በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋን እረኞች ታዘዙ

የይሖዋን እረኞች ታዘዙ

“ነፍሳችሁን ተግተው ስለሚጠብቁ . . . በመካከላችሁ ግንባር ቀደም ሆነው አመራር ለሚሰጧችሁ ታዘዙ እንዲሁም ተገዙ።”—ዕብ. 13:17

1, 2. ይሖዋ ራሱን ከእረኛ ጋር ያመሳሰለው ለምንድን ነው?

ይሖዋ ራሱን ከእረኛ ጋር አመሳስሎ ገልጿል። (ሕዝ. 34:11-14) ይህ አገላለጽ ይሖዋ ምን ዓይነት አምላክ እንደሆነ እንድንገነዘብ ይረዳናል። አፍቃሪ የሆነ አንድ ሰብዓዊ እረኛ በእሱ ሥር ያሉትን በጎች የመጠበቅና የመንከባከብ ሙሉ ኃላፊነት እንዳለበት ያውቃል። የግጦሽ ሣርና ውኃ ወዳለበት ቦታ ይወስዳቸዋል (መዝ. 23:1, 2)፤ ቀን ከሌት ይጠብቃቸዋል (ሉቃስ 2:8)፤ ከአዳኝ አውሬዎች ይታደጋቸዋል (1 ሳሙ. 17:34, 35)፤ ግልገሎቹን ይሸከማል (ኢሳ. 40:11)፤ የባዘኑትን ይፈልጋል እንዲሁም የተጎዱትን ይንከባከባል።—ሕዝ. 34:16

2 በጥንት ዘመን የነበሩት የይሖዋ ሕዝቦች በዋነኛነት በከብት እርባታና በግብርና ሥራ በሚተዳደር ኅብረተሰብ ውስጥ ይኖሩ ስለነበር ይሖዋ አምላክ ራሱን ከአንድ አፍቃሪ እረኛ ጋር ማመሳሰሉ ያለውን ትልቅ ትርጉም በሚገባ ይገነዘቡ ነበር። በጎች ተመችቷቸው እንዲያድጉ እንክብካቤ ሊደረግላቸውና ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ ያውቃሉ። በመንፈሳዊ ሁኔታም ሰዎች ተመሳሳይ ትኩረት ያሻቸዋል። (ማር. 6:34) ሰዎች ጥሩ የሆነ መንፈሳዊ እንክብካቤና አመራር ካላገኙ ይጎዳሉ። እረኛ ወይም ‘ጠባቂ የሌላቸው በጎች’ እንደሚበታተኑ ሁሉ ሰዎችም እንዲህ ያለ አመራር ካላገኙ ለአደጋ የተጋለጡ ይሆናሉ ብሎም ከትክክለኛው ጎዳና ይርቃሉ። (1 ነገ. 22:17) ሆኖም ይሖዋ በፍቅር ተገፋፍቶ ለሕዝቡ የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ ያሟላል።

3. በዚህ የጥናት ርዕስ ምን እንመረምራለን?

3 ይሖዋ ራሱን እንደ እረኛ አድርጎ መግለጹ በእኛም ዘመን ቢሆን ትልቅ ትርጉም አለው። ዛሬም ቢሆን ይሖዋ በበግ የተመሰሉትን ሕዝቦቹን ይንከባከባል። በአሁኑ ጊዜ በጎቹን የሚመራውና የሚያስፈልጋቸውን ነገር የሚያሟላው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት። በተጨማሪም በጎቹ ይሖዋ ለሚያሳያቸው ፍቅራዊ አሳቢነት ምን ምላሽ መስጠት እንዳለባቸው እንመረምራለን።

ጥሩው እረኛ የበታች እረኞችን ሾሟል

4. ኢየሱስ የይሖዋን በጎች በመንከባከብ ረገድ ምን ሚና ይጫወታል?

4 ይሖዋ ኢየሱስን የክርስቲያን ጉባኤ ራስ አድርጎ ሾሞታል። (ኤፌ. 1:22, 23) ኢየሱስ “ጥሩ እረኛ” እንደመሆኑ መጠን  የአባቱን ፍላጎት፣ ዓላማና ባሕርያት ያንጸባርቃል። እንዲያውም ኢየሱስ “ነፍሱን ለበጎቹ ሲል አሳልፎ” ሰጥቷል። (ዮሐ. 10:11, 15) ኢየሱስ የከፈለው ቤዛዊ መሥዋዕት ለሰው ዘር ትልቅ ስጦታ ነው! (ማቴ. 20:28) ይሖዋ “[በኢየሱስ] እንደሚያምን በተግባር የሚያሳይ ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ” እንዲጠፋ አይፈልግም።—ዮሐ. 3:16

5, 6. (ሀ) ኢየሱስ በጎቹን እንዲንከባከቡ እነማንን ሾሟል? በጎቹ ከዚህ ዝግጅት እንዲጠቀሙ ምን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል? (ለ) የጉባኤ ሽማግሌዎችን እንድንታዘዝ የሚያነሳሳን ዋነኛው ምክንያት ምን መሆን አለበት?

5 በጎቹ ጥሩ እረኛ ለሆነው ለኢየሱስ ክርስቶስ ምላሽ የሚሰጡት እንዴት ነው? ኢየሱስ “በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ፤ እኔም አውቃቸዋለሁ፤ እነሱም ይከተሉኛል” ሲል ተናግሯል። (ዮሐ. 10:27) ጥሩ እረኛ የሆነውን የኢየሱስን ድምፅ መስማት በማንኛውም ሁኔታ የእሱን አመራር መከተል ማለት ነው። ይህም እሱ ከሾማቸው መንፈሳዊ የበታች እረኞች ጋር መተባበርን ይጨምራል። ኢየሱስ ሐዋርያቱና ደቀ መዛሙርቱ እሱ የጀመረውን ሥራ ማከናወናቸውን እንደሚቀጥሉ አመልክቷል። የእሱን ‘ግልገሎች እንዲመግቡ’ እና ‘እንዲያስተምሩ’ አዟቸዋል። (ማቴ. 28:20፤ ዮሐንስ 21:15-17ን አንብብ።) ምሥራቹ እየተስፋፋና የደቀ መዛሙርቱ ቁጥር እየጨመረ ሲሄድ ኢየሱስ የጎለመሱ ክርስቲያኖች እረኛ ሆነው ጉባኤዎቹን እንዲንከባከቡ ዝግጅት አደረገ።—ኤፌ. 4:11, 12

6 ሐዋርያው ጳውሎስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩትን የኤፌሶን ጉባኤ የበላይ ተመልካቾች ባነጋገረበት ወቅት ‘የአምላክን ጉባኤ እንዲጠብቁ’ መንፈስ ቅዱስ የበላይ ተመልካቾች አድርጎ እንደሾማቸው ገልጾላቸው ነበር። (ሥራ 20:28) ዛሬም ቢሆን ሁኔታው ተመሳሳይ ነው፤ በአሁኑ ጊዜ ያሉት ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾችም የሚሾሙት በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የተጻፉትን ቅዱስ ጽሑፋዊ ብቃቶች አሟልተው ነው። በመሆኑም ለክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች መታዘዛችን ለሁለቱ ታላላቅ እረኞች ማለትም ለይሖዋና ለኢየሱስ አክብሮት እንዳለን ያሳያል። (ሉቃስ 10:16) ለሽማግሌዎች እንድንገዛ የሚያነሳሳን ዋነኛው ምክንያት ይህ መሆን አለበት። ይሁንና እንዲህ እንድናደርግ የሚያነሳሱ ሌሎች ምክንያቶችም አሉ።

7. ሽማግሌዎች ከይሖዋ ጋር ጥሩ ዝምድና ይዘህ እንድትኖር የሚረዱህ እንዴት ነው?

7 ሽማግሌዎች ለእምነት ባልንጀሮቻቸው አመራር በሚሰጡበት ጊዜ በቀጥታ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመረኮዘ አሊያም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በሰፈሩ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ የተመሠረተ ማበረታቻና ምክር ያካፍላሉ። እንዲህ ያለ አመራር በሚሰጡበት ጊዜ ዓላማቸው ወንድሞቻቸው ሕይወታቸውን እንዴት ሊመሩ እንደሚገባ መመሪያ መስጠት አይደለም። (2 ቆሮ. 1:24) ከዚህ ይልቅ ዓላማቸው ክርስቲያን ባልንጀሮቻቸው ጥሩ ውሳኔዎች ማድረግ እንዲችሉ የሚረዱ ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያዎችን ማካፈልና በጉባኤው ውስጥ ሥርዓትና ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ ነው። (1 ቆሮ. 14:33, 40) ሽማግሌዎች ‘ነፍሳችሁን ይጠብቃሉ’ ሲባል እያንዳንዱ የጉባኤ አባል ከይሖዋ ጋር ጥሩ ዝምድና ይዞ እንዲኖር መርዳት ይፈልጋሉ ማለት ነው። በመሆኑም አንድ ወንድም ወይም አንዲት እህት “የተሳሳተ እርምጃ” ሊወስዱ መሆኑን ወይም መውሰዳቸውን በሚረዱበት ጊዜ ቶሎ እርዳታ ለመስጠት ጥረት ያደርጋሉ። (ገላ. 6:1, 2፤ ይሁዳ 22) እነዚህ ነጥቦች “ግንባር ቀደም ሆነው አመራር” የሚሰጡንን ወንድሞች እንድንታዘዝ የሚያነሳሱ አጥጋቢ ምክንያቶች አይደሉም?—ዕብራውያን 13:17ን አንብብ።

8. ሽማግሌዎች የአምላክን መንጋ የሚጠብቁት እንዴት ነው?

8 መንፈሳዊ እረኛ የነበረው ሐዋርያው ጳውሎስ በቆላስይስ ለነበሩት ወንድሞች እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በክርስቶስ ላይ ሳይሆን በዓለም መሠረታዊ ነገሮች እንዲሁም በሰው ወግ ላይ በተመሠረተ ፍልስፍናና ከንቱ ማታለያ ማንም አጥምዶ እንዳይወስዳችሁ ተጠንቀቁ።” (ቆላ. 2:8) ይህ ማስጠንቀቂያ ሽማግሌዎች የሚሰጡንን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ተግባራዊ እንድናደርግ የሚያነሳሳንን ሌላ ምክንያት ይጠቁመናል። ሽማግሌዎች የጉባኤው አባላት እምነታቸውን ለመሸርሸር ከሚሞክሩ ሰዎች እንዲርቁ በመርዳት መንጋውን ይጠብቃሉ። ሐዋርያው ጴጥሮስ ‘ጸንተው ያልቆሙትን ነፍሳት በማማለል’ ኃጢአት እንዲሠሩ ለማድረግ የሚሞክሩ “ሐሰተኛ ነቢያት” እና “ሐሰተኛ አስተማሪዎች” እንደሚነሱ አስጠንቅቋል። (2 ጴጥ.  2:1, 14) በዛሬው ጊዜ ያሉ ሽማግሌዎችም አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ተመሳሳይ ማስጠንቀቂያ መስጠት አለባቸው። የጎለመሱ ክርስቲያን ወንዶች እንደመሆናቸው መጠን የሕይወት ተሞክሮ አላቸው። በተጨማሪም ከመሾማቸው በፊት የጠራ የቅዱሳን ጽሑፎች እውቀት እንዳላቸውና ጤናማውን ትምህርት ለማስተማር ብቁ እንደሆኑ አስመሥክረዋል። (1 ጢሞ. 3:2፤ ቲቶ 1:9) ጉልምስናቸው፣ ሚዛናዊነታቸውና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተው ጥበባቸው ለመንጋው ጥሩ አመራር እንዲሰጡ ያስችላቸዋል።

አንድ እረኛ መንጋውን እንደሚጠብቅ ሁሉ ሽማግሌዎችም በአደራ የተሰጧቸውን በጎች ይጠብቃሉ (አንቀጽ 8ን ተመልከት)

ጥሩው እረኛ በጎቹን ይመግባል እንዲሁም ይጠብቃል

 

9. በአሁኑ ጊዜ ኢየሱስ የክርስቲያን ጉባኤን የሚመራውና የሚመግበው እንዴት ነው?

9 ይሖዋ በድርጅቱ በኩል ዓለም አቀፍ ለሆነው የወንድማማች ማኅበር የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ ያቀርባል። በጽሑፎቻችን አማካኝነት ብዙ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር እናገኛለን። ከዚህም ሌላ ድርጅቱ በደብዳቤዎች አሊያም በተጓዥ የበላይ ተመልካቾች በኩል በሚተላለፉ መመሪያዎች አማካኝነት በቀጥታ ለሽማግሌዎች አመራር የሚሰጥባቸው ጊዜያት አሉ። በእነዚህ መንገዶች በጎቹ ግልጽ የሆነ መመሪያ ያገኛሉ።

10. መንፈሳዊ እረኞች ከመንጋው ርቀው የባዘኑትን በተመለከተ ምን ኃላፊነት አለባቸው?

10 የበላይ ተመልካቾች የእያንዳንዱን የጉባኤ አባል በተለይ ደግሞ ራሳቸውን ለችግር ያጋለጡትን ወይም በመንፈሳዊ የታመሙትን ወንድሞችና እህቶች መንፈሳዊ ጤንነት የመጠበቅና የመንከባከብ ኃላፊነት አለባቸው። (ያዕቆብ 5:14, 15ን አንብብ።) ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ ከመንጋው ርቀው እየባዘኑ ሊሆን ይችላል፤ ደግሞም በክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎች መካፈል አቁመው ይሆናል።  እንዲህ ያለ ሁኔታ በሚከሰትበት ጊዜ አሳቢ የሆነ ሽማግሌ እያንዳንዱን የጠፋ በግ ለማግኘትና ወደ መንጋው ማለትም ወደ ጉባኤ እንዲመለስ ለማበረታታት አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ እንደሚያደርግ ጥርጥር የለውም! ኢየሱስ “በሰማይ ያለው አባቴ ከእነዚህ ከታናናሾቹ መካከል አንዱም እንዲጠፋ አይፈልግም” ሲል ገልጿል።—ማቴ. 18:12-14

የበታች እረኞችን ጉድለት በተመለከተ ምን አመለካከት ሊኖረን ይገባል?

11. አንዳንዶች የሽማግሌዎችን አመራር መከተል ፈታኝ ሊሆንባቸው የሚችለው ለምንድን ነው?

11 ይሖዋና ኢየሱስ ፍጹም እረኞች ናቸው። ጉባኤዎችን ለመንከባከብ የሚጠቀሙባቸው ሰብዓዊ የበታች እረኞች ግን ፍጹማን አይደሉም። ይህ እውነታ አንዳንዶች የሽማግሌዎችን አመራር መከተል ፈታኝ እንዲሆንባቸው ሊያደርግ ይችላል። እነዚህ ወንድሞች ‘እነሱም እንደ እኛው ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎች ናቸው። የእነሱን ምክር የምንሰማበት ምን ምክንያት አለ?’ ብለው ያስቡ ይሆናል። ሽማግሌዎች ፍጹማን እንዳልሆኑ አይካድም። ይሁን እንጂ እነሱ ያለባቸውን ጉድለትና ድክመት በተመለከተ ትክክለኛ አመለካከት ሊኖረን ይገባል።

12, 13. (ሀ) ቀደም ባሉት ጊዜያት አምላክ የሾማቸው አገልጋዮች ምን ስህተት ሠርተዋል? (ለ) ኃላፊነት የነበራቸው ሰዎች የሠሯቸው ስህተቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመዘገቡት ለምንድን ነው?

12 ቀደም ባሉት ጊዜያት ይሖዋ ሕዝቡን ለመምራት የተጠቀመባቸው ሰዎች የነበረባቸውን ጉድለት ቅዱሳን መጻሕፍት በግልጽ ይናገራሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ዳዊት የእስራኤል ንጉሥና መሪ እንዲሆን ተቀብቶ ነበር። ይሁንና በፈተና ተሸንፎ የወደቀ ሲሆን ምንዝርና ነፍስ ግድያ ፈጽሟል። (2 ሳሙ. 12:7-9) በተጨማሪም የሐዋርያው ጴጥሮስን ሁኔታ እንመልከት። በመጀመሪያው መቶ ዘመን በነበረው የክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ትልቅ ኃላፊነት የነበረው ቢሆንም ከባድ ስህተቶች ሠርቷል። (ማቴ. 16:18, 19፤ ዮሐ. 13:38፤ 18:27፤ ገላ. 2:11-14) አዳምና ሔዋን ከኖሩበት ዘመን አንስቶ ከኢየሱስ በቀር ፍጹም የሆነ ሰው ኖሮ አያውቅም።

13 ይሖዋ የሾማቸው አገልጋዮቹ የፈጸሙትን ስህተት የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች እንዲጽፉ ያደረገው ለምንድን ነው? አምላክ ይህን ያደረገበት አንዱ ምክንያት ሕዝቡን ለመምራት ፍጹም ያልሆኑ ሰዎችን መጠቀም እንደሚችል ለማሳየት ነው። እንዲያውም መቼም ቢሆን ሕዝቡን የመራው ፍጹም ያልሆኑ ሰዎችን ተጠቅሞ ነው። በመሆኑም በዛሬው ጊዜ አመራር እየሰጡን ያሉት ወንድሞች አለፍጽምና በእነሱ ላይ ለማጉረምረም ወይም ሥልጣናቸውን ለመናቅ ሰበብ ሊሆነን አይገባም። ይሖዋ እንዲህ ያሉ ወንድሞችን እንድናከብራቸውና እንድንታዘዛቸው ይጠብቅብናል።ዘፀአት 16:2, 8ን አንብብ።

14, 15. በጥንት ዘመን ይሖዋ ለሕዝቡ መመሪያ ከሰጠበት መንገድ ምን ትምህርት እናገኛለን?

14 በዛሬው ጊዜ አመራር እየሰጡን ላሉት ወንድሞች መታዘዝ በጣም አስፈላጊ ነው። በጥንት ዘመን ይሖዋ አስቸጋሪ በሆኑ ወቅቶች ለሕዝቡ እንዴት መመሪያ ይሰጥ እንደነበር እስቲ ለማሰብ ሞክር። እስራኤላውያን የጥንቷን ግብፅ ለቀው በወጡ ጊዜ የአምላክን መመሪያ ያገኙ የነበረው በሙሴና በአሮን በኩል ነበር። እስራኤላውያን ከአሥረኛው መቅሰፍት ለመዳን ልዩ እራት እንዲያዘጋጁ እንዲሁም የታረደውን በግ ደም ወስደው በቤታቸው ደጃፍ ላይ የሚገኘውን መቃንና ጉበን እንዲቀቡ የተሰጣቸውን መመሪያ ተግባራዊ ማድረግ ነበረባቸው። ይህን መመሪያ ያገኙት በቀጥታ ከሰማይ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ የእስራኤልን ሕዝብ አለቆች መስማት ይጠበቅባቸው ነበር፤ እነዚህ አለቆች ደግሞ ዝርዝር መመሪያዎችን ያገኙት በሙሴ በኩል ነበር። (ዘፀ. 12:1-7, 21-23, 29) በዚያን ጊዜ ይሖዋ ለሕዝቡ መመሪያዎችን ለማስተላለፍ ሙሴንና የሕዝቡን አለቆች ተጠቅሟል። በዛሬው ጊዜም ክርስቲያን ሽማግሌዎች ተመሳሳይ ሚና ይጫወታሉ።

15 ይሖዋ ሕይወት አድን የሆኑ መመሪያዎችን በሰዎች ወይም በመላእክት አማካኝነት እንዳስተላለፈ የሚገልጹ ሌሎች በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን ታስታውስ ይሆናል። በእነዚህ ሁሉ ጊዜያት አምላክ ለወኪሎቹ ሥልጣን ሰጥቷቸዋል። መልእክተኞቹ በስሙ ይናገሩ የነበረ ከመሆኑም  ሌላ ሕዝቡ በአስቸጋሪ ጊዜያት ሕይወታቸውን ለማዳን ምን ማድረግ እንዳለባቸው ይነግሯቸው ነበር። ይሖዋ አርማጌዶን ሲመጣ ተመሳሳይ ነገር ሊያደርግ ይችላል ብለን መጠበቃችን ምክንያታዊ አይሆንም? እርግጥ ነው፣ በዛሬው ጊዜ ይሖዋን ወይም ድርጅቱን ወክለው የመሥራት ኃላፊነት የተሰጣቸው ሽማግሌዎች ሁሉ ሥልጣናቸውን አላግባብ እንዳይጠቀሙበት ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል።

“አንድ መንጋ ይሆናሉ፤ እረኛውም አንድ”

16. ትኩረት ሰጥተን ማዳመጥ የሚኖርብን የትኛውን “ድምፅ” ነው?

16 የይሖዋ ሕዝቦች ‘በአንድ እረኛ’ ይኸውም በኢየሱስ ክርስቶስ የሚመሩ “አንድ መንጋ” ናቸው። (ዮሐ. 10:16) ኢየሱስ “እስከ ሥርዓቱ መደምደሚያ ድረስ ሁልጊዜ” ከደቀ መዛሙርቱ ጋር እንደሚሆን ተናግሮ ነበር። (ማቴ. 28:20) በሰማይ ያለ ንጉሥ እንደመሆኑ መጠን የሰይጣንን ዓለም ከማጥፋቱ በፊት ደረጃ በደረጃ የሚከናወኑትን ነገሮች ሙሉ በሙሉ የመቆጣጠር ሥልጣን አለው። በአምላክ መንጋ ውስጥ አንድነታችንና ደህንነታችን ተጠብቆ መኖር እንድንችል በየትኛው መንገድ መሄድ እንዳለብን የሚነግረንን ‘ከኋላችን የሚሰማውን ድምፅ’ መታዘዝ አለብን። ይህ “ድምፅ” በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተገለጸውን የአምላክ ቅዱስ መንፈስ የሚናገረውን ሐሳብ እንዲሁም ይሖዋና ኢየሱስ የበታች እረኞች አድርገው በሾሟቸው ሰዎች አማካኝነት የሚናገሩትን ቃል ይጨምራል።ኢሳይያስ 30:21ን እና ራእይ 3:22ን አንብብ።

ሽማግሌዎች በነጠላ ወላጅ የሚተዳደሩ ቤተሰቦችን መጥፎ ከሆነ ወዳጅነት ለመጠበቅ ጥረት ያደርጋሉ (አንቀጽ 17ንና 18ን ተመልከት)

17, 18. (ሀ) የአምላክ መንጋ ምን አደጋ ተደቅኖበታል? ይሁንና ስለ ምን ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን እንማራለን?

17 መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሰይጣን “የሚውጠውን በመፈለግ እንደሚያገሳ አንበሳ ይንጎራደዳል” ሲል ይገልጻል። (1 ጴጥ. 5:8) ሰይጣን እጅግ እንደተራበ የዱር አውሬ የተዘናጉትን ወይም ከመንጋው ርቀው የባዘኑትን አድኖ ለመያዝ ምቹ የሆነውን ጊዜ አድብቶ ይጠባበቃል። ከቀሩት የመንጋው አባላት ጋርም ሆነ ‘ከነፍሳችን እረኛና የበላይ ተመልካች’ ጋር እጅግ ተቀራርበን እንድንኖር ሊያነሳሳን የሚገባው አንዱ ዋና ምክንያት ይህ ነው። (1 ጴጥ. 2:25) ታላቁን መከራ በሕይወት የሚያልፉ ሰዎችን በተመለከተ ራእይ 7:17 እንዲህ ይላል፦ “በጉ [ኢየሱስ] እረኛቸው ይሆናል፤ ወደ ሕይወት ውኃ ምንጭም ይመራቸዋል። አምላክም እንባን ሁሉ ከዓይኖቻቸው ላይ ይጠርጋል።” ከዚህ የተሻለ ምን ተስፋ ሊኖር ይችላል?

18 ክርስቲያን ሽማግሌዎች መንፈሳዊ የበታች እረኞች ሆነው የሚጫወቱትን ወሳኝ ሚና ተመልክተናል፤ በመሆኑም ‘እነዚህ የተሾሙ ወንዶች የኢየሱስን በጎች በተገቢው መንገድ መያዝ የሚችሉት እንዴት ነው?’ ብለን መጠየቃችን የተገባ ነው። የሚቀጥለው የጥናት ርዕስ ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሰጣል።