴቶች

ፓፑዋ ኒው ጊኒ

[ምንጭ]

Based on NASA/Visible Earth imagery

[በገጽ 24 እና 25 ላይ የሚገኝ ካርታ]

ባመገ

ተርዝዴይ ደሴት

ሞኧ ደሴት

ዋረበር ደሴት

ፐሩመ ደሴት

መቢኦግ ደሴት

ሳይባይ ደሴት

ድወርን ደሴት

ቦይጉ ደሴት

ፓፑዋ ኒው ጊኒ

[ምንጭ]

Based on NASA/Visible Earth imagery

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ተርዝዴይ ደሴት ላይ ከጀልባ ስንወርድ

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሳይባይ ደሴት ለጥየቃ ስንሄድ

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በቶክ ፒሰን ቋንቋ ምሥራቹ ሲሰበክ