በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ አይሁዳውያን በብዙ ቦታዎች ተበትነው ይኖሩ የነበሩት ለምንድን ነው?

ኢየሱስ፣ ያዳምጡት ለነበሩት አይሁዳውያን እሱ ወደሚሄድበት ሊመጡ እንደማይችሉ በነገራቸው ጊዜ እርስ በርሳቸው “ይህ ሰው፣ . . . ወዴት ለመሄድ ቢያስብ ነው? በግሪኮች መካከል ተበታትነው ወደሚኖሩት ወገኖቻችን ሄዶ . . . ሊያስተምር ፈልጎ ይሆን?” ተባብለው ነበር። (ዮሐንስ 7:32-36) ኢየሱስ ይህን ከተናገረ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ክርስቲያን ሚስዮናውያን የመንግሥቱን ምሥራች በሜዲትራኒያን ባሕር ዙሪያ ተበትነው ለሚኖሩ አይሁዶች አዳረሱ።—የሐዋርያት ሥራ 2:5-11፤ 9:2፤ 13:5, 13, 14፤ 14:1፤ 16:1-3፤ 17:1፤ 18:12, 19፤ 28:16, 17

አይሁዳውያን በብዙ ቦታዎች የተበተኑት በተለያዩ ጊዜያት ድል ያደረጓቸው ብሔራት በግዞት ስለወሰዷቸው ነበር። በመጀመሪያ በ740 ከክርስቶስ ልደት በፊት አሦራውያን፣ ከዚያም በ607 ከክርስቶስ ልደት በፊት ባቢሎናውያን እስራኤላውያንን ማርከው ወደ አገራቸው ወስደዋቸው ነበር። በምርኮ ከተወሰዱት ውስጥ ወደ እስራኤል ምድር የተመለሱት ጥቂቶች ብቻ ነበሩ። (ኢሳይያስ 10:21, 22) የተቀሩት አይሁዳውያን ግን ባሉበት ቀሩ።

በዚህም ምክንያት በአምስተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት የአይሁዳውያን ማኅበረሰብ በአሦር ግዛት ሥር በነበሩ 127 አገሮች ውስጥ ይገኙ ነበር። (አስቴር 1:1፤ 3:8) አይሁዳውያን፣ ሰዎች የእነሱን እምነት እንዲቀበሉ ለማድረግ መጣራቸው ውሎ አድሮ ብዙ ቁጥር ያላቸው ሕዝቦች ስለ ይሖዋና ለአይሁዳውያን ስለሰጠው ሕግ መጠነኛ እውቀት እንዲኖራቸው አድርጓል። (ማቴዎስ 23:15) በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ በርካታ አይሁዳውያን በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በዋለው የጰንጠቆስጤ በዓል ላይ ለመገኘት ወደ ኢየሩሳሌም የመጡ ሲሆን በዚያም ስለ ኢየሱስ ተሰብኮላቸዋል። አይሁዳውያን በመላው የሮማ ግዛት ተበትነው ይኖሩ የነበረ መሆኑ የክርስትና ሃይማኖት በከፍተኛ ፍጥነት እንዲስፋፋ አስተዋጽኦ አድርጓል።

ንጉሥ ሰለሞን ምን ያህል ወርቅ ነበረው?

ቅዱሳን መጻሕፍት፣ የጢሮስ ንጉሥ ኪራም ለሰለሞን 4,000 ኪሎ ግራም ወርቅ እንደላከለትና የሳባ ንግሥትም ተመሳሳይ መጠን ያለው ወርቅ በስጦታ እንዳበረከተችለት ከመግለጻቸውም ሌላ የራሱ የሰለሞን የንግድ መርከቦች ከኦፊር ከ15,000 ኪሎ ግራም በላይ ወርቅ እንዳመጡለት ይናገራሉ። መጽሐፍ ቅዱስ “ለሰሎሞን በየዓመቱ የሚገባለት ስድስት መቶ ሥልሳ ስድስት መክሊት [ወይም ከ25,000 ኪሎ ግራም በላይ] ወርቅ ነበር” ይላል። (1 ነገሥት 9:14, 28፤ 10:10, 14) ይህ ሊታመን የሚችል ነገር ነው? በዚያን ዘመን በነገሥታት እጅ ይገኝ የነበረው የወርቅ ክምችት ምን ያህል ነበር?

ምሁራን ተአማኒነቱን ያረጋገጡለት ተቀርጾ የተገኘ አንድ ጽሑፍ፣ የግብጹ ፈርኦን ሣልሳዊ ቱትሞሰ (በ16ኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት) በካርናክ ለሚገኘው የአሙንራ ቤተ መቅደስ 13,500 ኪሎ ግራም ገደማ የሚመዝን ወርቅ በስጦታ እንደሰጠ ይናገራል። በስምንተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት የአሦር ንጉሥ ሣልሳዊ ቴልጌልቴልፌልሶር ከ4,000 ኪሎ ግራም በላይ የሚመዝን ወርቅ ከጢሮስ ግብር ተቀብሏል። ዳግማዊ ሳርጎን ይህንኑ የሚያህል መጠን ያለው ወርቅ ለባቢሎን አማልክት በስጦታ አበርክቷል። የመቄዶንያው ንጉሥ ዳግማዊ ፊሊፕ (359-336 ከክርስቶስ ልደት በፊት) ትሬስ ውስጥ የማዕድን ክምችት ካለበት ከፓንጌየም አካባቢ በየዓመቱ ከ28,000 ኪሎ ግራም በላይ የሚመዝን ወርቅ ያወጣ እንደነበር ተዘግቧል።

የፊሊፕ ልጅ ታላቁ እስክንድር (336-323 ከክርስቶስ ልደት በፊት) የፋርሳውያን ከተማ የሆነችውን ሱሳን በተቆጣጠረበት ወቅት ከሱሳ ከአንድ ሚሊዮን ኪሎ ግራም በላይ የሚመዝን ወርቅ፣ ከመላው የፋርስ ግዛት ደግሞ ወደ ሰባት ሚሊዮን ኪሎ ግራም የሚጠጋ ወርቅ እንደወሰደ ይነገራል። ስለዚህ ከእነዚህ ዘገባዎች አንጻር ሲታይ መጽሐፍ ቅዱስ ንጉሥ ሰለሞን የነበረውን ወርቅ አስመልክቶ ያሰፈረው ዘገባ የተጋነነ አይደለም።