በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ሁልጊዜ ግብዣ’ ላይ ነህ?

‘ሁልጊዜ ግብዣ’ ላይ ነህ?

“ልቡ የሚያዝን ሰው ዘመኑ ሁሉ የከፋች ናት፤ የልብ ደስታ ግን ሁልጊዜ እንደ ግብዣ ነው።”—ምሳሌ 15:15 የ1954 ትርጉም

የእነዚህ ቃላት ትርጉም ምንድን ነው? አንድ ሰው ያለበትን አእምሯዊና ስሜታዊ ሁኔታ የሚያመለክቱ ናቸው። “ልቡ የሚያዝን ሰው” ብዙ ጊዜ የሚያስበው አሉታዊ ነገሮችን ነው፤ ይህ ደግሞ ‘ዘመኑን ሁሉ’ ወይም ሕይወቱን “የከፋ” ያደርግበታል። በአንጻሩ ደግሞ “የልብ ደስታ” ያለው ሰው አዎንታዊ በሆኑ ነገሮች ላይ ለማተኮር ይሞክራል፤ ይህም ውስጣዊ ደስታ እንዲሰማው ስለሚያደርግ ‘ሁልጊዜ ግብዣ’ ላይ ነው።

ሁላችንም በተወሰነ መጠንም ቢሆን ደስታችንን የሚሰርቁ ችግሮች ያጋጥሙናል። ሆኖም በአስቸጋሪ ጊዜያት ደስታችንን እንዳናጣ የሚያደርጉ አንዳንድ ነገሮችን ማድረግ እንችላለን። መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል እንመልከት።

  • ነገ ስለሚሆነው ነገር በመጨነቅ የዛሬ ደስታችሁ እንዳይጠፋባችሁ ተጠንቀቁ። ኢየሱስ ክርስቶስ “ስለ ነገ ፈጽሞ አትጨነቁ፤ ምክንያቱም ነገ የራሱ የሆኑ የሚያስጨንቁ ነገሮች አሉት። እያንዳንዱ ቀን የራሱ የሆነ በቂ ችግር አለው” ብሏል።—ማቴዎስ 6:34

  • ባጋጠሟችሁ መልካም ነገሮች ላይ ለማተኮር ሞክሩ። እንዲያውም የሐዘን ስሜት ሲሰማችሁ እነዚህን አስደሳች ነገሮች በዝርዝር በመጻፍ ለምን በእነዚህ ነገሮች ላይ አታሰላስሉም? በተጨማሪም ከዚህ በፊት ስለፈጸማችሁት ስህተት ወይም መጥፎ ድርጊት አታብሰልስሉ። ከስህተታችሁ ትምህርት በመውሰድ ወደፊት ግፉ። የኋላ መመልከቻ መስታወቱን ለአፍታ ብቻ እንደሚመለከት አሽከርካሪ ለመሆን ጥረት አድርጉ፤ እንዲህ ያለ አሽከርካሪ ዓይኑን መስታወቱ ላይ እንደተከለ አይቀርም። በተጨማሪም ‘በአምላክ ዘንድ ይቅርታ እንዳለ’ ሁልጊዜ አስታውሱ።—መዝሙር 130:4

  • የሚያስጨንቅ ሁኔታ በሚያጋጥማችሁ ጊዜ ሊያጽናናችሁ ለሚችል ሰው የልባችሁን አውጥታችሁ ተናገሩ። ምሳሌ 12:25 “ሥጉ ልብ ሰውን በሐዘን ይወጥራል፤ መልካም ቃል ግን ደስ ያሰኘዋል” ይላል። ይህ “መልካም ቃል” ከቤተሰብ አባል ወይም ከታመነ ወዳጅ ማለትም ራስ ወዳድ ወይም አፍራሽ አመለካከት ያለው ሳይሆን ‘ዘወትር ፍቅሩን ከሚያሳይ’ ጓደኛ ሊመጣ ይችላል።—ምሳሌ 17:17 የ1980 ትርጉም

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት ጥበብ የተንጸባረቀባቸው አባባሎች ብዙዎች ተፈታታኝ በሆኑ ጊዜያት ሳይቀር ይበልጥ ደስተኞች እንዲሆኑ አስችለዋቸዋል። እነዚህ ድንቅ አባባሎች አንተንም እንዲረዱህ ምኞታችን ነው።