በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ዘመናችን የደረሰበት አስገራሚ ታሪክ

መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ዘመናችን የደረሰበት አስገራሚ ታሪክ

መጽሐፍ ቅዱስ በታሪክ ዘመናት ሁሉ በስፋት በመሰራጨት ረገድ ተወዳዳሪ የለውም፤ እስከ አሁን ድረስ 4.8 ቢሊዮን የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች እንደተሰራጩ ይገመታል። በ2007 ብቻ ከ64,600,000 በላይ ቅጂዎች ታትመዋል። ለማወዳደር ይረዳን ዘንድ በዚህ ዓመት ከፍተኛ ሽያጭ ያገኘውን የልብ ወለድ መጽሐፍ ብንመለከት በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ መጀመሪያ ላይ የታተመው በ12 ሚሊዮን ቅጂዎች ነበር።

መጽሐፍ ቅዱስ በዓለም ላይ በብዛት በመታተም ረገድ ተወዳዳሪ የሌለው መጽሐፍ ከመሆኑ በፊት ብዙ ችግሮችን አልፏል። በታሪክ ዘመናት ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስ እንዳይሰራጭ ታግዷል እንዲሁም ተቃጥሏል፤ በተጨማሪም መጽሐፉን ሲተረጉሙ የተገኙ ሰዎች እንግልት ደርሶባቸዋል ብሎም ተገድለዋል። ያም ቢሆን ግን የመጽሐፍ ቅዱስን ሕልውና አደጋ ላይ የጣለው መጽሐፉን ለማንበብና ከጥፋት ለመታደግ በሚጥሩት ሰዎች ላይ ይደርስ የነበረው ከፍተኛ ስደት አልነበረም፤ ይበልጥ አሳሳቢ የነበረው መጽሐፉ በጊዜ ሂደት አርጅቶ ከጥቅም ውጭ የመሆኑ ነገር ነበር። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ የ66 ትናንሽ መጻሕፍት ስብስብ ሲሆን ከእነዚህ መጻሕፍት ውስጥ እጅግ ጥንታዊ የሆኑት የተጻፉት ወይም የተጠናቀሩት ከ3,000 ከሚበልጡ ዓመታት በፊት ነበር፤ እነዚህን መጻሕፍት የጻፏቸው እስራኤላውያን ነበሩ። በመንፈስ መሪነት የተጻፉትን እነዚህን መልእክቶች መጀመሪያ ላይ የጻፏቸውም ሆነ ከዚያ በኋላ የገለበጧቸው ሰዎች ጽሑፉን ያሰፈሩት እንደ ፓፒረስና ብራና ባሉት በቀላሉ ሊበላሹ የሚችሉ ነገሮች ላይ ነበር። ከመጀመሪያዎቹ ቅጂዎች መካከል እስካሁን የተገኘ የለም። ሆኖም የተወሰኑ አሊያም በዛ ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን የያዙ ከመጀመሪያዎቹ ቅጂዎች የተገለበጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ጥንታዊ ቅጂዎች በቁፋሮ ተገኝተዋል። በቁፋሮ ከተገኙት ከእነዚህ ቅጂዎች አንዱ በከፊል የተገኘው የዮሐንስ ወንጌል ሲሆን ይህ ቅጂ የተዘጋጀው ሐዋርያው ዮሐንስ መጀመሪያ ወንጌሉን ከጻፈ በኋላ ባሉት ጥቂት አሥርተ ዓመታት ውስጥ ነበር።

“ከጥንቶቹ የግሪክና የላቲን ሥነ ጽሑፎች ፍጹም በተለየ መልኩ በዕብራይስጥ በተጻፉት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች [ብሉይ ኪዳን] ውስጥ ያለው ሐሳብ በጣም በሚያስገርም ሁኔታ በትክክል ተላልፏል።”—ፕሮፌሰር ሁልዮ ትሪቦይ ባሬራ

የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች እስከ ዛሬ ድረስ መቆየታቸው አስገራሚ የሆነው ለምንድን ነው? ደግሞስ በዘመናችን የሚገኙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች የመጀመሪያዎቹ ጸሐፊዎች ያሰፈሩትን መልእክት ምን ያህል በትክክል አስተላልፈዋል?

ሌሎች ጥንታዊ ጽሑፎች የት ደረሱ?

በጥንቶቹ እስራኤላውያን ዘመን የኖሩ ሌሎች ብሔራት የጻፏቸው ጽሑፎች የት እንደደረሱ ስናስብ መጽሐፍ ቅዱስ እስከ ዘመናችን መቆየቱ እጅግ የሚያስገርም ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ፊንቄያውያን በመጀመሪያው ሺህ ዓመት (ዓ.ዓ.) የእስራኤላውያን ጎረቤቶች ነበሩ። የባሕር ላይ ንግድ የሚያካሂዱት እነዚህ ሕዝቦች፣ በፊደላት የመጻፍ ስልት በመላው የሜድትራንያን አካባቢ እንዲስፋፋ አድርገዋል። እንዲሁም ፊንቄያውያን ከግብፅና በግሪክ ግዛት ውስጥ ከሚገኙት አገሮች ጋር የፓፒረስ ንግድን በስፋት በማካሄድ ከፍተኛ ትርፍ ያጋብሱ ነበር። ያም ሆኖ ናሽናል ጂኦግራፊክ የተባለው መጽሔት ስለ ፊንቄያውያን ሲገልጽ እንዲህ ይላል፦ “በአብዛኛው፣ በቀላሉ በሚበላሸው በፓፒረስ ላይ የሰፈሩት የፊንቄያውያን ጽሑፎች ከጊዜ ብዛት በመበላሸታቸው በአሁኑ ጊዜ ስለ እነሱ የምናውቀው ነገር በዋነኝነት ጠላቶቻቸው በጻፏቸው የተዛቡ መረጃዎች ላይ የተመሠረተ ነው። ፊንቄያውያን ብዙ የሥነ ጽሑፍ ክምችት እንደነበራቸው የሚነገር ቢሆንም ከረጅም ጊዜ በፊት ሙሉ በሙሉ ጠፍቷል።”

ስለ ጥንቶቹ ግብፃውያን ጽሑፎችስ ምን ማለት ይቻላል? ግብፃውያን ሥዕላዊ የአጻጻፍ ዘዴን ተጠቅመው በቤተ መቅደስ ግድግዳዎችም ሆነ በሌሎች ቦታዎች ላይ ቅርጾችን በመሥራት ወይም በመሳል ረገድ የታወቁ ናቸው። ግብፃውያን ለመጻፊያ የሚያገለግሉ የፓፒረስ ወረቀቶች በመፈልሰፍም ይታወቃሉ። ይሁን እንጂ ስለ ጥንታዊቷ ግብፅ ሥልጣኔ የሚያጠኑት ኬኔዝ አንደርሰን ኪችን የተባሉ ተመራማሪ በፓፒረስ ላይ የተጻፉ የግብፅ ዘገባዎችን በተመለከተ እንዲህ ብለዋል፦ “ከ3000 [ዓ.ዓ.] ገደማ አንስቶ የግሪካውያንና የሮማውያን ዘመን እስከጀመረበት ጊዜ ድረስ በፓፒረስ ላይ ከሰፈሩት ጽሑፎች መካከል 99 በመቶ ያህል የሚሆኑት ሙሉ በሙሉ እንደጠፉ ይገመታል።”

በፓፒረስ ላይ ስለተጻፉት የሮማውያን ጽሑፎችስ ምን ማለት ይቻላል? እስቲ የሚከተለውን ምሳሌ እንመልከት። ሮማን ሚልተሪ ሪከርድስ ኦን ፓፓይረስ የተባለው መጽሐፍ እንደዘገበው የሮም ወታደሮች በዓመት ውስጥ ሦስት ጊዜ ይከፈላቸው የነበረ ይመስላል፤ ክፍያው መከናወኑን ለማሳየት ከፓፒረስ የተሠሩ ሰነዶች ይዘጋጁ ነበር። ከአውግስጦስ የግዛት ዘመን (27 ዓ.ዓ.–14 ዓ.ም.) እስከ ዲዮቅላጢን የግዛት ዘመን ድረስ (284-305 ዓ.ም) ባሉት 300 ዓመታት ውስጥ 225,000,000 ሰነዶች እንደሚኖሩ ይገመታል። ከእነዚህ ሰነዶች መካከል የተረፉት ምን ያህል ናቸው? ሊነበብ በሚችል ሁኔታ ላይ የተገኙት ሁለት ሰነዶች ብቻ ናቸው።

በፓፒረስ ላይ ከተጻፉት ጥንታዊ ሰነዶች መካከል የተረፉት በጣም ጥቂት የሆኑት ለምንድን ነው? እንደ ፓፒረስ እንዲሁም ለመጻፊያነት በሰፊው ይሠራበት እንደነበረው እንደ ብራና ያሉ በቀላሉ የሚበላሹ ነገሮች እርጥበት አዘል በሆነ የአየር ንብረት ውስጥ ለረጅም ጊዜ መቆየት አይችሉም። ዚ አንከር ባይብል ዲክሽነሪ እንዲህ ይላል፦ “የአካባቢው የአየር ንብረት ባለው ተጽዕኖ የተነሳ [በመጀመሪያው ሺህ ዓመት (ዓ.ዓ.)] በፓፒረስ ላይ የተጻፉ መዛግብት ሳይበላሹ ለረጅም ጊዜ መቆየት የሚችሉት ደረቅ በሆነ በረሃማ አካባቢ ከሆኑና በዋሻ ወይም በቤት ውስጥ ከተቀመጡ ብቻ ነው።”

ስለ መጽሐፍ ቅዱስስ ምን ማለት ይቻላል?

ከሁኔታዎቹ ለመረዳት እንደሚቻለው የመጀመሪያዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት የተጻፉት ፊንቄያውያን፣ ግብፃውያንና ሮማውያን እንደተጠቀሙባቸው ባሉ በቀላሉ በሚበላሹ ነገሮች ላይ ነበር። ታዲያ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈረው መልእክት ከመጥፋት ተርፎ በዓለም ላይ ከታተሙት መጻሕፍት ሁሉ ተወዳዳሪ የማይገኝለት ለመሆን የበቃው ለምንድን ነው? ፕሮፌሰር ጄምስ ኩግል እንደገለጹት አንዱ ምክንያት የመጀመሪያዎቹ ቅጂዎች “መጽሐፍ ቅዱስ እየተጻፈ በነበረበት ዘመንም እንኳ በተደጋጋሚ ጊዜ” በመገልበጣቸው ነው። 

በዘመናችን ያሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ከጥንቶቹ ቅጂዎች ጋር ሲወዳደሩ ልዩነት አላቸው? የሙት ባሕር ጥቅልሎች በመባል የሚታወቁትን ጥንታዊ ቅጂዎች እንዲያጠኑና እንዲያሳትሙ ኃላፊነት ከተሰጣቸው ባለሞያዎች አንዱ የሆኑት ፕሮፌሰር ሁልዮ ትሪቦይ ባሬራ እንዲህ ብለዋል፦ “ከጥንቶቹ የግሪክና የላቲን ሥነ ጽሑፎች ፍጹም በተለየ መልኩ በዕብራይስጥ በተጻፉት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ውስጥ ያለው ሐሳብ በጣም በሚያስገርም ሁኔታ በትክክል ተላልፏል።” ፍሬድሪክ ብሩስ የተባሉት ታዋቂ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑር ደግሞ እንዲህ ብለዋል፦ “የአዲስ ኪዳንን [ትክክለኛነት] የሚያሳዩት ማስረጃዎች በጥንት ዘመን የነበሩ ጸሐፊዎች ያዘጋጇቸው በርካታ ጽሑፎች ካሏቸው ማስረጃዎች ጋር ሲወዳደሩ በጣም ብዙ ናቸው፤ ያም ሆኖ የእነዚህን ጽሑፎች ትክክለኛነት ማንም ሰው አይጠራጠርም።” ብሩስ አክለውም እንዲህ ብለዋል፦ “አዲስ ኪዳን የዓለማዊ ጽሑፎች ስብስብ ቢሆን ኖሮ ትክክለኛነቱ ፈጽሞ ጥርጣሬ ውስጥ አይገባም ነበር።” በእርግጥም፣ መጽሐፍ ቅዱስ አስገራሚ መጽሐፍ ነው። ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ለማንበብ ጊዜ ትመድባለህ?—1 ጴጥሮስ 1:24, 25

በእጅ የተጻፉ 6,000 ገደማ የሚሆኑ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት (ብሉይ ኪዳን) ቅጂዎች እንዲሁም 5,000 ገደማ የሚሆኑ የግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት (አዲስ ኪዳን) ቅጂዎች አሁንም ድረስ ይገኛሉ