በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ማረጥ የሚያስከትላቸውን አስቸጋሪ ሁኔታዎች መቋቋም

ማረጥ የሚያስከትላቸውን አስቸጋሪ ሁኔታዎች መቋቋም

“ያለምንም ምክንያት ድንገት ሳይታሰብ በሐዘን ስሜት ተዋጥኩ። አለቀስኩ፣ ላብድ ነው እንዴ ብዬም አሰብኩ።”—ሮንድሮ፣ * ዕድሜ 50

“ጠዋት ከእንቅልፍህ ስትነቃ ቤቱ ተዝረክርኮ ታገኘዋለህ። ዕቃዎችህን ፈልገህ ማግኘት አትችልም። ለዓመታት ያላንዳች ችግር ታከናውነው የነበረው ነገር አሁን በጣም ከባድ መስሎ ይሰማሃል፣ ምክንያቱ ግን አይገባህም።”—ሀንታ፣ ዕድሜ 55

እነዚህ ሴቶች እንዲህ የተሰማቸው ታመው አይደለም። ከዚህ ይልቅ የሚያርጡበት ዕድሜ ላይ በመድረሳቸው ነው፤ ይህ ደግሞ በአንዲት ሴት ሕይወት ውስጥ የሚከሰት ተፈጥሯዊ የሆነ ለውጥ ሲሆን ይህ ወቅት መውለድ የምታቆምበት ጊዜ ነው። አንቺስ ወደዚህ ዕድሜ እየተቃረብሽ ነው? ወይም ደግሞ በዚህ ሂደት ውስጥ እያለፍሽ ነው? ያም ሆነ ይህ፣ አንቺም ሆንሽ በዙሪያሽ ያሉ ሰዎች ስለዚህ ለውጥ ይበልጥ ባወቃችሁ መጠን ከዚህ ጋር ተያይዘው የሚመጡ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ለመቋቋም ይበልጥ ዝግጁ ትሆናላችሁ።

የማረጥ ሂደት

የማረጥ ሂደት ቅድመ ማረጥ ተብሎም የሚጠራ ሲሆን ወደ ማረጥ የሚያሸጋግረውን ሂደትና ራሱ ማረጥንም ያጠቃልላል። * ይሁንና በተለምዶ “ማረጥ” የሚለው ቃል ጠቅላላውን ሂደት ያመለክታል።

አብዛኞቹ ሴቶች ቅድመ ማረጥ የሚጀምራቸው በ40ዎቹ ዕድሜ ውስጥ ሲሆን በሌሎች ሴቶች ላይ ግን እስከ 60ዎቹ ዕድሜ ድረስ ሊዘገይ ይችላል። በአብዛኞቹ ሁኔታዎች የወር አበባ ማየት የሚቋረጠው ቀስ በቀስ ነው። በሆርሞኖች መዛባት የተነሳ አንዲት ሴት የወር አበባዋ ጊዜውን ጠብቆ ላይመጣ ወይም ባልተጠበቀ ጊዜ ሊመጣ አሊያም ሲመጣ ብዙ ደም ሊፈሳት ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ የወር አበባው በድንገት ምናልባትም በአንድ ጀምበር ለዘለቄታው የሚቋረጥበት ጊዜ አለ፤ እንዲህ ያለ ሁኔታ የሚያጋጥማቸው ሴቶች ግን ጥቂት ናቸው።

“እያንዳንዷ ሴት ከማረጥ ጋር በተያያዘ የሚያጋጥማት ሁኔታ የተለያየ ነው” በማለት ሜኖፖዝ ጋይድቡክ የተሰኘው መጽሐፍ ይናገራል። መጽሐፉ አክሎም “ከማረጥ ጋር ተያይዞ የሚመጣውና በጣም የተለመደው ምቾት የሚነሳ ችግር ሙቀትና ላብ ሲሆን ከዚያ በኋላ ብርድ ብርድ የማለት ስሜት ሊከተል ይችላል” በማለት ይናገራል። እነዚህ ሁኔታዎች እንቅልፍ ሊነሱና ኃይል ሊያሳጡ ይችላሉ። ታዲያ ይህ ችግር ለምን ያህል  ጊዜ ይቆያል? ዘ ሜኖፖዝ ቡክ እንደሚለው ከሆነ “አንዳንድ ሴቶች በማረጥ ሂደት ውስጥ ለአንድ ወይም ለሁለት ዓመት ያህል ሳይበዛ በየተወሰነ ጊዜ የሙቀትና የማላብ ስሜት ሊሰማቸው ይችላል። ሌሎች ደግሞ ለብዙ ዓመታት ይቆይባቸዋል። ከቀረቡት ሪፖርቶች መረዳት እንደሚቻለው በቀሪ ሕይወታቸው በሙሉ አለፍ አለፍ እያለ ይህ የሙቀትና የማላብ ስሜት የሚሰማቸው ሴቶች በጣም ጥቂት ናቸው።” *

በተጨማሪም አንዲት ሴት በሆርሞኖች መዛባት የተነሳ ድብታና የስሜት መለዋወጥ ሊያጋጥማት ይችላል፤ ይህ ደግሞ በቀላሉ እንድታለቅስ አልፎ ተርፎም ትኩረት የመሰብሰብና የመርሳት ችግር እንዲያጋጥማት ያደርጋል። እንዲህ ሲባል ግን “እነዚህ ችግሮች በሙሉ በሁሉም ሴቶች ላይ ይደርሳሉ ማለት አይደለም” በማለት ዘ ሜኖፖዝ ቡክ ይናገራል። በእርግጥም አንዳንዶች የሚያጋጥሟቸው ችግሮች በጣም ጥቂት ናቸው፤ ምናልባትም ጨርሶ ላያጋጥማቸው ይችላል።

መቋቋም የሚቻልበት መንገድ

የአኗኗር ለውጥ ማድረግ አንዳንድ ችግሮችን ሊቀንስ ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ የሚያጨሱ ሴቶች ሲጋራ በማቆም የሙቀትና የማላብ ስሜቱ የሚከሰትበትን ጊዜ መቀነስ ይችላሉ። በተጨማሪም ብዙ ሴቶች በአመጋገባቸው ላይ ለውጥ ማድረጋቸው ይኸውም ሙቀትና ላብ ሊቀሰቅሱ የሚችሉ እንደ አልኮል መጠጥ፣ ካፌንና ቅመም ወይም ስኳር የበዛባቸው ምግቦች መቀነሳቸው ወይም እስከነጭራሹ መተዋቸው ጠቅሟቸዋል። እርግጥ ነው፣ በደንብ መመገብ ማለትም የተመጣጠኑና የተለያዩ ምግቦችን መብላት አስፈላጊ ነው።

አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግም ከማረጥ ጋር ተያይዘው የሚመጡ የሕመም ስሜቶችን ለመቀነስ በእጅጉ ሊረዳ ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ እንቅልፍ የማጣትን ችግር ሊቀንስ እንዲሁም በስሜት፣ በአጥንት ጥንካሬና በጥቅሉ ሲታይ በጤና ላይ ጉልህ መሻሻልን ሊያመጣ ይችላል። *

በግልጽ ተወያዩ

“ጉዳዩን አምቃችሁ በመያዝ መሠቃየት አያስፈልጋችሁም” በማለት ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ሮንድሮ ተናግራለች። “ከቅርብ የቤተሰባችሁ አባላት ወይም ወዳጆቻችሁ ጋር በግልጽ ከተነጋገራችሁ በእናንተ ላይ የሚደርሰውን ነገር ሲመለከቱ ከልክ በላይ አይጨነቁም።” እንዲያውም ይበልጥ ታጋሾችና ስሜታችሁን የሚረዱላችሁ ሊሆኑ ይችላሉ። አንደኛ ቆሮንቶስ 13:4 “ፍቅር ታጋሽና ደግ ነው” በማለት ይናገራል።

በተጨማሪም የመውለድ ችሎታቸውን በማጣታቸው ያዘኑትን ጨምሮ ብዙ ሴቶች መጸለያቸው ጠቅሟቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ “[አምላክ] በመከራችን ሁሉ ያጽናናናል” በማለት ማረጋገጫ ይሰጠናል። (2 ቆሮንቶስ 1:4) በተጨማሪም የማረጥ ሂደት ጊዜያዊ መሆኑን ማወቅ ያጽናናል። የማረጡ ሂደት ካለፈ በኋላ ለጤንነታቸው ጥሩ እንክብካቤ የሚያደርጉ ሴቶች ኃይላቸው የሚታደስ ሲሆን በቀሪው ዕድሜያቸው ደስታና እርካታ ያለው ሕይወት መምራት ይችላሉ።

^ አን.2 ስሞቹ ተቀይረዋል።

^ አን.6 ሐኪሞች አንዲት ሴት አርጣለች የሚሉት ላለፈው 1 ዓመት የወር አበባ ሳታይ ከቆየች ነው።

^ አን.8 የታይሮይድ በሽታንና ኢንፌክሽኖችን ጨምሮ አንዳንድ በሽታዎች አልፎ ተርፎም የተወሰኑ የሕክምና ዓይነቶች የሙቀትና የማላብ ስሜት ሊያመጡ ይችላሉ። ይህ ምልክት ከማረጥ ጋር የተያያዘ ነው ብሎ ከመደምደም በፊት በእነዚህ ችግሮች ምክንያት የተከሰተ መሆን አለመሆኑን በደንብ ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው።

^ አን.12 ሐኪሞች በማረጥ ሂደት ውስጥ የሚገኙ ታካሚዎቻቸው ችግሩን በተሻለ መንገድ መቋቋም እንዲችሉ ለመርዳት ሲሉ ሆርሞኖችን፣ ለምግብ ማሟያነት የተዘጋጁ መድኃኒቶችን፣ ለጭንቀት የሚታዘዙ መድኃኒቶችንና ሌሎች ነገሮችን ሊያዝዙ ይችሉ ይሆናል። ንቁ! አንድን ዓይነት ምርት ወይም ሕክምና ለይቶ በመጥቀስ የተሻለ እንደሆነ የሚገልጽ ሐሳብ አያቀርብም።