በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ለቤተሰብ | ትዳር

ኩርፊያን ማስወገድ የሚቻልበት መንገድ

ኩርፊያን ማስወገድ የሚቻልበት መንገድ

ተፈታታኙ ነገር

በፍቅር አብረው እንደሚኖሩ ቃል የገቡ ሰዎች፣ ለበርካታ ሰዓታት እንዲያውም ለበርካታ ቀናት ተኮራርፈው እስከ መቆየት የሚደርሱት ለምንድን ነው? ‘ቢያንስ ከመጨቃጨቅ እንርቃለን’ የሚል ምክንያት ለራሳቸው ይሰጡ ይሆናል። ሆኖም ይህ ችግሩን አይፈታውም፤ እንዲሁም ሁለቱም በውስጣቸው ደስ የማይል ስሜት ይሰማቸዋል።

ምክንያቱ ምንድን ነው?

በቀል። አንዳንድ ባለትዳሮች ኩርፊያን እንደ መበቀያ መሣሪያ አድርገው ይጠቀሙበታል። ለምሳሌ አንድ ባል፣ ሚስቱን ሳያማክር ለቅዳሜና እሁድ እቅድ ያወጣ ይሆናል። ሚስቱ ይህን ስታውቅ ስለ እሷ ምንም እንደማያስብ በቁጣ ትናገራለች። እሱ ደግሞ ትንሹን ነገር እንደምታጋንን ይናገራል። በዚህ ጊዜ ሚስቱ ተናድዳ ጥላው ትሄዳለች፤ ከዚያም ታኮርፈዋለች። ባልዋን ማኩረፏ “እንዲህ እንደተቃጠልኩማ አልቀርም፤ እኔም አሳይሃለሁ” የማለት ያህል ነው።

ሐሳብ ማስለወጥ። አንዳንዶች ኩርፊያን የፈለጉትን ነገር ለማግኘት እንደ መሣሪያ አድርገው ይጠቀሙበታል። ለምሳሌ አንድ ባልና ሚስት ሽርሽር ለመሄድ እቅድ እያወጡ ነው እንበል። ሚስትየው ወላጆቿን ይዛ መሄድ ትፈልጋለች። በዚህ ጊዜ ባልየው ይቃወማል። “ያገባሁት አንቺን እንጂ ወላጆችሽን አይደለም” ይላታል። ከዚያም ተሸንፋ ሐሳቡን እንድትቀበል ለማድረግ ሲል ያኮርፋታል።

እርግጥ ነው፣ የተፈጠረው አለመግባባት እየተጋጋለ ከሄደ ባልና ሚስቱ ለአጭር ጊዜ ዝም መባባላቸው ስሜታቸው እንዲረጋጋ ለማድረግ ያስችላል። እንዲህ ያለው ዝምታ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስም “ለዝምታ ጊዜ አለው” ይላል። (መክብብ 3:7) ይሁን እንጂ ዝምታን ለበቀል ወይም ሐሳብን ለማስለወጥ ከተጠቀምንበት ኩርፊያው የተፈጠረውን ግጭት ከማራዘም አልፎ ባልና ሚስቱ አንዳቸው ለሌላው ያላቸው አክብሮት እንዲሸረሸር ያደርጋል። ታዲያ እንዲህ ያለው ሁኔታ በእናንተ ላይ እንዳይደርስ ማድረግ የምትችሉት እንዴት ነው?

 ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

የመጀመሪያው እርምጃ ኩርፊያ ጊዜያዊ መፍትሔ ከማስገኘት ያለፈ ፋይዳ እንደሌለው መረዳት ነው። እርግጥ ነው፣ ለማናገር ፈቃደኛ አለመሆን የመበቀል ጥማታችሁን ሊያረካ ወይም የትዳር ጓደኛችሁን ሐሳብ ሊያስለውጥ ይችል ይሆናል። ይሁንና እንደምትወዱት ቃል የገባችሁለትን ሰው መያዝ ያለባችሁ በዚህ መንገድ ነው? ግጭቶችን ለመፍታት የሚያስችሉ የተሻሉ መንገዶች አሉ።

አስተዋይ ሁኑ። መጽሐፍ ቅዱስ ፍቅር “አይበሳጭም” ይላል። (1 ቆሮንቶስ 13:4, 5) ስለዚህ “ፈጽሞ ሰው የሚልህን አትሰማም” ወይም “ሁልጊዜ እንዳረፈድሽ ነው” እንደሚሉ ያሉ በስሜት የተነገሩ አባባሎች በቁጣ እንድትገነፍሉ ሊያደርጓችሁ አይገባም። ከዚህ ይልቅ ከአባባሎቹ በስተ ጀርባ ያለውን ነገር ለማስተዋል ሞክሩ። ለምሳሌ “ፈጽሞ ሰው የሚልህን አትሰማም” የሚለው አነጋገር የያዘው ትክክለኛ መልእክት “የእኔን አመለካከት በቁም ነገር የምትመለከተው አይመስለኝም” ማለት ሊሆን ይችላል።—የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት፦ ምሳሌ 14:29

የትዳር ጓደኛችሁን እንደ ባላጋራ ሳይሆን እንደ አጋር አድርጋችሁ ተመልከቱ

ድምፃችሁን ቀነስ አድርጉ። በባልና ሚስቱ መካከል የተፈጠረው አለመግባባት በአጭሩ ካልተቋጨ ውይይታቸው መጋጋሉ አይቀርም። ይሁንና እየተጋጋለ የመጣውን አለመግባባት ማብረድ የምትችሉበት መንገድ አለ። ይህ መንገድ ምንድን ነው? ትዳራችሁን መታደግ (እንግሊዝኛ) የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “ድምፅህን ዝቅ አድርገህ መናገርህና የትዳር ጓደኛህን አመለካከት መረዳትህ ውጥረቱ እንዲበርድና ውይይቱ እየተጋጋለ እንዳይሄድ ስለሚያደርጉ ውጤታማ ዘዴዎች ናቸው። በአብዛኛው እንዲህ ማድረግ ብቻ በቂ ሊሆን ይችላል።”—የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት፦ ምሳሌ 26:20

“እኔ” ከማለት ይልቅ “እኛ” ብላችሁ አስቡ። መጽሐፍ ቅዱስ “እያንዳንዱ ሰው ዘወትር የራሱን ጥቅም ሳይሆን የሌላውን ሰው ጥቅም ይፈልግ” ይላል። (1 ቆሮንቶስ 10:24) የትዳር ጓደኛችሁን እንደ ባላጋራ ሳይሆን እንደ አጋር አድርጋችሁ የምትመለከቱ ከሆነ አንዳችሁ ሌላውን ቅር የማሰኘት፣ የማኩረፍ እንዲሁም የመጨቃጨቅ አጋጣሚያችሁ አነስተኛ ይሆናል።—የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት፦ መክብብ 7:9

ማኩረፍ ከሚከተለው የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ጋር ይቃረናል፦ “ከእናንተ እያንዳንዱ ራሱን እንደሚወድ ሁሉ ሚስቱንም ይውደድ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ሚስት ባሏን በጥልቅ ልታከብር ይገባል።” (ኤፌሶን 5:33) መኮራረፍ በትዳራችሁ ውስጥ ምንም ዓይነት ቦታ እንዳይኖረው ለማድረግ ለምን ቃል አትገባቡም?