በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የትዳር ጓደኛቸውን በሞት ያጡ ሰዎች የሚያስፈልጋቸው ምንድን ነው? እንዴትስ ልትረዳቸው ትችላለህ?

የትዳር ጓደኛቸውን በሞት ያጡ ሰዎች የሚያስፈልጋቸው ምንድን ነው? እንዴትስ ልትረዳቸው ትችላለህ?

የትዳር ጓደኛቸውን በሞት ያጡ ሰዎች የሚያስፈልጋቸው ምንድን ነው? እንዴትስ ልትረዳቸው ትችላለህ?

በአንድ አነስተኛ ቤት ውስጥ የምትኖረው ዣን ደብዛዛ ብርሃን ባለው ምግብ ቤቷ ውስጥ በደመ ነፍስ ሳህን እየደረደረች ነው። ደግሞም የሆነ ነገር መቅመስ አለባት። ጠረጴዛው ላይ ሳህን የደረደረችው ለሁለት ሰው መሆኑን በድንገት ስትመለከት . . . ራሷን መቆጣጠር አቅቷት አለቀሰች። ለሁለት ሰው የሚሆን ሳህን የደረደረችው ልማድ ሆኖባት እንጂ ውዱ ባለቤቷ ከሞተ ሁለት ዓመት አልፎታል።

ይህ ሁኔታ ያልደረሰበት ሰው የትዳር ጓደኛን በሞት ማጣት የሚያስከትለው ሐዘን ምን ያህል እንደሚያንገበግብ ፈጽሞ ሊገባው አይችልም። እውነት ነው፣ የሰው አእምሮ ይህን አሳዛኝ እውነታ ወዲያው አይቀበለውም። በረል የተባሉ የ72 ዓመት አረጋዊት የባለቤታቸውን ድንገተኛ ሞት መቀበል ከብዷቸው ነበር። በረል እንዲህ ብለዋል፦ “ሳስበው ሁኔታው እውነት አይመስለኝም። ከዚህ በኋላ ባለቤቴ ተመልሶ በዚህ በር የማይገባ መሆኑን አምኖ መቀበል ይከብደኛል።”

አንዳንድ ሰዎች እግራቸው ወይም እጃቸው ከተቆረጠ በኋላም እንኳ የተቆረጠው አካላቸው በቦታው ያለ ሆኖ ይሰማቸዋል። በተመሳሳይም ሐዘን የደረሰባቸው ሰዎች አንዳንድ ጊዜ በሕይወት የሌለውን የሚወዱትን አጋራቸውን በሕዝብ መካከል ያዩት ይመስላቸዋል ወይም የትዳር ጓደኛቸው አጠገባቸው ያለ ይመስል ከእሱ ጋር ሊያወሩ ይችላሉ።

የትዳር አጋራቸውን በሞት በማጣታቸው ምክንያት የሚሠቃዩ ሰዎች ጓደኞችና የቤተሰብ አባላት ብዙውን ጊዜ እነሱን ለመርዳት ምን ማድረግ እንዳለባቸው ላያውቁ ይችላሉ። አንተስ የሚወደውን የትዳር ጓደኛውን በሞት ያጣ ሰው ታውቃለህ? ታዲያ እንዴት ልትረዳው ትችላለህ? የትዳር ጓደኛቸውን በሞት ያጡ ሰዎችን በሐዘናቸው ወቅት ለመርዳት ምን ነገር ማወቅ አለብህ? ሐዘን የደረሰባቸውን ሰዎች ቀስ በቀስ ደስታቸው እንዲመለስላቸው ልትረዳቸው የምትችለው እንዴት ነው?

ልታደርጋቸው የማይገቡ ነገሮች

የቤተሰብ አባላትና ጓደኞች፣ የሚወዱት ሰው በሐዘን ሲደቆስ ሲያዩ ስለሚጨነቁ ከአሳቢነት ተነሳስተው ይህ ግለሰብ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ እንዳያዝን ይጫኑት ይሆናል። ይሁንና የትዳር ጓደኛቸውን በሞት ባጡ 700 የሚያህሉ ግለሰቦች ላይ ጥናት ያደረገ አንድ ተመራማሪ “ሐዘኑ ይህን ያህል ጊዜ መቆየት አለበት ብሎ ‘ጊዜ መመደብ’ አይቻልም” በማለት ጽፏል። በመሆኑም እንዳያዝኑ ለማከላከል ከመሞከር ይልቅ ሐዘናቸውን እንዲገልጹ ነፃነት ስጣቸው።—ዘፍጥረት 37:34, 35፤ ኢዮብ 10:1

ከቀብር ሥነ ሥርዓቱ ጋር በተያያዘ አስፈላጊውን እርዳታ ማበርከትህ የተገባ ቢሆንም እያንዳንዱን ነገር መቆጣጠር እንዳለብህ ሊሰማህ አይገባም። የትዳር ጓደኛውን በሞት ያጣው የ49 ዓመቱ ፖል እንዲህ ይላል፦ “አስፈላጊውን እርዳታ ያበረከቱልኝ ሰዎች ዝግጅቱን በዋነኝነት እኔ እንድቆጣጠረው ማድረጋቸው ጥሩ ነበር። የባለቤቴ የቀብር ሥነ ሥርዓት በጥሩ ሁኔታ መከናወኑ ለእኔ ትልቅ ነገር ነበር። እሷን ለማክበር ላደርገው የምችለው የመጨረሻው ነገር ይህ እንደሆነ ይሰማኛል።”

እርግጥ ነው፣ አብዛኞቹ ሰዎች የሚደረግላቸውን አንዳንድ እርዳታ ያደንቃሉ። አይሊን የተባሉ የ68 ዓመት መበለት እንዲህ ብለዋል፦ “በወቅቱ አእምሮዬ ስላልተረጋጋ የቀብር ሥነ ሥርዓቱን ማስፈጸምና አንዳንድ ጉዳዮችን ማስጨረስ ለእኔ በጣም ከባድ ነበር። ደስ የሚለው ልጄና ባለቤቱ ረድተውኛል።”

ከዚህም በተጨማሪ ስለሞተው ግለሰብ ለማውራት ወደኋላ አትበል። ቀደም ሲል የተጠቀሱት በረል እንዲህ ብለዋል፦ “ጓደኞቼ በጣም ደግፈውኛል። ይሁንና ብዙዎች ስለ ባለቤቴ ስለ ጆን አንስተው ማውራት እንደማይፈልጉ ተመልክቻለሁ። መፈጠሩን እንኳ የረሱት ይመስላል፤ ይህ ደግሞ ጎድቶኛል።” የትዳር ጓደኛቸውን በሞት ያጡ ሰዎች ስለ ሞተው ሰው በግልጽ መናገር የሚፈልጉበት ጊዜ ይኖራል። የሞተው ግለሰብ የፈጸመው የደግነት ተግባር ወይም አብራችሁ ያደረጋችሁት አንድ የሚያስቅ ታሪክ አለ? ካለ ፈርተህ ዝም አትበል፤ ከዚህ ይልቅ ታሪኩን አንስተህ ለትዳር ጓደኛው አጫውተው። በተናገርከው ነገር እንደተደሰተ ከተሰማህ ስለ ግለሰቡ ታደንቀው የነበረውን ባሕርይ ወይም እሱ መሞቱ ምን ያህል እንዳጎደለህ ንገረው። እንዲህ ማድረግህ በትዳር ጓደኛው ሞት ያዘነው እሱ ብቻ እንዳልሆነ እንዲሰማው ሊያደርግ ይችላል።—ሮም 12:15

በሐዘን ላይ ላለው ሰው የሚያስፈልገውን እርዳታ ስትሰጥ ከመጠን በላይ ምክር እንዳታበዛ ተጠንቀቅ። አንዳንድ ውሳኔዎችን እንዲያደርግ ከማጣደፍ ተቆጠብ። * ከዚህ ይልቅ የማመዛዘን ችሎታህን ተጠቅመህ እንዲህ እያልክ ራስህን ጠይቅ፦ ‘በሕይወቱ ውስጥ ትልቅ ለውጥ ያጋጠመውን ጓደኛዬን ወይም ዘመዴን ለመርዳት የትኞቹን በጎ እርምጃዎች መውሰድ እችላለሁ?’

ልታደርጋቸው የምትችላቸው ነገሮች

የትዳር ጓደኛቸውን በሞት ያጡ ሰዎች በለቅሶው ሰሞን ተግባራዊ እርዳታ ቢያገኙ ደስ እንደሚላቸው እሙን ነው። ምግብ ማዘጋጀት፣ ከሩቅ የመጡ ዘመዶቹን ቤትህ ማሳረፍ ወይም ከሐዘንተኛው ጋር ጊዜ ማሳለፍ ትችል ይሆን?

በተጨማሪም ወንዶችና ሴቶች ሐዘናቸውን የሚገልጹበትና ብቸኝነትን የሚጋፈጡበት መንገድ የተለያየ መሆኑን መገንዘብ ይኖርብሃል። ለምሳሌ ያህል፣ በአንዳንድ የዓለም ክፍሎች የትዳር ጓደኛቸው ከሞቱባቸው ወንዶች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የትዳር ጓደኛቸው ከሞተች በአንድ ዓመት ከስድስት ወር ጊዜ ውስጥ እንደገና ያገባሉ፤ ይህ ሁኔታ ግን በሴቶች ዘንድ የተለመደ አይደለም። ልዩነት እንዲፈጠር ያደረገው ምንድን ነው?

ብዙዎች ካላቸው አስተሳሰብ በተቃራኒ ወንዶች ብዙውን ጊዜ እንደገና የሚያገቡት አካላዊ ፍላጎታቸውን ወይም የፆታ ስሜታቸውን ለማርካት አይደለም። አብዛኞቹ ወንዶች የውስጣቸውን አውጥተው ለሚስቶቻቸው የመንገር ዝንባሌ ስላላቸው የትዳር ጓደኛቸውን በሞት ሲያጡ ብቸኝነት ያጠቃቸዋል። በሌላ በኩል ግን መበለቶች አንዳንድ ጊዜ የባሎቻቸው ጓደኞች ቢረሷቸውም እንኳ ስሜታዊ ድጋፍ ለማግኘት የበኩላቸውን ጥረት ያደርጋሉ። በፍጥነት አዲስ ግንኙነት መመሥረት የራሱ አደጋ ቢኖረውም ሚስቶቻቸው የሞቱባቸው ወንዶች እንደገና ማግባት ከብቸኝነት ለመገላገል ብቸኛው አማራጭ ሆኖ የሚታያቸው ለዚህ ነው። መበለቶች ግን ድጋፍ ለማግኘት ጥረት ማድረጋቸው ብቸኝነት የሚያስከትለውን ሥቃይ በተሻለ መንገድ እንዲቋቋሙ ያስችላቸዋል።

የትዳር ጓደኛውን በሞት ያጣው ጓደኛህ ወይም ዘመድህ ወንድም ይሁን ሴት ይህ ሰው የሚሰማው የብቸኝነት ስሜት ቀለል እንዲልለት ለመርዳት ምን ማድረግ ትችላለህ? የ49 ዓመቷ ሄለን የተባለች መበለት እንዲህ ትላለች፦ “ብዙዎች የመርዳት ፍላጎት አላቸው፤ ግን ቅድሚያውን ወስደው ለመርዳት ጥረት አያደርጉም። ‘ልረዳህ የምችለው ነገር ካለ ንገረኝ’ ሲሉ ብዙ ጊዜ ይሰማሉ። ይሁንና አንድ ሰው መጥቶ ‘ገበያ ልሄድ ነው፤ ከእኔ ጋር መሄድ ትፈልጊያለሽ?’ ቢለኝ በጣም ደስ ይለኛል።” ባለቤቱን በካንሰር በሽታ ያጣው ፖል ሰዎች ሲጋብዙት ደስ የሚለው ለምን እንደሆነ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “አንዳንድ ጊዜ ከሰዎች ጋር መቀላቀልም ሆነ ስለ ሁኔታህ ከእነሱ ጋር ማውራት አትፈልግ ይሆናል። ይሁንና አንድ ምሽት ከሰዎች ጋር ስታሳልፍ ጥሩ ስሜት ስለሚሰማህ ብቸኝነት አይሰማህም። ሰዎች ስለ አንተ ከልባቸው እንደሚያስቡ ስታውቅ ነገሮች ቀለል ይሉልሃል።” *

ራስን በሌሎች ቦታ ማድረግ—የሚደነቅ ባሕርይ

ሄለን ስሜታዊ ድጋፍ ይበልጥ ያስፈለጋት አብዛኞቹ ዘመዶቿ የዕለት ተዕለት ተግባራቸውን ሲጀምሩ እንደሆነ ተናግራለች። “በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ቀናት ውስጥ ጓደኞችህና ቤተሰቦችህ ከአጠገብህ አይጠፉም፤ ይሁንና ከዚያ በኋላ ሁሉም የዘወትር እንቅስቃሴውን ይጀምራል። አንተ ግን እንደዚያ ማድረግ አትችልም” በማለት ተናግራለች። እውነተኛ ጓደኞች ይህን ሐቅ ተገንዝበው ሐዘን ከደረሰበት ሰው ጋር ጊዜ ያሳልፋሉ፤ እንዲሁም ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ይሰጣሉ።

የትዳር ጓደኛቸውን በሞት ያጡ ሰዎች በተለይ የጋብቻ በዓላቸው በሚከበርበት ወይም የትዳር ጓደኛቸው በሞተበት ዕለት አብሯቸው የሚሆን ሰው ያስፈልጋቸው ይሆናል። ቀደም ሲል የተጠቀሱት አይሊን በጋብቻ በዓላቸው ቀን የብቸኝነት ስሜት እንዳያጠቃቸው ልጃቸው እንደሚረዳቸው ተናግረዋል። እንዲህ ብለዋል፦ “ኬቨን የተባለው ልጄ በየዓመቱ በዚያን ዕለት መጥቶ ይዞኝ ይሄዳል። ከእሱ ጋር ምሳ እንበላለን፤ ይህ ዕለት ከልጄ ጋር አብሬ የማሳልፈው ልዩ ቀን ነው።” የትዳር ጓደኛውን በሞት ያጣ የቤተሰብ አባል ወይም ጓደኛ ካለህ አስቸጋሪ የሚሆንበትን ይህን ዕለት ለምን በማስታወሻህ ላይ አትመዘግብም? ከዚያም አንተ ወይም ሌላ ሰው ከእነሱ ጋር እንዲሆን ዝግጅት ማድረግ ትችላለህ።—ምሳሌ 17:17 NW

የትዳር ጓደኛቸውን በሞት ያጡ ሰዎች ራሳቸው የመጽናኛ ምንጭ ሊሆኑ እንደሚችሉ አንዳንዶች ይናገራሉ። የትዳር ጓደኛቸውን በሞት ካጡ ስምንት ዓመት የሆናቸው አኒ ከአንዲት ሌላ መበለት ጋር ያላቸውን ቅርርብ አስመልክተው ሲናገሩ “ቆራጥ አቋም ያላት መሆኑ በጣም ያስገረመኝ ከመሆኑም በላይ ወደፊት እንድገፋ አበረታቶኛል” ብለዋል።

አዎን፣ የትዳር ጓደኛቸውን በሞት ያጡ ሰዎች የተወሰነ ጊዜ ካለፈ በኋላ ለሌሎች የብርታትና የተስፋ ምንጭ ሊሆኑ ይችላሉ። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተጠቅሰው የምናገኛቸው ሁለት መበለቶች ማለትም ወጣቷ ሩትና አማቷ ኑኃሚ እርስ በርስ መረዳዳታቸው ጠቅሟቸዋል። ልብ የሚነካው ይህ ዘገባ እነዚህ ሁለት ሴቶች አንዳቸው ለሌላው አሳቢነት ማሳየታቸው ሐዘናቸውንም ሆነ ያጋጠሟቸውን ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንዲቋቋሙ እንዴት እንደረዳቸው ለማወቅ ያስችላል።—ሩት 1:15-17፤ 3:1፤ 4:14, 15

ለመፈወስ ጊዜ አለው

የትዳር ጓደኛቸውን በሞት ያጡ ሰዎች ሕይወታቸውን በአዲስ መንፈስ መምራት እንዲችሉ በሞት ስለተለያቸው ሰው ብቻ በማሰብ ራሳቸውን እንዳይጥሉ ሚዛናዊ መሆን አለባቸው። ጠቢቡ ንጉሥ ሰለሞን “ለማልቀስ ጊዜ አለው” ብሏል። አክሎም “ለመፈወስም ጊዜ” መኖር እንዳለበት ተናግሯል።—መክብብ 3:3, 4 የ1954 ትርጉም

ከላይ የተገለጸው ፖል ከትዳር ጓደኛው ጋር ያሳለፈውን ጊዜ መርሳት ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሆነ ለማስረዳት አንድ ምሳሌ ተጠቅሟል። እንዲህ ብሏል፦ “እኔና ባለቤቴ ተጠላልፈው እንዳደጉ ሁለት ዛፎች ነበርን። ነገር ግን አንዱ ዛፍ ሞቶ ከቦታው ሲነሳ ሌላኛውን ዛፍ ወልጋዳ ያስመስለዋል። ብቻዬን መሆኔ እንግዳ ነገር ነው።” አንዳንዶች በሞት ለተለያቸው የትዳር ጓደኛቸው ታማኝ ለመሆን ካላቸው ፍላጎት የተነሳ የድሮውን ትዝታ መርሳት አይፈልጉም። ሌሎች ደግሞ አስደሳች በሆኑ እንቅስቃሴዎች መካፈላቸው ሟቹን እንደ መክዳት ሆኖ ስለሚሰማቸው ከሌሎች ጋር ወጣ ብለው መዝናናትም ሆነ ጊዜ ማሳለፍ አይፈልጉም። ታዲያ የትዳር ጓደኛቸውን በሞት ያጡ ሰዎች ቀስ በቀስ ተፈውሰው ወይም ተጽናንተው የራሳቸውን ሕይወት እንዲመሩ መርዳት የሚቻለው እንዴት ነው?

የመጀመሪያው እርምጃ ግለሰቡ ስሜቱን አውጥቶ እንዲናገር መርዳት ሊሆን ይችላል። የትዳር ጓደኛውን በሞት ካጣ ስድስት ዓመት ያለፈው ኸርበርት እንዲህ ብሏል፦ “ቤቴ የመጡ እንግዶች ጸጥ ብለው ተቀምጠው በአእምሮዬ ውስጥ የሚጉላላውን ሐሳብ አውጥቼ ስናገር በጥሞና ሲያዳምጡኝ በጣም ደስ ይለኛል። ብዙ ጊዜ ሰዎች እንዲህ ዓይነት ባሕርይ ካለው ሰው ጋር መሆን ደስ እንደማይላቸው አውቃለሁ፤ ይሁንና ችግሬን ስለሚረዱልኝ አመሰግናቸዋለሁ።” ፖል አዘውትሮ ቅድሚያውን በመውሰድ ስላለበት ሁኔታ የሚጠይቀው አንድ የጎለመሰ ጓደኛው በሚያደርግለት ነገር ልቡ በጣም ተነክቷል። ፖል “ከልብ በመነጨ ስሜት በደግነት የሚያደርግልኝን ነገር አደንቃለሁ፤ ብዙውን ጊዜ እኔም በወቅቱ የተሰማኝን ስሜት አጫውተዋለሁ” በማለት ተናግሯል።—ምሳሌ 18:24

አንድ ሰው እንደ ቁጭት፣ የጥፋተኝነት ስሜት ወይም ንዴት ያሉ የተደበላለቁ ስሜቶችን አውጥቶ መናገሩ የትዳር ጓደኛውን ሞት አምኖ እንዲቀበል ይረዳዋል። ንጉሥ ዳዊት፣ ‘ለመነሳት’ የሚያስችለውን ብርታት ያስገኘለት እንዲሁም ሕፃን ልጁ በእርግጥ መሞቱን አምኖ እንዲቀበል ያስቻለው የቅርብ ወዳጁ ለሆነው ለይሖዋ አምላክ የልቡን ግልጥልጥ አድርጎ መናገሩ ነበር።—2 ሳሙኤል 12:19-23

ሐዘንተኛው መጀመሪያ ላይ በጣም ከባድ ሊሆንበት ቢችልም ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴውን መጀመሩ አስፈላጊ ነው። አንዳንድ ነገሮችን ስታደርግ ለምሳሌ፣ ገበያ ስትወጣ ወይም በእግርህ ስትንሸራሸር ሐዘንተኛው አብሮህ እንዲሄድ ማድረግ ትችል ይሆን? አንዳንድ ሥራዎችን እንዲያግዝህ ልትጠይቀው ትችላለህ? ሐዘን የደረሰባቸው ሰዎች ብቸኝነት እንዳያጠቃቸው መርዳት የሚቻልበት ሌላው መንገድ ይህ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ልጆችህን ከሐዘንተኛዋ ጋር እንዲውሉ ወይም አንድ የምግብ ዓይነት እንዴት እንደሚዘጋጅ እንድታሳይህ ማድረግ ትችላለች? ሐዘንተኛው ቤት ውስጥ አንዳንድ ነገሮችን በመጠገን ሊረዳህ ይችላል? እንዲህ ማድረጋችሁ ሐዘንተኛው አእምሮውን በሚያነቃቃ ሥራ እንዲካፈል የሚያስችለው ከመሆኑም ሌላ ሕይወቱ ዓላማ እንዳለው እንዲሰማው ያደርጋል።

የትዳር ጓደኛውን በሞት ያጣው ግለሰብ ስሜቱን አውጥቶ ለሌሎች መናገሩ ደስታው ቀስ በቀስ እንዲመለስለት ሊያደርግ ብሎም በሕይወቱ ውስጥ አዳዲስ ግቦችን እንዲያወጣ ሊገፋፋው ይችላል። ባሏን በሞት ያጣችውና 44 ዓመት የሆናት ዮኔት የተባለች የልጆች እናት ሁኔታ ይህን ያሳያል። እንዲህ በማለት ተናግራለች፦ “ወደ ወትሮው እንቅስቃሴዬ መመለስ በጣም አስቸጋሪ ነበር! የቤት ውስጥ ሥራዎችን መሥራት፣ ገንዘብን አብቃቅቶ መኖርና ሦስት ልጆችን መንከባከብ ከባድ ነበር።” ይሁንና ዮኔት በጊዜ ሂደት ሕይወቷን በተደራጀ ሁኔታ መምራትና ከልጆቿም ጋር በተሻለ መንገድ ሐሳብ ለሐሳብ መግባባት ችላለች። እንዲሁም የቅርብ ጓደኞቿ የሚያደርጉላትን ድጋፍ መቀበል እንዳለባት ተምራለች።

‘ሕይወት ምንጊዜም ውድ ስጦታ ነው’

ጓደኞችና የቤተሰብ አባላት ውጤታማ እርዳታ ለመስጠት ምክንያታዊ መሆን ያስፈልጋቸዋል። የትዳር ጓደኛቸውን በሞት ያጡ ሰዎች ተስፋቸውና የሚያደርጉት ለውጥ ለወራት አልፎ ተርፎም ለዓመታት ሊዋዥቅ ይችላል። አንዳንድ ጊዜ አንጻራዊ መረጋጋት ይሰማቸዋል፤ በሌላ ጊዜ ደግሞ በመንፈስ ጭንቀት ሊዋጡ ይችላሉ። በእርግጥም ‘የልባቸው ጭንቀት’ ከባድ ሊሆን ይችላል።—1 ነገሥት 8:38, 39

የትዳር ጓደኛውን በሞት ያጣ ሰው ከገሃዱ ዓለም ራሱን እንዳያገልና በብቸኝነት ስሜት እንዳይዋጥ በዚህ የሐዘን ወቅት ደግነት የሚንጸባረቅበት ማበረታቻ ያስፈልገዋል። እንዲህ ያለው ማበረታቻ የትዳር ጓደኛቸውን ያጡ በርካታ ሰዎች አዲስ የሕይወት አቅጣጫ እንዲከተሉ ረድቷቸዋል። ባለቤታቸውን በሞት ያጡትና በአሁኑ ጊዜ በአፍሪካ ውስጥ የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊ ሆነው የሚያገለግሉት ክሎድ የተባሉ የ60 ዓመት ሰው “ሕይወት ምንጊዜም ሌላው ቀርቶ የሚወዱትን የትዳር ጓደኛ በሞት መለየት ከሚያስከትለው ሐዘን በኋላም እንኳ ውድ ስጦታ ነው” በማለት ተናግረዋል።

እርግጥ ነው፣ አንድ ሰው የትዳር ጓደኛውን በሞት ካጣ በኋላ ሕይወቱ እንደ ቀድሞው አይሆንም። ያም ቢሆን የሚወዱትን ሰው በሞት የተነጠቁ ሰዎች ሌሎችን መርዳት የሚችሉበት በርካታ አጋጣሚዎች አሏቸው።—መክብብ 11:7, 8

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.11 በገጽ 12 ላይ የሚገኘውን  “ማስታወሻ ወይስ መተከዣ?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

^ አን.16 ሐዘን ለደረሰበት ሰው ተግባራዊ እርዳታ ለመስጠት የሚያስችል ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን የምትወዱት ሰው ሲሞት የተባለውን ብሮሹር ከገጽ 20 እስከ 25 ተመልከት።

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

እውነተኛ ጓደኞች ሐዘን ከደረሰበት ሰው ጋር ጊዜ ያሳልፋሉ፤ እንዲሁም ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ይሰጣሉ

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

 ማስታወሻ ወይስ መተከዣ?

ከጥቂት ዓመታት በፊት ባለቤቷን ያጣችው ሄለን እንዲህ ብላለች፦ “ባለቤቴ ይጠቀምባቸው የነበሩ ዕቃዎችን አስቀምጫቸዋለሁ። ጊዜ እያለፈ በሄደ መጠን እነዚህ ዕቃዎች ይበልጥ አስደሳች የሆነ ትዝታ እንዲኖረኝ አስችለውኛል። ስሜቴ በጊዜ ሂደት ሊለወጥ ስለሚችል አሁን አንዱንም ዕቃ ቢሆን መጣል አልፈልግም።”

ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ የትዳር ጓደኛውን ከአምስት ዓመት በፊት በሞት ያጣው ክሎድ እንዲህ ይላል፦ “እንደ እኔ እንደ እኔ ከሆነ እሷን ለማስታወስ ትጠቀምባቸው የነበሩትን ዕቃዎች ሰብስቤ ማስቀመጥ አያስፈልገኝም። ዕቃዎቿን በሙሉ ማስወገዴ እውነታውን እንድቀበልና ከሐዘኔ እንድጽናና ረድቶኛል።”

ከላይ ያሉት ሐሳቦች ሰዎች ከሟቾች ዕቃ ጋር በተያያዘ የተለያየ አመለካከት ሊኖራቸው እንደሚችል ያሳያሉ። በመሆኑም ጥበበኛ የሆኑ ጓደኞችና ዘመዶች በዚህ ረገድ የራሳቸውን አመለካከት በሌሎች ላይ ከመጫን ይቆጠባሉ።—ገላትያ 6:2, 5

[በገጽ 9 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

በተለይ የአንተን እርዳታ የሚፈልጉበት የተወሰኑ ቀናት አሉ?

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አብረውህ ወጣ እንዲሉ መጋበዝ እንዳለብህ አትርሳ

[በገጽ 10 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ በምታደርግበት ወይም በምትዝናናበት ወቅት የትዳር ጓደኛቸውን በሞት ያጡ ሰዎች አብረውህ እንዲሆኑ አድርግ