በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

አደገኛ ዕፆችን ይወስድ እንዲሁም ሞተር ብስክሌት መንዳትና ስፖርት ይወድ የነበረ ሰው በሙሉ ጊዜው አምላክን ለማገልገል የመረጠው ለምንድን ነው? ቁማር በመጫወት ይተዳደር የነበረ ሰው ከዚህ ሱስ ተላቅቆ የሚያስከብር ሥራ በመሥራት ቤተሰቡን ማስተዳደር እንዲጀምር ያነሳሳው ምንድን ነው? በይሖዋ ምሥክር ቤተሰብ ውስጥ ብታድግም የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች መከተሏን አቁማ የነበረች አንዲት ወጣት አኗኗሯን መለስ ብላ እንድትገመግም ያደረጋት ምንድን ነው? እስቲ እነዚህ ሰዎች የሚሉትን እንስማ።

አጭር የሕይወት ታሪክ

ስም፦ ቴረንስ ኦብራየን

ዕድሜ፦ 57

አገር፦ አውስትራሊያ

የኋላ ታሪክ፦ አደገኛ ዕፅ ይወስድ እንዲሁም ሞተር ብስክሌት መንዳት ይወድ የነበረ

የቀድሞ ሕይወቴ፦ የልጅነት ሕይወቴን ያሳለፍኩት የኩዊንስላንድ ግዛት ዋና ከተማ በሆነችውና እንቅስቃሴ በሚበዛባት በብሪዝበን ነበር። ቤተሰቦቼ ካቶሊኮች ነበሩ፤ ሆኖም ስምንት ዓመት ሲሆነኝ ቤተ ክርስቲያን መሄድ አቆምን፤ ከዚያ በኋላም ስለ ሃይማኖት ተወያይተን አናውቅም። አሥር ዓመት ሲሆነኝ ቤተሰባችን አውስትራሊያ ውስጥ ወደሚገኘው ጎልድ ኮስት የተባለ ከተማ ተዛወረ። የምንኖረው በባሕር ዳርቻ አጠገብ ስለነበር በአሥራዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ አካባቢ እያለሁ ጊዜዬን የማሳልፈው በመዋኘትና በውኃ ላይ ሸርተቴ በመጫወት ነበር።

ያም ሆኖ በልጅነቴ ደስተኛ አልነበርኩም። የስምንት ዓመት ልጅ እያለሁ አባቴ ጥሎን ሄደ። እናቴ በድጋሚ ያገባች ሲሆን የአልኮል መጠጦችን መጠጣትና መጨቃጨቅ በቤተሰባችን ውስጥ የተለመደ ነገር ነበር። በወላጆቼ መካከል ከፍተኛ ጭቅጭቅ ተፈጥሮ በነበረበት አንድ ምሽት፣ ወደፊት ሚስት ካገባሁ ከባለቤቴ ጋር በፍጹም እንደማልጨቃጨቅ አልጋዬ ላይ ቁጭ ብዬ ቃል ገባሁ። በቤተሰባችን ውስጥ እንዲህ ዓይነት ችግሮች ቢኖሩም እናቴ፣ የእንጀራ አባቴ እንዲሁም እኛ ስድስት ልጆች እንቀራረብ ነበር።

በአሥራዎቹ ዕድሜ መጨረሻ ላይ እያለሁ አብዛኞቹ እኩዮቼ ዓመፀኞች ሆኑ። ማሪዋና እና ሌሎች ዕፆችን ይወስዱ፣ ትንባሆ ያጨሱ እንዲሁም አልኮል ከመጠን በላይ ይጠጡ ነበር። እኔም እንደ እኩዮቼ ግዴለሽነት የተንጸባረቀበት እንዲህ ዓይነት ሕይወት መምራት ጀመርኩ። ሞተር ብስክሌት መንዳትም ያስደስተኝ ነበር። በተደጋጋሚ ጊዜያት ከባድ አደጋ ቢደርስብኝም ለሞተር ብስክሌት ያለኝ ፍቅር አልቀነሰም፤ እንዲያውም መላውን አውስትራሊያ በሞተር ብስክሌት ለመዞር ወሰንኩ።

የፈለግኩትን ለማድረግ ነፃነት ቢኖረኝም የዓለምን ሁኔታ ስመለከት እንዲሁም አብዛኞቹ ሰዎች በሰው ልጆች ላይ እየደረሱ ስላሉት ችግሮች ግድ እንደሌላቸው ሳስብ ብዙ ጊዜ እጨነቅ ነበር። ስለ አምላክ፣ ስለ ሃይማኖትና በዓለም ላይ ስላሉት ሁኔታዎች እውነቱን ለማወቅ እጓጓ ነበር። ይሁን እንጂ ያሉኝን ጥያቄዎች ለሁለት የካቶሊክ ቀሳውስት ሳቀርብ የሰጡኝ መልስ እንደጠበቅሁት ባለመሆኑ ግራ ተጋባሁ። ከተለያዩ የፕሮቴስታንት አገልጋዮች ጋር በተመሳሳይ ርዕሶች ላይ ውይይት ባደርግም እነሱም የሰጡኝ መልስ አላረካኝም። ከዚያም አንድ ጓደኛዬ ኤዲ ከተባለ የይሖዋ ምሥክር ጋር እንድገናኝ ዝግጅት አደረገ። ከኤዲ ጋር አራት ጊዜ የተወያየን ሲሆን በእያንዳንዱ ውይይት ላይ ላሉኝ ጥያቄዎች መልስ የሰጠኝ ከመጽሐፍ ቅዱስ ነበር። ገና በመጀመሪያው ውይይታችን ወቅት የተለየ ነገር እንዳገኘሁ ታውቆኝ ነበር። ይሁን እንጂ በዚያ ወቅት በማንኛውም መልኩ አኗኗሬን መለወጥ አስፈላጊ ሆኖ አልታየኝም።

መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው? አውስትራሊያን በምዞርበት ወቅት በጉዞዬ ላይ ካገኘሁት ሌላ የይሖዋ ምሥክር ጋር ተወያይቼ ነበር። ሆኖም ወደ ኩዊንስላንድ ከተመለስኩ በኋላ ለስድስት ወራት ያህል ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር አልተገናኘሁም።

አንድ ቀን ከሥራ ወደ ቤቴ ስመለስ ጥሩ አለባበስ ያላቸውና ቦርሳ የያዙ ሁለት ወንዶች መንገድ ላይ ተመለከትኩ፤ የይሖዋ ምሥክሮች እንደሆኑ ስለገመትኩ ሄጄ አነጋገርኳቸው። ሰዎቹ እንደገመትኩት የይሖዋ ምሥክሮች መሆናቸውን ስረዳ መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያስጠኑኝ ጠየቅኳቸው። ጊዜ ሳላጠፋ የይሖዋ ምሥክሮች ወደሚያደርጓቸው ስብሰባዎች መሄድ የጀመርኩ ሲሆን እንዲያውም በ1973 በሲድኒ በተደረገው ትልቅ ስብሰባ ላይ ተገኘሁ። ይሁንና ቤተሰቤ በተለይም እናቴ ምን እያደረግሁ እንደሆነ ሲያውቁ በጣም ተበሳጩ። በዚህና በሌሎች ምክንያቶች የተነሳ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መገናኘቴን አቆምኩ። ለአንድ ዓመት ያህል በጣም በምወደው የክሪኬት ጨዋታ ተጠምጄ ነበር።

ውሎ አድሮ ግን በሕይወቴ ውስጥ እውነተኛ ደስታ ያገኘሁት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን በማጠናበት ወቅት ብቻ እንደነበር ተገነዘብኩ። እንደገና ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር በመገናኘት ወደ ስብሰባዎች መሄድ ጀመርኩ። በተጨማሪም ዕፅ ከሚወስዱ ጓደኞቼ ጋር የነበረኝን ግንኙነት አቋረጥኩ።

በሕይወቴ ውስጥ እነዚህን ለውጦች እንዳደርግ ይበልጥ የረዳኝ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለሚገኘው ኢዮብ የተባለ ሰው የተማርኩት ነገር ነው። ቢል የተባለ ደግ ሆኖም ጥብቅ የሆነ በዕድሜ የገፋ የይሖዋ ምሥክር በቋሚነት መጽሐፍ ቅዱስን ያወያየኝ ነበር። የኢዮብን ታሪክ ካጠናን በኋላ ቢል፣ ‘ሰይጣን፣ በሙሉ ልብ አምላክን እንደማያገለግል በመግለጽ ከኢዮብ ሌላ ማንን የከሰሰ ይመስልሃል?’ በማለት ጠየቀኝ። (ኢዮብ 2:3-5) እኔም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱትን የማውቃቸውን ሰዎች በሙሉ ስጠቅስለት ቢል በትዕግሥት ካዳመጠኝ በኋላ “አዎን፣ እነሱንም ከስሷቸዋል” በማለት መለሰልኝ። ከዚያም ፊት ለፊት እየተመለከተኝ “ሰይጣን በአንተም ላይ ተመሳሳይ ክስ ሰንዝሯል!” አለኝ። በዚህ ጊዜ ክው ብዬ ቀረሁ። ከዚያ በፊት የማጠናቸው መሠረታዊ ትምህርቶች እውነት እንደሆኑ አውቄ ነበር። በዚያን ዕለት ግን የተማርኩትን ነገር በተግባር ማዋል ያለብኝ ለምን እንደሆነ ተገነዘብኩ። ከአራት ወር በኋላ ተጠምቄ የይሖዋ ምሥክር ሆንኩ።

ያገኘሁት ጥቅም፦ የመጽሐፍ ቅዱስን መሥፈርቶች ተግባራዊ ባላደርግ ኖሮ አሁን ሕይወቴ ምን ይመስል እንደነበር ሳስብ ይዘገንነኛል። በሕይወት እንደማልኖር የታወቀ ነው። አብዛኞቹ የቀድሞ ጓደኞቼ ዕፅ ወይም አልኮል ከመውሰድ ጋር በተያያዘ ሕይወታቸውን አጥተዋል፤ በትዳራቸውም ደስተኛ አልነበሩም። የእኔም ሕይወት ቢሆን ከዚህ የተለየ ሊሆን እንደማይችል አስባለሁ።

በአሁኑ ጊዜ ባለትዳር ስሆን እኔና ባለቤቴ ማርጋሬት አውስትራሊያ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ እያገለገልን ነው። ከቤተሰቦቼ መካከል አንዳቸውም ቢሆን ይሖዋን አያመልኩም። ሆኖም ባለፉት ዓመታት እኔና ማርጋሬት ነጠላ የሆኑና ያገቡ የተለያዩ ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠናን ሲሆን እነሱም እንደ እኔ በሕይወታቸው ውስጥ ለውጥ አድርገዋል። በዚህ መሃል በርካታ ግሩም ወዳጆች አፍርተናል። ከዚህም በተጨማሪ በይሖዋ ምሥክሮች ቤተሰብ ውስጥ ያደገችው ማርጋሬት ከ40 ዓመታት ገደማ በፊት የገባሁትን ቃል እንድጠብቅ ረድታኛለች። ከ25 ለሚበልጡ ዓመታት አስደሳች የትዳር ሕይወት አሳልፈናል። በሁሉም ነገር እንስማማለን ማለት ባይሆንም እስካሁን ድረስ በመካከላችን ጭቅጭቅ ተነስቶ አያውቅም። ለዚህም ምክንያቱ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሆነ ሁለታችንም ይሰማናል።

አጭር የሕይወት ታሪክ

ስም፦ ማሳሂሮ ኦካባያሺ

ዕድሜ፦ 39

አገር፦ ጃፓን

የኋላ ታሪክ፦ ቁማርተኛ የነበረ

የቀድሞ ሕይወቴ፦ ያደግሁት ከነጎያ ከተማ በባቡር የግማሽ ሰዓት መንገድ ርቀት ላይ በምትገኝ ኢዋኩራ በተባለች አነስተኛ መንደር ውስጥ ነው። አባቴም ሆነ እናቴ በጣም ደግ ሰዎች እንደነበሩ አስታውሳለሁ። ከጊዜ በኋላ ግን አባቴ ያኩዛ ወይም ወሮበላ እንደነበርና አምስት አባላት ያሉትን ቤተሰባችንን ለተወሰነ ጊዜ ያህል የሚያስተዳድረው በማጭበርበር እንደነበረ አወቅሁ። አባቴ በየቀኑ በጣም ይጠጣ ስለነበር 20 ዓመት ሲሆነኝ በጉበት በሽታ ምክንያት ሞተ።

አባቴ ኮሪያዊ በመሆኑ አብዛኛውን ጊዜ ቤተሰባችን በሌላው ኅብረተሰብ መድሎ ይደርስበት ነበር። በዚህና በሌሎች ችግሮች የተነሳ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ እያለሁ ሕይወቴ የተመሰቃቀለ ነበር። ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ብገባም ትምህርት ቤት የምሄደው አልፎ አልፎ ነበር፤ ከአንድ ዓመት በኋላም ትምህርቴን አቋረጥኩ። ከዚያ ቀደም ጥፋት በመሥራት ስሜ በፖሊስ መዝገብ ላይ ሰፍሮ ነበር፤ ይህ ሁኔታ በአባቴ ኮሪያዊ ከመሆኔ ጋር ተዳምሮ ሥራ ማግኘት አስቸጋሪ እንዲሆንብኝ አደረገ። ውሎ አድሮ ሥራ ባገኝም በጉልበቴ ላይ ጉዳት ስለደረሰብኝ ከባድ ሥራ መሥራት አልቻልኩም።

ከጊዜ በኋላ፣ ፐቺንኮ የተባለ የቁማር ጨዋታ በመጫወት መተዳደር ጀመርኩ። በዚያን ወቅት ከአንዲት ሴት ጋር እኖር የነበረ ሲሆን እሷም የሚያስከብር ሥራ እንድይዝና እንዳገባት ትፈልግ ነበር። ሆኖም በቁማር ብዙ ገንዘብ አገኝ ስለነበር በአኗኗሬ ላይ ለውጥ ማድረግ አልፈለግሁም።

መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው? አንድ ቀን አንድ የይሖዋ ምሥክር ቤታችን መጣና ሕይወት—እንዴት ተገኘ? በዝግመተ ለውጥ ወይስ በፍጥረት? (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ሰጠኝ። ይህንን ጥያቄ በጭራሽ አስቤበት አላውቅም ነበር። መጽሐፉን ካነበብኩት በኋላ ግን ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የበለጠ ለማወቅ ፈቃደኛ ሆንኩ። ‘ሰዎች ከሞቱ በኋላ ምን ይሆናሉ?’ የሚለው ጥያቄ ሁልጊዜ በአእምሮዬ ይመላለስ ነበር። ይህንንና ሌሎች ጥያቄዎቼን በተመለከተ ከመጽሐፍ ቅዱስ ያገኘሁት ግልጽ መልስ ዓይኖቼ የበሩ ያህል ሆኖ እንዲሰማኝ አደረገኝ።

ከመጽሐፍ ቅዱስ የተማርኩትን ነገር ተግባራዊ ማድረግ እንዳለብኝ ስለተገነዘብኩ ጋብቻዬን ሕጋዊ አደረግሁ፤ ማጨስ አቆምኩ፣ ወርቃማ ቀለም ተቀብቶ የነበረውን ረጅም ፀጉሬን ተቆረጥኩ እንዲሁም አለባበሴ ሥርዓታማ እንዲሆን አደረግሁ። ከዚህም በተጨማሪ ቁማር መጫወት አቆምኩ።

እነዚህን ለውጦች ማድረግ ቀላል አልነበረም። ለምሳሌ ትንባሆ ማጨስን በራሴ ኃይል ማቆም አልቻልኩም ነበር። ይሁን እንጂ አጥብቄ በመጸለይና በይሖዋ አምላክ ላይ በመታመን ማጨስ ላቆም ችያለሁ። በተጨማሪም ፐቺንኮ መጫወት ካቆምኩ በኋላ ያገኘሁት የመጀመሪያ ሥራ ተፈታታኝ ሆኖብኝ ነበር። በዚህ ሥራ የማገኘው ገቢ ቁማር በመጫወት አገኘው ከነበረው በግማሽ ያነሰ ከመሆኑም ሌላ ሥራው ከባድና ውጥረት የበዛበት ነበር። ፈታኝ በነበረው በዚያ ወቅት ከረዱኝ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች አንዱ ፊልጵስዩስ 4:6, 7 ነው። ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “ስለ ምንም ነገር አትጨነቁ፤ ከዚህ ይልቅ ስለ ሁሉም ነገር በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር ልመናችሁን ለአምላክ አቅርቡ፤ ከማሰብ ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነው የአምላክ ሰላም በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት ልባችሁንና አእምሯችሁን ይጠብቃል።” የዚህን ጥቅስ እውነተኝነት በሕይወቴ ውስጥ ብዙ ጊዜ ተመልክቻለሁ።

ያገኘሁት ጥቅም፦ መጽሐፍ ቅዱስን ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ማጥናት ስጀምር ባለቤቴ ደስተኛ አልነበረችም። ሆኖም በአኗኗሬ ረገድ ያደረግኩትን ትልቅ ለውጥ ስትመለከት እሷም ከእኔ ጋር ማጥናትና በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባዎች ላይ አብራኝ መገኘት ጀመረች። አሁን ሁለታችንም የይሖዋ ምሥክሮች ነን። አምላክን በአንድነት ማገልገል መቻል እንዴት ያለ በረከት ነው!

መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ከመጀመሬ በፊት ደስተኛ እንደሆንኩ ይሰማኝ ነበር። አሁን ግን እውነተኛ ደስታ ምን ማለት እንደሆነ አውቄያለሁ። በመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርቶች መሠረት መኖር ቀላል እንዳልሆነ ባይካድም ከሁሉ የተሻለ ሕይወት እንድንመራ እንደሚያስችለን እርግጠኛ ነኝ።

አጭር የሕይወት ታሪክ

ስም፦ ኤሊዛቤት ጄን ስኮፊልድ

ዕድሜ፦ 35

አገር፦ ታላቋ ብሪታንያ

የኋላ ታሪክ፦ በሕይወቷ ውስጥ ዋነኛ ግቧ መዝናናት ነበረ

የቀድሞ ሕይወቴ፦ ያደግሁት በስኮትላንድ ከግላስጎው ከተማ ወጣ ብላ በምትገኝ ሃርድጌት በተባለች አነስተኛ መንደር ውስጥ ነው። የይሖዋ ምሥክር የሆነችው እናቴ ሰባት ዓመት ሲሆነኝ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ታስተምረኝ ጀመር። አሥራ ሰባት ዓመት ሲሆነኝ ግን ይበልጥ የሚያስደስተኝ ከትምህርት ቤት ጓደኞቼ ጋር በመሆን ወደ ጭፈራ ቤቶች መሄድ፣ ሄቪ ሜታል የተባለውን ሙዚቃ ማዳመጥ እንዲሁም መጠጣት ነበር። ስለ መንፈሳዊ ነገሮች በጭራሽ አላስብም ነበር። በሕይወቴ ውስጥ ትልቅ ቦታ የምሰጠው ነገር ቅዳሜና እሁድን በመዝናናት ማሳለፍ ነበር። ሆኖም 21 ዓመት ሲሆነኝ ይህ ሁሉ ተቀየረ።

አንዳንድ ዘመዶቼን ለመጠየቅ ወደ ሰሜን አየርላንድ ሄድኩ። እዚያ እያለሁም ኦሬንጅ ዎክ በመባል የሚታወቀውን የፕሮቴስታንቶች ሰልፍ ተመለከትኩ። በዚያ ወቅት በፕሮቴስታንቶችና በካቶሊኮች መካከል ያየሁት ከፍተኛ ጥላቻ እንዲሁም የሚያንጸባርቁት ጠባብ አስተሳሰብ በጣም ያስደነገጠኝ ከመሆኑም ሌላ እንድነቃ አደረገኝ። እናቴ ከመጽሐፍ ቅዱስ ያስተማረችኝን ነገሮች አስታወስኩ፤ አምላክ በፍቅር ላይ የተመሠረቱትን የእሱን መሥፈርቶች ችላ የሚሉ ሰዎችን ፈጽሞ እንደማይቀበል አውቅ ነበር። አምላክ በሚፈልግብኝ መንገድ ከመኖር ይልቅ የራሴን ፍላጎት ብቻ ሳሳድድ እንደኖርኩ ገባኝ። ወደ ትውልድ አገሬ ወደ ስኮትላንድ ስመለስ የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርቶች በቁም ነገር ለመመርመር ወሰንኩ።

መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው? ባደግሁበት ከተማ የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጉት ስብሰባ ላይ እንደገና መገኘት ስጀምር እንግድነት ተሰምቶኝና ፈርቼ ነበር። ይሁንና ሁሉም ሞቅ ባለ ስሜት ተቀበሉኝ። ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተማርኳቸውን ነገሮች በሥራ ላይ ማዋል ስጀምር አንዲት በጣም ደግ የሆነች የጉባኤው አባል ልዩ ትኩረት ሰጠችኝ። እንደገና የጉባኤው አባል እንደሆንኩ እንዲሰማኝ አደረገችኝ። የቀድሞ ጓደኞቼ ወደ ጭፈራ ቤቶች አብሬያቸው እንድሄድ በተደጋጋሚ ቢጠይቁኝም እኔ ግን በመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርቶች መሠረት ሕይወቴን ለመምራት እንደቆረጥኩ ነገርኳቸው። ከጊዜ በኋላ ከእኔ ጋር የነበራቸውን ግንኙነት አቋረጡ።

ቀደም ሲል መጽሐፍ ቅዱስን የሕግ መጽሐፍ እንደሆነ ብቻ አድርጌ እመለከተው ነበር። አሁን ግን አመለካከቴ ተቀይሯል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱት ሰዎች ልክ እንደ እኔ ዓይነት ስሜትና ድክመት ያላቸው በገሃዱ ዓለም የኖሩ ሰዎች እንደሆኑ ተረድቻለሁ። እነሱም እንደ እኔ ስህተት የሠሩ ቢሆንም ከልባቸው ይቅርታ ሲጠይቁ ይሖዋ አምላክ ምሕረት አድርጎላቸዋል። ይህን ማወቄ ወጣት እያለሁ ለአምላክ ጀርባዬን ሰጥቼ የነበረ ቢሆንም እሱን ለማስደሰት ከልቤ ጥረት ካደረግሁ ይቅር እንደሚለኝና ቀደም ሲል የሠራኋቸውን ስህተቶች እንደሚረሳ እንድተማመን አደረገኝ።

የእናቴ ምግባርም በጥልቅ ይነካኝ ነበር። እኔ አምላክን ብተወውም እሷ ፈጽሞ እንዲህ አላደረገችም። በታማኝነት በመጽናት የተወችው ምሳሌ ይሖዋን ማገልገል ምንም ዓይነት ጥረት ቢደረግለት የማያስቆጭ እንደሆነ እንድገነዘብ ረዳኝ። ትንሽ ልጅ እያለሁ ከእናቴ ጋር ከቤት ወደ ቤት ማገልገል በፍጹም አያስደስተኝም ነበር፤ ለሰዎች በመስበክ ረጅም ሰዓት ማሳለፍማ ጨርሶ የማላስበው ነገር ነበር። አሁን ግን በ⁠ማቴዎስ 6:31-33 ላይ የሚገኘው ኢየሱስ የገባው ቃል በሕይወቴ ውስጥ ይፈጸም እንደሆነ ለማየት ወሰንኩ። ኢየሱስ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “‘ምን እንበላለን?’ ወይም ‘ምን እንጠጣለን?’ ወይም ደግሞ ‘ምን እንለብሳለን?’ ብላችሁ ፈጽሞ አትጨነቁ። . . . በሰማይ የሚኖረው አባታችሁ እነዚህ ሁሉ እንደሚያስፈልጓችሁ ያውቃል። እንግዲያው ከሁሉ አስቀድማችሁ የአምላክን መንግሥትና ጽድቅ መፈለጋችሁን ቀጥሉ፤ እነዚህም ነገሮች ሁሉ ይሰጧችኋል።” ተጠምቄ የይሖዋ ምሥክር ከሆንኩ ብዙም ሳልቆይ የሙሉ ቀን ሥራዬን አቆምኩ፤ ከዚያም በሳምንት ውስጥ ለተወሰኑ ሰዓታት ብቻ እየሠራሁ በሙሉ ጊዜዬ አምላክን ማገልገል ጀመርኩ።

ያገኘሁት ጥቅም፦ ወጣት እያለሁ በሕይወቴ ውስጥ ትልቅ ቦታ የምሰጠው ነገር መዝናናት በነበረበት ወቅት ፈጽሞ ደስታ አልነበረኝም። ሕይወቴ ባዶ ነበር። ይሖዋን በሙሉ ጊዜ በማገልገል ላይ ያተኮረ ሕይወት በምመራበት በአሁኑ ጊዜ ግን እርካታ አግኝቻለሁ። ሕይወቴ ዓላማና ትርጉም ያለው ሆኗል። በአሁኑ ጊዜ ባለትዳር ስሆን እኔና ባለቤቴ በየሳምንቱ ወደተለያዩ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች በመሄድ ወንድሞቻችንን እናበረታታቸዋለን። ይህ ሥራ በሕይወቴ ውስጥ ታላቅ መብት እንደሆነ ይሰማኛል። ይሖዋ ሌላ ዕድል ስለሰጠኝ በጣም አመሰግነዋለሁ!

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ገና በመጀመሪያው ውይይታችን ወቅት የተለየ ነገር እንዳገኘሁ ታውቆኝ ነበር። ይሁን እንጂ በዚያ ወቅት በማንኛውም መልኩ አኗኗሬን መለወጥ አስፈላጊ ሆኖ አልታየኝም”

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ትንባሆ ማጨስን በራሴ ኃይል ማቆም አልቻልኩም ነበር። ይሁን እንጂ አጥብቄ በመጸለይና በይሖዋ አምላክ ላይ በመታመን ማጨስ ላቆም ችያለሁ”

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ቀደም ሲል መጽሐፍ ቅዱስን የሕግ መጽሐፍ እንደሆነ ብቻ አድርጌ እመለከተው ነበር። አሁን ግን አመለካከቴ ተቀይሯል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱት ሰዎች ልክ እንደ እኔ ዓይነት ስሜትና ድክመት ያላቸው በገሃዱ ዓለም የኖሩ ሰዎች እንደሆኑ ተረድቻለሁ”