በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በአንድ ወቅት ገናና የነበሩት “የተርሴስ መርከቦች”

በአንድ ወቅት ገናና የነበሩት “የተርሴስ መርከቦች”

 በአንድ ወቅት ገናና የነበሩት “የተርሴስ መርከቦች”

“የተርሴስ መርከቦች፣ ሸቀጥሽን አጓጓዙልሽ።” —ሕዝቅኤል 27:25

የተርሴስ መርከቦች ንጉሥ ሰለሞን ባለጸጋ እንዲሆን ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል። እነዚህን መርከቦች ይሠሩ የነበሩት ሕዝቦች የግሪክኛና የላቲን ፊደላት እንዲገኙ አስተዋጽኦ አድርገዋል። በተጨማሪም ቢብሎስ የተባለች ከተማ የቆረቆሩ ሲሆን የዚህች ከተማ ስያሜ በብዙ ቋንቋዎች መጽሐፍ ቅዱስ ለሚጠራበት ቃል መገኛ ሆኗል።

የተርሴስን መርከቦች ይሠሩና ይገለገሉባቸው የነበሩት እነማን ናቸው? መርከቦቹ ስያሜያቸውን ያገኙት ከየት ነው? ከእነዚህ ሕዝቦችና ከመርከቦቻቸው ጋር የተያያዙ ታሪኮች የመጽሐፍ ቅዱስን ትክክለኛነት የሚመሰክሩት እንዴት ነው?

የሜዲትራኒያን ባሕር ጌቶች

የተርሴስ መርከቦች በሚል ስያሜ የሚታወቁትን መርከቦች የሠሩት ፊንቄያውያን ናቸው። ፊንቄያውያን ክርስቶስ ከመወለዱ ከሺህ ዓመት ገደማ በፊት ጀምሮ የታወቁ ባሕረኞች ነበሩ። እነዚህ ሕዝቦች ይኖሩ የነበረው ከሞላ ጎደል የዛሬዋ ሊባኖስ በምትገኝበት የባሕር ጠረፍ ላይ ነው። በስተ ሰሜን፣ በስተ  ምሥራቅና በስተ ደቡብ ሌሎች ሕዝቦች ያዋስኗቸው የነበረ ሲሆን በስተ ምዕራብ ደግሞ የሜዲትራኒያን ባሕር ተንጣሎ ይገኛል። ፊንቄያውያን ሀብት ለማግኘት ይተማመኑ የነበረው በዚህ ባሕር ነበር።

ከጊዜ በኋላ ፊንቄያውያን ባሕረኞች አስተማማኝ የሆኑ የንግድ መርከቦችን ሠሩ። ትርፋቸው እየጨመረ ሲመጣና ቴክኖሎጂው እያደገ ሲሄድ ረጅም ጉዞ የማድረግ አቅም ያላቸውን ትላልቅ መርከቦች ሠሩ። ፊንቄያውያን ቆጵሮስን፣ ሰርዲንያንና ባሊያሪክ ደሴቶችን ካዳረሱ በኋላ የሰሜን አፍሪካን የባሕር ዳርቻ ይዘው ስፔን እስከሚደርሱ ድረስ ወደ ምዕራብ አቀኑ። (በሚቀጥለው ገጽ ላይ የሚገኘውን ካርታ ተመልከት።)

መርከብ በመሥራትና በመጠገን ሙያ የተካኑት ፊንቄያውያን 30 ሜትር ርዝመት ያላቸውን ትላልቅ ጀልባዎች ይሠሩ ነበር። ለባሕር ላይ ጉዞ የተሠሩት እነዚህ መርከቦች ከፊንቄ ተነስተው ተርሴስ ትገኝበት ነበር ተብሎ እስከሚታሰበው እስከ ደቡባዊ ስፔን ድረስ 4,000 ኪሎ ሜትር ያህል ይጓዙ ስለነበር “የተርሴስ መርከቦች” የሚል ስያሜ አግኝተዋል። *

ፊንቄያውያን ዓለምን ለመግዛት ቆርጠው የተነሱ ሕዝቦች አልነበሩ ይሆናል፤ ሆኖም ገንዘብ የማካበት ከፍተኛ ፍላጎት ነበራቸው። ለዚህም እንዲረዳቸው በየስፍራው የንግድ ማዕከሎችን አቋቁመው ነበር። በመሆኑም ፊንቄያውያን በንግዱ ዘርፍ የሜዲትራኒያን ባሕር ጌቶች መሆን ችለው ነበር።

ከሜዲትራኒያን ባሕር ተሻገሩ

ፊንቄያውያን አሳሾች ትርፍ ለማጋበስ ከነበራቸው ከፍተኛ ፍላጎት የተነሳ ወደ አትላንቲክ ውቅያኖስ አለፉ። ከዚያም የስፔንን ደቡባዊ የባሕር ዳርቻ ይዘው ታርቴሰስ እስከሚባለው አካባቢ ድረስ ተጓዙ። ከክርስቶስ ልደት በፊት በ1100 ገደማ ጋዲር ብለው የጠሯትን ከተማ ቆረቆሩ። በአሁኑ ጊዜ ካዲዝ ተብላ የምትጠራው በስፔን የምትገኘው ይህች የወደብ ከተማ በዚያን ዘመን በምዕራብ አውሮፓ ከነበሩት ትላልቅ ከተሞች አንዷ ለመሆን በቅታ ነበር።

ፊንቄያውያን ከሚሸጧቸው ሸቀጦች መካከል ጨው፣ ወይን ጠጅ፣ የደረቀ ዓሣ፣ ዝግባ፣ ጥድ፣ ከብረት የተሠሩ ዕቃዎች፣ መስታወት፣ ጥልፍ፣ ምርጥ ሊኖ ጨርቅና ታዋቂ በሆነው የጢሮስ ወይን ጠጅ ቀለም የተነከረ ጨርቅ ይገኙበታል። ስፔንስ ለፊንቄያውያን ነጋዴዎች ልታቀርብ የምትችለው ምን ሀብት ነበራት?

 በሜዲትራኒያን ባሕር ዙሪያ ከሚገኙ አገሮች ሁሉ የበለጠ ብዙ ብርና ሌሎች ውድ ማዕድናት የሚገኙት በደቡባዊ ስፔን ነበር። ነቢዩ ሕዝቅኤል የፊንቄያውያን ዋነኛ የወደብ ከተማ የነበረችውን ጢሮስን አስመልክቶ እንዲህ ብሏል፦ “ከሀብትሽ ብዛት የተነሣ፣ ተርሴስ [ወይም ስፔን] ከአንቺ ጋር የንግድ ልውውጥ ታደርግ ነበር፤ ብርና ብረት፣ ቈርቈሮና እርሳስ አምጥታ ሸቀጥሽን ትለውጥ ነበር።”—ሕዝቅኤል 27:12 

ፊንቄያውያን ከካዲዝ አቅራቢያ በሚገኘው በጓዳልክዊቨር ወንዝ አካባቢ ተዝቆ የማያልቅ የማዕድን ክምችት አገኙ። በዛሬው ጊዜ ሪዮ ቲንቶ ከሚባለው ከዚሁ አካባቢ እነዚህ ማዕድናት ይወጣሉ። ለሦስት ሺህ ዓመታት ገደማ ከፍተኛ ጥራት ያለው የብረት ማዕድን ከዚህ ቦታ ሲወጣ ኖሯል።

በስፔናውያንና በፊንቄያውያን መካከል የነበረው የንግድ ግንኙነት በጣም ጠንካራ ስለነበር ፊንቄያውያን የስፔንን የብር ገበያ ተቆጣጥረውት ነበር። የስፔን ብር ወደ ፊንቄ ሌላው ቀርቶ በአቅራቢያው ወደምትገኘው እስራኤል በገፍ ይገባ ነበር። የእስራኤሉ ንጉሥ ሰለሞንና የፊንቄያውያን ንጉሥ ኪራም የንግድ ሸሪክ ነበሩ። በዚህም ምክንያት በሰለሞን ዘመን ብር ‘ዋጋ እንደሌለው’ ተደርጎ ይታይ ነበር።—1 ነገሥት 10:21 *

ፊንቄያውያን የተዋጣላቸው ነጋዴዎች ቢሆኑም ጨካኞች ነበሩ። አንዳንድ ጊዜ፣ የሚሸጡ ዕቃዎች እናሳያችኋለን በሚል ሰበብ ሰዎችን ወደ መርከቦቻቸው ካስገቡ በኋላ ባሪያዎች ያደርጓቸው እንደነበር ይነገራል። እንዲያውም የንግድ ሸሪኮቻቸው የነበሩትን እስራኤላውያንን የከዷቸው ሲሆን ለባርነትም ሸጠዋቸዋል። በመሆኑም ዕብራውያን ነቢያት የፊንቄያውያን ከተማ የነበረችው ጢሮስ እንደምትጠፋ ትንቢት ተናገሩ። እነዚህ ትንቢቶች፣ ታላቁ እስክንድር በ332 ከክርስቶስ ልደት በፊት ጢሮስን ሲያጠፋት ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል። (ኢዩኤል 3:6፤ አሞጽ 1:9, 10) የፊንቄያውያን ዘመን ያበቃው በዚህ ወቅት ነበር።

ፊንቄያውያን ትተውት ያለፉት ቅርስ

ጠንቃቃ የሆኑ ነጋዴዎች እንደሚያደርጉት ሁሉ ፊንቄያውያንም የንግድ ውላቸውን በጽሑፍ ያሰፍሩ ነበር። ፊንቄያውያን ከጥንት የዕብራይስጥ ፊደላት ጋር የሚመሳሰሉ ሆሄያት ነበሯቸው። ሌሎች ሕዝቦች የፊንቄያውያን ሆሄያት ጠቃሚ መሆናቸውን ተገንዝበው ነበር። እነዚህ ፊደላት ጥቂት ማስተካከያ ከተደረገላቸው በኋላ ለግሪክኛ ሆሄያት መፈጠር መሠረት ሆነዋል። በዛሬው ጊዜ በስፋት የሚሠራባቸው የላቲን ሆሄያት የተገኙት ደግሞ ከግሪክኛ ፊደላት ነው።

በተጨማሪም የፊንቄያውያን ታዋቂ ከተማ የነበረችው ቢብሎስ፣ ዘመናዊው ወረቀት ከመፈልሰፉ በፊት ለመጻፊያነት ያገለግል የነበረው ፓፒረስ እንደልብ የሚገኝባት ቦታ ሆና ነበር። ፓፒረስ ለጽሕፈት አገልግሎት መዋሉ መጻሕፍትን ለማዘጋጀት ሥራ በር ከፍቷል። እንዲያውም በስርጭቱ ተወዳዳሪ ያልተገኘለት መጽሐፍ ማለትም መጽሐፍ ቅዱስ በብዙ ቋንቋዎች ለሚጠራበት ቃል መገኛ የሆነው ቢብሎስ የተባለው ስያሜ ነው። በእርግጥም ስለ ፊንቄያውያንና ስለ መርከቦቻቸው የሚናገሩት የታሪክ ዘገባዎች መጽሐፍ ቅዱስ እውነተኛ መሆኑን ያረጋግጡልናል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.8 ከጊዜ በኋላ “የተርሴስ መርከቦች” የሚለው ስያሜ በባሕር ላይ ረጅም ጉዞ የማድረግ አቅም ያላቸውን የመርከብ ዓይነቶች ለማመልከት ይሠራበት ጀመር።

^ አን.15 የሰለሞን “የተርሴስ የንግድ መርከቦች” ከኪራም የንግድ መርከቦች ጋር በመሆን በቀይ ባሕርና ከዚያም አልፈው ይነግዱ የነበረ ሲሆን መነሻቸውም ጽዮንጋብር ሳይሆን አይቀርም።—1 ነገሥት 10:22

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

የፊንቄያውያን የንግድ መስመር

ስፔን

ታርቴሰስ

ጓዳልክዊቨር ወንዝ

ጋዲር

ኮርሲካ

ባሊያሪክ ደሴቶች

ሰርዲንያ

ሲሲሊ

ቀርጤስ

ቆጵሮስ

ቢብሎስ

ጢሮስ

ሜዲትራኒያን ባሕር

ጽዮንጋብር

ቀይ ባሕር

አፍሪካ

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የፊንቄያውያንን መርከብ የሚያሳይ ከሦስተኛው እስከ አራተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት ያገለግል የነበረ ሳንቲም

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የፊንቄያውያን ከተማ ፍርስራሽ፤ ካዲዝ፣ ስፔን

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

Museo Naval, Madrid

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሳንቲም፦ Museo Arqueológico Municipal. Puerto de Sta. María, Cádiz; የከተማ ፍርስራሽ፦ Yacimiento Arqueológico de Doña Blanca, Pto. de Sta. María, Cádiz, España