በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች የፕሮቴስታንት ሃይማኖት ተከታዮች ናቸው?

የይሖዋ ምሥክሮች የፕሮቴስታንት ሃይማኖት ተከታዮች ናቸው?

አንባቢያን የሚያነሱት ጥያቄ

የይሖዋ ምሥክሮች የፕሮቴስታንት ሃይማኖት ተከታዮች ናቸው?

የይሖዋ ምሥክሮች ራሳቸውን የፕሮቴስታንት ሃይማኖት ተከታይ እንደሆኑ አድርገው አይቆጥሩም። ለምን?

የፕሮቴስታንት ሃይማኖት የጀመረው በ16ኛው መቶ ዘመን በአውሮፓ በሮም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ላይ ተሃድሶ ለማካሄድ በተደረገው ጥረት ነው። “ፕሮቴስታንት” የሚለው መጠሪያ መጀመሪያ ላይ የተሠራበት የማርቲን ሉተር ተከታዮችን ለማመልከት ሲሆን ይህ የሆነው በ1529 በሽፓየር በተደረገው ስብሰባ ላይ ነበር። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ቃሉ፣ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ላይ የተካሄደው ተሃድሶ ያለውን መርሆና ዓላማ የሚከተሉ ሰዎችን በጠቅላላ ለማመልከት ይሠራበት ጀመር። ሚርያም-ዌብስተርስ ኮሊጂየት ዲክሽነሪ፣ 11ኛው እትም ፕሮቴስታንት የሚለውን ቃል ሲፈታው “ጳጳሱ ያላቸውን ዓለም አቀፋዊ የበላይነት ከማይቀበሉ እንዲሁም በአምላክ ፊት መጽደቅ የሚቻለው በእምነት ብቻ እንደሆነ፣ አማኞች ሁሉ ቀሳውስት መሆን እንደሚችሉ እንዲሁም የእውነት ምንጭ መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ እንደሆነ የሚናገረውን የተሃድሶውን ትምህርት ከሚደግፉ በርካታ የእምነት ድርጅቶች በአንዱ ውስጥ አባል የሆነን ግለሰብ” እንደሚያመለክት ገልጿል።

የይሖዋ ምሥክሮች ጳጳሱ ያላቸውን ዓለም አቀፋዊ የበላይነት የማይቀበሉ እንዲሁም የእውነት ምንጭ መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ እንደሆነ ሙሉ በሙሉ የሚስማሙ ቢሆንም ከፕሮቴስታንት ሃይማኖቶች ጋር በርካታ ሰፊ ልዩነቶች አሏቸው። ዚ ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ሪሊጅን የይሖዋ ምሥክሮች “የተለዩ” እንደሆኑ ይገልጻል። የይሖዋ ምሥክሮች የሚለዩባቸውን ሦስት መንገዶች እንመልከት።

አንደኛ፣ የፕሮቴስታንት ሃይማኖቶች በካቶሊክ ውስጥ ያሉትን አንዳንድ እምነቶች ባይቀበሉም እንደ ሥላሴ፣ ገሃነመ እሳትና የሰው ነፍስ አትሞትም እንደሚሉት ያሉ የካቶሊክ ትምህርቶችን ይቀበላሉ። የይሖዋ ምሥክሮች ግን እንዲህ ያሉት መሠረተ ትምህርቶች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር እንደሚጋጩ ብቻ ሳይሆን ሰዎች ስለ አምላክ የተሳሳተ አመለካከት እንዲያድርባቸው የሚያደርጉ እንደሆኑ ያምናሉ።—ገጽ 4-7⁠ን ተመልከት።

ሁለተኛ፣ የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖት ዓላማው አንድን ቤተ ክርስቲያን መቃወም ሳይሆን ጠቃሚ ነገሮችን ማስተማር ነው። የይሖዋ ምሥክሮች የሚከተለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር በቁም ነገር ይመለከቱታል፦ “የጌታም አገልጋይ ሊጣላ አይገባውም፤ ይልቁን ለሰው ሁሉ ገር፣ ለማስተማር ብቃት ያለው፣ ትዕግሥተኛም መሆን ይገባዋል፤ . . . የሚቃወሙትን በየዋህነት የሚያቃና መሆን ይኖርበታል።” (2 ጢሞቴዎስ 2:24, 25 አ.መ.ት) እርግጥ ነው፣ የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስ በሚያስተምረውና በርካታ ሃይማኖታዊ ቡድኖች በሚያስተምሩት ትምህርት መካከል ያሉት ልዩነቶች ለሰዎች ግልጽ እንዲሆኑ ያደርጋሉ። ይህን የሚያደርጉበት ዓላማ ግን በሌሎች ሃይማኖታዊ ድርጅቶች ውስጥ ተሃድሶ ለማካሄድ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ዓላማቸው ቅን ልብ ያላቸው ግለሰቦች ስለ አምላክና ስለ ቃሉ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ መርዳት ነው። (ቆላስይስ 1:9, 10) የሌላ እምነት ተከታይ የሆኑ ሰዎች ማብቂያ የሌለው ንትርክ የሚፈጥሩ ከሆነ የይሖዋ ምሥክሮች ፍሬ ቢስ ከሆነ ክርክር ይርቃሉ።—2 ጢሞቴዎስ 2:23

ሦስተኛ፣ በመቶዎች በሚቆጠሩ የእምነት ድርጅቶች ከተከፋፈለው የፕሮቴስታንት ሃይማኖት በተለየ መልኩ የይሖዋ ምሥክሮች አንድነት ያለው ዓለም አቀፋዊ የወንድማማች ኅብረት አላቸው። በ230 አገሮች የሚኖሩት የይሖዋ ምሥክሮች የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረተ ትምህርቶች በተመለከተ ሐዋርያው ጳውሎስ ‘ንግግራችሁ አንድ ይሁን’ በማለት የሰጠውን ምክር ይከተላሉ። በመካከላቸው መከፋፈል የለም። ከዚህ ይልቅ “በአስተሳሰብም ሆነ በዓላማ ፍጹም አንድነት” እንዲኖራቸው ከልብ ይጥራሉ። (1 ቆሮንቶስ 1:10) ከእምነት ባልንጀሮቻቸው ጋር “አንድ ላይ በሚያስተሳስረው የሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ” ጥረት ያደርጋሉ።—ኤፌሶን 4:3