በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክ ምን እያደረገ ነው?

አምላክ ምን እያደረገ ነው?

አምላክ ምን እያደረገ ነው?

“ይሖዋ ሆይ፣ ርቀህ የምትቆመው ለምንድን ነው? በመከራ ጊዜ ራስህን የምትሰውረው ለምንድን ነው?” *መዝሙር 10:1 NW

በዜናዎች ላይ የሚቀርቡ አርዕስተ ዜናዎች የምንኖረው “በመከራ ጊዜ” ውስጥ እንደሆነ ያረጋግጣሉ። ሐዘን ቤታችንን ሲያንኳኳ ይኸውም በግለሰብ ደረጃ ወንጀል ሲደርስብን፣ ከባድ አደጋ ሲያጋጥመን ወይም የምንወደውን ሰው በሞት ስንነጠቅ እንደሚከተለው ብለን እንጠይቅ ይሆናል፦ አምላክ ይህን ነገር ይመለከት ይሆን? የእኛ ጉዳይ ግድ ይሰጠው ይሆን? ለመሆኑስ አምላክ አለ?

ይሁን እንጂ አምላክ አንድ እርምጃ እንዲወስድ የምንጠብቀው የተሳሳተ አስተሳሰብ ይዘን ሊሆን እንደሚችል አስበህ ታውቃለህ? ይህን ሁኔታ በምሳሌ ለመመልከት ያህል፣ አባቱ ወደ ሥራ በመሄዱ ምክንያት በጣም የተናደደን አንድ ትንሽ ልጅ በዓይነ ሕሊናህ ተመልከት። ልጁ አባቱን ስለናፈቀ የአባቱን መምጣት በጉጉት ይጠባበቃል። ልጁ ብቻውን እንደተተወ ይሰማዋል። ቀኑን ሙሉ “አባዬ የት አለ?” እያለ ይጠይቃል።

የልጁ አስተሳሰብ የተሳሳተ እንደሆነ በቀላሉ መገንዘብ እንችላለን። በዚያ ወቅት አባቱ ለመላው ቤተሰብ የሚያስፈልገውን ነገር ለማሟላት እየሠራ ነው። እኛም በተመሳሳይ “አምላክ የት አለ?” ብለን የምንጠይቀው የተሳሳተ አስተሳሰብ ይዘን ሊሆን ይችላል።

ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንዶች አምላክ በደል የሚፈጽሙ ሰዎችን ተከታትሎ ወዲያውኑ የቅጣት እርምጃ እንዲወስድ ይፈልጉ ይሆናል። ሌሎች ደግሞ አምላክን ስጦታ ያድላል ተብሎ እንደሚታሰበው እንደ ገና አባት አድርገው በማሰብ ሥራና የትዳር ጓደኛ እንዲሰጣቸው አልፎ ተርፎም የሎተሪ አሸናፊ እንዲያደርጋቸው ይጠብቃሉ።

ከላይ የተጠቀሰው ዓይነት አመለካከት ያላቸው ሰዎች ‘አምላክ ወዲያውኑ ፍትሕን ካላስፈጸመልን ወይም የጠየቅነውን ነገር ካላሟላልን ለሚደርስብን መከራ ግድ አይሰጠውም ወይም የሚያስፈልገንን ነገር አያውቅም ማለት ነው’ ብለው ያስባሉ። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው አስተሳሰብ ፈጽሞ ከእውነታው የራቀ ነው። አሁን ባለንበት ጊዜ ይሖዋ አምላክ ብዙዎች በሚፈልጉት መንገድ ባይሆንም ለመላው የሰው ዘር ጥቅም የሚያስገኝ ተግባር እያከናወነ ነው።

ታዲያ አምላክ ምን እያደረገ ነው? የዚህን ጥያቄ መልስ ለማግኘት በሰው ልጅ ታሪክ መጀመሪያ ላይ የተፈጸመውን ሰዎች ከአምላክ ጋር የነበራቸው ግንኙነት በእጅጉ እንደተበላሸ የሚገልጸውን ዘገባ መለስ ብለን መመልከታችን አስፈላጊ ነው፤ እርግጥ የተበላሸው ግንኙነት የማይስተካከል አይደለም።

ኃጢአት ያስከተለው ጉዳት

እስቲ ለብዙ ዓመታት ውልቅልቁ ወጥቶ የነበረን አንድ ቤት በዓይነ ሕሊናህ ተመልከት። የዚህ ቤት ጣሪያ የተነቃቀለ ሲሆን በሮቹ ወላልቀዋል፤ እንዲሁም ቤቱ በውጪ በኩል ፈራርሷል። በአንድ ወቅት ይህ ቤት ጥሩ ይዞታ ነበረው፤ አሁን ግን እንደዚያ አይደለም። በቤቱ ላይ ከደረሰው ጉዳት አንጻር ሲታይ ቤቱን ማደስ ቀላል እንዳልሆነ አይካድም፤ ጉዳቱ በአንድ ጀምበር የሚስተካከል አይደለም።

አሁን ደግሞ ሰይጣን የተባለው የማይታይ መንፈሳዊ ፍጡር የዛሬ 6,000 ዓመት ገደማ አዳምና ሔዋን በአምላክ ላይ እንዲያምፁ ባደረገበት ወቅት በሰው ዘር ላይ የደረሰውን ጉዳት አስብ። ይህ ከመከሰቱ በፊት የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ፍጹም ጤንነት ኖሯቸው እነሱም ሆኑ ዘሮቻቸው ለዘላለም የመኖር ተስፋ ነበራቸው። (ዘፍጥረት 1:28) ይሁን እንጂ አዳምና ሔዋን ኃጢአት በሠሩ ጊዜ የመጪውን ትውልድ ሕይወት ያመሰቃቀሉት ያህል ነበር።

ይህ ዓመፅ ያስከተለው ጉዳት በቀላሉ የሚታይ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ “በአንድ ሰው [በአዳም] አማካኝነት ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ፤ በኃጢአትም ምክንያት ሞት መጣ” ይላል። (ሮም 5:12) ኃጢአት ሞት ከማስከተሉም ባሻገር ከፈጣሪያችን ጋር ያለንን ዝምድና አበላሽቶብናል፤ እንዲሁም አካላዊ፣ አእምሯዊና ስሜታዊ ጉዳት አምጥቶብናል። በዚህም ምክንያት ያለንበት ሁኔታ ቀደም ሲል ከጠቀስነው የፈራረሰ ቤት ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ጻድቁ ኢዮብ፣ ሰው “ዘመኑ አጭርና በመከራ የተሞላ ነው” ብሎ በተናገረ ጊዜ ያለንበትን ሁኔታ በትክክል ገልጿል።—ኢዮብ 14:1

ይሁንና አዳምና ሔዋን ኃጢአት ከሠሩ በኋላ አምላክ የሰውን ዘር ጨርሶ ትቶት ይሆን? በፍጹም! እንዲያውም በሰማይ የሚኖረው አባታችን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ለሰው ዘር ጥቅም የሚያስገኝ ተግባር እያከናወነ ነው። አምላክ ለእኛ እያደረገልን ያለውን ነገር በሚገባ ለመረዳት እንድንችል አንድን ቤት ለማደስ መወሰድ ያለባቸውን ሦስት እርምጃዎች እንዲሁም እነዚህ እርምጃዎች አምላክ የሰው ልጆችን ለማደስ ከሚወስዳቸው እርምጃዎች ጋር እንዴት እንደሚዛመዱ እንመልከት።

1 የቤቱ ባለቤት በቤቱ ላይ የደረሰውን ጉዳት በጥንቃቄ ከመረመረ በኋላ ቤቱን ለማደስ ወይም ለማፍረስ መወሰን ይኖርበታል።

ይሖዋ አምላክ፣ በኤደን ዓመፅ ከተፈጸመ በኋላ ወዲያውኑ የሰው ልጆችን ለማደስ ዓላማ እንዳለው ገለጸ። የዓመፁ ቆስቋሽ የነበረውን በዓይን የማይታይ መንፈሳዊ ፍጡር እንዲህ ብሎት ነበር፦ “በአንተና በሴቲቱ፣ በዘርህና በዘሯ መካከል፣ ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፤ አንተም ተረከዙን ትቀጠቅጣለህ።”—ዘፍጥረት 3:15

ይሖዋ እነዚህን ቃላት መናገሩ በኤደን ለተነሳው ዓመፅ ዋና ቆስቋሽ የነበረውን ሰይጣንን ለማጥፋት ቃል መግባቱን ያሳያል። (ሮም 16:20፤ ራእይ 12:9) ከዚህም በተጨማሪ ወደፊት የሚመጣው ‘ዘር’ የሰው ልጆችን ከኃጢአት እንደሚዋጃቸው ትንቢት ተናግሯል። * (1 ዮሐንስ 3:8) ይሖዋ የገባቸው እነዚህ ተስፋዎች አምላክ የፍጥረት ሥራውን የማጥፋት ሳይሆን የማደስ ዓላማ እንዳለው በግልጽ ያሳያሉ። ይሁንና የሰውን ዘር የማደሱ ሥራ ጊዜ ይጠይቃል።

2 አንድ መሐንዲስ ቤቱን የማደሱ ሥራ ምን ነገሮችን እንደሚያካትት ለማሳየት ንድፍ ያዘጋጃል።

ይሖዋ አምላክ እስራኤላውያን የሚመሩባቸውን ሕግጋት የሰጣቸው ከመሆኑም በላይ እሱን የሚያመልኩበትን ቤተ መቅደስ ንድፍ ሰጥቷቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ “እነዚህ ነገሮች ለሚመጡት ነገሮች ጥላ ናቸው” ይላል። (ቆላስይስ 2:17) እነዚህ ነገሮች ልክ እንደ ንድፍ አንድን የላቀ ነገር ያመለክታሉ።

ለምሳሌ ያህል፣ እስራኤላውያን የኃጢአት ይቅርታ ለማግኘት የእንስሳት መሥዋዕት ያቀርቡ ነበር። (ዘሌዋውያን 17:11) ይህ ድርጊት ለሰው ዘር እውነተኛ ስርየት ለማስገኘት ከመቶ ዓመታት በኋላ ለሚቀርበው የላቀ መሥዋዕት ጥላ ነበር። * እስራኤላውያን አምልኮ ያቀርቡበት የነበረው የማደሪያው ድንኳንም ሆነ የቤተ መቅደሱ ንድፍ ወደፊት የሚመጣው መሲሕ መሥዋዕታዊ ሞት ከሚሞትበት ጊዜ አንስቶ ወደ ሰማይ እስከሚያርግበት ጊዜ ድረስ የሚወስዳቸውን እርምጃዎች ያመለክታል።—በገጽ 7 ላይ የሚገኘውን ሠንጠረዥ ተመልከት።

3 ንድፉን ተከትሎ እድሳቱን የሚያከናውን ሰው ይመርጣል።

እስራኤላውያን መሥዋዕት ያቀርቡበት የነበረውን ንድፍ የሚከተለውና የሰው ልጆችን ለመዋጀት ሕይወቱን መሥዋዕት አድርጎ የሚያቀርበው ተስፋ የተደረገበት መሲሕ ኢየሱስ ነበር። መጥምቁ ዮሐንስ ኢየሱስን “የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግደው የአምላክ በግ” በማለት መጥራቱ የተገባ ነው። (ዮሐንስ 1:29) ኢየሱስ የተሰጠውን ተልዕኮ በፈቃደኝነት ተቀብሏል። “ከሰማይ የመጣሁት የእኔን ፈቃድ ሳይሆን የላከኝን ፈቃድ ለማድረግ ነው” በማለት ተናግሯል።—ዮሐንስ 6:38

ኢየሱስ “በብዙዎች ምትክ ነፍሱን ቤዛ አድርጎ [እንዲሰጥ]” ብቻ ሳይሆን ከተከታዮቹ ጋር የመንግሥት ቃል ኪዳን እንዲገባም ጭምር የአምላክ ፈቃድ ነበር። (ማቴዎስ 20:28፤ ሉቃስ 22:29, 30) አምላክ በመንግሥቱ አማካኝነት ለሰው ልጆች ያለውን ዓላማ ከግብ ያደርሳል። ስለ አምላክ መንግሥት የሚናገረው መልእክት፣ አምላክ የምድርን ጉዳዮች ተከታትሎ የሚያስፈጽም መንግሥት በሰማይ እንዳቋቋመ ስለሚገልጽ “ምሥራች” ተብሎ ይጠራል።—ማቴዎስ 24:14፤ ዳንኤል 2:44 *

የእድሳቱ ሥራ ቀጥሏል

ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት ለተከታዮቹ እንዲህ የሚል ትእዛዝ ሰጥቷቸው ነበር፦ “ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ . . . እነሆም እኔ እስከ ሥርዓቱ መደምደሚያ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።”—ማቴዎስ 28:19, 20

በመሆኑም የሰው ልጆች እድሳት በኢየሱስ ሞት የሚያበቃ ነገር አይደለም። የአምላክ መንግሥት የምድርን ጉዳዮች መቆጣጠር እስከሚጀምርበት “እስከ ሥርዓቱ መደምደሚያ ድረስ” ይቀጥላል። ይህ ጊዜ በጣም ቀርቧል። እንዲህ የምንለው ኢየሱስ ‘የሥርዓቱን መደምደሚያ’ አስመልክቶ የተናገረው ምልክት በአሁኑ ጊዜ ፍጻሜውን እያገኘ በመሆኑ ነው። *ማቴዎስ 24:3-14፤ ሉቃስ 21:7-11፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:1-5

በዛሬው ጊዜ በ236 አገሮች የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት ምሥራች እንዲሰበክ የሰጠውን ትእዛዝ እየፈጸሙ ነው። እንዲያውም አሁን እያነበብክ ያለኸው ይህ መጽሔት ስለ አምላክ መንግሥትና መንግሥቱ ስለሚያከናውናቸው ነገሮች ይበልጥ እንድትማር አንተን ለመርዳት ታስቦ የሚዘጋጅ ነው። በእያንዳንዱ የመጠበቂያ ግንብ እትም ገጽ 2 ላይ እንዲህ የሚል ሐሳብ ታገኛለህ፦ “[ይህ] መጽሔት . . . የአምላክ መንግሥት ማለትም በሰማይ ያለው እውን መስተዳድር በቅርቡ ክፋትን ሁሉ በማጥፋት ምድርን ወደ ገነትነት እንደሚለውጥ የሚገልጸውን ምሥራች በማብሰር ሰዎችን ያጽናናል። እኛ የዘላለም ሕይወት እንድናገኝ ሲል በሞተውና በአሁኑ ጊዜ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ በመግዛት ላይ በሚገኘው በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ እምነት እንዲኖረን ያበረታታል።”

እርግጥ ነው፣ በአሁኑ ጊዜም አሸባሪዎች ስለፈጸሙት ጥቃት ወይም ስለ ተፈጥሮ አደጋ ልትሰማ አሊያም አንተ ራስህ አንድ አሳዛኝ ሁኔታ ያጋጥምህ ይሆናል። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስን ስታጠና አምላክ የሰው ልጆችን እንዳልተወ የሚያረጋግጥ ማስረጃ ታገኛለህ። እንዲያውም አምላክ “ከእያንዳንዳችን የራቀ” አይደለም። (የሐዋርያት ሥራ 17:27) አምላክ የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ያበላሹትን ነገር ለማደስ የገባውን ቃል ይፈጽማል።ኢሳይያስ 55:11

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.2 በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ይሖዋ የአምላክ ስም ነው።

^ አን.16 ዘፍጥረት 3:15⁠ን በተመለከተ ዝርዝር ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ወደ ይሖዋ ቅረብ የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 19⁠ን ተመልከት።

^ አን.19 ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 5⁠ን ተመልከት።

^ አን.22 ስለ አምላክ መንግሥት ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 8⁠ን ተመልከት።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሰንጠረዥ/ሥዕሎች]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

‘የእውነተኛው አምሳያ’​—የማደሪያው ድንኳን የሚያመለክተው ነገር

መሠዊያው

አምላክ የኢየሱስን መሥዋዕት ለመቀበል ፈቃደኛ መሆኑን ያመለክታል። —ዕብራውያን 13:10-12

ሊቀ ካህናቱ

ኢየሱስ።—ዕብራውያን 9:11

1 በማስተሰረያ ቀን ሊቀ ካህናቱ ለሕዝቡ ኃጢአት መሥዋዕት ያቀርብ ነበር።—ዘሌዋውያን 16:15, 29-31

1 ኒሳን 14, 33 ዓ.ም. ኢየሱስ ለእኛ ሲል ሕይወቱን መሥዋዕት አድርጎ አቅርቧል።—ዕብራውያን 10:5-10፤ 1 ዮሐንስ 2:1, 2

ቅድስት

ኢየሱስ በመንፈስ የተወለደበትን ሁኔታ ያመለክታል።—ማቴዎስ 3:16, 17፤ ሮም 8:14-17፤ ዕብራውያን 5:4-6

መጋረጃ

ምድራዊውን ሕይወት ከሰማያዊው ሕይወት ያገደውን የኢየሱስን ሥጋዊ አካል ያመለክታል።—1 ቆሮንቶስ 15:44, 50፤ ዕብራውያን 6:19, 20፤ 10:19, 20

2 ሊቀ ካህናቱ፣ በመጋረጃው በኩል አልፎ ከቅድስቱ ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ ይገባል።

2 ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ‘በመጋረጃው በኩል አልፎ’ ወደ ሰማይ በማረግ “ስለ እኛ በአምላክ ፊት ይታይ ዘንድ በቀጥታ ወደ ሰማይ ገብቷል።”—ዕብራውያን 9:24-28

ቅድስተ ቅዱሳን

ሰማይ።—ዕብራውያን 9:24

3 ሊቀ ካህናቱ ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ ከገባ በኋላ የመሥዋዕቱን ደም በቃል ኪዳኑ ታቦት ፊት ይረጫል።—ዘሌዋውያን 16:12-14

3 ኢየሱስ የፈሰሰውን ደሙን ዋጋ በማቅረብ ለኃጢአታችን እውነተኛ ስርየት አስገኝቷል።—ዕብራውያን 9:12, 24፤ 1 ጴጥሮስ 3:21, 22