በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በዛሬው ጊዜ ሰባቱ እረኞችና ስምንቱ አለቆች እነማን ናቸው?

በዛሬው ጊዜ ሰባቱ እረኞችና ስምንቱ አለቆች እነማን ናቸው?

“ሰባት እረኞችን፣ እንዲያውም ስምንት አለቆችን እናስነሣበታለን።”—ሚክ. 5:5

1. ሶርያና እስራኤል ግንባር ፈጥረው የጠነሰሱት ሴራ ሊሳካ የማይችለው ለምንድን ነው?

የእስራኤል ንጉሥ እና የሶርያ ንጉሥ በ762 ዓ.ዓ. እና በ759 ዓ.ዓ. መካከል ባለው ጊዜ ውስጥ በይሁዳ መንግሥት ላይ ጦርነት አውጀው ነበር። ዓላማቸው ምንድን ነው? ኢየሩሳሌምን መውረርና ንጉሥ አካዝን ከዙፋኑ ማስወገድ እንዲሁም እሱን በሌላ ሰው ምናልባትም የንጉሥ ዳዊት ዘር ባልሆነ ሰው መተካት ነበር። (ኢሳ. 7:5, 6) የእስራኤል ንጉሥ በዚህ ረገድ የተሻለ ግንዛቤ ሊኖረው ይገባ ነበር። ይሖዋ ከዳዊት ዘሮች አንዱ በእሱ ዙፋን ላይ ለዘላለም እንደሚቀመጥ ቃል ገብቷል፤ የአምላክ ቃል ደግሞ መቼም ቢሆን ሳይፈጸም አይቀርም።—ኢያሱ 23:14፤ 2 ሳሙ. 7:16

2-4. ኢሳይያስ 7:14, 16 (ሀ) በስምንተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. (ለ) በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት እንደሆነ አብራራ።

2 መጀመሪያ ላይ ሶርያና እስራኤል ድል የሚቀናቸው ይመስሉ ነበር። በአንድ ውጊያ ብቻ አካዝ ያሰለፋቸው 120,000 ጀግና ተዋጊዎች አለቁ! ‘የንጉሡ ልጁ’ መዕሤያም ተገደለ። (2 ዜና 28:6, 7) ይሁንና ይሖዋ የሚፈጸመውን ነገር ሁሉ ይመለከት ነበር። ለዳዊት የገባውን ቃል አልዘነጋም፤ በመሆኑም በነቢዩ ኢሳይያስ አማካኝነት በጣም የሚያበረታታ መልእክት ላከ።

3 ኢሳይያስ እንዲህ አለ፦ “እነሆ፤ ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፤ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች። . . . ሕፃኑ ክፉውን መተውና መልካሙን መምረጥ ከመቻሉ በፊት የፈራሃቸው የሁለቱ ነገሥታት [የሶርያና የእስራኤል] ምድር ባድማ ይሆናል።” (ኢሳ. 7:14, 16) የዚህ ትንቢት የመጀመሪያው ክፍል አብዛኛውን ጊዜ ከመሲሑ መወለድ ጋር ተያይዞ ይገለጻል፤ ደግሞም ትክክል ነው። (ማቴ. 1:23) ይሁን እንጂ “ሁለቱ ነገሥታት” ማለትም የሶርያ ንጉሥና የእስራኤል ንጉሥ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. በይሁዳ ላይ የፈጠሩት ስጋት አልነበረም፤ በመሆኑም ስለ አማኑኤል የሚናገረው ትንቢት  የመጀመሪያውን ፍጻሜ በኢሳይያስ ዘመን አግኝቶ መሆን አለበት።

4 ኢሳይያስ ይህን አስገራሚ ትንቢት ከተናገረ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ሚስቱ ፀነሰችና ማኸር ሻላል ሃሽ ባዝ የተባለ ወንድ ልጅ ወለደችለት። ይህ ልጅ ኢሳይያስ የተናገረለት “አማኑኤል” ሊሆን ይችላል። * በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን አንድ ልጅ ሲወለድ አንድን ለየት ያለ ክስተት ለመዘከር የሚያስችል ስም ሊወጣለት ይችላል፤ ሆኖም ወላጆቹና ዘመዶቹ የሚጠሩት በሌላ ስም ይሆናል። (2 ሳሙ. 12:24, 25) ኢየሱስ፣ አማኑኤል በሚለው ስም ተጠርቶ እንደሚያውቅ የሚያሳይ አንድም ማስረጃ የለም።ኢሳይያስ 7:14ን እና 8:3, 4ን አንብብ።

5. ንጉሥ አካዝ ማስተዋል የጎደለው ውሳኔ አድርጓል የምንለው ለምንድን ነው?

5 እስራኤልና ሶርያ በይሁዳ ላይ ባነጣጠሩበት ወቅት ጠንካራ ወታደራዊ ኃይል ያለው ሌላ መንግሥት ያንኑ አካባቢ ለመቆጣጠር ቋምጦ ነበር። ይህ ወታደራዊ ኃይል የዓለም ኃያል መንግሥት ሆኖ ብቅ ያለው የአሦር መንግሥት ነው። ኢሳይያስ 8:3, 4 እንደሚለው አሦር በስተ ደቡብ የሚገኘውን የይሁዳን መንግሥት ከማጥቃቱ በፊት ‘የደማስቆን ሀብት’ እና ‘የሰማርያን ምርኮ’ ይወስዳል። እምነት የለሹ አካዝ በኢሳይያስ በኩል በተነገረው የአምላክ ቃል ከመታመን ይልቅ ከአሦራውያን ጋር ማስተዋል የጎደለው ስምምነት አደረገ፤ በመሆኑም የኋላ ኋላ ይሁዳ በአሦራውያን የጭቆና ቀንበር ሥር ልትወድቅ ችላለች። (2 ነገ. 16:7-10) የይሁዳ እረኛ የነበረው አካዝ የተጣለበትን ኃላፊነት በአግባቡ ሳይወጣ ቀርቷል! ራሳችንን እንዲህ ብለን መጠየቅ እንችላለን፦ ‘ውሳኔ የሚጠይቅ ከባድ ጉዳይ ሲያጋጥመኝ እምነት የምጥለው በአምላክ ላይ ነው ወይስ በሰው?’—ምሳሌ 3:5, 6

ለየት ያለ አካሄድ የተከተለ አዲስ እረኛ

6. የአካዝንና የሕዝቅያስን አገዛዝ አወዳድር።

6 አካዝ በ746 ዓ.ዓ. ሞቶ ልጁ ሕዝቅያስ ሲነግሥ ይሁዳ በቁሳዊ ተራቁታ፣ በመንፈሳዊም ደህይታ ነበር። ወጣቱ ንጉሥ ዙፋን ላይ ከወጣ በኋላ ቅድሚያ የሚሰጠው ነገር ምን ይሆን? የተንኮታኮተው የይሁዳ ኢኮኖሚ እንዲያንሰራራ ለማድረግ ይጥር ይሆን? በፍጹም። ሕዝቅያስ መንፈሳዊ ሰው ከመሆኑም ሌላ ለሕዝቡ ጥሩ እረኛ ነበር። መጀመሪያ የወሰደው እርምጃ ንጹሑን አምልኮ መልሶ ማቋቋምና ዓመፀኛ የሆነው ብሔር ከይሖዋ ጋር የነበረው የተዳከመ ዝምድና እንዲጠናከር ማድረግ ነበር። ሕዝቅያስ አምላክ ከእሱ የሚጠብቀውን ነገር በተገነዘበ ጊዜ በቆራጥነት እርምጃ ወስዷል። ለእኛ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነው!—2 ዜና 29:1-19

7. ሌዋውያኑ የአዲሱ ንጉሥ ድጋፍ እንደማይለያቸው ማረጋገጫ ማግኘታቸው በጣም ጠቃሚ የነበረው ለምንድን ነው?

7 ሌዋውያኑ ንጹሑን አምልኮ መልሶ በማቋቋሙ ሥራ ወሳኝ ሚና ነበራቸው። በመሆኑም ሕዝቅያስ ከእነሱ ጋር ተገናኝቶ ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው ማረጋገጫ ሰጣቸው። በዚያ ስብሰባ ላይ የተገኙት ታማኝ ሌዋውያን ንጉሡ ‘በፊቱ አገልጋዮቹ እንድትሆኑ ይሖዋ መርጦአችኋል’ ባላቸው ጊዜ የደስታ እንባ በጉንጫቸው ላይ ሲወርድ በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። (2 ዜና 29:11) ሌዋውያኑ ንጹሑን አምልኮ እንዲያራምዱ ግልጽ መመሪያ ተሰጥቷቸው ነበር።

8. ሕዝቅያስ የሕዝቡ መንፈሳዊነት እንዲያንሰራራ ለማድረግ ምን ተጨማሪ እርምጃዎች ወስዷል? ይህስ ምን ውጤት አስገኘ?

8 ሕዝቅያስ ታላቅ የፋሲካ በዓል በማዘጋጀት መላው የይሁዳና የእስራኤል ሕዝብ በበዓሉ ላይ እንዲገኝ ጋበዘ፤ ከዚያም ለሰባት ቀን የሚቆየውን ያልቦካ ቂጣ በዓል አከበሩ። ሕዝቡ በበዓሉ እጅግ ከመደሰቱ የተነሳ በዓሉ ለሌላ ሰባት ቀን ተራዘመ። መጽሐፍ ቅዱስ “ከእስራኤል ንጉሥ ከዳዊት ልጅ ከሰሎሞን ጊዜ አንሥቶ በኢየሩሳሌም እንዲህ ያለ በዓል ተደርጎ ስለማያውቅ፣ በኢየሩሳሌም ታላቅ ደስታ ሆነ” በማለት ይዘግባል። (2 ዜና 30:25, 26) በዚህ መንፈሳዊ ድግስ የተነሳ መላው ሕዝብ እጅግ ተነቃቅቶ ነበር! ሁለተኛ ዜና መዋዕል 31:1 ቀጥሎ የተከናወነውን ነገር እንዲህ ሲል ይገልጻል፦ ‘ይህ ሁሉ ከተፈጸመ በኋላ የማምለኪያ ድንጋዮችን  ሰባበሩ፤ የአሼራ ምስል ዐምዶችን ቈረጡ፤ የኰረብታ መስገጃዎችንና መሠዊያዎችን አጠፉ።’ በመሆኑም የይሁዳ ሕዝብ ከፍተኛ ለውጥ በማድረግ ወደ ይሖዋ ተመለሰ። ወደፊት ከሚመጣው ሁኔታ አንጻር ሲታይ ይህ መንፈሳዊ የማንጻት ሥራ መከናወኑ በጣም አስፈላጊ ነበር።

ንጉሡ ችግር ተደቀነበት

9. (ሀ) የእስራኤል ዕቅድ የከሸፈው እንዴት ነው? (ለ) መጀመሪያ ላይ ሰናክሬም በይሁዳ ምን ስኬት አግኝቶ ነበር?

9 ኢሳይያስ በተናገረው መሠረት አሦራውያን በስተ ሰሜን ያለውን የእስራኤልን መንግሥት ድል አድርገው ነዋሪዎቹን በግዞት ወሰዱ፤ በመሆኑም እስራኤል በዳዊት ዙፋን ላይ የተቀመጠውን ንጉሥ ገልብጣ የዳዊት ዘር ባልሆነ ሰው ለመተካት የነበራት ዕቅድ ከሸፈ። ስለ አሦርስ ዕቅድ ምን ማለት ይቻላል? አሦራውያን በመቀጠል ዓይናቸውን በይሁዳ ላይ ጣሉ። “ሕዝቅያስ በነገሠ በዐሥራ አራተኛው ዓመት፣ የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም የተመሸጉትን የይሁዳን ከተሞች ሁሉ አደጋ ጥሎ ያዛቸው።” ሰናክሬም በጥቅሉ 46 የይሁዳ ከተሞችን ድል እንዳደረገ ዘገባዎች ያሳያሉ። በዚያን ወቅት ኢየሩሳሌም ውስጥ ብትኖር ኖሮ ምን ሊሰማህ እንደሚችል አስብ። የአሦራውያን ሠራዊት በፍጥነት እየገሰገሰ የይሁዳን ከተሞች አንድ በአንድ ድል በማድረግ ወደ ኢየሩሳሌም ተቃርቧል።—2 ነገ. 18:13

10. ሚክያስ 5:5, 6 ላይ የሚገኘው ሐሳብ ሕዝቅያስን አበረታቶት መሆን አለበት የምንለው ለምንድን ነው?

10 ሕዝቅያስ አደጋ እያንዣበበ መሆኑን በሚገባ ተረድቷል፤ ይሁንና ከሃዲ የነበረው አባቱ አካዝ እንዳደረገው የአረማዊ ብሔርን እርዳታ ከመጠየቅ ይልቅ በይሖዋ ታምኗል። (2 ዜና 28:20, 21) በእሱ ዘመን የኖረው ነቢዩ ሚክያስ አሦርን በተመለከተ የተናገረውን የሚከተለውን ትንቢት ሳያውቅ አይቀርም፦ “አሦራዊ ምድራችንን ሲወር፣ . . . ሰባት እረኞችን፣ እንዲያውም ስምንት አለቆችን እናስነሣበታለን። የአሦርን ምድር በሰይፍ . . . ይገዛሉ።” (ሚክ. 5:5, 6) በመንፈስ መሪነት የተነገሩት እነዚህ ቃላት በዓይነቱ ልዩ የሆነ አንድ ሠራዊት በአሦራውያን ላይ እንደሚነሳና ወራሪው ኃይል በመጨረሻ ድል እንደሚደረግ ስለሚያሳዩ ሕዝቅያስን አበረታተውት መሆን አለበት።

11. ስለ ሰባት እረኞችና ስለ ስምንት አለቆች የሚናገረው ትንቢት ዋነኛ ፍጻሜውን የሚያገኘው መቼ ነው?

11 ስለ ሰባት እረኞችና ስለ ስምንት አለቆች የሚናገረው ትንቢት ዋነኛ ወይም የላቀ ፍጻሜውን የሚያገኘው “ከቀድሞ ዘመን የሆነ፣ የእስራኤል ገዥ” የተባለው ኢየሱስ ከተወለደ ከረጅም ጊዜ በኋላ ነው። (ሚክያስ 5:1, 2ን አንብብ።) ይህ የሚፈጸመው የይሖዋ አገልጋዮች ሕልውና በዘመናዊው “አሦራዊ” አደጋ ላይ በሚወድቅበት ጊዜ  ነው። ይሖዋ አስፈሪውን ጠላት ለመጋፈጥ አሁን እየገዛ ባለው ልጁ አማካኝነት የትኛውን ሠራዊት ያንቀሳቅስ ይሆን? የዚህን ጥያቄ መልስ በኋላ ላይ እንመለከታለን። በመጀመሪያ ግን ሕዝቅያስ አሦራውያን እየዛቱ በነበረበት ወቅት ከወሰደው እርምጃ ምን ትምህርት እንደምናገኝ እንመልከት።

ሕዝቅያስ ጥበብ የተንጸባረቀበት እርምጃ ወሰደ

12. ሕዝቅያስና የቅርብ ረዳቶቹ የአምላክን ሕዝብ ከአደጋ ለመጠበቅ ምን እርምጃ ወስደዋል?

12 ይሖዋ እኛ ማድረግ የማንችለውን ነገር ለእኛ ሲል ለማድረግ ምንጊዜም ፈቃደኛ ነው፤ ይሁንና ማድረግ የምንችለውን ነገር እንድናደርግ ይጠብቅብናል። ሕዝቅያስ “ከሹማምንቱና ከጦር አለቆቹ ጋር” ከተማከረ በኋላ “ከከተማዪቱ ውጭ ያሉት የውሃ ምንጮች እንዲዘጉ” ወሰነ። “ከዚህ በኋላም ንጉሡ ጠንክሮ በመሥራት፣ ከቅጥሩ የፈራረሱትን ሁሉ ጠገነ፤ በላዩም ማማ ሠራበት፤ በውጭ በኩልም ሌላ ቅጥር [ገነባ]። . . . እንደዚሁም ብዙ የጦር መሣሪያዎችንና ጋሻዎችን ሠራ።” (2 ዜና 32:3-5) ይሖዋ ሕዝቡን ለመጠበቅና ለመንከባከብ በወቅቱ በነበሩ በርካታ ደፋር ሰዎች የተጠቀመ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ሕዝቅያስ፣ አለቆቹና ታማኝ ነቢያት ይገኙበታል።

13. ሕዝቅያስ ሕዝቡን ለሚሰነዘርባቸው ጥቃት ለማዘጋጀት ከሁሉ ይበልጥ ጠቃሚ የሆነ ምን እርምጃ ወስዷል? አብራራ።

13 ሕዝቅያስ በመቀጠል ያደረገው ነገር ውኃውን ከመዝጋት ወይም የከተማዋን ግንቦች ከማጠናከር የበለጠ ጥቅም ያለው ነበር። ሕዝቅያስ አሳቢ እረኛ እንደመሆኑ መጠን ሕዝቡን ሰብስቦ እንዲህ በማለት አበረታታቸው፦ “ከእኛ ጋር ያለው ከእርሱ ጋር ካለው ስለሚበልጥ፣ የአሦርን ንጉሥና አብሮት ያለውን ብዙ ሰራዊት አትፍሩ፤ አትደንግጡም። ከእነርሱ ጋር ያለው የሥጋ ክንድ ሲሆን፣ ከእኛ ጋር ያለው ግን የሚረዳንና ጠላታችንን የሚዋጋልን አምላካችን እግዚአብሔር ነው።” ይህ እንዴት ያለ እምነት የሚያጠናክር ማሳሰቢያ ነው! በእርግጥም ይሖዋ ለሕዝቡ ይዋጋል። ሕዝቡ ይህን ሲሰማ “የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ በተናገረው ቃል ተበረታታ።” ሕዝቡ እንዲበረታታ ያደረገው ‘ሕዝቅያስ የተናገረው ቃል’ መሆኑን ልብ በሉ። ይሖዋ በነቢዩ አማካኝነት አስቀድሞ እንደተናገረው ሕዝቅያስ፣ አለቆቹና ኃያላኑ ሰዎች እንዲሁም ነቢዩ ሚክያስና ነቢዩ ኢሳይያስ ጥሩ እረኞች መሆናቸውን አስመሥክረዋል።—2 ዜና 32:7, 8፤ ሚክያስ 5:5, 6ን አንብብ።

ሕዝቅያስ የተናገረው ነገር ሕዝቡን አበረታቶት ነበር (አንቀጽ 12ንና 13ን ተመልከት)

14. ራፋስቂስ ምን ለማድረግ ሞክሯል? ሕዝቡስ ምን ምላሽ ሰጠ?

14 የአሦር ንጉሥ ከኢየሩሳሌም በስተ ደቡብ ምዕራብ በምትገኘው በለኪሶ ሰፈረ። ከዚህ ቦታ ሦስት መልእክተኞች በመላክ ከተማዋ እጅ እንድትሰጥ መመሪያ አስተላለፈ። ራፋስቂስ የሚል የማዕረግ ስም ያለው የንጉሡ ቃል አቀባይ የተለያዩ ዘዴዎችን ተጠቅሟል። በዕብራይስጥ ቋንቋ በመናገር ሕዝቡ ንጉሡን እንዲከዳና ለአሦራውያን እጅ እንዲሰጥ ለመገፋፋት ሞክሯል፤ ደግሞም የተደላደለ ኑሮ ወደሚኖሩበት ምድር እንደሚያፈልሳቸው በመግለጽ የውሸት ተስፋ ሰጥቷቸዋል። (2 ነገሥት 18:31, 32ን አንብብ።) ከዚያም ራፋስቂስ የተለያዩ ብሔራት አማልክት አምላኪዎቻቸውን ማስጣል እንዳልቻሉ ሁሉ ይሖዋም አይሁዳውያኑን ከአሦራውያን መዳፍ መታደግ እንደማይችል አስረግጦ ተናገረ። ሕዝቡ ጥበብ የተንጸባረቀበት እርምጃ በመውሰድ በሐሰት ወሬና ክስ ለተሞላው ለዚህ ፕሮፓጋንዳ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥቧል፤ ዛሬም የይሖዋ አገልጋዮች አብዛኛውን ጊዜ ተመሳሳይ ነገር ያደርጋሉ።—2 ነገሥት 18:35, 36ን አንብብ።

15. ከኢየሩሳሌም ነዋሪዎች የሚጠበቀው ነገር ምን ነበር? ይሖዋ ከተማዋን ያዳናት እንዴት ነው?

15 ሕዝቅያስ ሁኔታው እንዳስጨነቀው ግልጽ ነው፤ ይሁንና ከሌላ ብሔር እርዳታ ለማግኘት ከመሞከር ይልቅ ወደ ነቢዩ ኢሳይያስ መልእክተኞች ላከ። ኢሳይያስ ሕዝቅያስን “[ሰናክሬም] ወደዚች ከተማ ፈጽሞ አይገባም፤ አንዲትም ፍላጻ አይወረውርባትም” አለው። (2 ነገ. 19:32) ከኢየሩሳሌም ነዋሪዎች የሚጠበቅ ነገር ቢኖር በአቋማቸው መጽናት ነው። ይሖዋ ለይሁዳ ይዋጋል። ደግሞም ተዋግቷል! “በዚያችም ሌሊት  የእግዚአብሔር መልአክ ወጥቶ ከአሦራውያን ሰፈር መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ ሰው ገደለ።” (2 ነገ. 19:35) የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ሊድኑ የቻሉት ሕዝቅያስ የከተማዋን የውኃ ምንጭ በመዝጋቱ ወይም ቅጥሮቿን በመገንባቱ ሳይሆን በመለኮታዊ ጣልቃ ገብነት ነው።

ለዘመናችን የሚሆን ትምህርት

16. (ሀ) በዛሬው ጊዜ የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች እነማንን ያመለክታሉ? (ለ) ‘አሦራዊው’ ማንን ያመለክታል? (ሐ) ሰባቱ እረኞችና ስምንቱ አለቆች እነማንን ያመለክታሉ?

16 ስለ ሰባት እረኞችና ስምንት አለቆች የሚገልጸው ትንቢት ዋነኛ ፍጻሜውን የሚያገኘው በእኛ ዘመን ነው። በጥንቷ ኢየሩሳሌም ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ከአሦራውያን ጥቃት ተሰንዝሮባቸው ነበር። በቅርቡ ዘመናዊው “አሦራዊ” አቅመ ቢስ መስለው በሚታዩት የይሖዋ ሕዝቦች ላይ ጥቃት ይሰነዝራል፤ የጥቃቱ ዓላማ እነሱን ጠራርጎ ማጥፋት ነው። ቅዱሳን መጻሕፍት ስለዚህ ጥቃት እንዲሁም ‘የማጎጉ ጎግ’ ስለሚሰነዝረው ጥቃት፣ ‘የሰሜኑ ንጉሥ’ ስለሚሰነዝረው ጥቃትና “የምድር ነገሥታት” ስለሚሰነዝሩት ጥቃት ይገልጻሉ። (ሕዝ. 38:2, 10-13፤ ዳን. 11:40, 44, 45፤ ራእይ 17:14፤ 19:19) እነዚህ ራሳቸውን የቻሉ የተለያዩ ጥቃቶች ናቸው? የተለያዩ ጥቃቶች ላይሆኑ ይችላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ አንድን ጥቃት ለማመልከት የተለያየ ስያሜ ሊጠቀም ይችላል። በሚክያስ ትንቢት መሠረት ይሖዋ በዚህ ምሕረት የለሽ ጠላት ይኸውም ‘በአሦራዊው’ ላይ የሚያስነሳው የትኛውን ሠራዊት ነው? ፈጽሞ የማይታሰብ ሠራዊት ይኸውም “ሰባት እረኞችን፣ እንዲያውም ስምንት አለቆችን” እንደሚጠቀም ትንቢቱ ይጠቁማል። (ሚክ. 5:5) እነዚህ እረኞችና አለቆች የጉባኤ ሽማግሌዎች ናቸው። (1 ጴጥ. 5:2) በዛሬው ጊዜ ይሖዋ ውድ በጎቹን እረኛ ሆነው የሚጠብቁ በርካታ መንፈሳዊ ወንዶችን ያስነሳ ሲሆን ይህን ያደረገው ወደፊት ዘመናዊው “አሦራዊ” ለሚሰነዝረው ጥቃት ሕዝቡ ከወዲሁ ተጠናክሮ እንዲቆይ ለማድረግ ነው። * ሚክያስ የተናገረው ትንቢት እረኞቹ ‘የአሦርን ምድር በሰይፍ እንደሚገዙ’ ይገልጻል። (ሚክ. 5:6) ‘ከጦር መሣሪያዎቻቸው’ መካከል ‘የመንፈስ ሰይፍ’ ይኸውም የአምላክ ቃል ይገኝበታል።—2 ቆሮ. 10:4፤ ኤፌ. 6:17

17. ሽማግሌዎች እስካሁን ከተብራራው ሐሳብ ሊጨብጧቸው የሚችሉ አራት ነጥቦች ምንድን ናቸው?

17 ይህን ርዕስ እያነበቡ ያሉ ሽማግሌዎች እስካሁን ከተብራራው ሐሳብ ሊጨብጧቸው የሚችሉ አንዳንድ ጠቃሚ ነጥቦች አሉ፦ (1) ወደፊት ‘አሦራዊው’ ለሚሰነዝረው ጥቃት ከወዲሁ ለመዘጋጀት ልንወስደው የምንችለው ከሁሉ የተሻለ እርምጃ በአምላክ ላይ ያለንን እምነት ማጠናከርና ወንድሞቻችንም ተመሳሳይ ነገር እንዲያደርጉ መርዳት ነው። (2) ‘አሦራዊው’ ጥቃት በሚሰነዝርበት ጊዜ ሽማግሌዎች ይሖዋ እንደሚታደገን ሙሉ እምነት ሊኖራቸው ይገባል። (3) በዚያን ወቅት ከይሖዋ ድርጅት የምናገኘው ለመዳን የሚያበቃ መመሪያ ከሰብዓዊ አመለካከት አንጻር የሚያዋጣ ላይመስል ይችላል። መመሪያው ከሰብዓዊ አመለካከትም ሆነ ከስትራቴጂ አንጻር አሳማኝ መስሎ ታየንም አልታየን ማንኛውንም መመሪያ ለመታዘዝ ሁላችንም ዝግጁ መሆን ይኖርብናል። (4) ትምክህታቸውን በዓለማዊ ትምህርት፣ በቁሳዊ ነገሮች ወይም በሰብዓዊ ተቋማት ላይ የጣሉ ሁሉ አስተሳሰባቸውን ማስተካከል የሚችሉበት ጊዜ አሁን ነው። ሽማግሌዎች እምነታቸው እየተዳከመ ላለ ሁሉ እርዳታ ለመስጠት ምንጊዜም ዝግጁ መሆን አለባቸው።

18. በዚህ ዘገባ ላይ ማሰላሰላችን ወደፊት ሊጠቅመን የሚችለው እንዴት ነው?

18 በዚህ ዘመን ያሉ የአምላክ አገልጋዮች፣ በሕዝቅያስ ዘመን ኢየሩሳሌም ውስጥ እንደነበሩት መውጫ ያጡ አይሁዳውያን አቅመ ቢስ መስለው የሚታዩበት ጊዜ ይመጣል። በዚያን ጊዜ፣ ሕዝቅያስ የተናገራቸው ቃላት ሁላችንንም ሊያበረታቱን ይችላሉ። ከጠላቶቻችን “ጋር ያለው የሥጋ ክንድ ሲሆን፣ ከእኛ ጋር ያለው ግን የሚረዳንና ጠላታችንን የሚዋጋልን አምላካችን” ይሖዋ መሆኑን ፈጽሞ አንዘንጋ!—2 ዜና 32:8

^ አን.4 በኢሳይያስ 7:14 ላይ “ድንግል” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጡ ቃል ያገባችንም ሴት ሊያመለክት ይችላል። በመሆኑም ይህ ቃል የኢሳይያስን ሚስትም ሆነ አይሁዳዊቷን ድንግል ማርያምን ሊያመለክት ይችላል።

^ አን.16 በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ሰባት ቁጥር አብዛኛውን ጊዜ ሙላትን ለማመልከት ተሠርቶበታል። ከሰባት በአንድ የሚበልጠው ስምንት ቁጥር ደግሞ አንዳንድ ጊዜ ብዛትን ያመለክታል።