በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አንድ ስህተት ወደ ሌላ ስህተት ይመራል

አንድ ስህተት ወደ ሌላ ስህተት ይመራል

ሐዋርያው ጳውሎስ በአንደኛው መቶ ዘመን ሁለተኛ አጋማሽ ላይ ይኖሩ ለነበሩ ክርስቲያኖች እንዲህ የሚል ማሳሰቢያ ሰጥቶ ነበር፦ “በክርስቶስ ላይ ሳይሆን በዓለም መሠረታዊ ነገሮች እንዲሁም በሰው ወግ ላይ በተመሠረተ ፍልስፍናና ከንቱ ማታለያ ማንም አጥምዶ እንዳይወስዳችሁ ተጠንቀቁ።”—ቆላስይስ 2:8

ጳውሎስ እንዲህ ያለ ማስጠንቀቂያ ቢሰጥም ከሁለተኛው መቶ ዘመን አጋማሽ ጀምሮ የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች ስለ እምነታቸው ማብራሪያ ለመስጠት የጥንት ፈላስፎችን ጽንሰ ሐሳቦች መጠቀም ጀመሩ። ይህን ያደረጉት ለምን ነበር? በሮም ግዛት ውስጥ በነበሩ የተማሩ ሰዎች ዘንድ ተቀባይነት የማግኘትና በዚህ መንገድ ብዙዎችን ወደ ክርስትና የመለወጥ ሐሳብ ስለነበራቸው ነው።

እንደዚህ ካደረጉት ክርስቲያኖች መካከል በጣም ታዋቂ የነበረው ጀስቲን ማርተር ሲሆን እሱም የአምላክ ቃል አቀባይ የሆነው ኢየሱስ ሰው ሆኖ ወደ ምድር ከመምጣቱ ከረጅም ጊዜ በፊት ለግሪክ ፈላስፎች ራሱን እንደገለጠ ያምን ነበር። ጀስቲንና እንደ እሱ ዓይነት አስተሳሰብ የነበራቸው ሌሎች መምህራን፣ ፍልስፍና እና አፈ ታሪክ ከክርስትና ጋር መቀላቀሉ ይህ ሃይማኖት የሁሉንም የሰው ዘር ፍላጎት የሚያሟላ እንዲሆን ያደርገዋል የሚል አመለካከት ነበራቸው።

ጀስቲን ማርተር ያስፋፋው የክርስትና እምነት ብዙዎች ወደዚህ ሃይማኖት እንዲለወጡ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል። ይሁንና እነዚያ ክርስቲያኖች አንድን የተሳሳተ ትምህርት መቀበላቸው ሌሎች የተሳሳቱ ትምህርቶች እንዲወለዱ ምክንያት ሆኗል፤ እንዲሁም በአሁኑ ጊዜ የክርስትና መሠረተ ትምህርት እንደሆኑ በስፋት የሚታመንባቸው ትምህርቶች እንዲፈጠሩ አድርጓል። ከዚህ ቀጥሎ በቀረቡት የማመሳከሪያ ጽሑፎች ላይ ያለውን ሐሳብ ከትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ጋር ማወዳደርህ እነዚህ ትምህርቶች ምን ያህል የተሳሳቱ እንደሆኑ ለመገንዘብ ያስችልሃል።