በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሰው ሲሞት ምን ይሆናል?

ሰው ሲሞት ምን ይሆናል?

 ሰው ሲሞት ምን ይሆናል?

“የክፉ ሰዎችን ነፍሳት ጨምሮ ሁሉም ነፍሳት ዘላለማዊ ናቸው . . . ሊጠፋ በማይችል የበቀል እሳት ለዘላለም ይቀጣሉ፤ ስለማይሞቱ ሥቃያቸው እንዲያበቃ ማድረግ አይችሉም።”—የእስክንድርያው ክሌመንት፣ በሁለተኛውና በሦስተኛው መቶ ዘመን ከክ. ል. በኋላ የነበረ ጸሐፊ

እንደ ክሌመንት ሁሉ ሲኦል የመሠቃያ ቦታ ነው የሚለውን ትምህርት የሚያስፋፉ ሰዎች፣ ነፍስ አትሞትም ብለው ያምናሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ትምህርት ይደግፋል? የአምላክ ቃል ለሚከተሉት ጥያቄዎች የሚሰጠውን መልስ እንመልከት።

የመጀመሪያው ሰው አዳም የማትሞት ነፍስ ነበረችው? መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አዳም አፈጣጠር ሲናገር “እግዚአብሔር አምላክ ከምድር ዐፈር ወስዶ ሰውን አበጀው፤ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስ እፍ አለበት፤ ሰውም ሕያው ነፍስ ሆነ” ይላል። (ዘፍጥረት 2:7) ይህ ጥቅስ አዳም ነፍስ ተሰጠው እንደማይል ልብ በል።

አዳም ኃጢአት ከሠራ በኋላ ምን ሆነ? አምላክ የበየነበት በሲኦል ውስጥ ለዘላለም እንዲሠቃይ አይደለም። ከዚህ ይልቅ “ከምድር ስለ ተገኘህ፣ ወደ መጣህበት መሬት እስክትመለስ ድረስ እንጀራህን በፊትህ ላብ ትበላለህ፤ ዐፈር ነህና ወደ ዐፈር ትመለሳለህ” ብሎታል። (ዘፍጥረት 3:19) አምላክ፣ አዳም ከሞተ በኋላ የትኛውም የአካሉ ክፍል በሕይወት እንደሚቀጥል የሚጠቁም ነገር አልተናገረም። አዳም ሞተ ማለት ነፍስ የነበረው አዳም ሞተ ማለት ነው።

የማትሞት ነፍስ ያለችው ሰው አለ? አምላክ ለነቢዩ ሕዝቅኤል “ኀጢአት የምትሠራ ነፍስ እርሷ ትሞታለች” ብሎታል። (ሕዝቅኤል 18:4) ሐዋርያው ጳውሎስም እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ኀጢአት በአንድ ሰው [በአዳም] በኩል ወደ ዓለም እንደ ገባ ሁሉ፣ ሞትም በኀጢአት በኩል ገብቶአል፤ በዚሁ መንገድ ሞት ወደ ሰዎች ሁሉ መጣ፤ ምክንያቱም ሁሉም ኀጢአትን  ሠርተዋል።” (ሮሜ 5:12) ሁሉም ሰው ኃጢአት ስለሚሠራ ነፍስ ሁሉ ይሞታል ብሎ ማሰቡ ምክንያታዊ ነው።

የሞተ ነፍስ የሚያውቀው ነገር ወይም የሚሰማው ስሜት አለ? የአምላክ ቃል “ሕያዋን እንደሚሞቱ ያውቃሉና፤ ሙታን ግን ምንም አያውቁም” በማለት ይናገራል። (መክብብ 9:5) መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች በሚሞቱበት ጊዜ ምን እንደሚሆኑ ሲገልጽ “ወደ መሬታቸውም ይመለሳሉ፤ ያን ጊዜም ዕቅዳቸው እንዳልነበር ይሆናል” ይላል። (መዝሙር 146:4) ሙታን ‘ምንም የማያውቁ’ እና “ዕቅዳቸው እንዳልነበር” የሚሆን ከሆነ በሲኦል ውስጥ እንዴት ሊሠቃዩ ይችላሉ?

ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ያመሳሰለው ከእንቅልፍ ጋር ነው። * (ዮሐንስ 11:11-14) ይሁንና አንዳንዶች ኢየሱስ ዘላለማዊ እሳት እንዳለና ኃጢአተኞችም ወደዚያ እንደሚጣሉ አስተምሯል ብለው ይከራከሩ ይሆናል። ኢየሱስ ይህን በተመለከተ ምን እንደተናገረ እስቲ እንመልከት።

[የግርጌ ማስታወሻ]