በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እውነተኛው የሕይወት ትርጉም ምንድን ነው?

እውነተኛው የሕይወት ትርጉም ምንድን ነው?

እውነተኛው የሕይወት ትርጉም ምንድን ነው?

የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪና የ17 ዓመት ወጣት የሆነው ጄሲ የሕይወት ትርጉም ምን እንደሆነ ሲጠየቅ “እስትንፋስህ እስካለች ድረስ የቻልከውን ያህል ተደሰት” በማለት መልሷል። ሱዚ ደግሞ ከዚህ የተለየ አመለካከት አላት። “እንደ እኔ እምነት የሕይወት ትርጉም አንተው እንዳደረግከው የሚሆን ነው” ብላለች።

አንተስ ስለ ሕይወት ትርጉም አስበህ ታውቃለህ? ለመላው የሰው ዘር የሚሆን አንድ የሕይወት ዓላማ ይኖር ይሆን? ወይስ ሱዚ እንዳለችው የሕይወት ትርጉም እኛው እንዳደረግነው የሚሆን ነው? የምንኖርበት ኅብረተሰብ በቴክኖሎጂ የደረሰበት የእድገት ደረጃ ምንም ይሁን ምን የሕይወትን ትርጉም የማወቅ ተፈጥሯዊ ፍላጎት አለን። አብዛኞቻችን በሕይወታችን ውስጥ በአንድ ወቅት ላይ ‘በሕይወት የምንኖረው ለምንድን ነው?’ ብለን መጠየቃችን አይቀርም።

ዘመናዊ ሳይንስ የዚህን ጥያቄ መልስ ለማግኘት ያላደረገው ጥረት የለም። ታዲያ ምን መልስ አገኘ? የሥነ ልቡና እና የሥነ እንስሳት ፕሮፌሰር የሆኑት ዴቪድ ባረሽ “በዝግመተ ለውጥ ሒደት ውስጥ ሕይወት ይህ ነው የሚባል ትርጉም የለውም” በማለት ተናግረዋል። በዝግመተ ለውጥ የሚያምኑ የሥነ ሕይወት ሊቃውንት ሕይወት ያላቸው ነገሮች ዓላማቸው በሕይወት መቆየትና መራባት ብቻ ነው ብለው ያምናሉ። በመሆኑም ፕሮፌሰር ባረሽ እንዲህ የሚል አስተያየት ሰጥተዋል፦ “ዓላማ በሌለውና ለሰዎች ደንታ ቢስ በሆነው በዚህ እጅግ ሰፊ አጽናፈ ዓለም ውስጥ በማሰብ ችሎታችን ተጠቅመን በነፃነት፣ ሆነ ብለን በምናደርጋቸው ምርጫዎች አማካኝነት ሕይወታችን ትርጉም እንዲኖረው ማድረግ የእኛ ፋንታ ነው።”

የመኖራችን ዓላማና ትርጉም ምንጭ

የሕይወት ትርጉሙ እያንዳንዱ ሰው የፈለገውን ማደረጉ ነውን? አምላክ ዓላማና ትርጉም በሌለው ጽንፈ ዓለም ውስጥ ያለ ዓላማ እንድንባዝን አልተወንም። ከዚህ ይልቅ በዚህ ምድር ላይ የተፈጠርንበት ዓላማ እንዳለን መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ወደ ሕልውና የመጣነው እንዲያው በአጋጣሚ አይደለም። ፈጣሪ ምድርን ለሰው ልጆች መኖሪያነት ለማዘጋጀት በርካታ ዘመናት እንደወሰደበት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። በአጋጣሚ የተገኘ አንዳች ነገር የለም። አምላክ እያንዳንዱን ነገር “እጅግ መልካም” አድርጎ ፈጥሯል። (ዘፍጥረት 1:31፤ ኢሳይያስ 45:18) ለምን? አምላክ ለሰው ዓላማ ስለነበረው ነው።

ደስ የሚለው ግን አምላክ በቀጥታ ጣልቃ በመግባትም ይሁን በአንድ ዓይነት ተፈጥሯዊ ሒደት አማካኝነት የእያንዳንዱን ግለሰብ የወደፊት ዕጣ አስቀድሞ አልወሰነም። በዘር የወረስናቸው ነገሮች ተጽዕኖ የሚያሳድሩብን ቢሆንም በአብዛኛው የምናደርጋቸውን ነገሮች አስበን ማድረግ እንችላለን። የሕይወት አቅጣጫችንን የመምረጥ ነጻነት አለን።

በሕይወታችን የፈለግነውን የማድረግ ነጻነት ቢኖረንም ውሳኔ በምናደርግበት ጊዜ አምላክን ግምት ውስጥ አለማስገባታችን ትልቅ ስህተት ይሆንብናል። እንደ እውነቱ ከሆነ ብዙዎች እውነተኛው የሕይወት ትርጉምና ዓላማ ከአምላክ ጋር ካለን ዝምድና ጋር የተቆራኘ እንደሆነ ተገንዝበዋል። ቃል በቃል ሲተረጎም “ይሆናል” የሚል ፍቺ ያለው ይሖዋ የሚለው የአምላክ የግል ስም በአምላክና በሕይወት ትርጉም መካከል ያለውን ግንኙነት ጎላ አድርጎ ይገልጻል። (ዘፀአት 6:3 የ1879 ትርጉም፤ መዝሙር 83:18 NW) ስሙ፣ አምላክ ቃል የገባውን ሁሉ ደረጃ በደረጃ ይፈጽማል እንዲሁም ዓላማውን ምንጊዜም ከዳር ያደርሳል ማለት ነው። (ዘፀአት 3:14 NW፤ ኢሳይያስ 55:10, 11) እስቲ ስሙ ስላለው ትርጉም ቆም ብለህ አስብ። ይሖዋ የሚለው ስም የእውነተኛው ሕይወት ዓላማ ምንጭ እርሱ ብቻ መሆኑን ያረጋግጥልናል።

አንድ ሰው የፈጣሪን ሕልውና መቀበሉ ብቻ እንኳ ሕይወትን በሚመለከት ባለው አመለካከት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራል። የ19 ዓመቷ ሊኔት “ይሖዋ የፈጠራቸውን አስደናቂ ነገሮች ሁሉ መመልከቴና የተፈጠሩበትን ዓላማ መገንዘቤ እኔም የተፈጠርኩት በዓላማ እንደሆነ እንድገነዘብ ያደርገኛል” ትላለች። አምበር ደግሞ እንዲህ ትላለች፦ “ሰዎች ‘አምላክ መኖር አለመኖሩን’ እንደማያውቁ ሲናገሩ መስማቴ እኔ ማወቄን እንዳደንቅ ያደርገኛል። የፈጠራቸው ነገሮች ብቻ እንኳ ይሖዋ ስለመኖሩ ማስረጃ ይሆናሉ።” (ሮሜ 1:20) እርግጥ ነው፣ ፈጣሪ መኖሩን መቀበልና ከእርሱ ጋር ትርጉም ያለው ወዳጅነት መመሥረት ሁለት የተለያዩ ነገሮች ናቸው።

ከአምላክ ጋር ወዳጅነት መመሥረት

መጽሐፍ ቅዱስ በዚህም ረገድ ሊረዳን ይችላል። የመጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያ ምዕራፎች ይሖዋ አምላክ አፍቃሪ አባት ስለመሆኑ ግልጽ ማስረጃ ይሰጡናል። ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋ አዳምንና ሔዋንን ፈጥሮ የፈጣሪያቸውን ማንነት በራሳቸው ጥረት እንዲደርሱበት አላደረገም። ከዚህ ይልቅ በየጊዜው ያነጋግራቸው ነበር። እንዲሁም በዔድን ገነት ውስጥ ካስቀመጣቸው በኋላ ራሳቸውን በራሳቸው እንዲመሩ ትቷቸው ሌሎች ጉዳዮችን ማከናወን አልጀመረም። ከዚህ ይልቅ ሕይወታቸውን በተሻለ መንገድ ለመምራት የሚያስችላቸውን ግልጽ መመሪያ ሰጥቷቸዋል። አርኪ ሥራ የሰጣቸው ከመሆኑም በላይ ቀጣይነት ያለው ትምህርት የሚያገኙበትን ዝግጅት አድርጎላቸዋል። (ዘፍጥረት 1:26-30፤ 2:7-9) አንተስ አሳቢና አፍቃሪ ከሆነ አባት የምትጠብቀው ይህን አይደለም? አሁን ደግሞ ይህ ምን ማለት እንደሆነ ቆም ብለህ አስብ። ዲንየል እንዲህ ትላለች፦ “ይሖዋ ምድርን እንደፈጠረና በፍጥረት ሥራዎቹ የመደሰት ችሎታ እንዲኖረን አድርጎ እንደሠራን ማወቄ ደስተኞች እንድንሆን የሚፈልግ መሆኑን እንድገነዘብ አድርጎኛል።”

ከዚህም በላይ እንደማንኛውም ጥሩ አባት ሁሉ ይሖዋም ልጆቹ በሙሉ ከእርሱ ጋር በግል እንዲቀራረቡ ይፈልጋል። የሐዋርያት ሥራ 17:27 ይህን በሚመለከት “እርሱ ከእያንዳንዳችን የራቀ . . . አይደለም” በማለት ማረጋገጫ ይሰጠናል። ታዲያ ይህን ማወቃችን ምን ጥቅም አለው? አምበር እንዲህ ትላለች፦ “ይሖዋን ማወቄ ፈጽሞ ብቻዬን እንዳልሆንኩ እንዲሰማኝ አድርጎኛል። ምንም ዓይነት ሁኔታ ቢያጋጥመኝ ምንጊዜም የምመካበት አምላክ አለኝ።” ከዚህም በላይ ይሖዋን ይበልጥ ባወቅኸው ቁጥር ደግ፣ ትክክለኛና ጥሩ መሆኑን ትገነዘባለህ። እንዲሁም ልትተማመንበት ትችላለህ። ጄፍ እንዲህ ይላል፦ “ይሖዋን የቅርብ ወዳጄ ካደረግሁት በኋላ ከእርሱ የተሻለ ለችግሬ ፈጥኖ የሚደርስ እንደሌለ አውቄአለሁ።”

የሚያሳዝነው ግን፣ ስለ ይሖዋ በርካታ መጥፎ ነገሮች ተብለዋል። በሰዎች ላይ ለሚደርሰው ሥቃይና ሃይማኖተኛ ነን የሚሉ ሰዎች ለሚፈጽሙት በደል ጣት የሚቀሰረው በእርሱ ላይ ነው። በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ለተፈጸሙት አንዳንድ አሰቃቂ ግፎች የሚወቀሰው እርሱ ነው። በአንጻሩ ግን ዘዳግም 32:4, 5 እንዲህ ይላል፦ “መንገዱም ሁሉ ትክክል ነው፤ . . . በእርሱ ላይ ክፋት ፈጽመዋል፤ ከነውራቸው የተነሣ ከእንግዲህ ልጆቹ አይደሉም።” በመሆኑም እውነታውን መርምረን የማወቅ ግዴታ አለብን።—ዘዳግም 30:19, 20

የአምላክ ዓላማ ይፈጸማል

ውሳኔያችን ምንም ይሁን ምን እርሱ ለምድርና ለሰው ልጆች ያለውን ዓላማ ሙሉ በሙሉ እንዳይፈጽም ሊያግደው የሚችል አንዳች ነገር አይኖርም። ደግሞም እኮ እርሱ ፈጣሪ ነው። ታዲያ ዓላማው ምንድን ነው? ኢየሱስ ክርስቶስ በተራራ ስብከቱ ላይ “የዋሆች ብፁዓን ናቸው፤ ምድርን ይወርሳሉና” በማለት ዓላማው ምን እንደሆነ ገልጿል። በኋላም የእርሱ ሐዋርያ ለነበረው ለዮሐንስ አምላክ ‘ምድርን ያጠፏትን ለማጥፋት’ እንደቆረጠ ገልጾለታል። (ማቴዎስ 5:5፤ ራእይ 11:18) አምላክ የፍጥረት ሥራዎቹን ባከናወነበት ወቅት ኢየሱስ አብሮት ስለነበር የአምላክ የመጀመሪያ ዓላማ ፍጹም የሆኑ የሰው ልጆች በምድራዊ ገነት ውስጥ ለዘላለም እንዲኖሩ ማድረግ እንደነበር ያውቃል። (ዘፍጥረት 1:26, 27፤ ዮሐንስ 1:1-3) አምላክ ደግሞ አይለወጥም። (ሚልክያስ 3:6) “እንደ ዐቀድሁት በእርግጥ ይከናወናል፤ እንደ አሰብሁትም ይሆናል” በማለት ቃል ገብቶልናል።—ኢሳይያስ 14:24

በዘመናችን ይሖዋ አንድነት ያለው ኅብረተሰብ ለመገንባት የሚያስችል መሠረት መጣል ጀምሯል። ይህ ኅበረተሰብ የሚመሠረተው ዛሬ እንዳለው ዓለም በስግብግብነትና በግል ጥቅም ላይ ሳይሆን ለአምላክና ለሰዎች በሚኖረው ፍቅር ላይ ነው። (ዮሐንስ 13:35፤ ኤፌሶን 4:15, 16፤ ፊልጵስዩስ 2:1-4) እንዲሁም ተልእኳቸውን ከግብ ለማድረስ ይኸውም ይህ ሥርዓት ከመደምደሙ በፊት የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለመስበክ ከፍተኛ ፍላጎትና ቁርጠኝነት ያላቸው ሰዎች በፈቃደኝነት የሚመሠርቱት ኅብረተሰብ ነው። (ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20) ከ230 በሚበልጡ አገሮች የሚኖሩ ከስድስት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ክርስቲያኖች አሁንም እንኳ በፍቅርና በዓለም ኣቀፋዊ የወንድማማችነት መንፈስ በአንድነት ይሖዋን በማምለክ ላይ ናቸው።

ሕይወትህ ትርጉም እንዲኖረው አድርግ

ሕይወትህ ይበልጥ ትርጉም ያለው እንዲሆንልህ የምትፈልግ ከሆነ ይሖዋ አምላክ ከሕዝቦቹ ይኸውም ‘ከጻድቁ ሕዝብ’ ጋር አሁኑኑ መቀራረብ እንድትጀምር እየጋበዘህ መሆኑን እንድታውቅ እንፈልጋለን። (ኢሳይያስ 26:2) ይሁን እንጂ ‘በዚህ ክርስቲያናዊ ኅብረተሰብ ውስጥ ሕይወት ምን ይመስል ይሆን? ከእነርሱ ጋር ብቀራረብ ይበጀኛል?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። እስቲ አንዳንድ ወጣቶች የሚሉትን አዳምጥ፦

ክዌንተን፦ “ጉባኤ ከዓለም ተጽዕኖ የምጠለልበት ቦታ ነው። ይሖዋ ስለ እኔ እንደሚያስብ ማወቄ እርሱ በእርግጥ እንዳለና ደስተኛ እንድሆን የሚፈልግ መሆኑን እንድገነዘብ ረድቶኛል።”

ጄፍ፦ “ማበረታቻ ማግኘት ከምችልበት ከጉባኤ የተሻለ ምንም ቦታ የለም። እዚያ ስሄድ የወንድሞቼንና የእህቶቼን ድጋፍና ማበረታቻ አገኛለሁ። እነርሱ በእርግጥ ቤተሰቦቼ ናቸው።”

ሊኔት፦ “አንድ ሰው የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ሲቀበልና ይሖዋን ለማገልገል ሲወስን ማየት ከሚያስገኘው ደስታ ጋር የሚተካከል አንዳች ነገር የለም። ይህ ለእኔ ታላቅ እርካታ ያስገኝልኛል።”

ኮዲ፦ “ይሖዋን ባላውቅ ኖሮ ሕይወቴ ከንቱ ይሆን ነበር። እንደ ሌሎች በርካታ ወጣቶች ሁሉ እኔም ደስታ ፍለጋ ከወዲያ ወዲህ እባዝን ነበር፤ ለዚያውም ላላገኘው! አሁን ግን፣ ይሖዋ ከእርሱ ጋር ወዳጅነት የመመሥረት ታላቅ መብት ሰጥቶኛል፤ ይህም ሕይወቴ ትርጉም እንዲኖረው ረድቶኛል።”

አንተስ የሕይወትን ትርጉም ለማወቅ ለምን አትመረምርም? ወደ ፈጣሪህ ወደ ይሖዋ አምላክ ይበልጥ በመቅረብ ሕይወትህ እውነተኛ ትርጉም እንዲኖረው ማድረግ እንደምትችል ትረዳለህ።

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከአምላክ ጋር የምንመሠርተው ወዳጅነት ሕይወታችን ትርጉም እንዲኖረው ያስችለናል

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

NASA photo