በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋ የሚለው የአምላክ ስም በግብፃውያን ቤተ መቅደስ ውስጥ ተገኘ

ይሖዋ የሚለው የአምላክ ስም በግብፃውያን ቤተ መቅደስ ውስጥ ተገኘ

ይሖዋ የሚለው የአምላክ ስም በግብፃውያን ቤተ መቅደስ ውስጥ ተገኘ

ይሖዋ ወይም ያህዌህ የሚለው መለኮታዊ ስም ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ በሌሎች ቦታዎች መጻፍ የጀመረው ከመቼ አንስቶ ነው? አንዳንድ ምሑራን በ14ኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. እንኳ ይጻፍ እንደነበር አስረግጠው ይናገራሉ። እንዲህ የሚሉት ለምንድን ነው?

ግብፃውያን እስከ 1370 ዓ.ዓ. ገደማ ድረስ በርካታ አገሮችን ድል አድርገው ነበር። በዚያን ጊዜ የነበረው ገዥ ሳልሳዊ ፈርዖን አሜንሆቴፕ (አሚኖፊስ) በአሁኑ ጊዜ ሱዳን ተብላ በምትጠራው ኑቢያ ውስጥ ሶሌብ በሚባል አካባቢ ዕፁብ ድንቅ ቤተ መቅደስ ገንብቶ ነበር። አርኪኦሎጂስቶች ይህን ቤተ መቅደስ በቁፋሮ ያገኙ ሲሆን በቤተ መቅደሱ ውስጥ የይሖዋን ስም የሚወክሉትን የሐወሐ የሚሉት የዕብራይስጥ ፊደላት በግብፃውያን ሥዕላዊ የአጻጻፍ ስልት ተጽፈው አግኝተዋል። ይህ ጽሑፍ የአምላክ ስም ከሚገኝባቸው ነገሮች መካከል እጅግ ጥንታዊ እንደሆነ ከሚታመነው ከታዋቂው የሞዓባውያን ጽላት ከ500 ዓመት በፊት የተጻፈ ነው። የመጽሐፍ ቅዱሱ አምላክ ስም በግብፃውያን ቤተ መቅደስ ውስጥ እንዴት ሊገኝ ቻለ?

“የያሁ ምድር ሻሱ”

ሳልሳዊ ፈርዖን አሜንሆቴፕ ቤተ መቅደሱን የሠራው አሙንራ ለተባለው አምላክ ነው። ከአባይ ወንዝ በስተ ምዕራብ የሚገኘው ይህ ቤተ መቅደስ 120 ሜትር ርዝመት አለው። አሜንሆቴፕ በዚያ ቤተ መቅደስ ከሚገኙ ክፍሎች መካከል በአንዱ ውስጥ የሚገኘውን ዓምድ የታችኛውን ክፍል ለማስጌጥ በቁጥጥር ሥር እንዳደረጋቸው የገለጻቸውን የቦታዎች ስም ዝርዝር በግብፃውያን ሥዕላዊ የአጻጻፍ ስልት ጽፏል። እያንዳንዱ ቦታ በአንድ እስረኛ የተወከለ ሲሆን እስረኛው የአገሩ ወይም የሕዝቡ ስም የተቀረጸበት ጋሻ ይዞ እጁ ወደኋላ ተጠፍሮ ታስሮ ይታያል። በዓምዱ ላይ ከተጻፉት ቦታዎች መካከል ሻሱ ወይም ሹሱ የተባሉ በርካታ ሕዝቦች የሚኖሩባቸው ምድሮች ይገኙበታል። ሻሱ የተባሉት ሕዝቦች እነማን ናቸው?

ሻሱ የሚለው ስም ግብፃውያን በስተ ምሥራቅ ከሚገኘው ድንበራቸው ባሻገር የሚኖሩትን በደዊ የተባሉ የተናቁ ነገዶችን ለመጥራት የሚጠቀሙበት የወል ስም ነው። የሻሱ ምድሮች ደቡባዊ ፓለስቲናን፣ ደቡባዊ ትራንስጆርዳንን እና ሲናን ያካትታሉ። አንዳንድ ተመራማሪዎች የሻሱ እንደሆኑ ተደርገው የተገለጹት ምድሮች በስተ ሰሜን እስከ ሊባኖስና ሶርያ ድረስ ያለውን ምድር ጭምር እንደሚያካትቱ ይናገራሉ። ሶሌብ ውስጥ ንጉሡ በቁጥጥሩ ሥር እንዳደረጋቸው አድርጎ ከዘረዘራቸው ቦታዎች መካከል “ያህዌ በሾሱ ምድር፣” “የያሁ ምድር ሻሱ” ወይም “የሻሱ የሃወ ምድር” ተብሎ በተለያየ መንገድ የሚነበበው ይገኝበታል። ስለ ጥንታዊቷ ግብፅ ሥልጣኔ የሚያጠኑት ዣን ለክላን፣ ሶሌብ ውስጥ በጋሻ ላይ ተቀርጾ የሚገኘው ስም “የሐወሐ ከሚለው የመጽሐፍ ቅዱሱ አምላክ ‘ቴትራግራም’ ጋር ይመሳሰላል” በማለት ተናግረዋል።

አብዛኞቹ ምሑራን በዚህና በሌሎች ተመሳሳይ ቦታዎች ላይ የተገለጸው ያሁ ወይም ያህዌ የሚለው ስም የአንድን ቦታ ወይም አውራጃ ስም የሚያመለክት እንደሆነ ያምናሉ። ሽሙል አሂቱፍ የተባሉ ምሑር፣ ተቀርጾ የተገኘው ጽሑፍ “የእስራኤል አምላክ የሆነው የዬሁ አምላኪዎች ነገድ የተጓዙበትን አካባቢ” እንደሚያመለክት ተናግረዋል። * እኚህ ምሑር የደረሱበት መደምደሚያ ትክክል ከሆነ ይህ የቦታ ስም የጥንቶቹን ሴማውያንን በተመለከተ አካባቢያቸውንም ሆነ አምላካቸውን በአንድ ላይ ከሚገልጹት በርካታ ምሳሌዎች መካከል አንዱ ይሆናል ማለት ነው። ሌላው ምሳሌ ደግሞ የአሦርን ምድርና ዋናውን አምላካቸውን የሚያመለክተው አሱር ነው።

የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑርና አርኪኦሎጂስት የሆኑት ሮላን ደቮ፣ በኑቢያ ቤተ መቅደስ ውስጥ የተገኘውን የተቀረጸ ጽሑፍ አስመልክተው እንዲህ ብለዋል፦ “የእስራኤል የቀድሞ አባቶች ጠንካራ ግንኙነት ባደረጉበት ክልል ውስጥ በሁለተኛው ሺህ አጋማሽ ዓመተ ዓለምም እንኳ ከእስራኤል አምላክ ስም ጋር በጣም የሚመሳሰል የቦታ ወይም የሰው ስም ነበር።”

አሁንም ድረስ ከፍ ተደርጎ የሚታየው ስም

ያህዌ የሚለው ስም በግብፃውያን ሥዕላዊ የአጻጻፍ ስልት ተጽፎ የሚገኘው በሶሌብ፣ ኑቢያ ብቻ አይደለም። በሶሌብ የሚገኘው ዝርዝር ቅጂዎች እንደሆኑ የሚታሰቡት ጽሑፎች በኧማረ ዌስት እና አክሳ በሚገኘው የዳግማዊ ራምሴስ ቤተ መቅደሶች ውስጥ ጭምር ይገኛሉ። ኧማረ በሚገኘው የቦታዎች ዝርዝር ውስጥ የተካተተው “ያህዌ በሾሱ አገር” የሚለው ጽሑፍ የሾሱ ሌሎች አካባቢዎች እንደሆኑ ተደርገው ከሚታሰቡት ከሴይርና ከላባን ጽሑፍ ጋር ይመሳሰላል። መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህን አካባቢዎች ከደቡባዊ ፓለስቲና፣ ከኤዶምና ከሲና ጋር አያይዞ ይገልጻቸዋል። (ዘፍጥረት 36:8፤ ዘዳግም 1:1) እነዚህ አካባቢዎች እስራኤላውያን ወደ ግብፅ ከመሄዳቸው በፊትም ሆነ በኋላ ይሖዋን የሚያውቁ እንዲሁም የሚያመልኩ ሰዎች የኖሩባቸው ቦታዎች ናቸው።—ዘፍጥረት 36:17, 18፤ ዘኍልቍ 13:26

በጥንት ጽሑፎች ውስጥ ከተጠቀሱት የሌሎች አማልክት ስሞች በተቃራኒ ይሖዋ የሚለው የመጽሐፍ ቅዱሱ አምላክ ስም አሁንም ድረስ በስፋት የሚሠራበት ከመሆኑም በላይ በብዙዎች ዘንድ ከፍ ተደርጎ ይታያል። ለምሳሌ ያህል፣ ከ230 በሚበልጡ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ከሰባት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ሰዎች የአምላክን ስም እንዲያውቁ ብቻ ሳይሆን ይሖዋ በሚለው በዚህ ልዩ ስም ወደሚጠራው አምላክ እንዲቀርቡ ለመርዳት ጊዜያቸውን መሥዋዕት ያደርጋሉ።—መዝሙር 83:18 NW፤ ያዕቆብ 4:8

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.7 አንዳንድ ምሑራን ይህ በግብፃውያን ሥዕላዊ የአጻጻፍ ስልት የተጻፈው ጽሑፍ ሻሱ የሚለው ቃል “ያህዌህ የተባለው አምላክ ተከታዮችን” የሚያመለክት መሆኑን ይጠራጠራሉ። ከዚህ ይልቅ በውል የማይታወቀው የዚህ ምድር ስም የአጋጣሚ ጉዳይ ሆኖ ከእስራኤል አምላክ ስም ጋር እንደተመሳሰለ ይሰማቸዋል።

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

የመጽሐፍ ቅዱሱ አምላክ ስም አረማውያን በነበሩት በግብፃውያን ቤተ መቅደስ ውስጥ እንዴት ሊገኝ ቻለ?

[በገጽ  21 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ግብፅ

በሶሌብ የሚገኘው ቤተ መቅደስ

ሱዳን

የአባይ ወንዝ

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከቤተ መቅደሱ ዓምድ ጋር ተመሳስሎ የተሠራ

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሶሌብ፣ ሱዳን የሚገኘው የአሙንራ ቤተ መቅደስ ፍርስራሽ

[ምንጭ]

Ed Scott/Pixtal/age fotostock

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ከጀርባ ያለው ሥዕል፦ Asian and Middle Eastern Division/The New York Public Library/Astor, Lenox and Tilden Foundations