ዘፀአት 6:1-30

  • ነፃ እንደሚወጡ ዳግመኛ ተስፋ ተሰጣቸው (1-13)

    • ይሖዋ ስሙን ሙሉ በሙሉ አልገለጠላቸውም ነበር (2, 3)

  • የሙሴና የአሮን የዘር ሐረግ (14-27)

  • ሙሴ በድጋሚ ፈርዖን ፊት ቀረበ (28-30)

6  በመሆኑም ይሖዋ ሙሴን “አሁን በፈርዖን ላይ የማደርገውን ታያለህ።+ በኃያል ክንድ ተገዶ ይለቃቸዋል፤ በኃያል ክንድ ተገዶም ከምድሩ እንዲወጡ ያደርጋቸዋል” አለው።+  ከዚያም አምላክ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “እኔ ይሖዋ ነኝ።  ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለያዕቆብ ሁሉን ቻይ አምላክ+ ሆኜ እገለጥላቸው ነበር፤ ይሖዋ የሚለውን ስሜን+ በተመለከተ ግን ራሴን ሙሉ በሙሉ አልገለጥኩላቸውም።+  በተጨማሪም የከነአንን ምድር ማለትም የባዕድ አገር ሰው ሆነው የኖሩባትን ምድር ልሰጣቸው ከእነሱ ጋር ቃል ኪዳን ገብቻለሁ።+  እንግዲህ አሁን ግብፃውያን በባርነት እየገዟቸው ያሉት የእስራኤል ሰዎች እያሰሙት ያለውን የሥቃይ ጩኸት ሰምቻለሁ፤ ቃል ኪዳኔንም አስባለሁ።+  “ስለዚህ እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፦ ‘እኔ ይሖዋ ነኝ፤ ከግብፃውያን ከባድ ሸክም ነፃ አወጣችኋለሁ፤ ከጫኑባችሁም የባርነት ቀንበር አላቅቃችኋለሁ፤+ በተዘረጋ* ክንድና በታላቅ ፍርድ እታደጋችኋለሁ።+  የራሴ ሕዝብ አድርጌ እወስዳችኋለሁ፤ አምላካችሁም እሆናለሁ፤+ እናንተም ከግብፃውያን ከባድ ሸክም ነፃ የማወጣችሁ እኔ አምላካችሁ ይሖዋ መሆኔን በእርግጥ ታውቃላችሁ።  ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለያዕቆብ ለመስጠት እጄን አንስቼ ወደማልኩላቸው ምድር አስገባችኋለሁ፤ ርስት አድርጌም እሰጣችኋለሁ።+ እኔ ይሖዋ ነኝ።’”+  ከዚያም ሙሴ ለእስራኤላውያን ይህን መልእክት ነገራቸው፤ እነሱ ግን ተስፋ ከመቁረጣቸውና አስከፊ ከሆነው የባርነት ሕይወታቸው የተነሳ ሊሰሙት ፈቃደኞች አልሆኑም።+ 10  ይሖዋም ሙሴን እንዲህ አለው፦ 11  “ወደ ግብፁ ንጉሥ ወደ ፈርዖን ገብተህ እስራኤላውያንን ከምድሩ እንዲያሰናብታቸው ንገረው።” 12  ሆኖም ሙሴ “እንግዲህ እስራኤላውያን ሊሰሙኝ ፈቃደኛ አልሆኑም፤+ ታዲያ የመናገር ችግር ያለብኝን* እኔን፣ ፈርዖን እንዴት ብሎ ሊሰማኝ ይችላል?”+ በማለት ለይሖዋ መለሰ። 13  ይሖዋ ግን እስራኤላውያንን ከግብፅ ምድር ለማውጣት ለእነሱና ለግብፁ ንጉሥ ለፈርዖን ማስተላለፍ ያለባቸውን ትእዛዝ ለሙሴና ለአሮን በድጋሚ ነገራቸው። 14  የአባቶቻቸው ቤት መሪዎችም እነዚህ ናቸው፦ የእስራኤል የበኩር ልጅ የሮቤል+ ወንዶች ልጆች ሃኖክ፣ ፓሉ፣ ኤስሮን እና ካርሚ ነበሩ።+ እነዚህ የሮቤል ቤተሰቦች ናቸው። 15  የስምዖን ወንዶች ልጆች የሙኤል፣ ያሚን፣ ኦሃድ፣ ያኪን፣ ጾሃር እና ከአንዲት ከነአናዊት የወለደው ሻኡል ነበሩ።+ እነዚህ የስምዖን ቤተሰቦች ናቸው። 16  የሌዊ+ ወንዶች ልጆች በየቤተሰብ የዘር ሐረጋቸው ስማቸው ይህ ነው፦ ጌድሶን፣ ቀአት እና ሜራሪ።+ ሌዊ 137 ዓመት ኖረ። 17  የጌድሶን ወንዶች ልጆች በየቤተሰባቸው ሊብኒ እና ሺምአይ ነበሩ።+ 18  የቀአት ወንዶች ልጆች አምራም፣ ይጽሃር፣ ኬብሮን እና ዑዚኤል ነበሩ።+ ቀአት 133 ዓመት ኖረ። 19  የሜራሪ ወንዶች ልጆች ማህሊ እና ሙሺ ነበሩ። የሌዋውያን ቤተሰቦች በየቤተሰብ የዘር ሐረጋቸው እነዚህ ነበሩ።+ 20  አምራም የአባቱን እህት ዮካቤድን አገባ።+ እሷም አሮንንና ሙሴን ወለደችለት።+ አምራም 137 ዓመት ኖረ። 21  የይጽሃር ወንዶች ልጆች ቆሬ፣+ ኔፌግ እና ዚክሪ ነበሩ። 22  የዑዚኤል ወንዶች ልጆች ሚሳኤል፣ ኤሊጻፋን+ እና ሲትሪ ነበሩ። 23  አሮን የነአሶን+ እህት የሆነችውን የአሚናዳብን ልጅ ኤሊሼባን አገባ። እሷም ናዳብን፣ አቢሁን፣ አልዓዛርን እና ኢታምርን ወለደችለት።+ 24  የቆሬ ወንዶች ልጆች አሲር፣ ሕልቃና እና አቢያሳፍ ነበሩ።+ የቆሬያውያን ቤተሰቦች እነዚህ ናቸው።+ 25  የአሮን ልጅ አልዓዛር+ ከፑቲኤል ልጆች መካከል አንዷን አገባ። እሷም ፊንሃስን+ ወለደችለት። የሌዋውያን የአባቶች ቤት መሪዎች በየቤተሰባቸው እነዚህ ናቸው።+ 26  ይሖዋ “የእስራኤልን ሕዝብ በቡድን በቡድን* በማድረግ ከግብፅ ምድር ይዛችሁ ውጡ”+ ብሎ የነገራቸው አሮንና ሙሴ እነዚህ ናቸው። 27  የእስራኤልን ሕዝብ ከግብፅ ለማውጣት የግብፁን ንጉሥ ፈርዖንን ያነጋገሩት ሙሴና አሮን ነበሩ።+ 28  ይሖዋ በግብፅ ምድር ሙሴን ባነጋገረበት በዚያ ዕለት 29  ይሖዋ ሙሴን “እኔ ይሖዋ ነኝ። የምነግርህን ሁሉ ለግብፁ ንጉሥ ለፈርዖን ንገረው” አለው። 30  ከዚያም ሙሴ ይሖዋን “እኔ እንደሆነ የመናገር ችግር አለብኝ፤* ታዲያ ፈርዖን እንዴት ብሎ ይሰማኛል?” አለው።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “በኃያል።”
ቃል በቃል “ከንፈሮቼ ያልተገረዙትን።”
ቃል በቃል “በየሠራዊታቸው።”
ቃል በቃል “ከንፈሮቼ አልተገረዙም።”