በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የምትገነባው በአሸዋ ላይ ነው ወይስ በዓለት ላይ?

የምትገነባው በአሸዋ ላይ ነው ወይስ በዓለት ላይ?

የምትገነባው በአሸዋ ላይ ነው ወይስ በዓለት ላይ?

መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብ ትወዳለህ? ወይስ ከአንድ የይሖዋ ምሥክር ጋር መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትረህ እያጠናህ ነው? ከሆነ የቀሰምከው እውቀት ይህ ዓለም በችግር የተሞላው ለምን እንደሆነ የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖርህ እንደረዳህ ምንም ጥርጥር የለውም። (ራእይ 12:9, 12) ከዚህም በተጨማሪ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች በሕይወትህ ውስጥ አስጨናቂ ሁኔታዎች ባጋጠሙህ ጊዜ እንዳጽናኑህ ብሎም ተስፋ እንደፈነጠቁልህ ግልጽ ነው።—መዝሙር 145:14፤ 147:3፤ 2 ጴጥሮስ 3:13

ትክክለኛ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ማግኘት የክርስቶስ ተከታይ ለመሆን የሚፈልጉ ሰዎች ሊወስዱት የሚገባ አስፈላጊ እርምጃ ነው። ይሁንና ይህ ብቻውን በቂ ነው? አይደለም። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ በተለይ እምነቱ በሚፈተንበት ወቅት እውነተኛ ክርስቲያን ሆኖ መቀጠል እንዲችል ሊወስደው የሚገባ ሌላም እርምጃ አለ። ይህ እርምጃ ምንድን ነው? መልሱን ለማወቅ ኢየሱስ በገሊላ በሚገኝ አንድ ተራራ ላይ ሆኖ የሰጠውን ንግግር ማለትም የተራራውን ስብከት በአጭሩ እንመልከት።—ማቴዎስ 5:1, 2

ሁለት ቤቶች ተፈተኑ

የተራራው ስብከት ምን ትምህርቶችን እንደያዘ ታውቃለህ? ይህን ዝነኛ ስብከት በማቴዎስና በሉቃስ ወንጌሎች ውስጥ ማግኘት ትችላለህ። (ማቴዎስ 5:1 እስከ 7:29፤ ሉቃስ 6:20-49) ጠቅላላውን ስብከት በ20 ደቂቃ ውስጥ አንብቦ መጨረስ የሚቻል ቢሆንም ከዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት የተወሰዱ ከ20 በላይ ጥቅሶችና ከ50 የሚበልጡ ምሳሌያዊ አነጋገሮች ይዟል። በተለይም ስለ ሁለት ቤቶች ግንባታ የሚናገረው ምሳሌ ኢየሱስ የስብከቱ መደምደሚያ አድርጎ የተጠቀመበት በመሆኑ ከሌሎቹ ጎላ ብሎ ይታያል። ይህ ምሳሌ የያዘውን ቁም ነገር ከተረዳህ ምንም ዓይነት የእምነት ፈተና ቢያጋጥምህ የክርስቶስ ተከታይ በመሆን ጸንተህ መቆም የምትችለው እንዴት እንደሆነ ማስተዋል ትችላለህ።

ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “እንግዲህ ይህን ቃሌን ሰምቶ በተግባር የሚያውል፣ ቤቱን በዐለት ላይ የሠራን ብልኅ ሰው ይመስላል። ዶፍ ወረደ፤ ጐርፍም ጐረፈ፤ ነፋስም ነፈሰ፤ ያንን ቤት መታው፤ በዐለት መሠረትም ላይ ስለ ተመሠረተ አልወደቀም። ይህን ቃሌን ሰምቶ በተግባር የማያውለው ግን ቤቱን በአሸዋ ላይ የሠራን ሞኝ ሰው ይመስላል። ዶፍ ወረደ፤ ጐርፍም ጐረፈ፤ ነፋስም ነፈሰ፤ ያንን ቤት መታው፤ ቤቱም ወደቀ፤ አወዳደቁም የከፋ ነበር።”—ማቴዎስ 7:24-27

“አጥልቆ የቈፈረ” ሰው

ኢየሱስ ቤት ስለሠሩት ሁለት ሰዎች በተናገረው ምሳሌ ላይ ለደቀ መዛሙርቱ ሊያስተላልፍ የፈለገው ጠቃሚ ትምህርት ምን ነበር? ይህን ለማወቅ ኢየሱስ የተናገረውን ምሳሌ በጥንቃቄ መመርመር ይኖርብሃል። ስለ ሁለቱ ቤቶች ምን አስተዋልክ? ሁለቱም ቤቶች ለመጥፎ የአየር ሁኔታ ተጋልጠዋል። ቤቶቹ ሲታዩ ተመሳሳይ ሊመስሉ ይችላሉ። የተሠሩትም በአንድ አካባቢ እንዲያውም ጎን ለጎን ሊሆን ይችላል። ያም ሆኖ አንደኛው ቤት የተገነባው በአሸዋ ላይ ሲሆን ሌላኛው ግን በዓለት ላይ ነው። ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? በሉቃስ ወንጌል ላይ እንደተገለጸው ብልህ የሆነው ሰው ዓለት እስኪያገኝ ድረስ ‘በጥልቀት ቈፍሯል።’ (ሉቃስ 6:48) በመሆኑም የገነባው ቤት መጥፎውን የአየር ሁኔታ መቋቋም ችሏል።

ኢየሱስ ማጉላት የፈለገው ነጥብ ምንድን ነው? ኢየሱስ ምሳሌውን የተናገረው ስለ ቤቶቹ ዓይነት ወይም ስለተገነቡበት ሥፍራ አሊያም ደግሞ ስለ አየሩ ሁኔታ አስከፊነት ለመግለጽ ሳይሆን ቤቶቹን የሠሯቸው ሰዎች ያደረጉትን ነገር ለማጉላት ነው። አንደኛው ሰው አጥልቆ የቆፈረ ሲሆን ሌላኛው ግን እንዲህ አላደረገም። ታዲያ አንተስ እንደ ብልሁ ሰው በጥልቀት መቆፈር የምትችለው እንዴት ነው? ኢየሱስ የምሳሌውን ፍሬ ነገር ጠቅለል አድርጎ ሲያስቀምጥ እንዲህ ብሏል፦ “እኔ የምለውን አታደርጉም፤ ታዲያ ለምን፣ ‘ጌታ ሆይ፤ ጌታ ሆይ’ ትሉኛላችሁ? ወደ እኔ የሚመጣ፣ ቃሌንም ሰምቶ የሚፈጽም ሁሉ ማንን እንደሚመስል ላሳያችሁ፤ . . . አጥልቆ የቈፈረና በዐለት ላይ መሠረቱን የመሠረተ ሰው ይመስላል።”—ሉቃስ 6:46-48

የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርቶች መስማት ወይም መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ብቻውን መቆፈር ስለማይጠይቅ ቤትን በአሸዋ ላይ ከመገንባት ተለይቶ አይታይም። ዓለት ለማግኘት በጥልቀት መቆፈር እንደሚያስፈልግ ሁሉ የክርስቶስን ትምህርቶች ሥራ ላይ ማዋልም ከፍተኛ ጥረት ማድረግን ይጠይቃል።

በመሆኑም የክርስቶስ ተከታይ በመሆን መጽናትህ የተመካው የሰማኸውን ነገር ተግባራዊ በማድረግህ ላይ ነው። ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትህ ያገኘሃቸውን ትምህርቶች በዕለት ተዕለት ሕይወትህ ተግባራዊ የምታደርግ ከሆነ በጥልቀት እንደቆፈረው ብልህ ሰው ትሆናለህ። ስለሆነም እያንዳንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ እንደሚከተለው በማለት ቆም ብሎ ራሱን መጠየቅ አለበት፦ ‘ሰሚ ብቻ ነኝ ወይስ የሰማሁትን ነገር በተግባር አውላለሁ? መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብና በማጥናት ብቻ እረካለሁ ወይስ ውሳኔ በማደርግበት ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስን ትእዛዝ እከተላለሁ?’

በጥልቀት መቆፈር የሚያስገኘው ጥቅም

የሆሴን ተሞክሮ ተመልከት። ወላጆቹ ለመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር መመሪያዎች አክብሮት እንዲኖረው አድርገው ቢያሳድጉትም ሆሴ የአምላክን ቃል በግሉ የማጥናት ልማድ አልነበረውም። ሆሴ እንዲህ ብሏል፦ “ለብቻዬ መኖር በጀመርኩበት ወቅት ጥሩ ሰው ለመሆን ጥረት አደርግ የነበረ ቢሆንም ከመጥፎ ጓደኞች ጋር ገጠምኩ። በመሆኑም አደገኛ ዕፆችን መውሰድና የጾታ ብልግና መፈጸም የጀመርኩ ሲሆን ሁልጊዜ ከሰዎች ጋር እጣላ ነበር።”

በመጨረሻም ሆሴ አኗኗሩን ለማስተካከልና መጽሐፍ ቅዱስን በቁም ነገር ለማጥናት ወሰነ። እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “አኗኗሬን እንድለውጥ ካነሳሱኝ ምክንያቶች አንዱ የኢየሱስን የተራራ ስብከት ማንበቤና ትምህርቱ የያዘውን ቁም ነገር መረዳቴ ነበር። ይሁን እንጂ ባሕርዬንና አኗኗሬን ለማስተካከል ጊዜ ወስዶብኛል። መጀመሪያ ላይ ‘ጓደኞቼ’ ምን ይሉኛል የሚል ፍርሃት የነበረኝ ቢሆንም ይህን ፍርሃቴን ማሸነፍ ቻልኩ። መዋሸትና ጸያፍ ቃላትን መናገር ያቆምኩ ሲሆን የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ላይ መገኘትም ጀመርኩ። ኢየሱስ እንደተናገረው አኗኗርን ቀላል ማድረግና የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር በሥራ ላይ ማዋል በእርግጥም ዘላቂ ደስታ እንደሚያመጣ ተገንዝቤያለሁ።”—ማቴዎስ 5:3-12

በዓለት ላይ ለመገንባት በጥልቀት መቆፈርህ ማለትም ከአምላክ ቃል የተማርካቸውን ነገሮች በሥራ ላይ ለማዋል መጣርህ ምን ጥቅም ያስገኝልሃል? ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “ጐርፍ በመጣ ጊዜ የውሃው ሙላት ያን ቤት ገፋው፤ በሚገባ ስለ ታነጸም ሊያነቃንቀው አልቻለም።” (ሉቃስ 6:48) የተማርከውን በተግባር በማዋል እምነትህን በደንብ የምትገነባ ከሆነ ጎርፍ መሰል ፈተናዎች እምነትህን ሊያጠፉት ይቅርና ሊነቀንቁት እንኳ እንደማይችሉ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ። ይህ እንዴት የሚያጽናና ሐሳብ ነው!

የኢየሱስ ወንድም የሆነው ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ፣ የአምላክ ቃል የሚናገረውን ለመስማት ብቻ ሳይሆን የሚሰሙትን በሥራ ላይ ለማዋል የሚጥሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የሚያገኙትን ሌላ በረከት ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ቃሉ የሚናገረውን አድርጉ እንጂ ሰሚዎች ብቻ [አትሁኑ።] . . . ነጻ የሚያወጣውን ፍጹም ሕግ ተመልክቶ የሚጸና፣ የሰማውን የሚያደርግና የማይረሳ ሰው በሥራው የተባረከ [“ደስተኛ፣” NW] ይሆናል።”—ያዕቆብ 1:22-25

በእርግጥም የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር በሥራ ላይ የሚያውሉ ሰዎች እውነተኛ ደስታ ያገኛሉ። እንዲህ ያለው ደስታ ደግሞ የክርስቶስ ተከታዮች እምነታቸውንና ለአምላክ ያላቸውን ፍቅር እውነተኝነት የሚፈትኑ ጎርፍ መሰል ፈተናዎችን በጽናት እንዲቋቋሙ ጥንካሬ ይሰጣቸዋል።

አንተስ ምን ለማድረግ አስበሃል?

ኢየሱስ፣ ይሖዋ አምላክን ለማገልገል ከፈለግን በሕይወታችን ውስጥ ምርጫ ማድረግ የግድ አስፈላጊ መሆኑን በተራራ ስብከቱ ላይ ጎላ አድርጎ ገልጿል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ሰው ጤናማ ወይም ታማሚ ዓይን እንደሚኖረው፣ አምላክን ወይም ገንዘብን እንደሚያገለግልና በጠባቡ ወይም በሰፊው መንገድ ላይ እንደሚጓዝ አስተምሯል። (ማቴዎስ 6:22-24፤ 7:13, 14) ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ ቤት ስለሠሩት ሁለት ሰዎች በተናገረው የመደምደሚያ ምሳሌ ላይ ለደቀ መዛሙርቱ ብልሁን ወይም ሞኙን ሰው የመምሰል ምርጫ አቅርቦላቸዋል።

ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትህ ያገኘኸውን ትምህርት በሥራ ላይ ማዋልህን የምትቀጥል ከሆነ ብልሁን ሰው እየመሰልክ ነው። አዎ፣ በዓለት ላይ ለመገንባት በጥልቀት መቆፈርህ አሁንም ሆነ ወደፊት በረከት ያስገኝልሃል።—ምሳሌ 10:25

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መጽናታችን የተመካው የተማርነውን ተግባራዊ በማድረጋችን ላይ ነው