በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው?

ልጆችን ኃላፊነት የሚሰማቸው እንዲሆኑ አድርጎ ማሳደግ

ልጆችን ኃላፊነት የሚሰማቸው እንዲሆኑ አድርጎ ማሳደግ

ጆርጅ፦ * “ሁልጊዜ ማታ ማታ የሚጠብቀኝ አንድ ሥራ አለ። የአራት ዓመቱ ወንድ ልጄ ማይክል ቤት ውስጥ መጫወቻዎቹን በየቦታው አዝረክርኮ ይተዋል። እሱን ከማስተኛቴ በፊት ያዝረከረከውን እንዲሰበስብ ለማድረግ እጥር ነበር። ይሁንና በዚህ ጊዜ ማይክል መጮህና መነጫነጭ ይጀምራል። አንዳንድ ጊዜ ስለምበሳጭ እኔም እጮህበታለሁ፤ ይሁንና ይህ ሁለታችንም መጥፎ ስሜት እንዲሰማን ከማድረግ በቀር የሚፈይደው ነገር አልነበረም። ወደ መኝታ የምንሄድበት ሰዓት አስደሳች እንዲሆን እፈልጋለሁ። በመሆኑም ያዝረከረከውን እንዲያነሳሳ ከማድረግ ይልቅ እኔው ራሴ መሰብሰብ ጀመርኩ።”

ኤመሊ፦ “ችግሩ የጀመረው የ13 ዓመቷ ሴት ልጄ ጄኒ አስተማሪዋ የሰጠችውን የቤት ሥራ መረዳት ባስቸገራት ጊዜ ነበር። ጄኒ ከትምህርት ቤት ከተመለሰች በኋላ ለአንድ ሰዓት ያህል አለቀሰች። እኔም ያልገባትን ነገር እንድታስረዳት አስተማሪዋን እንድትጠይቅ አበረታትቻት ነበር፤ ይሁን እንጂ ጄኒ አስተማሪዋ ክፉ ስለሆነች እሷን ለማነጋገር ድፍረት እንደሌላት በመግለጽ ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ እንዳልሆነች ነገረችኝ። ወዲያውኑ የመጣልኝ ነገር ቀጥታ ወደ ትምህርት ቤት ሄጄ ለአስተማሪዋ የተሰማኝን ሁሉ መናገር ነበር። ማንም ሰው ልጄን እንዲህ ሊያሳዝናት እንደማይገባ ተሰምቶኝ ነበር!”

አንተስ አንዳንዴ እንደ ጆርጅና ኤመሊ ይሰማሃል? እንደ እነዚህ ወላጆች ሁሉ ብዙዎች ልጃቸው ከአንድ ችግር ጋር ሲታገል ወይም ሲያዝን ዝም ብሎ መመልከት ይከብዳቸዋል። ወላጆች ልጆቻቸውን ከአደጋ ለመጠበቅ መሞከራቸው ተፈጥሯዊ ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ከላይ የተጠቀሱት ሁኔታዎች እነዚህ ወላጆች ልጆቻቸው ኃላፊነት የሚሰማቸው ሆነው እንዲያድጉ ጠቃሚ ትምህርት የሚሰጡበት ጥሩ አጋጣሚ ከፍቶላቸው ነበር። የ4 ዓመትና የ13 ዓመት ልጅ ሊሰጣቸው የሚችለው ትምህርት የተለያየ ሊሆን እንደሚችል እሙን ነው።

ይሁንና እውነቱን ለመናገር ልጃችሁ ለሚያጋጥመው ችግር ሁልጊዜ ከለላ ልትሆኑለት አትችሉም። ውሎ አድሮ ልጁ አባቱንና እናቱን ትቶ “የራሱን የኃላፊነት ሸክም ይሸከማል።” (ገላትያ 6:5፤ ዘፍጥረት 2:24) ወላጆች ልጆቻቸው ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ባሕርይ እንዲያሳዩ፣ አሳቢና ኃላፊነት የሚሰማቸው ሰዎች እንዲሆኑ በማስተማር ራሳቸውን እንዲችሉ ማድረግ አለባቸው። ይህ ደግሞ ቀላል ሥራ አይደለም!

ደስ የሚለው ነገር፣ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር የነበረው ግንኙነት ለወላጆች ግሩም ምሳሌ ይሆናል። እርግጥ ነው፣ ኢየሱስ ልጆች አልነበሩትም። ደቀ መዛሙርቱን የመረጠውና ያሠለጠነው ሥራውን እሱ ከሄደም በኋላ እንዲሠሩት ኃላፊነት ለመስጠት ነበር። (ማቴዎስ 28:19, 20) ኢየሱስ ያከናወነው ነገር እያንዳንዱ ወላጅ ሊደርስበት ከሚፈልገው ግብ ጋር ማለትም ልጆቹን ኃላፊነት የሚሰማቸው እንዲሆኑ አድርጎ ከማሳደግ ጋር ተመሳሳይ ነው። ኢየሱስ ለወላጆች ምሳሌ የሚሆንባቸውን ሦስት መንገዶች ብቻ እንመልከት።

ለልጃችሁ “አርዓያ” ሁኑ።

ኢየሱስ በምድራዊ ሕይወቱ ማብቂያ አካባቢ ለደቀ መዛሙርቱ “እኔ እንዳደረግኩላችሁ እናንተም እንደዚሁ እንድታደርጉ አርዓያ ሆኜላችኋለሁ” ብሏቸው ነበር። (ዮሐንስ 13:15) በተመሳሳይም ወላጆች ኃላፊነት የሚሰማው ሰው መሆን ምን ማለት እንደሆነ ለልጆቻቸው ማስረዳት እንዲሁም ምሳሌ መሆን ያስፈልጋቸዋል።

ራሳችሁን እንዲህ እያላችሁ ጠይቁ፦ ‘ሁልጊዜ ስላለብኝ ኃላፊነት የምሰነዝረው ሐሳብ አዎንታዊ ነው? ለሌሎች ጥቅም ስል በትጋት በመሥራቴ ስለማገኘው እርካታ አወራለሁ? ወይስ ቀላል ኑሮ ያላቸው ከሚመስሉ ሰዎች ጋር ራሴን እያወዳደርኩ እነጫነጫለሁ?’

እርግጥ ነው፣ ማንም ሰው ፍጹም አይደለም። አልፎ አልፎ ሁላችንም ከአቅማችን በላይ የሆነ ሸክም እንደተሸከምን ሆኖ ይሰማናል። ይሁን እንጂ ልጆቻችሁ ኃላፊነት የሚሰማው ሰው መሆን ያለውን ጠቀሜታና ዋጋማነት እንዲገነዘቡ መርዳት የምትችሉበት ከሁሉ የተሻለው መንገድ ምሳሌ በመሆን ሊሆን ይችላል።

እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦ ከተቻለ ልጃችሁን አልፎ አልፎ ወደ ሥራ ቦታችሁ በመውሰድ ቤተሰባችሁን በገንዘብ ለመደገፍ ምን እንደምትሠሩ አሳዩት። የእናንተ እርዳታ የሚያስፈልገው ሰው ካለ ልጃችሁን ይዛችሁት ሂዱ። ከዚያ በኋላ ያንን ኃላፊነት በመወጣታችሁ ያገኛችሁትን ደስታ ተነጋገሩ።—የሐዋርያት ሥራ 20:35

በምትጠብቁት ነገር ረገድ ምክንያታዊ ሁኑ።

ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ እንዲሠሩት ለሚፈልገው ሥራና ኃላፊነት ብቁ እስኪሆኑ ድረስ ጊዜ እንደሚወስድ ተገንዝቦ ነበር። በአንድ ወቅት “ገና ብዙ የምነግራችሁ ነገር አለኝ፤ አሁን ግን ልትሸከሙት አትችሉም” ብሏቸው ነበር። (ዮሐንስ 16:12) ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ሳያሠለጥናቸው ለብቻቸው የሚሠሩት ሥራ የሰጣቸው ጊዜ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ብዙ ነገሮችን እያስተማራቸው ከእነሱ ጋር ሰፋ ያለ ጊዜ ያሳልፍ ነበር። ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱን ብቻቸውን እንዲሄዱ የላካቸው በቂ ችሎታ እንዳላቸው በተሰማው ጊዜ ነበር።

በተመሳሳይም ወላጆች ልጆቻቸው በቂ ችሎታ ሳይኖራቸው ለትልልቅ ሰዎች የሚሰጡ ኃላፊነቶችን እንዲወስዱ መጠበቃቸው ምክንያታዊ አይደለም። ያም ሆኖ ልጆች እያደጉ ሲሄዱ ወላጆች ልጆቻቸው መሥራት ያለባቸውን ሥራና ሊቀበሉት የሚገባውን ኃላፊነት ለይተው ማወቅ ይኖርባቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ወላጆች ልጆቻቸው ንጽሕናቸውን እንዲጠብቁ፣ ክፍላቸውን እንዲያጸዱ፣ ሰዓት እንዲያከብሩና ገንዘብን በአግባቡ እንዲይዙ ሊያሠለጥኗቸው ይገባል። አንድ ልጅ ትምህርት ሲጀምር በትምህርት ቤት የሚሰጠውን የቤት ሥራ የመሥራት ኃላፊነት እንዳለበት እንዲገነዘብ ወላጆች ማሠልጠን ይኖርባቸዋል።

ወላጆች ልጁ የሚሠራውን ሥራ ከመስጠት ያለፈ ነገር ማድረግ ያስፈልጋቸዋል። በተጨማሪም ልጁ የሚሠራው ሥራ ውጤታማ እንዲሆን የሚያደርገውን ጥረት መደገፍ ይኖርባቸዋል። ቀደም ሲል የተጠቀሰው ጆርጅ ልጁ መጫወቻዎቹን እንዲሰበስብ ሲነገረው በጣም የሚበሳጨው ሥራው ከአቅሙ በላይ እንደሆነ ስለሚሰማው መሆኑን ተገነዘበ። ጆርጅ እንዲህ ብሏል፦ “መጫወቻዎቹን እንዲሰበስብ በማይክል ላይ ከመጮህ ይልቅ ሥራውን መሥራት የሚቻልበትን ዘዴ ለማስተማር ሞከርኩ።”

ታዲያ ጆርጅ ያደረገው ምን ነበር? ጆርጅ እንዲህ ብሏል፦ “በመጀመሪያ ማታ ማታ መጫወቻዎቹ መቼ መሰብሰብ እንዳለባቸው ሰዓት መደብኩ። ከዚያም በክፍሉ ውስጥ ከተዝረከረኩት መጫወቻዎች መካከል የተወሰኑትን ከማይክል ጋር መሰብሰብ ጀመርን። በፍጥነት የሚሰበስበው ማን እንደሆነ እንድንወዳደር በማድረግ ሥራውን ወደ ጨዋታ ቀየርኩት። ብዙም ሳይቆይ ይህ ሥራ ከመተኛታችን በፊት ከምናደርጋቸው ልማዶች አንዱ ሆነ። ማይክል መጫወቻዎቹን በፍጥነት ከሰበሰበ ከመተኛቱ በፊት ተጨማሪ ታሪክ እንደማነብለት ቃል እገባለታለሁ። ይሁንና ቶሎ ካልጨረሰ ታሪኩን አሳጥርበታለሁ።”

እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦ በቤት ውስጥ ጥሩ መንፈስ እንዲኖር እያንዳንዱ ልጅ ምን አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚችል ምክንያታዊ ሆናችሁ አስቡ። ‘ልጆቼ ሊሠሩት የሚችሉትን ነገር አሁንም እኔ እየሠራሁላቸው ነው?’ እያላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ። እንዲህ ከሆነ ልጆቻችሁ ሥራውን በራሳቸው መሥራት እንደሚችሉ እርግጠኞች እስክትሆኑ ድረስ አብራችኋቸው ሥሩ። ልጆቹ የተሰጣቸውን ሥራ የሚሠሩበት ሁኔታ ጥሩ ወይም መጥፎ ውጤት ሊያስገኝ እንደሚችል ግልጽ አድርጉላቸው። ከዚያም እንደሚሆን የተናገራችሁትን ቅጣት ፈጽሙት ወይም ጥሩ ከሠሩ የሚያስገኝላቸውን ሽልማት ስጧቸው።

ግልጽ መመሪያ ስጧቸው።

ኢየሱስ እንደማንኛውም ጥሩ አስተማሪ ሁሉ አንድን ነገር ለመማር ከሁሉ የተሻለው መንገድ ያንን ነገር መሥራት እንደሆነ ያውቅ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ብቻቸውን መሄድ እንደሚችሉ በተሰማው ወቅት ‘እሱ ሊሄድበት ወዳሰበው ከተማና ቦታ ሁሉ ቀድመውት እንዲሄዱ ሁለት ሁለት አድርጎ ላካቸው።’ (ሉቃስ 10:1) ይሁን እንጂ ሥራውን በራሳቸው እንዲወጡት አልተዋቸውም። ከዚህ ይልቅ እነሱን ከመላኩ በፊት ግልጽ መመሪያዎችን ሰጥቷቸዋል። (ሉቃስ 10:2-12) ደቀ መዛሙርቱም ተመልሰው ያገኙትን ውጤት ሲነግሩት አመስግኗቸዋል ብሎም አበረታቷቸዋል። (ሉቃስ 10:17-24) በእነሱ ችሎታ እንደሚተማመን የገለጸላቸው ከመሆኑም በላይ አድናቆቱንም ችሯቸዋል።

ልጆቻችሁ ከበድ ያሉ ኃላፊነቶች ሲያጋጥሟቸው ምን ታደርጋላችሁ? ልጆቻችሁ ለብስጭትና ለውድቀት እንዳይዳረጉ ስትሉ ከሚፈሩት ነገር ለማዳን ጥረት ታደርጋላችሁ? በደመ ነፍስ የምትሰጡት ምላሽ ልጃችሁን “ማዳን” ወይም የእሱን ሸክም መሸከም ሊሆን ይችላል።

እስቲ አስቡት፦ ሁልጊዜ ፈጥናችሁ በመድረስ ልጆቻችሁን በሆነ መንገድ “የምታድኗቸው” ከሆነ ለልጆቻችሁ ምን ዓይነት መልእክት እያስተላለፋችሁ ነው? በእነሱ እንደምትተማመኑና ባላቸው ችሎታ ላይ እምነት እንዳላችሁ እየጠቆማችሁ ነው? ወይስ በሁሉም ነገር በእናንተ ላይ መመካት እንዳለባቸውና ራሳቸውን መርዳት እንደማይችሉ ሕፃናት አድርጋችሁ እንደምትመለከቷቸው እያሳያችሁ ነው?

ለምሳሌ ያህል፣ ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ኤመሊ ልጇ ለገጠማት ችግር ምን አደረገች? ጣልቃ ከመግባት ይልቅ ጄኒ ራሷ ከአስተማሪዋ ጋር እንድትነጋገር ወሰነች። ኤመሊና ጄኒ አንድ ላይ በመሆን ጄኒ ትምህርት ቤት ሄዳ ልትጠይቃቸው የሚገቡ ጥያቄዎችን በዝርዝር ጻፉ። ከዚያም አስተማሪዋን መቼ ቀርባ ብታነጋግራት እንደሚሻል ተወያዩ። እንዲያውም አስተማሪዋን እንዴት አድርጋ ማነጋገር እንዳለባት ልምምድ አደረጉ። ኤመሊ እንዲህ ብላለች፦ “ጄኒ አስተማሪዋን ቀርባ ለማነጋገር ድፍረት አገኘች፤ አስተማሪዋም በራሷ ተነሳሽነት እሷን ቀርባ በማነጋገሯ አመሰገነቻት። ጄኒ በራሷ ኩራት የተሰማት ሲሆን እኔም ቢሆን ባደረገችው ነገር ኮርቻለሁ።”

እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦ ልጃችሁ አሁን ያጋጠመውን ተፈታታኝ ሁኔታ በጽሑፍ አስፍሩ። ከዚያም ልጃችሁን “ለማዳን” ሳትሞክሩ የገጠመውን ተፈታታኝ ሁኔታ እንዲቋቋም ለመርዳት ምን ማድረግ እንደምትችሉ ጻፉ። የገጠመውን ተፈታታኝ ሁኔታ ለማሸነፍ ሊወስደው የሚገባውን እርምጃ ከልጃችሁ ጋር ተለማመዱ። በችሎታው እንደምትተማመኑበት ለልጃችሁ ግለጹለት።

ሁልጊዜ ልጆቻችሁን ከችግር ለመከላከል የምትሞክሩ ከሆነ በሕይወታቸው የሚያጋጥሟቸው ተፈታታኝ ሁኔታዎችን ለመቋቋም የሚያስፈልጋቸውን ችሎታ እንዳያዳብሩ እያደረጋችኋቸው ሊሆን ይችላል። ከዚህ ይልቅ ልጆቻችሁን ኃላፊነት የሚሰማቸው ሰዎች አድርጋችሁ ለማሳደግ አሠልጥኗቸው። እንዲህ የምታደርጉ ከሆነ ከሁሉ የላቀ ውድ ስጦታ እየሰጣችኋቸው ነው።

^ አን.3 ስሞቹ ተቀይረዋል።

እንደሚከተለው እያላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ፦

  • ከልጆቼ በምጠብቀው ነገር ረገድ ምክንያታዊ ነኝ?

  • በሚሠሩት ነገር ውጤታማ እንዲሆኑ የሚያስፈልገውን ነገር እነግራቸዋለሁ? እንዲሁም አሳያቸዋለሁ?

  • ልጄን ካበረታታሁት ወይም ካመሰገንኩት ምን ያህል ጊዜ ሆኖኛል?