በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ቃለ ምልልስ | ኤልዳር ኔቦልሲን

ታዋቂ የፒያኖ ተጫዋች ስለሚያምንበት ነገር ምን ይላል?

ታዋቂ የፒያኖ ተጫዋች ስለሚያምንበት ነገር ምን ይላል?

የኡዝቤክስታን ተወላጅ የሆነው ኤልዳር ኔቦልሲን በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂነት ያገኘ የፒያኖ ተጫዋች ነው። ወደ ለንደን፣ ሞስኮ፣ ሴንት ፒተርስበርግ፣ ኒው ዮርክ፣ ፓሪስ፣ ሮም፣ ሲድኒ፣ ቶኪዮና ቪየና ብቻውን በመዘዋወር እዚያ ካሉ የተለያዩ ኦርኬስትራዎች ጋር ተጫውቷል። ኤልዳር ያደገው በሶቭየት ኅብረት ሲሆን ከልጅነቱ ጀምሮ አምላክ የለሽ ነበር። በኋላ ላይ ግን የሰው ልጆችን ወደ ሕልውና ያመጣ አንድ አፍቃሪ የሆነ ፈጣሪ መኖር አለበት የሚል መደምደሚያ ላይ ደረሰ። ንቁ! ስለ ሙዚቃ ሕይወቱና ስለ እምነቱ አነጋግሮታል።

ሙዚቀኛ ልትሆን የቻልከው እንዴት ነው?

ሁለቱም ወላጆቼ የፒያኖ ተጫዋቾች ናቸው። እኔን ፒያኖ ማስተማር የጀመሩት ገና የአምስት ዓመት ልጅ ሳለሁ ነበር። በኋላም ታሽከንት በሚገኘው ከፍተኛ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ተማርኩ።

ከኦርኬስትራ ጋር መጫወት ያሉት ተፈታታኝ ነገሮች ምን እንደሆኑ እስቲ ንገረን።

ሁሉም ኦርኬስትራዎች አንዳቸው ከሌላው ጋር አይመሳሰሉም። በተለያዩ መራሔ መዘምራን (ኮንዳክተር) እጅ እንዳሉ ትላልቅ የሙዚቃ መሣሪያዎች ናቸው። ብቻውን መጫወት ለለመደ ሙዚቀኛ (ሶሎ ተጫዋች) ከሌሎች ኦርኬስትራዎች ጋር ሲሆን ፈታኝ የሚሆንበት ዋነኛው ነገር ከመራሔ መዘምራኑ ጋር ተግባብቶ መጫወት ነው። ይህ ሁኔታ በቅርብ ወዳጆች መካከል ከሚደረግ ጭውውት ጋር ሊመሳሰል ይችላል፤ አንደኛው ወገን ሁልጊዜ ጨዋታውን ልምራ ከማለት ይልቅ ሁለቱም አንዳቸው ሌላውን ለማዳመጥ ፈቃደኛ መሆን ይኖርባቸዋል። እንዲህ ያለ መግባባት እንዲኖር ለሚደረገው ልምምድ ያለህ አጋጣሚ ደግሞ ብዙውን ጊዜ አንዴ ወይም ሁለቴ ብቻ ሊሆን ይችላል።

በልምምድ የምታሳልፈው ጊዜ ምን ያህል ነው?

በቀን ውስጥ ቢያንስ ለሦስት ሰዓት ልምምድ አደርጋለሁ። ይህን ጊዜ የምጠቀምበት አስቸጋሪ የሆኑ ክፍሎችን ለመለማመድ ብቻ ሳይሆን የማዘጋጀውን ሙዚቃ ሳልጫወተው እንዲሁ አወቃቀሩን ለማጥናት ጭምር ነው። ሌላው የማደርገው ነገር አቀናባሪው ያዘጋጃቸውን ሌሎች ሥራዎች ማዳመጥ ነው፤ እንዲህ ማድረጌ አሁን የምጫወተውን ሙዚቃ ይበልጥ በጥልቀት እንድገነዘብ ይረዳኛል።

አንድን ሰው ጥሩ የፒያኖ ተጫዋች ነው የሚያስብለው ምንድን ነው ትላለህ?

ፒያኖው ‘እንዲናገር’ ማድረግ መቻሉ ነው። ምን ማለቴ መሰለህ፣ ፒያኖ የምት ሙዚቃ መሣሪያ ነው። አንድን ኖታ ከመታህ በኋላ ድምፁ እየቀነሰ ይሄዳል እንጂ እንደ ትንፋሽ መሣሪያ ወይም እንደ ሰው  ድምፅ ረዘም ላለ ጊዜ አይቆይም ወይም እየጨመረ አይሄድም። የፒያኖ ተጫዋቹ ፈተና፣ የኖታው ድምፅ እየቀነሰ እንዳይሄድ ማድረግ ነው። ይህን የሚያደርገው ጣቶቹንና እጆቹን ረቂቅ በሆነ መንገድ በማንቀሳቀስና ይህን እንቅስቃሴ የድምፁን ቆይታና መክረር ከሚቆጣጠረው የቀኝ መርገጫው ጋር በማቀናጀት ነው። የፒያኖ ተጫዋቹ በእነዚህ አስቸጋሪ ቴክኒኮች የተካነ ሲሆን ፒያኖው የዋሽንት ወይም የጥሩንባ አሊያም የአንድ ኦርኬስትራ ዓይነት ድምፅ እንዲያወጣ ማድረግ ይችላል። በተጨማሪም ከሙዚቃ መሣሪያዎቹ ሁሉ የላቀውን ማለትም የሰውን ድምፅ ማስመሰል ይችላል።

ለሙዚቃ ጥልቅ ፍቅር እንዳለህ በግልጽ ያስታውቃል።

ልክ ነው፣ ለእኔ ሙዚቃ በቃላት መግለጽ የሚያስቸግሩ ምናልባትም ጨርሶ የማይቻሉ ስሜቶችን በቀጥታ ለመግለጽና ለማነሳሳት የሚያስችል ልዩ ቋንቋ ነው።

ለመንፈሳዊ ነገሮች ፍላጎት እንዲኖርህ ያደረገው ምንድን ነው?

አባቴ ከሞስኮ የተለያዩ መጻሕፍትን ያመጣ ስለነበር ቤታችን በመጻሕፍት የተሞላ ነበር። በተለይ አንድ መጽሐፍ ትኩረቴን በጣም ስቦት ነበር፤ ይህ መጽሐፍ ስለ ሰው ዘር አመጣጥና እስራኤላውያን ስላሳለፉት ታሪክ የሚገልጹ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን ይዟል። ሌላው ትኩረቴን የሳበው በይሖዋ ምሥክሮች የታተመው በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ የተባለው መጽሐፍ ነው። * የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን ግልጽ በሆነ መንገድ ማቅረቡ በጣም አስደነቀኝ። በ1991 ሙዚቃ ለመማር ወደ ስፔን ስሄድ መጽሐፉን ይዤው ሄጄ ስለነበረ ደጋግሜ አነበብኩት። በዚህ ጊዜ በስሜት ሳይሆን በጠንካራ ምክንያቶችና አሳማኝ በሆኑ ማስረጃዎች ላይ የተመሠረተ እምነት አገኘሁ።

በጣም ትኩረቴን የሳበው ትምህርት የሰው ልጆች በምድር ላይ ለዘላለም እንደሚኖሩ መጽሐፍ ቅዱስ የሰጠው ተስፋ ነው። በጣም ምክንያታዊ ሆኖ አግኝቼዋለሁ! በዚህ ጊዜ ገና ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር አልተገናኘሁም ነበር። ነገር ግን ካገኘኋቸው መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያስተምሩኝ ለመጠየቅ ወሰንኩ።

ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር የተገናኘኸው እንዴት ነው?

ይህን ውሳኔ ካደረግኩ ከጥቂት ቀናት በኋላ መጽሐፍ ቅዱስ በእጃቸው የያዙ ሁለት ሴቶች አገኘሁ። ‘እነዚህ ሴቶች በመጽሐፌ ውስጥ ከተጠቀሱት ሰዎች ጋር ይመሳሰላሉ’ ብዬ አሰብኩ። ‘ልክ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን እንደነበሩት ሰዎች እየሰበኩ ነው’ አልኩ። ወዲያው ከአንድ የይሖዋ ምሥክር ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመርኩ። በአሁኑ ጊዜ ከሁሉ የላቀ ደስታ የሚያስገኝልኝ፣ ሰዎች ስለ ፈጣሪ እንዲያውቁ መርዳት ነው።

ቀደም ሲል አምላክ የለሽ የነበርክ ሰው በፈጣሪ እንድታምን ያደረገህ ምንድን ነው?

ሙዚቃ ራሱ ነው። ሁሉም ሰው ማለት ይቻላል፣ ከእንስሳ በተለየ መንገድ ለሙዚቃ ልዩ ስሜት አለው። ሙዚቃ ደስታን፣ በራስ መተማመንን፣ ፍቅርንና ሌሎች ስሜቶችን በሙሉ መግለጽ ይችላል። በተፈጥሯችን ሙዚቃ ስንሰማ እንሳባለን። ይሁንና ሙዚቃ ለሕልውናችን አስፈላጊ ነገር ነው? ጠንካራው ብቻ በሕይወት ይቀጥላል የሚለውን የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ እውን እንዲሆን የሚያበረክተው አስተዋጽኦ አለ? አይመስለኝም። በእኔ አስተያየት እንደ ሞዛርትና ቤትሆቨን ያሉ ሰዎች የተጫወቱትን ሙዚቃ መፍጠርና ማጣጣም የሚችለው የሰው አንጎል በዝግመተ ለውጥ መጣ ብሎ ማመን ምክንያታዊ አይደለም። ከዚህ ይልቅ አንጎልን የሠራ ጥበበኛና አፍቃሪ የሆነ ፈጣሪ አለ ብሎ ማመን ይበልጥ ምክንያታዊ ሆኖ ይታየኛል።

መጽሐፍ ቅዱስ ውብ አወቃቀር፣ አስደናቂ ቅንብርና ለመላው የሰው ዘር የሚሆን ቀስቃሽ መልእክት የሚያስተላልፍ ሲምፎኒ ነው

መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል ነው ብለህ እንድታምን ያደረገህ ምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ በ1,600 ዓመታት ውስጥ 40 በሚያህሉ ሰዎች የተጻፈ የ66 ትናንሽ መጻሕፍት ስብስብ ነው። ‘አንድ ወጥ መልእክት ያለውን ይህን መጽሐፍ እንዲህ ባለ መልክ ማን ማቀነባበር ይችላል?’ ብዬ ራሴን ጠየቅኩ። ብቸኛው ምክንያታዊ መልስ ሆኖ ያገኘሁት ‘አምላክ ብቻ ነው’ የሚል ነው። ለእኔ መጽሐፍ ቅዱስ ውብ አወቃቀር፣ አስደናቂ ቅንብርና ለመላው የሰው ዘር የሚሆን ቀስቃሽ መልእክት የሚያስተላልፍ ሲምፎኒ ነው።

^ አን.15 በአሁኑ ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስጠኑት ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? በተባለው መጽሐፍ ነው። ይህን መጽሐፍ www.jw.org በተባለው ድረ ገጽ ላይ ማግኘት ይቻላል።