በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምሥራቹ በ500 ቋንቋዎች

ምሥራቹ በ500 ቋንቋዎች

ምሥራቹ በ500 ቋንቋዎች

በሩዋንዳ ተደርጎ በነበረው የእርስ በርስ ጦርነት ወቅት አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ተርጓሚዎች ቤት ንብረታቸውን ጥለው ሸሹ። ይሁን እንጂ በዚህ ወቅት ላፕቶፕ ኮምፒውተሮቻቸውን ይዘው ማምለጥ ችለው ነበር፤ ከዚያም እነዚህን ኮምፒውተሮች በመያዝ ወደ ስደተኞች ካምፕ ገቡ። ኮምፒውተሮቻቸውን ይዘው የሸሹት ለምን ነበር? ይህን ያደረጉት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን በኪንያሩዋንዳ ቋንቋ የመተርጎም ሥራቸውን መቀጠል እንዲችሉ ነበር።

በደቡባዊ ምሥራቅ እስያ የምትኖር አንዲት ወጣት፣ የሚሰማትን ድካምና የአየሩን ሙቀት እንዲሁም በየጊዜው የሚከሰተው የኤሌክትሪክ መቋረጥ በትርጉም ሥራዋ ላይ የሚፈጥረውን ጫና ተቋቁማ በውድቅት ሌሊት ኮምፒውተሯ ላይ እየጻፈች ነው። ይህች ወጣት ይህን የምታደርገው ለምንድን ነው? የምትተረጉመው ጽሑፍ የሚታተምበት ቀን ከማለፉ በፊት ለማድረስ ነው።

እነዚህ ተርጓሚዎች በዓለም ዙሪያ ከ190 በላይ በሆኑ ቦታዎች የሚሠራ 2,300 የሚሆኑ አባላት ያሉት የፈቃደኛ ሠራተኞች ሠራዊት ክፍል ናቸው። እነዚህ ፈቃደኛ ሠራተኞች ከ20 እስከ 90 በሚጠጋ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሲሆን ሰዎች በ500 ቋንቋዎች ከሚዘጋጀው የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ማጽናኛ ማግኘት እንዲችሉ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ይሠራሉ።—ራእይ 7:9

በበርካታ ቋንቋዎች ጽሑፎችን ማዘጋጀት

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የይሖዋ ምሥክሮች የትርጉም ሥራ ታይቶ በማይታወቅ መጠን እድገት አሳይቷል። ለምሳሌ በ1985 መጠበቂያ ግንብ በ23 ቋንቋዎች በተመሳሳይ ጊዜ ይታተም የነበረ ሲሆን ይህ በወቅቱ አስደናቂ ሥራ ነበር። በዛሬው ጊዜ መጠበቂያ ግንብ በ176 ቋንቋዎች ይታተማል፤ ይህ መጽሔት በእነዚህ ሁሉ ቋንቋዎች በተመሳሳይ ጊዜ የሚታተም ሲሆን ይህም በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ሰዎች በአንድ ወቅት አንድ ዓይነት ትምህርት እንዲያገኙ አስችሏቸዋል።

መጠበቂያ ግንብ ከሚታተምባቸው ቋንቋዎች ውስጥ ወደ 50 የሚሆኑት በሚነገርባቸው አካባቢዎች ከመጠበቂያ ግንብ ውጪ በቋሚነት የሚታተም ሌላ መጽሔት የለም። ለምን? የንግድ ማተሚያ ቤቶች በአገራቸው በሚነገሩ የተለያዩ ቋንቋዎች ጽሑፎችን ለማዘጋጀት የሚገፋፋቸው ነገር የለም። በዓለም ዙሪያ የሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች ግን በንብረታቸው የሌሎችን ጉድለት ለመሸፈን ሲሉ በፈቃደኝነት መዋጮ ያደርጋሉ፤ ይህ መዋጮ የአምላክ ቃል እንዲሁም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎች ሰዎች በሚያስፈልጋቸው ቦታ ሁሉ እንዲዳረስ ይረዳል።—2 ቆሮንቶስ 8:14

ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት በራሳቸው ቋንቋ ሲሰሙ በጣም ደስ ይላቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በኒካራጓ ውስጥ 200,000 ያህል ተናጋሪዎች ባሉት በሚስኪቶ ቋንቋ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎች በቅርቡ መዘጋጀት ጀምረዋል። አንዲት ሴት የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ * የተባለውን ጽሑፍ በሚስኪቶ ቋንቋ ለማግኘት ጠይቃ ነበር፤ መጽሐፉ ሲደርሳት የአካባቢው ፓስተር አብሯት ነበር። ፓስተሩ ይህንን የሚያምር መጽሐፍ ሲመለከት ለራሱ ሊወስደው ፈለገ። ይህ ፓስተር በመጽሐፉ ምትክ 20 ኪሎ ግራም ቡና እንደሚሰጣት ቢነግራትም ሴትየዋ መጽሐፉን ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነችም!

ባለፉት አሥር ዓመታት ሜክሲኮ ውስጥ ማያን፣ ናዋትልንና ጾጺልን ጨምሮ የአገሬው ተወላጆች በሚናገሯቸው ወደ 15 ገደማ በሚሆኑ ቋንቋዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎች ተተርጉመዋል። አሥር ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በዚህች አገር ያሉት የአገሬው ተወላጆች በሚናገሯቸው ቋንቋዎችና በምልክት ቋንቋ የሚመሩ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ከ72 ተነስተው ከ1,200 በላይ ሆነዋል። የይሖዋ ምሥክሮች የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት በሰዎች ልብ ውስጥ ለመትከል ቢጥሩም የእውነትን ዘር የሚያሳድገው አምላክ እንደሆነ ይገነዘባሉ።—1 ቆሮንቶስ 3:5-7

ዘመናዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም በ80 ቋንቋዎች

በቅርብ ዓመታት ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች አዲስ ዓለም የቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉም የተባለውን መጽሐፍ ቅዱስ በሙሉም ሆነ በከፊል በ80 ቋንቋዎች ለማዘጋጀት በትጋት ሲሠሩ ነበር። ሰዎች ይህ መጽሐፍ ቅዱስ በቋንቋቸው በመዘጋጀቱ ምን ተሰምቷቸዋል? በደቡብ አፍሪካ የሚኖር አንድ የይሖዋ ምሥክር በጽዋና ቋንቋ የተተረጎመውን መጽሐፍ ቅዱስ በተመለከተ እንዲህ ብሏል፦ “ይህ መጽሐፍ ቅዱስ ግሩም መሣሪያ ነው። የአምላክን ቃል ይበልጥ እንድረዳውና ከፍ አድርጌ እንድመለከተው ይረዳኛል። የተተረጎመው ለማንበብ በማይከብድና ደስ በሚል መንገድ ነው።” በሞዛምቢክ የሚኖር የጾንጋ ቋንቋ ተናጋሪ የሆነ አንድ ሰው እንዲህ ብሏል፦ “በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ በርካታ ጽሑፎች ቢኖሩንም መጽሐፍ ቅዱስ ከሌለን ሁኔታው ልክ ነጎድጓድና መብረቅ ኖሮ ዝናብ ባይዘንብ እንደማለት ነው! ሆኖም በጾንጋ ቋንቋ አዲስ ዓለም ትርጉም በወጣ ጊዜ ዝናብ የዘነበ ያህል ነበር።”

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ምሥራች የሚተረጉሙትና የሚያሠራጩት ሰዎች ጥንት የተነገረ አንድ ትንቢት አስገራሚ በሆነ መንገድ እንዲፈጸም እያደረጉ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ “ይህ የመንግሥቱ ምሥራች ለሕዝቦች ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል” ብሎ ነበር።—ማቴዎስ 24:14

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.8 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

አዲስ ዓለም ትርጉም

በሙሉ ወይም በከፊል የተተረጎመባቸው ቋንቋዎች

1950 1*

1970 7*

1990 13*

2000 36*

2010 80*

ሌሎች ጽሑፎች

1950 88*

1960 125*

1970 165*

1980 190*

1990 200*

2010 500*

*የቋንቋዎች ብዛት

[በገጽ 24, 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን በ500 ቋንቋዎች የሚተረጉሙ 2,300 የሚሆኑ ፈቃደኛ ሠራተኞች አሉ

ቤኒን

ስሎቬኒያ

ኢትዮጵያ

ብሪታንያ